Saturday, September 23, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹በትግራይ ክልል የወደሙ ትምህርት ቤቶች እስኪጠገኑ እንጠብቅ ብንል ከመቶ ቢሊዮን ብር በላይ ሊያስፈልግ ይችላል›› ኪሮስ ጉእሽ (ዶ/ር)፣ የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ

የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ በኮሮናና በጦርነት ተቋርጦ የቆየው መደበኛ ትምህርት ምዝገባ እንደሚጀምር ያስታወቀው ሚያዝያ 18 ቀን 2015 ዓ.ም. ነበር፡፡ ሚያዝያ 23 ቀን 2015 ዓ.ም. ደግሞ ከዓመታት መቋረጥ በኋላ በትግራይ ክልል ታዳጊዎች እንደገና ከፊደል ገበታ ጋር መገናኘታቸውን ትምህርት ቢሮው አስታውቋል፡፡ ከሰሞኑ በመቀሌ ከተማ በተካሄደ ዓውደ ጥናት የትግራይ ክልል ተማሪዎች በኮሮናና በጦርነት ትምህርት በማቋረጣቸው የገጠማቸውን ዘርፈ ብዙ ችግር የተመለከተ አዲስ ጥናት ይፋ ሆኗል፡፡ ይኼው ጥናት ይፋ ሲደረግ የተገኙት የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ኪሮስ ጉእሽ (ዶ/ር)፣ የክልሉ ትምህርት ዘርፍ የገጠመውን ቀውስ ለሪፖርተር በሰፊው ዘርዝረዋል፡፡ ዮናስ አማረ ከእሳቸው ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡- በትግራይ ክልል ክልል ጦርነቱ ሳቢያ በትምህርት ዘርፍ ላይ የደረሰውን ጉዳት የተመለከተ አዲስ የጥናት ውጤት ቀርቧል፡፡ የክልሉ የትምህርት ዘርፍ ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

ኪሮስ (ዶ/ር)፡- ለአራት ዓመታት ያህል በትግራይ ክልል ክልል ትምህርት ቆሟል፡፡ መጀመሪያ መጋቢት 8 ቀን 2012 ዓ.ም. በኮሮና ወረርሽኝ ሥጋት የተነሳ ትምህርት ቆሞ ነበር፡፡ ከዚያም የኮሮና ወረርሽኝ ተፅዕኖን በመቋቋም ትምህርቱን እንደገና ማስቀጠል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ስንዘጋጅ ነበር ጦርነቱ የተቀሰቀሰው፡፡ በዚህ የተነሳ ለአራት ዓመታት ወይም ለሰባት ሴሚስተሮች ትምህርት በክልሉ ተቋርጦ ቆይቷል፡፡ ትምህርት መቋረጥ አንዱ የዘርፉ ችግር ነው፡፡ ነገር ግን ከዚህ በባሰ የትምህርት ሥርዓት ዓምዶች ከሚባሉት መሠረታዊ ነገሮች አንዱ የሆነው ትምህርት ቤቶች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ብዙ ትምህርት ቤቶች ወድመዋል፣ ተሰባብረዋል፣ ተዘርፈዋል፣ ተጭነው ተወስደዋል፣ እንዲሁም ተቃጥለዋል፡፡ ይህ ደግሞ በአብዛኛው ሆን ተብሎ የተካሄደ ነው፡፡

ሌላው የትምህርት ዓምድ የሚባለው የሰው ኃይል ነው፡፡ በጦርነቱ መምህራኖቻችንም ልክ እንደ ሌላው የክልሉ ሕዝብ ሁሉ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ የተገደሉ መምህራን አሉ፣ ሕክምና አጥተው የሞቱ፣ የተፈናቀሉ፣ እንዲሁም የተሰደዱ መምህራን አሉ፡፡ ደመወዛቸው ለሁለትና ለሦስት ዓመታት ቆሞ ስለነበር የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ሕይወት ለመታደግ ወደ ተለያዩ ሥራዎች ለመግባት የተገደዱ መምህራን አሉ፡፡

ሦስተኛው ጉዳት ደግሞ በሥርዓተ ትምህርቱ ላይ የደረሰው ነው፡፡ ሕፃናት በዕድሜያቸው ልክ ሊማሩበት የሚገባ የትምህርት ደረጃ ላይ አይደሉም፡፡ በዚያን ጊዜ ለምሳሌ በ2012 ዓ.ም. የሦስት ዓመት ሕፃን የነበረ አሁን አንደኛ ክፍል መግቢያው ሰባተኛ ዓመት ላይ ይገኛል፡፡ ያኔ አራተኛ ዓመት ላይ የነበረ አሁን በስምንት ዓመቱ የሁለተኛ ክፍል ተማሪ መሆን ነበረበት፡፡ ያኔ አምስት ዓመቱ የነበረ አሁን ዘጠኝ ዓመት ሆኖት ሦስተኛ ክፍል ፊደል መቁጠር ነበረበት፡፡ ያኔ ስድስተኛ ዓመት ላይ የነበረ ደግሞ አሁን አራተኛ ክፍል የሚማር የአሥር ዓመት ታዳጊ መሆን ነበረበት፡፡

ነገር ግን ተማሪዎቻችን አሁን ትምህርቱን ካቆሙበት ነው ለመጀመር እየተገደዱ ያሉት፡፡ በዕድሜያቸው መግፋት ልክ ትምህርቱን መግፋት የሚችሉበት አጋጣሚ በመቋረጡ ተመልሰው ከታች ለመጀመር ተገደዋል፡፡ የሃይስኩል ተማሪዎችም ቢሆኑ ይኸው ችግር ነው የገጠማቸው፡፡ ያኔ 18 ዓመት የሞላው የ12ኛ ክፍል ተማሪ ዛሬ ዩኒቨርሲቲ ጨርሶ ሥራ መፈለጊያው ነበር፡፡ ነገር ግን ትምህርት መቀጠል ባለመቻሉ ከኮሌጅ፣ ከዩኒቨርሲቲ ወይም ከቲቬት ተመርቆ ሥራ በሚፈልግበት ዕድሜ በ23 ዓመቱ ወደ 12ኛ ክፍል ተመልሶ ለመማር ሊገደድ ነው፡፡

የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም ቢሆኑ ተያያዥ ችግር አጋጥሟቸዋል፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ካሪኩለም በ2012 ዓ.ም. ስለተቀየረ ያኔ ሁለተኛ፣ ሦስተኛና አራተኛ ዓመት ተማሪ የነበሩ ልጆች በጦርነቱ ምክንያት ዩኒቨርሲቲ ገብተው መማር አልቻሉም፡፡ አንዳንዶች እንደምንም በጦርነቱ መካከል ሾልከው በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ወዳሉ ዩኒቨርሲቲዎቻቸው ሄደው ለመቀጠል ቢሞክሩም፣ በነበረው ሁኔታ የዘር ጥቃት የደረሰባቸውና የታሰሩ ጭምር ነበሩ፡፡

አሁን ወደ ዩኒቨርሲቲዎች ገብተው ትምህርታቸውን ለመቀጠል የሚፈልጉ ተማሪዎቻችን ካሪኩለሙ ስለተቀየረ፣ የዲግሪ ፕሮግራም ከሦስት ወደ አራት ዓመት ስለተራዘመ ካቆሙበት ለመቀጠል ይረዝምባቸዋል፡፡ ትምህርት አቋርጠው ካሳለፉት ዓመት ጋር ሲደመር የሚያባክኑት ጊዜ ይጨምራል፡፡ በካሪኩለሙ መቀየር የተነሳ አንዳንድ ኮርሶችን አያገኙም፣ አንዳንዶቹ ጋ ምናልባትም ዲፓርትመንቱና ትምህርቱ ላይኖር ሁሉ ይችላል፡፡ ስለዚህ አሁን በትግራይ ክልል ክልል መሠረተ ልማቱ ብቻ ሳይሆን፣ የሰው ኃይሉና ሥርዓተ ትምህርቱ ጭምር በፈራረሰበት ሁኔታ ውስጥ ነው ያለው ማለት እንችላለን፡፡ አሁን በዚህ ሁኔታ ውስጥም ሆነን ትምህርት ለመጀመር እየተንቀሳቀስን ነው፡፡  

ዛሬ በመቀሌ የቀረበው የጥናት ውጤትም ሁለት ዓይነት ነገሮችን በመመዘን የቀረበ ነው፡፡ አንደኛው የትምህርት አቀባበል ወይም ‹‹ለርኒንግ ሎስ›› ችግር ነው፡፡ የሁለተኛ፣ የሦስተኛና የአራተኛ ክፍል ተማሪዎችን በመፈተሽ የቀረበ ነው፡፡ አንድ የአራተኛ ክፍል ተማሪ ሊያውቀው የሚገባ የማንበብ ክህሎት፣ ፊደላትን የመለየት ችሎታ፣ እንዲሁም ሒሳብ የማስላት ችሎታ ነው የተጠየቀው፡፡ የሁለተኛና የሦስተኛ ክፍሎችም በተመሳሳይ በትግርኛ፣ በእንግሊዝኛና በሒሳብ ዕውቀቶች ነው የተመዘኑት፡፡ የተገኘው ውጤትም እጅግ አስደንጋጭ ነበር የሆነው፡፡

ይህ ደግሞ የአንድ የትምህርት ዘርፍ ጉዳት ውጤት ብቻ ሳይሆን፣ በትግራይ ክልል ክልል በጦርነት የደረሰው ሁለንተናዊ ውድመት ነፀብራቅ ሆኖ የሚታይ ነው፡፡ ሌላው ጥናቱ ያየው የተማሪዎች፣ የመምህራንና የወላጆችን አዕምሯዊ ሁኔታ ነው፡፡ ይህም ቢሆን አጠቃላይ የትግራይ ሕዝብ በጦርነቱ ሳቢያ የሚገኝበትን ሥነ ልቦናዊ ጫና የሚያንፀባርቅ ውጤት የተገኘበት ነው፡፡ ጥናቱ ይህን በአኃዝ አስደግፎ አቀረበ እንጂ፣ በአጠቃላይ የትግራይ ሕዝብ የሥነ ልቦና ጫና ደርሶበታል፡፡

ጥናቱ መረጃን መሠረት ያደረገ የተግባር ዕርምጃ ለመውሰድ የሚያግዝ ነው፡፡ ጥናቱ ተፈናቃዮች የተጠለሉበትን ጣቢያ ብቻ ማዕከል ያደረገ ነው፡፡ ጥናቱ የተደረገው ጦርነቱ እንደቆመ ስለነበር መረጃ በበቂ ለመሰብሰብ የነበረው ሁኔታ አዳጋች ነበር፡፡ ይሁን እንጂ አስቸጋሪ ሁኔታዎችንም በማለፍ የክልሉን የትምህርት ዘርፍ በተመለከተ ተጨባጭ መረጃ ይዞ መምጣት ተችሏል፡፡ ይህ ደግሞ እኛም ለምንሠራው ሥራ፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት ለሚያደርጉት ድጋፍ፣ የፌደራል መንግሥቱ ለሚሠራቸው ሥራዎች ጠቃሚ ግብዓት የሚሰጥ ነው ብለን እናምናለን፡፡

ሪፖርተር፡- በትግራይ ክልል ክልል ከ77 እስከ 93 በመቶ የትምህርት መሠረተ ልማቶች ተጎድተዋል የሚል መረጃ ቀርቧል፡፡ ይህ በተጨባጭ የቀረበ ነው ይላሉ?

