Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናባለፉት 11 ወራት ብቻ ከአሥር ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች...

ባለፉት 11 ወራት ብቻ ከአሥር ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መያዛቸው ተነገረ

ቀን:

  • በኤርፖርት ወደ አገር ውስጥ የሚገባውና የሚወጣው አደንዛዥ ዕፅ ከፍተኛ ሆኗል ተብሏል

ካለፈው የበጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ126 በመቶ ብልጫ ያላቸውና ግምታቸው 10.2 ቢሊዮን ብር ዋጋ የሆነ ኮንትሮባንድ ዕቃዎች ሲዘዋወሩ መያዛቸውን፣ የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ከተያዙት የኮንትሮባንድ ገቢና ወጪ ዕቃዎች የጉምሩክ ኮሚሽን 41.8 በመቶ የሚሆኑትን ሲይዝ፣ ኮሚሽኑና ፌዴራል ፖሊስ በጋራ ባደረጉት እንቅስቃሴ 33.7 በመቶ የሚደርሱትን፣ የክልል የፀጥታ አካላት 12.5 በመቶ፣ የጉምሩክ፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የክልል ፀጥታ አካላት መከላከያን ጨምሮ በጋራ በመሆን 4.7 በመቶ የሚሆነውን በቁጥጥር ሥር እንዳዋሉ የገቢዎች ሚኒስቴር የ11 ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሰኔ 23 ቀን 2015 ዓ.ም. በፓርላማው ፕላን በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሲገመገም ተጠቅሷል፡፡

የሚያዙ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች በዚህ መጠናቸው ማደጉ፣ ጉዳዩ ትልቅ ትኩረት የሚፈልግና የብዙ አካላትን ቅንጅት የሚጠይቅ መሆኑን የገቢዎች ሚኒስቴር ገልጿል፡፡

የገቢዎች ሚኒስትር ወ/ሮ ዓይናለም ንጉሤ ኮንትሮባንድ አሁን ባለው ሁኔታ የተወሳሰበ፣ የኮንትሮባንዲስቶችም አቅምና ቴክኒክ በጣም እየተራቀቀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በንባብ ባቀረቡት ጥያቄ በገቢና ወጪ ኮንትሮባንድ የሚያዘው መጠን በከፍተኛ ደረጃ እያደገ መሆኑን፣ በቀጣይ ከምንጩ ለመቀነስ ምን ታቅዶ እየተሠራ ነው ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ገቢ ኮንትሮባንድ በ163 በመቶ፣ እንዲሁም ወጪ ኮንትሮባንድ በ254 በመቶ መጨመሩን በማስታወስና በገንዘብ ረገድም ከተያዘው ዕቅድ 178 በመቶ እንደተያዘ በመግለጽ፣ ለውጤቱ የነበሩ አስቻይ ሁኔታዎች ምንነታቸው እንዲገለጽ ለገቢዎች ሚኒስቴርና ለጉምሩክ ኮሚሽን የሥራ ኃላፊዎች ጥያቄ ቀርቧል፡፡

ይህ ብቻም ሳይሆን የጉምሩክ ኮሚሽን በዘጠኝ ወራት ከወጪ ንግድ ያገኘው ገቢ ከዕቅዱ ዝቅተኛ እንደሆነና ወጪና ገቢ ኮንትሮባንድ በሕጋዊ ንግድ ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ እንዴት እንደተገመገመ በመግለጽ፣ በተለይም ከፍተኛ ቅናሽ የታየባቸው እንደ ጫት፣ የቅባት እህሎች፣ የሥጋና የሥጋ ውጤቶች መሠረታዊ ምክንያታቸው ምን ነበር ሲሉ የቋሚ ኮሚቴ አባላት ጠይቀዋል፡፡

