- ነገሩ በዕቅዳችን መሠረት ጥሩ ውጤት ያመጣ ይመስለኛል፣ ትክክል ነኝ?
- በሚገባ ክቡር ሚኒስትር፣ ሴትየዋ ከሞላ ጎደል ያቀድናቸውን በሙሉ አድርገውታል።
- መቼም አንተ ተዓምረኛ ሰው ነህ፣ ለመሆኑ እንዴት ስትል አሰብከው?
- ሴትየዋን አውቃቸዋለሁ፣ ማንም ሰው በሕግ ጉዳይ እንዲመጣባቸው አይፈልጉም፣ ሲበዛ ወግ አጥባቂ ናቸው።
- ማንም በሕግ ጉዳይ እንዲመጣባቸው አይፈልጉም ስትል ምን ማለትህ ነው?
- ሕግን የሚፃረር ነገር ሊፈጽሙ ቀርቶ በሐሳብ ደረጃ እንኳን ለመወያየት አሻፈረኝ የሚሉ መሆናቸውን አውቃለሁ።
- እሺ?
- ስለዚህ የተሰረዘው ፓርቲ ሕጋዊ ሰውነት እንዲመለስ መንግሥት አዟል አልኳቸው።
- እሺ?
- እንደጠበቅኩት በቁጣ ቱግ አሉ።
- እሺ?
- ከዚያ የትኛው መንግሥት ነው ይህንን ያዘዘው ብለው ጠየቁኝ።
- እሺ?
- እኔም ያዘዙት ክቡር ሚኒስትሩ መሆናቸውን አሳወቅኳቸው።
- እሺ?
- እርሳቸው እኔን ሊያዙኝ አይችሉም የሚል በቁጣ የታጀበ ምላሽ ሰጡኝ።
- በሌላ ቀን ደውዬ ተረጋግተን እንድንወያይ ጠየቅኳቸውና ቀጠሮ ያዝን፣ በቀጠሮው መሠረትም መንግሥት ለአገር ሰላም ሲባል ዓለም አቀፍ ግዴታ ጭምር የተገባበት ጉዳይ በመሆኑ እንጂ ጣልቃ ለመግባት ተፈልጎ እንዳልሆነ አስረዳኋቸው፡፡
- እሺ?
- ይህንን ካረጋገጥኩላቸው በኋላ በጣም ተረጋጉና እንደዚያ ከሆነ ሕግን በማይጥስ መንገድ መፈጸም እንደሚቻል ገለጹልኝ።
- እንዴት? ምን ብለው?
- አንድ አንቀጽ የሕግ ማሻሻያ በፍጥነት ተዘጋጅቶ በፓርላማ በማፅደቅ የፓርቲውን ሕጋዊ ህልውና መመለስ እንደሚቻል አስረዱኝ።
- እኛስ ይኼን ማድረግ እንደሚቻል ጠፍቶን መስሏቸው ነው?
- እንደዚያ መሆኑ ነው… ዕቅዳችን ፈጽሞ አልገባቸውም።
- እሺ፣ ከዚያ በኋላስ?
- ባቀረቡት ምክረ ሐሳብ ላይ ተነጋግሬ እንደማሳውቃቸው ገልጬላቸው ተሰናበትኩና ከቀናት በኋላ መልሰን ተገናኘን።
- እሺ… ምን አደረግክ?
- ያቀረቡት ሐሳብ ተቀባይነት እንዳላገኘና በታዘዙት መሠረት የፓርቲው ሕጋዊ ሰውነት እንዲመለስ መወሰኑን ነገርኳቸው።
- እሺ?
- በንዴት ጦፉ… መናገር አቃታቸው፣ በኋላ የተባለውን ፈጽሞ እንደማይቀበሉና እንደማያደርጉ ገለጹልኝ።
- እሺ… ከዚያ ምን አደረግህ?
- ውሳኔውን ተቀብለው የማይፈጽሙ ከሆነ አንድ አማራጭ ብቻ እንደሚኖራቸው፣ እሱም በፈቃዳቸው ከኃላፊነት መልቀቅ መሆኑን ገለጽኩላቸው።
- ምን አሉ?
- ያንን ማድረግ አትችሉም… መንግሥት አይደለም የሾመኝ… ተጠሪነቴም ለመንግሥት አይደለም አሉኝ።
- እሺ ቀጥሎ ምን አደረግህ?
- በፈቃድዎት መልቀቂያ የማያቀርቡ ከሆነ የቦርድ አመራሮች የሚነሱበትን ሕጋዊ ሥነ ሥርዓት ለመጠቀም እንገደዳለን አልኳቸው።
- እንደዚያ ስትላቸው ምን አሉ?
- ለተወሰነ ደቂቃ በዝምታ ተወጥው ከቆዩ በኋላ የፈለጋችሁትን ማድረግ ትችላላችሁ ብለው ጥለውኝ ወጡ።
- እሺ… ከዚያ በኋላ ምን ተፈጠረ?
- ከሁለት ቀናት በኋላ ደውለው ሊያገኙኝ እንደሚፈልጉ ገለጹልኝና ተገናኘን።
- እሺ… ለምንድነው ለመገናኘት የፈለጉት?
- እንደሚደውሉልኝ እርግጠኛ ነበርኩ፣ እንደጠበቅኩትም ሐሳባቸውን መቀየራቸውን ገለጹልኝ።
- የፓርቲውን ሕጋዊ ሰውነት ለመመለስ?
- ኧረ በጭራሽ፡፡
- እ…?
- መልቀቂያ ለማስገባት ነው።
- ለካስ እንደዚህ ግትር ናቸው።
- ክቡር ሚኒስትር… ሴትየዋ በዚህ ባህሪያቸው የሚታወቁ በመሆኑ እኮ ነው ይህንን አጋጣሚ እንድንጠቀምበት የጠየቅሁዎት።
- አንተ መለኛ ነህ፣ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ማለት ይህ ነው፣ ግን አንድ ያልተመለሰ ነገር አለ።
- ምን?
- የቀሩት አመራሮችስ የሴትየዋን መርህ ተከትለው የፓርቲውን ሕጋዊ ሰውነት ለመመለስ ፈቃደኛ ባይሆኑስ?
- እኛም በቀጥታ ሕጋዊ ሰውነቱን መልሱ አንላቸውም።
- እና ምን ለማድረግ ነው ያቀድከው?
- በአዋጁ ላይ አንድ ማሻሻያ አንቀጽ ማፀደቅ።
- ምን የሚል ማሻሻያ አንቀጽ?
- አንድ ፓርቲ ነፍጡን ጥሎ በሰላም ለመታገል ከመንግሥት ጋር ከተስማማ ሕጋዊ ሰውነቱ ይመለስለታል የሚል።
- ይኼ ሴትየዋ ያቀረቡት ሐሳብ አይደለም አንዴ?
- በፊት ነበር፣ አሁን ግን የሴትየዋ አይደለም፡፡
- እንዴት?
- ለቀዋል!
- Advertisment -
- Advertisment -