ኪሮስ (ዶ/ር)፡- አዎን፣ ቅድም እንዳልኩት ነው፡፡ የትምህርት መሠረተ ልማት ጉዳት ሲባል ትምህርት ቤቱ ሕንፃውና በውስጡ ያሉ የትምህርት ቁሳቁሶች ውድመትን የሚጨምር ነው፡፡ ይህ አኃዝ በ2013 ዓ.ም. ብቻ የነበረውን ጉዳት እንጂ ሙሉውን የክልሉን የትምህርት መሠረተ ልማት ውድመት የሚያሳይ አይደለም፡፡ ከጥቅምት 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ሰኔ 2013 ዓ.ም. በነበረው ጦርነት የወደሙት ትምህርት ቤቶች አኃዝ ብቻ የሚያሳይ ነው፡፡ በወቅቱ ሐምሌና ነሐሴ ላይ የተደረገ ጥናት ላይ ብቻ ተመርኩዞ ነበር በመስከረም 2014 ዓ.ም. አካባቢ ውጤቱ የቀረበው፡፡ ሆኖም ጥናቱ ሁለት ክፍተቶች ነበሩበት፡፡ አንደኛው አጠቃላይ ትግራይን ያካተተ ጥናት አልነበረም፡፡ በጊዜው ምዕራብ ትግራይን አላጠናነውም፡፡ እዚያ መግባት እስካሁንም አልቻልንም፡፡ በኤርትራ ሠራዊት ቁጥጥር ሥር የነበሩ አካባቢዎችንም ማጥናት አልተቻለም፡፡ በጊዜው የነበረውን የመጓጓዣም ሆነ የትራንስፖርትና መገናኛ አገልግሎት የማግኘት ፈተናም ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡ በተለያዩ አቅጣጫዎች ተዟዙሮ መረጃ ለመሰብሰብ ምቹ ሁኔታ አልነበረም፡፡ ሌላው ውስንነት ደግሞ ነበር፡፡ በጥናቱ መፈተሽ የተቻለው የ2013 ዓ.ም. ጦርነት ውድመትን ብቻ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ በተቻለ መጠን ማዳረስ በተቻለባቸው አካባቢዎች በርካታ ትምህርት ቤቶችን በማጥናት ነበር፣ የተጠቀሰውን አኃዝ ያህል ውድመት እንደደረሰ ማረጋገጥ የተቻለው፡፡ ከዚያ በኋላ እስከ ጥቅምት 2015 ዓ.ም. መጠነ ሰፊ ውጊያዎች በትግራይ ክልል ተካሂደዋል፡፡ በዚያን ጊዜ ጉዳታቸው መለስተኛ የነበሩና ለጥቂት የተረፉ ትምህርት ቤቶች ከነበሩ፣ በተከታታይ በተደረጉ ውጊያዎች ሙሉ ለሙሉ የመውደም ዕድላቸው ሰፊ ነው፡፡ ለምሳሌ በአካል ሄጄ ካየሁት ውድመት አንዱን ላንሳልህ፡፡ ነበለት አካባቢ ከውጭ ዘመናዊ ዕቃዎች መጥተው የተገጠሙለት አዲስ ፕሪፓራቶሪ ትምህርት ቤት ነበር፡፡ የሻዕቢያ ሔሊኮፕተር አራት ጊዜ ተመላልሶ ነው ንብረቱን የወሰደው፡፡ ኮምፒዩተሩንም ሆነ ሌላውን ቁሳቁስ አንድም ሳይቀር ነው የተዘረፈው፡፡ በ2013 ዓ.ም. መጀመሪያ ሲገቡ ዕቃውን ወስደውታል፡፡ በ2015 ዓ.ም ተመልሰው ሲገቡ ደግሞ የነበረውን ሕንፃ እንኳን አውድመውት ሄደዋል፡፡

በብዙ የትግራይ አካባቢዎች እንደገና የተካሄደው ውጊያ ደርሶባቸዋል፡፡ ሰሜን ምዕራብ አካባቢ ብዙ ወረዳዎች፣ ማዕከላዊ ዞን ብዙ ወረዳዎች፣ ምሥራቃዊ ዞን ብዙ ወረዳዎች እንዲሁም ደቡባዊ ዞን ብዙ ወረዳዎች እንደገና ውጊያው ተካሂዶባቸዋል፡፡ ስለዚህ በትግራይ ክልል በከፊል ወድመው የነበሩና የተረፉ የሚባሉ ወደ ሰባት በመቶ ከነበሩ፣ በእንደገና ውጊያው ብዙዎቹ ሙሉ ለሙሉ የመውደም ዕድላቸው ሰፊ ነው ማለት ይቻላል፡፡  

ሪፖርተር፡- የትምህርት ቤት ውድመት መጠን እንዴት ነው የሚለካው?

ኪሮስ (ዶ/ር)፡- የአንድ ትምህርት ቤት ውድመት ዓይነት የሚገለጽባቸው መሠረታዊ መስፈርቶች (ኦፕሬሽናል ዴፊኔሽኖች) ይታወቃሉ፡፡ ወደ 40 በመቶ የማገልገል አቅሙን ያጣ ትምህርት ቤት ሙሉ ለሙሉ ወደመ ነው የሚባለው፡፡ በመለስተኛ ጥገና ወይ ዕድሳት ሳይሆን በእንደገና ግንባታ ነው ይህ ዓይነቱ የወደመ ትምህርት ቤት ወደ ሥራ መልሶ የሚገባው፡፡ በአንድ ትምህርት ቤት ውስጥ የነበሩ መቀመጫዎች፣ መጻፊያ ሰሌዳዎችና ችና ሌሎች መሠረታዊ የትምህርት ቁሳቁሶች ከወደሙ ሕንፃው ብቻውን እንኳ ቢቀር ልታስተምር አትችልም፡፡ የመልሶ ግንባታ ኢንቨስትመንትና ሥራ ይፈልጋል፡፡  

ምዕራብ ትግራይን ጨምሮ 2,492 ትምህርት ቤቶች ነው ያሉን፡፡ እነዚህ ትምህርት ቤቶች ሙሉ ለሙሉ የወደሙ ናቸው፡፡ በትግራይ ክልል ብዙዎቹ ውስጣቸው ብቻ ሳይሆን ሕንፃቸው ጭምር የወደመ ትምህርት ቤቶች ናቸው ያሉት፡፡ ለምሳሌ እዚሁ መሀል መቀሌ የሚገኘውን አፄ ዮሐንስ ትምህርት ቤት ብንመለከት ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ንብረት ነው ያጣው፡፡ በውስጡ የነበሩ ፕላዝማ ቴሌቪዥኖች፣ ኮምፒዩተሮች፣ የወረቀት ማባዣ ማሽኖችና ሌሎችም ቁሳቁሶች ተዘርፈዋል፡፡ ሕንፃው ከውጭ ደህና ቢመስልም በውስጡ ያሉ በሮች፣ መስኮቶች፣ መስታወቶች፣ ጠረጴዛዎችና ሌሎች ቁሳቁሶች ብዙ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡

መቀሌ ከተማ እምብርት ላይ ያለ አንድ ትምህርት ቤት ይህን ያህል ከባድ ጉዳት ካስተናገደ፣ በርቀት ቆላ ተምቤን ላይ የሚገኝ ትምህርት ቤት ሊገጥመው የሚችለውን ውድመት በቀላሉ መገመት ይቻላል፡፡ አፄ ዮሐንስን በመመልከት ብቻ አዲያቦ፣ ኢሮብ፣ ጉሎ መኮዳ ዛታ ኦፍላ አካባቢ፣ ወይም ምዕራብ ትግራይ ያለ ትምህርት ቤት ሊገጥመው የሚችለውን አደጋ ማሰብ ይቻላል፡፡ መቀሌ ያለው አፄ ዮሐንስ ቀጥታ የሚባል ውጊያ የተካሄደበት ቦታ ላይ ያለ ትምህርት ቤት ባይሆንም በከባድ ሁኔታ ውድመት ደርሶበታል፡፡ በውስጡ ምሽግ ተሠርቶበትና የጦር ካምፕ ሆኖ ነበር፡፡ ሩቅ በሆኑ ወይም ቀጥተኛ ውጊያ በተካሄደባቸው የትግራይ አካባቢዎች ያሉ ትምህርት ቤቶች ደግሞ፣ ከአፄ ዮሐንስ የባሰ እንጂ ያነሰ ጉዳት ሊገጥማቸው እንደማይችል ይጠበቃል፡፡

የትግራይ ትምህርት ቤቶች ደረሰባቸው ተብሎ ሲነገር የቆየው አኃዝ ሀቅ ቢሆንም፣ ነገር ግን የቆየ የ2013 ዓ.ም. ገጽታን ብቻ የሚያሳይ መረጃ ነው፡፡ ጦርነቱና ውድመቱ በአንዴ ብቻ ባለመቆሙና በመቀጠሉ ጉዳቱ ይጨምራል፡፡ አሁን ባይጠናም ውድመቱ ከዚያ አልፎ ከሚገመተው በላይ እጅግ ከፍተኛ እንደሚሆን መገመት ይቻላል፡፡ ከውድመቱ የተረፈ አለ ቢባል እንኳን ከዚያ በላይ መውደም ስለማይችል ብቻ የቆየ ነው የምለው፡፡ ምክንያቱም የሞተን ማንም እንደማይገድል ሁሉ አንዴ የወደመውን ደግሞ ለማውደም የሚፈልግ ባለመኖሩ የተረፈ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በክልሉ የትምህርት መሠረተ ልማቶች ሙሉ ለሙሉ ወድመዋል ተብሎ ከተገመተ በተማሪዎች፣ በወላጆችና በመምህራን ላይ የደረሰውም ጉዳት ከፍተኛ መሆኑ በጥናት ተደግፎ ከቀረበ፣ እንዲህ ባለው ሁኔታ ምን ዓይነት የትምህርት አሰጣጥ ለማስጀመር ነው የታሰበው? ትምህርት ለመጀመር የሚያስችል ምን ምቹ ሁኔታ አለ?

ኪሮስ (ዶ/ር)፡– የለም፣ ግን ምን ማድረግ ይቻላል፡፡ አማራጭ ሲኖር ነው ይህንን ከዚያ ብለህ የምታማርጠው፡፡ ባለው ነገር መጀመር አለበት ብሎ ነው ጊዜያዊ አስተዳደሩ የወሰነው፡፡ ይህን ችግር አጋነን ወይም በደንብ ሳናይ ቀርተን አይደለም ትምህርት እንጀምራለን እንደ ክልል የምንለው፡፡ እዚህ ካለው ከአፄ ዮሐንስ ጀምሮ ዞር ዞር ብሎ የደረሰውን ጉዳት በዓይን መታዘብ ይቻላል፡፡ በወደመ ነገርም ቢሆን ትምህርት መጀመር አለብን ስንል የራሱ የሆነ ትርጉም ስላለው ነው፡፡ የሰላም ስምምነት ተፈርሟል፡፡ ጊዜያዊ አስተዳደሩም የተቋቋመው በዚያ ስምምነት መሠረት ነው፡፡ ተምህርት ይጀመር ሲባል የትምህርት መጀመሩ ለሰላም ልዩ ትርጉም አለው፡፡ ትምህርት መጀመር ለተማሪዎች፣ ለወላጆችና ለመምህራን ትልቅ የአዕምሮ እረፍት የሚሰጥም ነው፡፡ ተማሪዎች ወጥተው መግባት መጀመራቸው፣ ከሌሎች ጓደኞቻቸው ጋር መዋል፣ ፊደል መቁጠርና መጫወታቸው በራሱ መደበኛ ሕይወት እንደገና መመለሱን የሚያበስር ነው፡፡ ፊደል ሲቆጥሩ፣ ቁጥር ሲያሰሉና ፈተና አለ ብለው ሲጨነቁ ያለፉበትን ሰቆቃ ረስተው መደበኛ ሕይወት ለመጀመር ያግዛቸዋል፡፡ መምህራንም ሆነ ወላጆች በልጆቹ የትምህርት ሒደት ላይ ማሰብና መጨነቅ ሲጀምሩ አንፃራዊ የአዕምሮ እረፍት ያገኛሉ ተብሎ ይገመታል፡፡ ትምህርት መጀመሩ ከዚህ አንፃር ጠቀሜታ አለው፡፡