የጉምሩክ ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ በገቢና ወጪ ኮንትሮባንድ የሚያዘው መጠን በከፍተኛ ደረጃ እያደገ መሆኑን፣ ኤርፖርት እንደ ምሳሌ ተወስዶ የቀረበውን ጥያቄ በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በኤርፖርት አካባቢ በኢትዮጵያ የኮንትሮባንድና የሕገወጥ ንግድ ሒደት ውስጥ ያልተለመዱ በርካታ ልምዶች ወደ ኢትዮጵያ እንደሚጋዙ፣ ለአብነትም ኮኬይንና የመሳሰሉት አደንዛዥ ዕፆች በከፍተኛ ደረጃ ከመጋዝ አልፈው በትራንዚት መልክ ከኢትዮጵያ ወደ ሌሎች አገሮች ለማስተላለፍ ኮንትሮባንዲስቶች በከፍተኛ ደረጃ እንደሚሠሩ አቶ ደበሌ አስረድተዋል፡፡

‹‹ባልተለመደ ሁኔታ ከፍተኛ ኪሎ ግራም ለምሳሌ 97 እና 98 ኪሎ ግራም ኮኬይን ከብራዚል ተነስቶ ኢትዮጵያ በሚያዝበት ጊዜ ብዙ ጥናቶችና ብዙ ምርምሮች መካሄድ አለበት፤›› ያሉት ኮሚሽኑ፣ ‹‹ጉዳዩ ሄዶ የሚያርፈው ጉምሩክ ኮሚሽን ላይ እንጂ ከየት ተነሳ? እንዴት ታሰበ? እንዴት ተዘጋጀ? በዚህ ኔትወርክ ውስጥ ያሉት አካላት እነማን ናቸው? ሰንሰለቱ ውስጥ እነ ማን ነበሩ? የሚለው ሳይታይ ከዚህ ሁሉ ሒደት በኋላ ነው ጉምሩክ መፈተሻ ጣቢያ ሲደርስ የሚያዘው፤›› የሚለውን በመግለጽ፣  እነዚህን ሁሉ በመረዳት ዕገዛው በዚያ ደረጃ ቢኖር የተሻለ ውጤት ይኖራል ብለዋል፡፡

በኤርፖርት ወደ አገር ውስጥ የሚገባም ሆነ ወደ ውጪ የሚወጣና በዘዴና በኔትወርክ ድብቅ በሆነ መንገድ የሚፈጸም ኮንትሮባንድ፣ ‹‹ከጊዜ ወደ ጊዜ ፈትኖናል፤›› ሲሉ ኮሚሽነሩ ለቋሚ ኮሚቴ አባላት አስረድተዋል፡፡  

‹‹በተለያየ መልክ የመንግሥት አካላት እጅ ያለበት ነው፡፡ የኮንትሮባንዲስቶቹን ዕቃዎችን ደብቀው የማምጣት ባህሪ መገመት ከሚቻለው በላይ ነው፡፡ በጣም ጥልቅ፣ ተከታታይና አንድ ዓይነት መንገድ የሌለው ነው፤›› ሲሉ አቶ ደበሌ አክለዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ጉምሩክ፣ ብሔራዊ መረጃ፣ ኢሚግሬሽንና ፌዴራል ፖሊስ የመሳሰሉ አካላትን ቅንጅት በተጠናከረ መንገድ ወደፊት ማምጣት፣ እንዲሁም ከእነዚህ ጋር የሚታከኩትን ማጥራትና ተከታታይ ዕርምጃ መውሰድ አስፈላጊ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ከወጪ ንግዱ የተገኘው ገቢ ከዕቅዱ አንፃር ዝቅተኛ የሆነበት የተለያየ ምክንያት ቢኖርም፣ ከአምራችና ከላኪ አኳያ ችግሩን ማየት ይገባል ተብሏል፡፡

