- በጦርነት ሳቢያ የቆመው የግድቡ ግንባታ በመጪው ዓመት ሊጀመር ነው ተብሏል
በ4.3 ቢሊዮን ብር ይጠናቀቃል ተብሎ 15.8 ቢሊዮን ብር ፈሶበት ያልተጠናቀቀውን የዛሬማ ሜይ ዴይ የመስኖ ግድብ ግንባታ ለማጠናቀቅ፣ ተጨማሪ በጀት እንደሚያስፈልግ ተነገረ፡፡
ወልቃይት ውስጥ የሚገኘው ግድቡ በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ግንባታው መቋረጡን፣ በ2003 ዓ.ም. ግንባታው ሲጀመር በ4.3 ቢሊዮን ብር በጀት ይጠናቀቃል ተብሎ እንደነበር፣ የዲዛይን ለውጥ በመደረጉ በ2009 ዓ.ም. ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ በጀት ፈሰስ ቢደረግለትም እንዳልተጠናቀቀ፣ አሁንም ተጨማሪ ገንዘብ እንደሚያስፈልገው የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር ለሪፖርተር ገልጿል፡፡
በሦስት ዓመታት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ከስምንት ዓመታት በላይ ወስዶ ያልተጠናቀቀውን ግድብ በ2016 በጀት ዓመት ግንባታውን እንደገና ለማስጀመር መታቀዱን፣ የሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነትና የኮሙዩኒኬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ብዙነህ ቶልቻ ተናግረዋል፡፡
‹‹ግንባታው ሙሉ ለሙሉ በጦርነቱ ምክንያት ተቋርጧል፤›› ያሉት አቶ ብዙነህ፣ ይሁን እንጂ በ2016 በጀት ዓመት ለማስጀመር ዕቅድ መያዙን አስረድተዋል፡፡
ግንባታውን ለማጠናቀቅ ተጨማሪ በጀት እንደሚያስፈልግ ገልጸው፣ ምን ያህል ተጨማሪ በጀት እንደሚያስፈልግ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ‹‹ግድቡ አሁን ያለበት ሁኔታ አይታወቅም፡፡ ግንባታውን ለማጠናቀቅ የሚያስፈልገውን የገንዘብ መጠን የሚታወቀው ግድቡ ያለበት አሁናዊ ሁኔታ ከተጠና በኋላ ነው፤›› ብለዋል፡፡
ሚኒስቴሩ በድጋሚ ያዘው በተባለው ዕቅድ መሠረት ግንባታውን መቼ ለማጠናቀቅ እንደታሰበ ሲያብራሩም፣ የፀጥታው ችግር ሙሉ ለሙሉ ተስተካክሎ መሥራት ከተቻለ በ2016 ዓ.ም. ሊጠናቀቅ እንደሚችል፣ በአንድ ዓመት ውስጥ ማጠናቀቅ ካልተቻለ ደግሞ ቢያንስ በ2017 በጀት ዓመት ሊጠናቀቅ እንደሚችል አቶ ብዙነህ ገልጸዋል፡፡
ምንም እንኳ የጉዳት መጠኑን በገንዘብ ማወቅ ባይቻልም ግንባታው በተያዘለት ዕቅድ መሠረት ባለመጠናቀቁ፣ ለስኳር ኮርፖሬሽን ከፍተኛ ጉዳት መሆኑን አክለዋል፡፡
የግድቡ ግንባታ ሲቋረጥ አፈጻጸሙ 93 በመቶ ደርሶ እንደነበር፣ ግንባታውን ለማጠናቀቅ የሚቀሩት ዋና የሚባሉ ቀሪ ሥራዎች የውኃ ማስወጫ ማማ (Intake Tower) እና የታናሉን ውስጥ ኮንክሪት ማልበስ እንደሆነ ተነግሯል፡፡
የውኃ ማውጫ ማማ ግንባታው አሥር በመቶ ብቻ ተሠርቶ በመቆሙ፣ የግድቡ 3.1 ኪሎ ሜትር ርዝመት ታናል ውስጡ ኮንክሪት አለመልበሱ ተጨማሪ ሥራ ይጠይቃል ተብሏል፡፡
ግድቡ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ 3.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ መያዝ እንደሚችል፣ 152 ሜትር ከፍታ እንደተሠራለት፣ 805 ሜትር የጎኑ ስፋት ተሠርቶ እንደተጠናቀቀ፣ የውኃ ማጠራቀሚያ 3.1 ኪሎ ሜትር ርዝመት ታናል እንዳለው፣ እንዲሁም የታናሉ ግንባታ 74.2 በመቶ እንደደረሰ አቶ ብዙነህ አስረድተዋል፡፡
በኢትዮጵያ በአጠቃላይ በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ያልተጠናቀቁና ተጨማሪ በጀት የጠየቁ ምን ያህል የመስኖ ፕሮጀክቶች እንዳሉ ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ብዙነህ፣ ቁጥሩን ለመግለጽ ዝግጅት እንደሚያስፈል ገልጸው የመስኖ ግንባታ ፕሮጅክቶች በሲሚንቶ እጥረት የመጠናቀቅ ችግር እንደሚያጋጥማቸው ተናግረዋል፡፡
የኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን የሚረከበኝ አጣሁ ያላቸው ስምንት የመስኖ ፕሮጀክቶች ጉዳይ ከምን እንደደረሰ ሲጠየቁም፣ ይህን ጥያቄ ለመመለስ ዝግጅት እንደሚያስፈልግ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
የዛሬማ ሜይ ዴይ ግድብ ፕሮጀክትን የማማከር ሥራ ሲያከናውን ነበር የተባለው የጣሊያን ኩባንያ በአካባቢው የፀጥታ ችግር ከመፈጠሩ በፊት ቦታውን ለቆ እንደወጣ፣ ከዚያ በኋላም የማማከር ሥራውን መታፈሪያ ኮንሰልቲንግ ኢንጂነሪንግ ኩባንያ እንደያዘው ተመላክቷል፡፡
የፕሮጀክቱ ዋና ሥራ ተቋራጭ ሱር ኮንስትራክሽን ኩባንያ፣ ንዑስ የሥራ ተቋራጩ ደግሞ የቻይና ጂያንዢ ዋተርና ኃይድሮ ፓወር የተሰኘ ኩባንያ እንደነበር ይታወሳል፡፡