የትግራይ አጠቃላይ መልሶ ግንባታ ጉዳይ እየተነሳ ነው፡፡ መልሶ ግንባታ ሲባል ደግሞ ከሰው ኃይል ግንባታ ነው የሚጀምረው፡፡ ሁሉም የመንግሥት መዋቅር የፈረሰ ነው፡፡ የዳኝነት፣ የማዘጋጃ፣ የፍትሕ፣ የግብርና የሁሉም ዓይነት መዋቅር ከሰው ኃይል ጀምሮ የፈረሰ ነው፡፡ ይህ ሁሉ የሰው ኃይል መሟላትን ይፈልጋል፡፡ ልክ እንደ ትምህርቱ ሁሉ የጤናውም ሆነ ሌላው ዘርፍ የተማረና ነገ ተመርቆ የሚያገለግል የሰው ኃይል ይፈልጋል፡፡ ስለዚህ እንደምንም ብሎ የሰው ኃይል ልማት ላይ ዛሬ ሥራ መጀመሩ አስፈላጊ ነው፡፡ የተጀመረ ሥራ ደግሞ ነገ ተነገ ወዲያ እየተሻሻለ ይሄዳል፡፡ ስለዚህ በፈለገው ዓይነት ሁኔታ ቢሆን ትምህርት መጀመር ነበረበት፡፡ ድንጋይ ላይ ተቀምጠው፣ መደብ ነገር ሠርተው፣ ጥላ ሥር ተጠቅመው፣ የተሰባበረ በር ላይም ቢሆን ጽፈው ልጆቻችን እንዲማሩ ጥረት እያደረግን ነው ያለነው፡፡

አማራጭ ስለሌለን የግድ መጀመር ስላለብን ወደ ሥራ ገብተናል፡፡ በትግራይ ክልል የወደሙ ትምህርት ቤቶች እስኪጠገኑ እንጠብቅ ብንል ከመቶ ቢሊዮን ብር በላይ ሊያስፈልግ ይችላል፡፡ በዚህ ሒደት ደግሞ ጊዜውም አብሮ ይባክናል፡፡ ትምህርት ለመጀመር መሠረተ ልማቱ እስኪጠገን እንቆይ ካልን ከዚህ በኋላ የአንድ ሳምንት ቆይታ ራሱ ትልቅ ተፅዕኖ አላት፡፡ አንድ ሳምንት በዘገየህ ቁጥር የብዙ ዓመት ጉዳት ሊኖረው ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- በክልሉ ትምህርት ዘርፍ የደረሰው አጠቃላይ ጉዳት በተመለከተ መረጃው አለ?

ኪሮስ (ዶ/ር)፡- ጥናቱን ጀምረነዋል፣ እየቆጠርን ነው፡፡ ቅድም ባስቀመጥናቸው የትምህርት ምሰሶዎች መሠረት የደረሰውን ጉዳት እያጠናን ነው፣ ገና አላለቀም፡፡ የደረሰውን አጠቃላይ ጉዳትና ለመጠገን የሚፈጀውን ወጪ አጣርተን እንደጨረስን ውጤቱን ይፋ እናደርጋለን፡፡ ጊዜ በጨመረ ቁጥር የተማሪዎች የመማር አቅም፣ የተማሪዎች የመማር ፍላጎትና የተማሪዎች የመማር ዕድል እያሽቆለቆለ ነው የሚሄደው፡፡ ዛሬ የቀረበው ጥናት ያለፉትን አራት ዓመታት የትምህርት መቋረጥ ጉዳት ምን ያህል ከፍተኛ እንደሆነ አረጋግጦልናል፡፡ ለምሳሌ በ2012 ዓ.ም. የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ የነበረች ልጅ ያኔ 16 ዓመቷ ከሆነ ዛሬ 20 ዓመት ደርሳለች፡፡ ዛሬ ተመልሳ የመማር ዕድል ታገኛለች ወይ? ከቤተሰቧ፣ ከማኅበረሰቡም ሆነ ከዕድሜዋ አንፃር አሁን ተመልሳ ልትማር የምትችልበት ዕድል አለ ወይ? የሚለው ፈታኝ ነው፡፡ የግዴታ መጀመር ነበረብን፣ ለዚያ ነው ወደ ተግባር የገባነው፡፡

ሪፖርተር፡የተፋጠነ የትምህርት አሰጣጥ (Accelerated Learning Program) እንደ አማራጭ እየተቀመጠ ነው፡፡ ይህ በትግራይ ክልል መተግበሩ ውጤታማ ይሆናል?

ኪሮስ (ዶ/ር)፡- ቀደም ብሎ በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎችም የተሞከረ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃም የተለመደ ነው፡፡ በኮሮና ወረርሽኝ ወቅትና ቀውስ ውስጥ በገቡ አገሮች ተሞክሮ ውጤታማ የሆነ ነው፡፡ አንዳንዴ የተማሪዎች ዕድሜና የሚማሩበት የትምህርት እርከን እስኪመጣጠን ድረስ የሚካሄድ ፕሮግራም ነው፡፡ የትምህርት ዓይነቶችንና የዕውቀት ዓይነቶችን በመለየት ወሳኝ የሚባሉትን ብቻ መርጠህ የምታስተምርበት፣ ወሳኝ ያልሆኑትን የምትተውበት ፕሮግራም ዓይነት ነው፡፡ በተለይ በአንደኛ ደረጃ ለምሳሌ አንደኛ ክፍል የገቡት ከ7 እስከ 11 ዓመት የሚሆናቸው ልጆች ከሆኑ የሰባት ዓመቱ ትክክለኛ በሚባል ዕድሜው ላይ የገባ ቢሆንም፣ 10 ወይም 11 ዓመቱ ላይ የሚገኝ ተማሪ ግን አንደኛ ክፍል ያነሰ ነው የሚሆንበት፡፡ በዚህ የዕድሜ እርከን ያሉ ልጆች በዕድሜያቸው መጨመር ከሕይወት የሚቀስሙት ዕውቀት በመኖሩ የተነሳ፣ ልክ እንደ ሰባት ዓመቱ ተማሪ መማር አይኖርባቸውም፡፡ መሠረታዊ የሒሳብ ዕውቀት ይኖረዋል፡፡ የስሜት ሕዋሳትን አገልግሎት በአግባቡ ሊያውቅ ይችላል፡፡ ጣቱን በመቁጠር ከመደመርና ከመቀነስ አላቀህ የሒሳብ አሠራር መንገዶችን ልታሳየው ትችላለህ፡፡ በዚህ ዕድሜው ላይ ያለ ታዳጊ እንደ ሰባት ዓመት ልጅ ዓይን ለምን ይጠቅማል ብለህ አታስተምረውም? ምክንያቱም በዕድሜው መግፋት የተነሳ ዓይን ለማየት ብቻ ሳይሆን ለመጥቀስ ጭምር ያገለግላል የሚል ዕውቀት ሁሉ ሊኖረው ይችላልና መሠረታዊ በሆኑ ዕውቀቶች ላይ ያተኮረ ትምህርት ነው የምትሰጠው፡፡

