Wednesday, October 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉዜጎችን ማጎሳቆል እስከ መቼ ይቀጥላል?

ዜጎችን ማጎሳቆል እስከ መቼ ይቀጥላል?

ቀን:

በቤኪ ዘሌ

አገሪቱን በማስተዳደር ላይ የሚገኘው በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሚመራው መንግሥት አገራዊ አንድነትን ማስጠበቅ ያቃተው ከመሆን ባለፈ፣ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በማፈንና በመርገጥ ላይ ነው፡፡ ላለፉት አራት ዓመታት አገሪቱ ያሳለፈችው አስከፊ የሆነና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ለሞት፣ እንዲሁም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩትን ደግሞ ለስደት የዳረገው አስከፊው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ጠባሳ፣ በተጨማሪም በኦነግ ሸኔ በየአካባቢው የሚካሄደው ግድያና ማፈናቀል የዜጎች የዕለት ተዕለት ራስ ምታት ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ 

አሁናዊ  የአገሪቱ  ነባራዊ ሁኔታ ሲዳሰስም የዜጎች በሰላም ወጥቶ የመግባት፣ የመሥራት፣ ከቦታ ወደ ቦታ የመንቀሳቀስ፣ እንዲሁም ንብረት የማፍራትና ቤተሰብ የመመሥረት መሠረታዊ የሆኑ የሰው ልጆች መብቶች እጅግ በከፍተኛ ሁኔታ ጥያቄ ምልክት ውስጥ  ገብቷል፡፡ ዜጎች በገዛ አገራቸው ላይ ተስፋ የቆረጡበትና ስደትን ብቸኛ አማራጭ በማድረግ በሕገወጥ መንገድ በመሰደድ ለከፍተኛ ሥቃይና እንግልት፣ እንዲሁም ለሞት በሰፊው የሚዳረጉበት ሁኔታ የአደባባይ ሀቅ ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ 

የአገሪቱ አሁናዊ ነባራዊ እውነታ እንደሚያሳየው ከሆነ ዜጎች ሰብዓዊ መብቶቻቸው በአደባባይ በየአካባቢው በሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኃይሎች የሚጨፈለቁበት፣ የሚታገቱበት፣ የሚገደሉበትና ከመኖሪያ ቀዬአቸው የሚሰደዱበት ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ገዥው መንግሥት ሕግ ማስከበር በሚል ፈሊጥ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥና በዙሪያዋ በሚገኘው ሸገር ከተማ አስተዳደር ሕገወጥ ቤቶች በሚል ሽፋን፣ ዜጎችን ለዘመናት ከኖሩበት መኖሪያ ቤታቸው በማፈናቀል በሰፊው በማፍረስ ላይ ይገኛል፡፡ ይህንንም የማፈናቀልና ዜጎችን መጠለያ አልባ የማድረግ ኢሰብዓዊ ተግባር የፌዴራሉ መንግሥት እየተመለከተ ምንም ዓይነት ማስተካከያም ሆነ ምላሽ ባለመስጠት፣ ባስም ሲል ድጋፍ በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ተግባር ባለው የአገሪቱ አስከፊና ጥልቅ  ችግር ላይ ተጨማሪ መዘዝ የሚያስከትል ከመሆኑ ባሻገር፣ የዜጎችን በአገራቸው በየትኛውም አካባቢ የመኖር መብት የሚጥስና አገሪቱንም ዋጋ የሚያስከፍል ይሆናል፡፡  

በሕግ ማስከበር ሽፋን ዜጎችን ከመኖሪያቸው የማፈናቀል ሕገወጥ ተግባር ብዙዎችን በተለይም ሕፃናትን፣ ሴቶችንና አረጋውያንን በአስከፊ ሁኔታ በጎዳና ላይ እንዲበተኑ በማድረግ ለከፋ ችግርና ለልመና በመዳረግ ላይ ሲሆን፣ ይህም ሁኔታ በቀጣይነት የራሱ የሆነ ማኅበራዊ ጫናና ውጥንቅጥ የሚያስከትል ጉዳይ ነው፡፡ የእነዚህ ዜጎች ሁኔታ የበለጠ የሚያከፋው ደግሞ ለምን ቤታቸው እንደሚፈርስባቸው ሲጠይቁ የሚሰጣቸው መልስ ማስፈራራት፣ እስርና ድብደባ ሲሆን፣ አሁን አሁን ደግሞ እስከ መገደል እያበቃቸው እንደሆነ የተለያዩ መረጃዎች እየወጡ ይገኛሉ፡፡ የዚህ ኢሰብዓዊ የሆነ የመኖሪያ ቤቶችን የማፍረስ ተግባር ብሔርን መሠረት ያደረገ መሆኑ፣ የበለጠ ዜጎችን የሚጎዳና አገር እንደሌለው የባይተዋርነት ስሜት እንዲሰማቸው የሚያደርግ ሕገወጥ ድርጊት ነው፡፡

