- በክልሉ የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለማቋቋም አሥር ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል ተብሏል
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባለፉት ሁለት ዓመታት በነበረው ግጭትና በተያያዥ ችግሮች የተነሳ ከ300 ሺሕ ተማሪዎች ውስጥ፣ ከ50 ሺሕ በላይ የሚሆኑት እስካሁን ድረስ ከትምህርት ገበታ ውጪ መሆናቸውን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡
የክልሉ ትምህርት ቢሮ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ምትኩ ዘነበ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከሚገኙ 300 ሺሕ ተማሪዎች ውስጥ አሁን በትምህርት ገበታ ላይ የሚገኙት 247,836 ተማሪዎች ናቸው፡፡
በዚህ መሠረት 82 በመቶ የሚሆኑ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ በማድረግ የተሻለ አፈጻጸም ማስመዝገብ መቻሉን የተናገሩት ዳይሬክተሩ፣ ከ50 ሺሕ በላይ የሆኑ ተማሪዎች ደግሞ በፀጥታ ችግር ምክንያት በጉልበት ብዝበዛ ሥራ ላይ በሰማራታቸው ትምህርታቸውን ማቆማቸውን አስረድተዋል፡፡
በክልሉ ውስጥ በአጠቃላይ 679 የትምህርት ተቋማት መኖራቸውን፣ ከእነዚህ ውስጥም አብዛኞቹ የትምህርት ተቋማት ለተከታታይ ሁለት ዓመታት ክልሉ ውስጥ ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ንብረታቸው ወድሟል ብለዋል፡፡
በተለይ ችግሩ የተከሰተው በመተከልና በካማሺ ዞኖች ውስጥ እንደሆነ ጠቅሰው፣ በእነዚህ ዞኖችም ሆነ በክልል ደረጃ በአሁኑ ወቅት ሰላም በመስፈኑ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ኮሚቴ ተዋቅሮ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በክልሉ ከትምህርት ገበታ ውጪ የሆኑ አብዛኞቹ ተማሪዎች የመጀመርያ ደረጃ ላይ የሚገኙ መሆናቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ ተማሪዎቹ ቁጥራቸው ከፍ ያለበት ምክንያት ቤተሰቦቻቸው ወይም የአካባቢው ነዋሪዎች ጉልበታቸውን እየተጠቀሙባቸው መሆኑን አቶ ምትኩ ተናግረዋል፡፡
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባለፉት ሁለት ዓመታት ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ከ200 በላይ ትምህርት ቤቶች በከፍተኛ ሁኔታ መውደማቸውን፣ የክልሉ ትምህርት ቢሮ የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ዳይሬክተር አቶ ዮሐንስ ሉሌ አስታውቀዋል፡፡
በክልሉ የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለማቋቋም ጥናት ባይደረግም፣ አሥር ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግና ገንዘቡም ከፍተኛ በመሆኑ ከተለያዩ ተቋማት ለማሰባሰብ ጥረት መጀመሩን ጠቁመዋል፡፡
በክልሉ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት ከመስጠት አኳያ ሰፊ ክፍተት እንዳለባቸው ገልጸው፣ ይህንን ክፍተት ለመሙላት ቢሮው ወጥ የሆነ አሠራር ዘርግቶ እየሠራ እንደሆነ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል በሁሉም ትምህርት ቤቶች የመጻሕፍት እጥረት እንዳለ የተናገሩት አቶ ዮሐንስ፣ ይህም ችግር በአገር አቀፍ ደረጃ ስለሆነ ብዙዎቹ ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ ችግር ውስጥ ናቸው ብለዋል፡፡