ስለዚህ ዕድሜያቸው ከፍ ብለው ዝቅ ያለ ክፍል ላይ የሚማሩ ተማሪዎችን የተመረጡ ትምህርቶች እያስተማርክ በተፋጠነ ሁኔታ የትምህርት እርከኖችን እንዲሸጋገር ማድረግ ይቻላል፡፡ ለምሳሌ በአንድ ዓመት ሁለት ሴሚስተር ይማር ከሆነ፣ ሦስትም አራትም እያስተማርክ የተመረጡ ትምህርቶችን ብቻ እየሰጠህ ታሸጋግረዋለህ፡፡ ይህን መሰሉን የተፋጠነ ትምህርት አሰጣጥ በትግራይ ክልል በሁሉም የትምህርት እርከኖች እንዲሰጥ አድርገናል፡፡ በአንደኛም ሆነ በሁለተኛ ደረጃ እንዲሰጥ አድርገናል፡፡ ነገርየው በአንደኛ ደረጃ ለመስጠት በተለይ ቀላል ነው፡፡ ከፍ እያሉ ሲኬድ ግን ትምህርቱን ለማጠፍ ወይም ለማሳጠር ከባድ ነው፡፡ የትምህርት ዓይነቶች በአብዛኛው በአግድመትም በወርድም ይገናኛሉ፡፡ አንተ ለምሳሌ በጋዜጠኝነት የተማርካቸው ትምህርቶች ከቋንቋ ትምህርቶች ጋር ይዛመዳሉ፡፡ የትምህርት እርከን በጨመረ ቁጥር የምንማራቸው ትምህርቶች አንዱ ከሌላው ወደ ጎንም ሆነ ወደ ላይም ይገናኛሉ፡፡

ወደ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ይህን የትምህርት አሰጣጥ ስናመጣው፣ ስትራቴጂክ የሆኑ ክፍሎችን በመለየት ነው ትምህርቶቹ እንዲሰጡ ያደረግነው፡፡ 12ኛ ክፍል ወደ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት ብሔራዊ ፈተና የሚፈተኗቸውን ትምህርቶች ብቻ ነው የለየነው፡፡ 12ኛ ክፍል ፈተና ላይ የማይመጡ ትምህርቶችን በሌላ መንገድ እንዲያውቋቸው ጥረት አድርገናል፡፡ ለምሳሌ 14 አካባቢ የነበረው የሃይስኩል ትምህርት ወደ ሰባት ስምንት እንዲወርድ አድርገናል፡፡ ሌሎቹን በሌላ መንገድ እንዲማሩ ማድረግ ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ሥነ ምግባርና ሥነ ዜጋ ትምህርትን በሚዲያም ማስተማር ይቻላል፡፡ የትምህርት ቤቱን ወይም የመምህራንን ትምህርት አሰጣጥ በመቀየር ልታስተምረው ትችላለህ፡፡ በሕይወትም ቢሆን ሥነ ምግባርን እየተማሩ ያድጋሉ፡፡ የአካል ብቃት ትምህርትን ለምሳሌ ሁሉም የራሱን ተሰጥኦ ተከትሎ ክለብ እንዲያቋቁም በማድረግ መሸፈን ይቻላል፡፡ ሌሎችን በዚህ መንገድ በማካካስ 12ኛ ክፍል የሚፈተኗቸውን ትምህርቶች ብቻ እንዲወስዱ እያደረግን ነው ያለነው፡፡

አንድ ሴሚስተር አራት ወር ነበር የነበረው፡፡ እሱን ቀንሰን ሁለት ወር ተኩል አድርገነዋል፡፡ አንዳንድ ትምህርቶች በመታጠፋቸው ወሳኞቹ ትምህርቶች የሚሰጡበት ሰፊ ጊዜ ማግኘት ተችሏል፡፡ ለምሳሌ ፊዚክስ፣ ኬሚስትሪና ባዮሎጂ የመሳሰሉ ትምህርቶች በሳምንት እያንዳንዳቸው አራት ክፍለ ጊዜ ነበር የሚሰጡት፡፡ አሁን ግን ሰፊ ጊዜ በመገኘቱ በሳምንት ስድስት ክፍለ ጊዜ እንዲሰጡ አድርገናል፡፡ በሳምንት ሦስቴ ይሰጡ የነበሩ ወደ አምስት ጊዜ መሰጠት የተቻለበት ዕድልም አለ፡፡ በአጠቃላይ ይህ ፈጣን የትምህርት አሰጣጥ በደንብ ታቅዶና ተዘጋጅተን ወደ መሬት የወረደ ሲሆን ተማሪዎች እየተማሩበት ይገኛል፡፡

ሪፖርተር፡በአወዛጋቢዎቹ አካባቢዎች የሚገኙ ተማሪዎች ዕጣ ፈንታ ምንድነው?

ኪሮስ (ዶ/ር)፡– ይህ ጥያቄ ለእኔ መቅረብ የነበረበት አልመሰለኝም፡፡ እስካሁን እጃችን ላይ አልገቡም፣ ነገር ግን እጃችን ላይ ሊገቡ ይገባል፡፡ የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ ስምንት ወር ሞልቶታል፡፡ በዚያ ስምምነት ላይ ከተቀመጡት ነጥቦች መካከል ደግሞ እነዚህ ሲቪሎች ወደ ነበሩበት ሁኔታ እንዲመለሱ የሚል ይገኝበታል፡፡ ግጭቶች በሕገ መንግሥቱ መሠረት ተፈተው የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ ቦታቸው መመለስ እንዳለባቸው ተቀምጧል፡፡ የውጭ ኃይል ተብሎ የተቀመጠው የኤርትራ ሠራዊት፣ እንዲሁም ከመከላከያ ውጪ ያሉ ታጣቂዎች ተብለው የተቀመጡት የአማራ ታጣቂዎች በስምምነቱ መሠረት ከትግራይ መውጣት አለባቸው፡፡ የትግራይ ሠራዊት በስምምነቱ መሠረት ከባድ መሣሪያዎችን ሲያስረክብ፣ እነዚህ ኃይሎችም እንደሚወጡ ይጠበቅ ነበር፡፡ እስካሁን መውጣት ነበረባቸው፡፡

