የኢትዮጵያ የነዳጅ ግብይት ሥርዓትን ሙሉ በሙሉ ይቀይራል የተባለውና የነዳጅ ኩባንያዎችና ማደያዎች በዲጂታል የክፍያ ዘዴ ብቻ እንዲጠቀሙ የሚያስገድድ የነዳጅ አቅርቦት አስተዳደር ሥርዓት፣ ከሐምሌ 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ ሊሆን ነው፡፡
ከኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው፣ በኢትዮጵያ ቴሌኮም የበለፀገው ይህ ሲስተም እስካሁን ከነዳጅ ግብይትና ሥርጭት ጋር ተያየዞ ይታዩ የነበሩ ሕገወጥ ተግባራትን ከማስቀረቱም በላይ፣ የነዳጅ ግብይትን በጥብቅ ለመቆጣጠር የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ኃይለ ማርያም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ማንኛውም የነዳጅ ኩባንያና ማደያ አዲስ በበለፀገው መተግበሪያ በመጠቀም ግብይታቸውን በዲጂታል የክፍያ ዘዴ ብቻ እንዲጠቀሙ የሚያስገድድ ነው፡፡
እስከ ዛሬ የነበረው አሠራር አንድ ነዳጅ ማደያ የሚረከበውን ነዳጅ በትክክል ለተጠቃሚዎቹ መሸጥ አለመሸጡን ለመቆጣጠር የሚያስችል አሠራር እንዳልነበር ያስታወሱት አቶ ታደሰ፣ አሁን ግን አዲሱ መተግበሪያ የነዳጅ ማደያዎች የሚረከቡትን ነዳጅ በአግባቡ መሸጥ አለመሸጣቸውን መቆጣጠር የሚያስችል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የየዕለት ሽያጫቸውንም በዚሁ ሲስተም ወዲያውኑ በመመዝገብ ቁጥጥር የሚደረግበት ሥርዓት የሚፈጥርና ሕገወጥነትን ለመከላከል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ታምኖበታል፡፡
ከሐምሌ 1 ቀን 2015 ጀምሮ የሚተገበረው ይህ ሲስተም አንድ የነዳጅ ማደያ የተረከበውን ነዳጅ ሸጦ ሳይጨርስ ሌላ ነዳጅ ማዘዝ እንዳይችል የሚያደርግ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የነዳጅ ኩባንያዎቹም ከነዳጅ ማደያዎች የሚቀበሉትን ትዕዛዝ የኢትዮጵያ ነዳጅ ድርጅት አፅድቆ በትክክል ነዳጅ ለጠየቀው የነዳጅ ማደያ መድረሱን፣ ይኸው ሲስተም ቁጥጥር እንደሚያደርግበት ጠቁመዋል፡፡
አዲሱ ሲስተም የነዳጅ ኩባንያዎች በጂቡቲ ሲያካሂዱ የነበረውንም ግብይት፣ በአዲስ አበባ በማዕከል እንዲፈጽሙ የሚያስችል መሆኑም ታውቋል፡፡
ከነዳጅ ማደያዎች የሚቀርብላቸው የነዳጅ ይቅረብልን ጥያቄና ግዥ ማስፈጸም ያለባቸው በዚሁ በተዘረጋው ሲስተም መሆኑን፣ ከዚህ ውጭ ግብይት እንደማይፈጸም አስታውቀዋል፡፡
መንግሥት የነዳጅ ግብይት በዲጂታል የክፍያ ዘዴ እንዲፈጸም ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ ሕገወጥ የነዳጅ ግብይት እንዲቀንስ በማድረጉ ረገድ አዎንታዊ ሁኔታዎች እንደታየ ያመለከቱት አቶ ታደሰ፣ አዲሱ አሠራር ደግሞ ወደ አገር የሚገባ ነዳጅ የት ቦታ ለማን እንደተሸጠ ለመቆጣጠር እንደሚያስችል አስረድተዋል፡፡
በኢትዮ ቴሌኮም በልፅጎ ከሐምሌ 1 ቀን ጀምሮ ሥራ ላይ የሚለው የነዳጅ አቅርቦት ማኔጅመንት ሥርዓት በመጀመርያ የሚተገበረው በአዲስ አበባና በሸገር ከተሞች ባሉ 160 ማደያዎች መሆኑ ታውቋል፡፡
ከእነዚህ ከተሞች ውጭ ባሉ ክልሎች በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ አስፈላጊው ዝግጅትና ሥልጠና ተሰጥቶ እንደሚተገበር አቶ ታደሰ ገልጸዋል፡፡ በአዲስ አበባና በሸገር ከተሞች ላሉ ማደያ ሠራተኞችና ባለንብረቶች አገልግሎቱን እንዴት እንደሚሰጡ በተግባር ሥልጠና የተሰጣቸው በመሆኑ፣ ከተጠቀሰው ቀን ጀምሮ ሽያጫቸውን በዚሁ የዲጂታል ክፍያ ዘዴ ግዥ መፈጸም ይጠበቅባቸዋል፡፡