ለአብነትም ጫት ከአምራች አኳያ ያለው ችግር ምንድነው? ምን ጥያቄ አለው? በብቃት አምርተው ወደ ገበያ የማያወጡበት፣ ኤክስፖርት የማያደርጉበት ምክንያት ምንድነው የሚለው ጥያቄ ኮሚሽኑ ሲገመግም መቆየቱን ያስረዱት አቶ ደበሌ አምራቹ በዚህ ዙሪያ ብዙ ቅሬታ እንዳለው፣ ‹‹አምርተን ለኤክስፖርት ልናቀርብ የሚያስችለን የተሟላ የግብይትና የዋጋ ሥርዓት የለም፤›› የሚለው አንዱ ችግር ነው ብለዋል፡፡

አምራቹ ላመረተው ተገቢና የተሟላ የግብይት ሥርዓት ካልተመቻቸለት ዋጋው በዚያው ልክ ለኤክስፖርት እንዲያዘጋጅ የሚያጓጓው ካልሆነ የሚመርጠው ሕገወጥነት ነው ተብሏል፡፡ ስለሆነም ከዚህ ጀምሮ መፍትሔ መፈለግ ጠቃሚ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

‹‹ጫት ላኪዎች ሕጋዊም ሕገወጥ ናቸው፡፡ ይኼንን በውል መለየት ያስፈልጋል፡፡ ፈቃድ ከማውጣት ጀምሮ የሚያወጡት ፈቃድ፣ የሚልኩት ጫት በቀን፣ በሳምንት፣ በወር ምን ያህል እንደሆነና ፈቃድ ከሰጣቸው አካላት ጋር የግዴታ ውል መግባት አለባቸው፡፡ ይኼ በትክክል አልተፈጸመም፣ ቁጥጥርም አይደረግበትም፣ የሚደረግበት ቁጥጥርም ተከታታይና ችግሩን ከሥረ መሠረቱ የሚነቅል አልሆነም፤›› በማለት አቶ ደበሌ ተናግረዋል፡፡

በድንበሮች አካባቢ ሠራዊትና የጉምሩክ ሠራተኞችን በማሠለፍ ችግሩን መወጣት እንደማይቻል፣ ከሥረ መሠረታቸው መታከምና መዳን ያለባቸው ጉዳዮች መኖራቸውን የጉምሩክ ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል፡፡

መንግሥታዊ ተቋማት ኤክስፖርትን ለማበረታታት የወሰዱት የሕግ ኃላፊነት እንዳለባቸውና የቁም እንስሳት፣ ማዕድናት፣ የቅባት እህሎች፣ የሥጋና ሥጋ ውጤቶችና ጫትን በተመለከተ የወሰዱት ኃላፊነት ፈቃድ ከመስጠት ጀምሮ፣ የግብይት ሥርዓትን ከማመቻቸት፣ ዋጋንና መዳረሻን በማመቻቸት ረገድ ተቋማት በሕግ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በትክክል መወጣት አለባቸው ተብሏል፡፡

በኮንትሮባንድ ወንጀል የተሳተፉ 1.077 ግለሰቦች ላይ አስተማሪ ዕርምጃ ተወስዷል ሲል የገቢዎች ሚኒስቴር በሪፖርቱ አቅርቧል፡፡  

የገቢዎች ሚኒስቴር እንዳስታወቀው፣ በተያዘው ዓመት 11 ወራት 405.09 ቢሊዮን ብር ገቢ ተሰብስቧል፡፡ ከአገር ውስጥ ገቢ የተሰበሰበው 243.62 ቢሊዮን ብር፣ ከውጭ ንግድ ቀረጥና ታክስ 161.48 ቢሊዮን ብር፣ አጠቃላይ ተሰብሳቢ ገቢው የዕቅዱን 98 በመቶ ያሳካ ነው ብሏል፡፡

ከተሰበሰበው ገቢ ወደ ገንዘብ ሚኒስቴር ፈሰስ የተደረገው 320.5 ቢሊዮን ብር እንደሆነ፣ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲመሳከር የ70.1 ቢሊዮን ብር  (28.04) በመቶ ዕድገት ያለው መሆኑ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...