በትግራይ ክልል በኩል ከባድ መሣሪያ ከማስረከብ በተጨማሪ መደረግ የሚገባቸው ነገሮች በሙሉ እየተተገበሩ ነው፡፡ የስምምነቱ ተፈጻሚነት በአግባቡ እየተከናወነ ነው፡፡ የኤርትራና አማራ ታጣቂዎች ግን እስካሁን በትግራይ ክልል መሬት ላይ ነው የሚገኙት፡፡ እነዚህን ኃይሎች እንዲወጡ ሊያደርግ የሚገባው አካል ነው በእነዚህ አካባቢዎች ለምን ትምህርት አልተጀመረም ተብሎ መጠየቅ ያለበት፡፡ በአጠቃላይ በእነዚህ አካባቢዎች 552 ትምህርት ቤቶች ይገኛሉ፡፡ በምዕራብ ትግራይ 222 ትምህርት ቤቶች በአማራ ታጣቂዎች ሥር ይገኛሉ፡፡ በሰሜን ምዕራብ ትግራይ 75 ትምህርት ቤቶች በአማራ ታጣቂዎች ሥር ሲሆኑ፣ 15 ትምህርት ቤቶች ደግሞ በኤርትራ ታጣቂዎች እጅ ናቸው፡፡ በማዕከላዊ ዞን ደግሞ 12 ትምህርት ቤቶች በኤርትራ ታጣቂዎች እጅ ናቸው፡፡ በምሥራቃዊ ዞንም በተመሳሳይ 46 ትምህርት ቤቶች በኤርትራ ሠራዊት ሥር አሉ፡፡ በደቡብ ትግራይ ዞን 182 ትምህርት ቤቶች በአማራ ታጣቂዎች እጅ ይገኛሉ፡፡

በአጠቃላይ 552 ትምህርት ቤቶች እጃችን አልገቡም ሲባል፣ ካሉን ትምህርት ቤቶች ወደ 22 በመቶዎቹ በእኛ ቁጥጥር ሥር የሉም እንደማለት ነው፡፡ ወደ 2,492 ትምህርት ቤቶች አሉን ሲባል ከእነዚህ መካከል በ552 ወይም በ22 በመቶ ትምህርት ቤቶቻችን ገብተው ሊማሩ የሚገባቸው በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች የመማር መብታቸውን ተነፍገዋል ማለት ነው፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች ተማሪዎች አሁንም ቢሆን ሰቆቃ እየተፈጸመባቸው ይገኛል፡፡ ከእነዚህ ቦታዎች ተፈናቅለው መቀሌ፣ ማይጨው፣ አዲግራት፣ አቢአዲህ፣ ዓድዋ፣ አክሱም፣ ሽሬ፣ ሽራሮ አካባቢዎች በመጠለያዎች ለመኖር የተገደዱ በርካቶች ናቸው፡፡

በእነዚህ አካባቢዎች ብዙ ዓይነት ጉዳት ነው እየደረሰ ያለው፡፡ ለምሳሌ የምዕራብ ትግራይ ሕዝብ ሦስት ቦታ ነው የተከፈለው፡፡ ምዕራብ ትግራይ አሁንም መውጣት ያልቻለው ሕዝብ ብዙ ሥቃይ እያገኘው ነው ያለው፡፡ ወደ ሱዳን የተሰደደው ደግሞ ካምፕ ውስጥ ተጠልሎ ለመኖር እንኳን ሱዳን ባለው ቀውስ የተነሳ ዕድሉ እየጠበበ ነው የሄደው፡፡ ከእነዚህ አካባቢዎች ተፈናቅሎ በትግራይ ክልል አስተዳደር ሥር ባሉ አካባቢዎች በመጠለያ የሚኖረውም ሕዝብ ቢሆን፣ በፈረሱና ገና ምንም ጥገና ባላዩ ትምህርት ቤቶች ነው ልጆቹን ለማስተማር እየተገደደ ያለው፡፡ ይህ ሁሉ ሕዝብ ሥቃዩ ሊቆምና ወደ ቦታው ተመልሶ ለመኖር ይገባል የሚለውን ጉዳይ ሁሉም ሰው የሚመለከተውን አካል መጠየቅ አለበት፡፡ ሰላሙን ሁሉም ሰው የሚፈልገው ከሆነ የሰላም ስምምነቱ ያስገኘውን ውጤት ሁሉም መጠየቅ አለበት፡፡

ሰላም በመፈጠሩ እናንተ ወደ መቀሌ ለመምጣት ችላችኋል፡፡ እኔም ወደ አዲስ አበባ እሄዳለሁ፣ ሌላ ሰውም ይመጣል ይሄዳል፡፡ የሰላም ትሩፋቱን እየተቃመስነው ነው ማለት ነው፡፡ ነገር ግን አሁንም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ወደ ቀዬአቸው አልተመለሱም፡፡ በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ደግሞ ወደ ትምህርት ቤት አልገቡም፡፡ ስለዚህ ለእነዚህ በመጠለያ ለተጠለሉ ሰዎች ሰላም ምናቸው ነው? በጦርነቱ ወቅትም ሆነ አሁንም በካምፕ ውስጥ ነው ያሉት፡፡ ስለዚህ ለእነዚህ ሰዎች የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመበት ከጥቅምት 23 በፊትና በኋላ ያለው ሁኔታ ልዩነት የለውም ማለት ነው፡፡ አሁን ደግሞ የዕርዳታ ሰጪዎች ዕርዳታ በመቋረጡ እነዚህ ዜጎች አስከፊ ሕይወት እየመሩ ነው፡፡ ስለዚህ ስምምነቱም ሆነ ሕገ መንግሥቱ ያስገድዳል፣ እነዚህ ሰዎች ወደ ቦታቸው መመለስ አለባቸው፡፡ የሚመለከተው አካልም ሊጠየቅበት ይገባል፡፡ እንደ ጋዜጠኛ እናንተም በእነዚህ አካባቢ ያሉ ተማሪዎች መቼ ነው ወደ ትምህርት የሚመለሱት ብላችሁ መጠየቅ አለባችሁ፡፡ የኤርትራ ሠራዊት ምን ይሠራል ብለህ የሚመለከተውን አካል ለምን አትጠይቅም? የምዕራብ ትግራይ ተፈናቃዮች መቼ ነው ወደ ቦታቸው የሚመለሱት ብለህ ለምን አትጠይቅም? ይህ እኮ ሁሉም ሰው ሊያነሳው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የተጠናከረ የትምህርት አገልግሎት ለመስጠት ክልሉ ምን ዓይነት ድጋፍ ይፈልጋል? ከፌደራል መንግሥትም ሆነ ከረድኤት ድርጅቶችና ከሌሎች ክልሎች ምን ድጋፍ ትፈልጋላችሁ?