በተለይም ደግሞ ሕዝቡ ለዘመናት ሐዘኑንና መከፋቱን ይዞ አምላኩን የሚማፀንባቸውና አቤት የሚልባቸውን የእምነት ተቋማትን የማፍረስና የማጥፋት ተግባር፣ ይቅር የማይባልና ለማኅበረሰቡ ያለውን ሰፊ ንቀትና ጥላቻ የሚያሳይ ነው፡፡ ይህንንም ተከትሎ በአገሪቱ በተከሰተው ግጭት ምንም ጥያቄ ባላነሱና ለምን የእምነት ተቋሞቻችን ይፈርሳሉ ባሉ ወጣቶች ላይ፣ የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት ዕርምጃ ብዙዎቹ ለሞትና ለዕድሜ ልክ የአካል ጉዳተኝነት የተደረጉበት ሁኔታ በቅርቡ ያየነው አረመኔያዊ ተግባር ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው መንግሥት መረጠኝ ለሚለው ማኅበረሰብ ምንም ዓይነት ክብርም ሆነ ቦታ እንደሌለው ነው፡፡

ከዚህ ተግባርም ጋር በተያያዘ በአካባቢው ለሚካሄደው የዜጎች ጉዳትና መፈናቀል መረጃ ለመያዝና ለመዘገብ የሚንቀሳቀሱ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና ጋዜጠኞችን በማጉላላትና ለእስር በመዳረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህም ሕገወጥ ተግባር ምን ያህል የዜጎችን ሰብዓዊ መብት የጣሰና አስከፊ መሆኑን የዓለም ማኅበረሰብ እንዳይመለከተው ያደረገና የመረጃ ክፍተትን የፈጠረ ድርጊት ነው፡፡

ወትሮውንም የአገሪቱን  ዜጎች  ከእጅ ወደ አፍ የሆነው የኑሮ ሁኔታ የባሰ የከፋ ያደረገው የኑሮ ውድነት ነዋሪዎችን በማማረር ላይ ባለበት ወቅት፣ እንዲሁም በመላ አገሪቱ በሚስተዋለው የፀጥታ ዕጦት ምክንያት ዜጎች በገፍ በሚሰደዱበትና በሚፈናቀሉበት ሁኔታ እንዲህ ዓይነት ሕገወጥ ተግባር ለዚያውም በመንግሥት የሚፈጸም መሆኑ አሳዛኝና የጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥት ለዜጎቹ ደኅንነትና ሰላም ደንታ ቢስ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ዜጎች ያላቸውን ጥሪትና ሀብት አሟጠው በገዙት መሬት ላይ የቀለሱትን መኖሪያ ቤት እንደ ቀላል ነገር በግሬደርና በትራክተር አፍርሶ፣ ነዋሪዎቹንና ንብረታቸውን ሜዳ ላይ መበተን ለደሃ ቆሜያለሁ ከሚል መንግሥት የሚጠበቅ ተግባር በፍፁም ሊሆን አይችልም፡፡

በተቃራኒው ደግሞ የሚገርመው የፌዴራሉና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በቢሊዮን ዶላሮች ለሚገነቡ እጅግ ዘመናዊ ቤተ መንግሥቶች በቅርቡ የመሠረት ድንጋይ በማስቀመጥ ላይ መሆናቸው ነው፡፡ ደሃው ዜጋ በስንት መከራ ከጉሮሮው ነጥቆና ፆሙን እያደረ የቀለሰውን መጠለያ በአንድ ኃላፊ ትዕዛዝ በሰዓታት ውስጥ አፍርሰውበት፣ ምንም የማያውቁ ልጆቹንና ቤተሰቡን ሜዳ ላይ የሚበትኑት፡፡ ይህ ነው እንግዲህ የዘመኑ ፖለቲከኞችና ገዥዎች የልማትና የዕድገት ዲስኩር፡፡ ይህን ያህል ቤቶች አፍርሰናል ብለው ሪፖርት በማቅረብ ሹመትና ዕድገት የሚጨመርላቸውና በደሃ ዕንባ ላይ እነሱ የሚሾሙትና የሚሸለሙት፡፡

የአንድ ሥርዓተ መንግሥት ዋነኛው ተግባሩ የዜጎቹን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን፣ እንዲሁም ሁለንተናዊ ሰላም የመጠበቅና የማስጠበቅ ኃላፊነት መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ነገር ግን በጠቅላዩ የሚመራው የብልፅግና መንግሥት ግን እያደረገ የሚገኘው በተቃራኒው መሆኑን የምናየው እውነታ ነው፡፡ በመንግሥት ሕገወጥ ተግባር ብቻ ዜጎች አስከፊና አሰቃቂ የሆነ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ፡፡

ይህም ተግባር ቀጣይነት ያለው መሆኑን በሚወጡ ሪፖርቶችና መረጃዎች፣ እንዲሁም በመንግሥት ባለሥልጣናት በሚሰጡ መግለጫዎች እየሰማን ሲሆን፣ ይህ ማለት ደግሞ የዜጎች መፈናቀልና ለጎዳና ሕይወት መዳረግ ይቀጥላል ማለት ነው፡፡ የአገራችን ቀጣይ ዕጣ ፋንታ አደጋ ውስጥ እየወደቀ መሆኑን በየዕለቱ በምንሰማቸውና በሚፈጸሙ ኢፍትሐዊነትና ሕገወጥ ድርጊቶች መመልከትና ማስተዋል እንችላለን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...