ኪሮስ (ዶ/ር)፡- ትምህርት ቤቶችን መጠገንና በቁሳቁስ ማሟላት ያስፈልጋል፡፡ መምህራኖቻችንን ማሠልጠንና ወደ መደበኛ ሥራ መመለስ ይገባል፡፡ በአጠቃላይ ዘርፈ ብዙ ድጋፎች ያስፈልጋሉ፡፡ የፋይናንስ ወይም የቁሳቁስ ብቻ ሳይሆን ቴክኒካዊ ድጋፎችም ያስፈልጋሉ፡፡ የትግራይ ሕፃናት ባለፉት ዓመታት ብዙ ነገር ደርሶባቸዋል፡፡ በትምህርት ቤት እየተጫወቱ እያለ በድሮን ሳይቀር ተመተዋል፡፡ በሕፃን ዓይናቸው ሊያዩት የማይገባ ብቻ ሳይሆን፣ አዕምሮና ልቦናቸውን የሚጎዳ በየትኛውም ወገን ላይ ሊፈጸም የማይገባ ሰቆቃን ተመልክተዋል፡፡ እነዚህ ታዳጊዎች እንዲህ ተፈጽሞብኝ ነበረ ብቻ እያሉ ሳይሆን፣ በጎም ነገር እያሰቡ ማደግ ነው ያለባቸው፡፡ ሕፃናቱ ይህም ተደርጎልኝ ነበር ብለው በጎ ነገሮችን እያስታወሱ እንዲያድጉ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ሁሉም ሰው እንዲህ እንዲያስቡ የሚያደርግ ድጋፍ ቢያደርግ እላለሁ፡፡ 

እኛ ዛሬ አለን፣ ነገ ግን የለንም እናልፋለን፡፡ ከእኛ በኋላ የሚተኩት ልጆቻችን ናቸው ነገም አብረው የሚኖሩት፡፡ ነገም ቢሆን ከአማራ፣ ከአፋርና ከኤርትራ ጋር ተጎራብተን መኖራችን የማይቀር ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሕፃናት የተደረገባቸውን ብቻ እያሰቡ ከሚኖሩ ካጋጠማቸው ችግር እንዲወጡ የተደረገላቸውን በጎ ነገርም እንዲያስቡ መደረግ አለበት፡፡ መታገዝ ስላለበት ብቻ አይደለም ትግራይን የምታግዘው፡፡ ሰው በመሆንህ ያስገድድሀል፣ መታገዝ ስላለበት ታግዘዋለህ፡፡ ነገር ግን ነገ ለምናስበው የጋራ ሰላምና ዕድገትም ስንል ነው ክልሉ መታገዝ አለበት የምንለው፡፡ ይህ ለነገ ሰላምና አንድነታችን የሚደረግ ኢንቨስትመንት ነው፡፡ ጦርነት ምንም የማይተረፍበት ውድመት ነው፡፡ መሣሪያ ከገዛህ ውድመቱን ለመጀመር በቂ ነው፡፡ ሰላም ግን እንደዚያ አይደለም፡፡ ሥራ ይፈልጋል፡፡ ኢንቨስትመንት ይፈልጋል፣ ልፋት ይጠይቃል፡፡ ነገር ግን ውጤቱ የሚትረፈረፍ ነው፡፡

ሰላም ለሰው ብቻ ሳይሆን ለእንስሳውም ሆነ ለሳር ቅጠሉ ሁሉ ያስፈልጋል፡፡ ጦርነት ለመጀመር ቀላል ነው፡፡ መጀመሪያ ትፎክራለህ፣ ከዚያ እውነትን ትቀብራለህ፣ ተከትሎ ደግሞ መግደል ትጀምራለህ፡፡ ያሳለፍነው ጦርነትም ልክ እንደዚሁ ነበር አጀማመሩ፡፡ ከጦርነቱ ቀድሞ ሚዲያዎች ታስተላልፉት የነበረው ዘገባ፣ ዶክመንተሪውና ሌላው ነገር ግጭት ቀስቃሽ ነበር፡፡ የጥላቻና የፍረጃ ንግግሮች ነበሩ፡፡ እነዚህ ሁሉ እውነት መቅበሪያ መንገዶች ነበሩ፡፡ አሁን ሰላም መጥቷል፡፡ ሰላም ሲመጣ ደግሞ የመጀመሪያው ነገር መሆን ያለበት የተቀበረውን እውነት ማውጣት ይሆናል፡፡ ስለዚህ ትግራይ ላይ የደረሰውን ነገር በሙሉ ፈልፍሎ በማውጣት ሚዲያዎች፣ የኒቨርሲቲዎች፣ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች፣ ሲቪክ ማኅበራትና ሌሎችም ሊሠሩበት ይገባል፡፡ እውነቱን አውጥቶ ፍትሕ የሚገባውን ፍትሕ መስጠት አስፈላጊ ነው፡፡ ይቅር የምንባባልበትና ካሳ የሚያስፈልገውን መለየት ያስፈልጋል፡፡ ለትግራይ የሚደረገው ዕርዳታ ይህንም ያካተተ ሊሆን ይገባል የሚል እምነት ነው ያለኝ፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች