Saturday, September 23, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትየኢትዮ ቴሌኮም የፓርላማ ሪፖርት ጥያቄና ማብራሪያ በሰብዓዊ መብቶችና በሕግ የበላይነት ዓይን

የኢትዮ ቴሌኮም የፓርላማ ሪፖርት ጥያቄና ማብራሪያ በሰብዓዊ መብቶችና በሕግ የበላይነት ዓይን

ቀን:

በገነት ዓለሙ

ከአምባገነንነት ወጥቶ ወደ ዴሞክራሲ ለመግባት፣ በመንበረ መንግሥቱ አውታራት ላይ የደረሱ ብልሽቶችን ለማስወገድ፣ በአስተሳሰብና በማኅበራዊ ግንኙነቶች ውስጥ የተፈጠሩ አደጋዎችን ለማስወገድ የተጀመረው ለውጥ አንዱ ምልክት አሁንም ሲውለበለብ የምናየው፣ በ2011 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ በወጣው የኮሙዩኒኬሽን ሕግ ውስጥ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲ መገንባት ማለት የመንግሥት ተቋማትን ገለልተኛና ነፃ አድርጎ ማቋቋም ይጠይቃልና የኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሕጉ፣ ‹‹…የቴሌኮሙዩኒኬሽን ገበያውን እንደ አገር ለማዋቀርና በቴሌኮሙዩኒኬሸን ገበያ ውድድርን ለማስፈን [አገር የነደፈውን] የፖሊሲ አቅጣጫ ለማሳካት ነፃ፣ ግልጽና ተጠያቂነት ያለው ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን አስፈላጊ በመሆኑ›› ብሎ መነሳቱ በራሱ አንድ ዕርምጃ ወደፊት ነበር፡፡

ከረዥም ጊዜ ጀምሮ፣ በተለይም ከ1945 ዓ.ም. ጀምሮ በአገር የበላይና ከፍተኛ ሕግ ውስጥ ሲጻፉ ከኖሩ መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች መካከል ሁለቱ ዛሬ የምንነጋገርበት የኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት እንደ ፍጥርጥሩ ወይ የሚደፍቃቸው፣ መብትና ነፃነታቸውን ድምጥማጡን የሚያጠፋባቸው፣ አለዚያም የሚያለመልማቸው፣ የሚያበለፅጋቸው ናቸው፡፡ ከምንነጋገርበት የሕይወት ዘርፍ አኳያ የምናተኩርባቸው መብቶችና ነፃነቶች የአንቀጽ 27 (የግል ሕይወት/ግላዊነት) እና የአንቀጽ 29 (የአመለካከትና ሐሳብን በነፃ የመያዝና የመግለጽ) መብቶች ናቸው፡፡ መሠረታዊ መብቶቻችንና ነፃነቶቻችን የተደነገጉበትና የተዘረዘሩበት የሕገ መንግሥቱ የምዕራፍ ሦስት መግቢያ የእነዚህን መብቶችና ነፃነቶች ተፈጻሚነትና አተረጓጎም ይደነግጋል፡፡  

በማንኛውም ደረጃ የሚገኙ የፌዴራል መንግሥትና የክልል ሕግ አውጪ፣ ሕግ አስፈጻሚና የዳኝነት አካሎች በዚህ ምዕራፍ የተካተቱትን ድንጋጌዎች የማክበርና የማስከበር ኃላፊነትና ግዴታ አለባቸው፡፡ እንዲሁም እነዚህ መሠረታዊ የመብቶችና የነፃነቶች ድንጋጌዎች ኢትዮጵያ ከተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ሕግጋት፣ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶችና ዓለም አቀፍ ሰነዶች መርሆዎች ጋር በተጣጣመ መንገድ ይተረጎማሉ ይላል፡፡ የጠቀስኩት የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 13 የአማርኛው ቅጂ ሦስት ጊዜ ደጋግሞ ‹‹ዓለም አቀፍ…›› እያለ የሚያነሳቸው ሰነዶች ዓይነትና ምንነት/ማንነት ያሳስታልና የእንግሊዝኛውን ቅጂ እንዳለ የማቀርበው ተራ የትርጉም ሥራ እንዲሠራልን ነው፡፡ (አንቀጽ 13 (2) English)

The fundamental rights and freedoms specified in this Chapter shall be interpreted in a manner conforming to the principles of the Universal Declaration of Human Rights, International Covenants on Human Rights and International instruments adopted by Ethiopia.  

በዚህ ግልጽ ድንጋጌ መሠረት የሰብዓዊ መብቶችና ነፃነቶቻችን ተፈጻሚነትና አተረጓጎም የውኃ ልካችን ኢንተርናሽናል ቢል ኦፍ ራይትስ ናቸው፡፡

እዚህ መለኪያና እዚህ የውኃ ልክ ውስጥ ከሚካተቱ ሕጎችና መርሆዎች መካከል አንዱ፣ ‹‹Declaration of Principles on Freedom of Expression in Africa›› ነው፡፡ የዚህ የአፍሪካ የሰብዓዊና የሕዝቦች መብቶች ኮሚሽን ዲክላሬሽን መርህ/ፕሪንሲፕል ሰባት ላይ የሚከተለውን ይደነግጋል፡፡

Regulatory Bodies for Broadcast and Telecommunications

  1. Any public authority that exercises powers in the areas of broadcast or telecommunications regulation should be independent and adequately protected against interference, particularly of a political or economic nature.
  2. The appointments process for members of a regulatory body should be open and transparent, involve the participation of civil society, and shall not be controlled by any particular political party.
  3. Any public authority that exercises powers in the areas of broadcast or telecommunications should be formally accountable to the pubic through a multi-party body.

በዚህ ረገድ የኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት አዋጅ ቁጥር 1148/2011 በመግቢያው ላይ የተገለጸውን የ‹‹ነፃ፣ ግልጽና ተጠያቂነት ያለው ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ማቋቋም አስፈላጊ›› መሆኑን መንግሥት መረዳቱ፣ ከዚህም መነሳቱ ቀደም ሲል እንደተገለጸው ትልቅ መነሻ ነው፡፡ ሕጉ በዚህ ብቻ ሳይወሰን ‹‹ነፃና ገለልተኛ›› ማለትን ተርጉሟል፡፡ ‹‹በአሠራር ተለይቶ የተቋቋመ በዚህ አዋጅ የተሰጠውን ሥልጣንና ተግባር ከማንኛውም ወገን ተፅዕኖ ነፃ ሆኖ በግልጽነትና በተጠያቂነት የሚፈጸምና ውሳኔ የሚሰጥ የመንግሥት ተቋም›› መሆኑ፣ ይህም ተቋም የኢትዮጵያ የኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን መሆኑ ተደንግጓል፡፡ ኢትዮጵያን ወደ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር የመለወጥ ዋና መሠረታዊ ቁምነገርና ግዳጅ፣ በአጠቃላይ ከየትኛውም ፓርቲ ወይም ቡድን ወገናዊነት ነፃ የሆነ የተቋም ግንባታ ይፈልጋል፡፡ የአገሪቱን የመንግሥት አውታራት ፓርቲያዊነት ማፅዳት ያስፈልጋል፡፡ የእነዚህን ተቋማት ነፃነትና ገለልተኛነት የሚወስነው ለምሳሌ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን፣ የሚዲያ ባለሥልጣን፣ ወዘተ የመሳሰሉትን ተፅዕኖ፣ ከጣልቃ ገብነት የተከለሉ/የተጋረዱ መሆናቸውን ከመልክና ከስም ያለፈ እውነት የሚያደርገው፣ ከፖለቲካ ቡድን መዳፍ ነፃ መሆናቸውን የሚያረጋግጠው ነፃና ገለልተኛ ተብለው በሕግ መቋቋማቸው ብቻ አይደለም፡፡

ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነው ቴሌኮሙዩኒኬሽንን ወይም የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎትን የሚቆጣጠሩና የሚሰጡ ተቋማትን የሚመለከተው ረዥም ጊዜ የኖርንበት፣ ወይም የኖረብን ልምዳችን ብዙ ነገር ያስመዘገበ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ቦርድ (በንጉሡ) እና በኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን (በደርግ) ዘመን አገልግሎት ሰጪውንና ተቆጣጣሪውን አካል ወይም የንግድ ሥራውን የሚሠራውንና የመንግሥቱን የቁጥጥር ተግባር የሚያከናውነውን አካል መለየትና ለየብቻ ማቋቋም ‹‹አላስፈለገም›› ነበር፡፡ በቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ዘርፍ፣ የኢትዮጵያ የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣንና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓይነት ወይም እንደ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክና የ(ኢትዮጵያ) ንግድ ባንክ ያለ ልዩ ልዩነት የአገልግሎት ሰጪው መሥሪያ ቤትና የተቆጣጠሪው ባለሥልጣን የየብቻ ህልውና አልነበረም፡፡ ‹‹የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ይበልጥ ቀልጣፋና አስተማማኝ ለማድረግ የቁጥጥር ተግባር የሚያከናውነውን አካል አገልግሎቱን ከሚሰጠው ድርጅት ለይቶ ማደራጀትና ቁጥጥሩ የሚካሄድበትን ሁኔታ መደንገግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ›› ተብሎ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ኤጀንሲ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን፣ በሌላ በኩል ደግሞ መጀመርያ የኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬሽን (አሁን ኢትዮ ቴሌኮም) የተባለው የልማት ድርጅት ለየብቻቸው የተቋቋሙት በ1989 ዓ.ም. ነው፡፡ በ1989 ዓ.ም. በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 10/89 ለመጀመርያ ጊዜ የመንግሥት የልማት ድርጅት ሆኖ ለብቻ የተቋቋመውና በተግባር ብቻ ሳይሆን በሕግ ጭምር ‹‹ብቸኛ የሆነው የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሰጪ ድርጅት›› (በአዋጅ ቁጥር 281/1994) ኮርፖሬሽን (አሁን ኮርፖሬሽኑን የተካው ኢትዩ ቴሌኮም ከውስጡ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ተለይቶ እንዲወጣ ቢፈቅድም፣ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ገበያውን ለውድድር የከፈተ ሕግ እስኪወጣና በተለይም ‹‹ኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን›› የተባለ ተቆጣጣሪ በአዋጅ እስኪቋቋም (ነሐሴ 2011 ዓ.ም.) ድረስ ኢትዮ ቴሌኮም ‹‹ተቆጣጣሪ›› የሌለበት፣ የምትከተለውና የምትገዛበት ሕግ አለህ፣ የማታልፈው ቀይ መስመር አለ የሚለው ‹‹ጠያቂ›› የሌለበት፣ በተለይም መንግሥት እንዳሻው የሚያዘው ብቸኛው ቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሰጪ ድርጅት ሆኖ ኖሯል፡፡ ይህንን ለዚያውም ስፈራ ስቸር በደንብ ያልገለጽኩትን የኢትዮ ቴሌኮም በዚያው በጥንቱ መንገድ፣ ተቆጣጠጣሪ የሌለበት ሆኖና መስሎ የመቀጠሉን ነገር አናምንም፣ ወይም አይገባንም፣ ወይም እንጠራጠራለን የሚሉ ካሉ ጉዳዩን ከተቆጣጣሪው ማለትም ከኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ኤጀንሲ ማዕዘን እንዲያዩት አሳስባለሁ፡፡ እንደ ሲቪል አቪዬሽን፣ እንደ ብሔራዊ ባንክ ለየትና ከፍ ያለ የመንግሥት ሥልጣን የተሰጠው ኤጀንሲ በሕግ የተወሰነውን የተቆጣጣሪነት የመንግሥት ሥልጣንና በዚህ ላይ የተመሠረተውን የንብረትና የሥራ ድርሻ ክፍፍል እንኳን በቅጡ ሳይረከብ፣ በአዲሱ የኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን የተተካ ተቋም ነው፡፡

ባለፈው ሳምንት ሰኔ 16 ቀን 2015 ዓ.ም. የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮ ቴሌኮምን የዘጠኝ ወራት ሪፖርት ሲያደምጥ የተሰሙትና የተነሱት ጉዳዮች ሁሉ፣ በመንግሥት የልማት ድርጅት ግቢ ውስጥ የሚሽከረከሩ ነበሩ፡፡ የመንግሥት የልማት ድርጅት በመንግሥት ይዞታ እስካለ ድረስ ውጤታማ፣ ምርታማና አትራፊ እንዲሆን መዋቀርና ሥርዓት ስለመዘርጋቱ፣ እንዲሁም ብቸኛው ተቋም መሆኑ ቀርቶ አዲስ ከገባው የግል ኩባንያ ጋር እየተወዳደረ ለመሥራት የሚያስችለውን ብቃትና ዝግጁነት እየያዘ ስለመሆኑ፣ የኮሙዩኒኬሽን አገልግሎቱ ‹‹ሁሉን አቀፍ ተደራሽነት›› ምን እንደሚመስል የሚመረምርና የሚጠይቅ ነበር፡፡ ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የቀረበውና ውይይት/ጥያቄና መልስ የተደረገበት ሪፖርት ከኮሚቴው ‹‹ሥልጣን›› ውጪ የሆነ የመሰለ ጥያቄ ያነሳው፣ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ኦፕሬተሩ በሚሰጠው የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ላይ ከጥር 2015 ዓ.ም. በኋላ ወይም ጀምሮ ገደብ መጣሉ፣ ይህም ገደብ በደንበኞቹ ላይ ችግር እየፈጠረ መሆኑ በተነሳበት ወቅት ነው፡፡

ጉዳዩ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን (ኢቲቪ) የዕለቱ የምሽት ዜና ውስጥ ተካትቶ የዜናው መክፈቻ ዓረፍተ ነገርም መሆን ችሎ ነበር፡፡ ‹‹በኢትዮጵያ ኢንተርኔት ላይ የተደረገው ገደብ ደንበኞች ላይ ችግር እየፈጠረ መሆኑን ኢትዮ ቴሌኮም አስታወቀ፡፡ ኢንተርኔትን ከቪፒኤን ማላቀቅና ገደቡን ማንሳት የተቋሙ የኢትዮ ቴሌኮም አለመሆኑን አስታውቋል›› ነበር የዜናው መክፈቻ፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ኢትዮ ቴሌኮም ገደብ መደረጉን፣ የተደረገው ገደብም በደንበኞቹ ላይ ችግር መፍጠሩን ያስታወቀው የሪፖርቱ አካል አድርጎ አይደለም፡፡ ኋላ ላይ ተጠይቆ፣ ‹‹…የአጠቃቀም ገደብ ይጣላል፣ ገደቦች ይጣላሉ… ገደብ ተጥሎ ነበር፣ ገደብ እየተጣለ ስለሆነ ለምን እስካሁን አልተነሳም?›› ብለው ጥያቄ ያቀረቡት ለዚያውም ከኢንዱስትሪ ቋሚ ኮሚቴ ተጋብዘው የተገኙት አባል ናቸው፡፡ በዚህ ጥያቄና ለጥያቄውም በተሰጠው (ሊሰጥ በተሞከረው) መልስ አማካይነት ነው፡፡ አሁን የምንነጋገርበትን፣ ከፍ ሲል በተጠቀሱት ሁለት መብቶችና ነፃነቶች ላይ የመንግሥት፣ የመንግሥት አግባብ ያለው ተቆጣጣሪ ባለሥልጣንና ወይም የሕግ ማስከበር ሥራ ላይ የተሠማሩ የመንግሥት አካላት፣ እንዲሁም የቴሌኮሙዩኒኬሽን ኦፕሬተሮች ብዙ ጊዜ የሚሸሸው፣ የማይደፈረውና የሚድበሰበሰው ሚና፣ ሥልጣን የተነካካው፣ ጫር ጫር የተደረገው፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም ሪፖርት በቀረበበት የፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ መድረክ ላይ በዚህ ሁኔታ እንደነገሩ የተነሳው፣ የ‹‹ማንኛውም ሰው ያለ ምንም ጣልቃ ገብነት ሐሳቡን የመግለጽ ነፃነት›› ላይ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ኦፕሬተሮች (የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት በመስጠት ሥራ ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎች) ሚና ነው፡፡ በዚህ ነፃነታችን ላይ፣ ማለትም ሕገ መንግሥቱ ላይ እንደተተረጎመውና እንደ ተፍታታው ‹‹በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ ወሰን ሳይደረግበት በቃልም ሆነ በጽሑፍ ወይም በኅትመት፣ በሥነ ጥበብ መላክ ወይም በመረጠው በማናቸውም የማሠራጫ ዘዴ ማንኛቸውም ዓይነት መረጃና ሐሳብ የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሠራጨት›› ነፃነታችን ላይ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ኦፕሬተሩ (ኢትዮ ቴሌኮም ሆነ ሳፋሪኮም) ምን ሊያደርጉ ይችላሉ? ፓርላማው መድረክ ላይ ዋና ጉዳይ ሆኖ ያልተነሳው፣ ምናልባትም በገደምዳሜ የተካነው የገደብ ነገር፣ የመዝጋት ነገር አሠራሩና ዝርዝሩ ቢፈራም ቢሸሽም ግልጽ መልስ የተሰጠው ግን ይህ ነገር የቴሌኮሙዩኒኬሽን ኦፕሬተሩ ‹‹የኢትዮ ቴሌኮም ማንዴት አይደለም›› ተብሎ ነው፡፡ ትርጉሙ ኩባንያው ይዘጋ ይከፈት የሚል ሥልጣን የእሱ አይደለም ማለት ነው፡፡ ‹‹የሚመለከተው የመንግሥት አካል… ከቪፒኤን ውጪ አክሰስ እንዲደረግ ፈቃድ ሲሰጠን…›› ችግሩን እንፈታለን መባሉንም ውይይቱ ውስጥ ተረድተናል፡፡

ተቋም በሚገነባ አገር ውስጥ፣ የተቋም ግንባታ ሥራው ከፓርቲም ሆነ ከሌላ አካል ወገናዊነት የፀዱ ሆነው በሕግና ለሕግ የሚገዙ፣ ገለልተኛ፣ ነፃ፣ የሕዝብን የመታመን ክብር ያገኙ ተቋማትን መገንባት ጭምር የአገርና የለውጡ አደራ በሆነበት አገር ውስጥ፣ ኢትዮ ቴሌኮም በዚህ ጉዳይ ሚናው ምን እንደሆነ የአሠራር ግልጽነትና ተጠያቂነት በሚፈቅደው ማዕቀፍ ውስጥ በቂ መግለጫና ተገቢ መልስ መሰጠት ያለበት ይመስለኛል፡፡ ዝም ብሎ ሆድ ይፍጀው የሚባል፣ መድበስበሱም የሚመረቅና ከተጠያቂነት ነፃ የሚደረግ አይደለም፡፡ ሪፖርት አቅራቢዋ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ፣ ‹‹ማንዴቱ የእኛ አይደለም፣ ይህንን ዕርምጃ የወሰደው የመንግሥት አካል ምክንያት አለው…›› ብለው ሲናገሩ፣ የእናንተ ሚና የኦፕሬተሮች የሥራ ድርሻና ኃላፊነት ትዕዛዝ መፈጸም፣ የተባሉትን ማድረግ ብቻ ነው? ‹‹ምክንያት አለው›› የሚሉት የሥልጣን አካልስ ከተቆጣጠሪው ባለሥልጣን ውጪ ያለ ጭምር ነው? ይህንንስ የሚገዛ፣ ሌላው ቢቀር አዲስ የመጣባችሁን ተወዳዳሪ ሆኖ በአሸናፊነት የመወጣት ከዚህ በፊት የማታውቁትን ፈተና የሚያግዝ የምትከተሉት ሕግና ደንብ አላችሁ? መመለስ ያለበት ዕርምና ነውር መሆኑ ሊቀር የሚገባ የአሠራር ግልጽነት መላኪያችሁ ነው፡፡

አዎ ነፃ ተቋም በመገንባት ሒደትና ይዘት ውስጥ የወጣው የኮሙዩኒኬሽን ሕግ/አዋጅ ቁጥር 1148/2011) ከሌሎች መካከል ለምሳሌ፣ ‹‹…የቴሌኮሙዩኒኬሽን ኦፕሬተሮች ኔትወርካቸውን ማለትም ለቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት አቅርቦት የሚውሉ የቴሌኮሙዩኒኬሽን መስመሮችና ተዛማጅ የማዞሪያ ሥርዓቶች) ለተፈቀደለት የመንግሥት አካል ሥልጣን ባለው ፍርድ ቤት በተሰጠው ትዕዛዝ መሠረት ተደራሽ ማድረግ አለባቸው ይላል፡፡ ይህ በተጨባጭ በተግባር እንዴት ይፈጸማል? የተፈቀደለት ባለሥልጣን ‹‹ምክንያት አለው››? የለውም? የምትወጡበት የአሠራር ፖሊሲ አለ? ገደብ የሚያደርገው፣ ‹‹ይዘጋ›› የሚለው፣ ወይም የፍጥነት ወሰን ላይ ‹‹ይቀነስ›› የሚባለው በሩቅ መቆጣጠሪያው ነው? ወይስ እናንተ ጋ ሆኖ ነው? የዚህስ ወጪ የመንግሥት (የታክስ ከፋዩ) ወይስ የኩባንያው (የደንበኞች) ነው? ሊነግሩን፣ ሊያብራሩ የሚገቡ የማናውቃቸው በርካታ እንደ ማይም (እንደ አላዋቂም እንደ ደንበኛም) የምናቀርባቸው ጥያቄዎች ናቸው፡፡

ይህ ጉዳይ ከጠቀስናቸው ሁለት መብቶች መካከል የአንዱ ሐሳብን በነፃ የመግለጽ ነፃነትን ብቻ የሚመለከተው ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 26 የተደነገገው የግለኝነት መብትም ሌላው ነፃነታችን ነው፡፡ እዚህም ላይ ቴሌ ያለውን የአሳላጭነትም ሆነ በሕግ መሠረት የቁጥጥር ‹‹ሚናና አስተዋጽኦ›› ማወቅ መብቶቻችን ነው፡፡ አትራፊም  የተዋጣለት የቴሌኮም ኦፕሬተር ሆኖ በአሸናፊነት የመውጣት መለኪያውም ይህንን ሁሉ አሟልቶ ነው፡፡

የቴሌፎን ንግግራችንም ሆነ የፖስታ ግለኝነት መብት ሕጎቻችን የቴሌፎንና የፖስታን ሥልጣኔ ያህል ረዥም ዕድሜ አላቸው፡፡ ለምሳሌ የ1958 ዓ.ም. የፖስታ አገልግሎት አዋጅ ይህንን ይደነግጋል፡፡

የግለኝነት ማረጋገጫ

  1. የፖስታ ግለኝነት በዚህ አዋጅ ተረጋግጧል፡፡ ስለሆነም በአገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ ሁናቴ በሚታወጅበት ወቅት ፖስታን መመርመር ይቻላል፡፡
  2. ለፖስታ ቤት የተሰጠ ማንኛውንም ፖስታ መክፈት፣ ማንበብ፣ መጣል፣ መቅደድ፣ መደበቅ ወይም መስረቅ ለማንም አይፈቀድም፡፡ የፖስታ ቤት ሠራተኛ በሥራው ምክንያት ያየውንና የሰማውን ማንኛውንም ነገር በማናቸውም ጊዜ ላልተፈቀደለት ሰው እንዳይገለጽ ተከልክሏል፡፡
  3. ማንኛውም አመላላሽ በኃላፊነቱ እንዲያደርስ በተሰጠው የፖስታ ከረጢት ላይ ጥፋት እንዳያደርስ ተከልክሏል፡፡

ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 26/9 (1)፣ (2) እና (3) የሚከተለውን ይደንግጋል፡፡

የግል ሕይወት የመከበርና የጠበቅ መብት

  1. ማንኛውም ሰው የግል ሕይወቱና ግላዊነቱ የመከበር መብት አለው፡፡ ይህ መብት መኖሪያ ቤቱ፣ ሰውነቱና ንብረቱ ከመመርመር፣ እንዲሁም በግል ይዞታው ያለ ንብረት ከመያዝ የመጠበቅ መብትን ያካትታል፡፡
  2. ማንኛውም ሰው በግል የሚጽፋቸውና የሚጻጻፋቸው፣ በፖስታ የሚልካቸው ደብዳቤዎች፣ እንዲሁም በቴሌፎን፣ በቴሌኮሙዩኒኬሽን፣ በኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች የሚያደርጋቸው ግንኙነቶች አይደፈሩም፡፡
  3. የመንግሥት ባለሥልጣናት እነዚህን መብቶች የማክበርና የማስከበር ግዴታ አለባቸው፡፡ አስገዳጅ ሁኔታዎች ሲፈጠሩና ብሔራዊ ደኅንነትን፣ የሕዝብን ሰላም፣ ወንጀልን በመከላከል፣ ጤናንና የሕዝብን የሞራል ሁኔታ በመጠበቅ፣ ወይም የሌሎችን መብትና ነፃነት በማስከበር ዓላማዎች ላይ በተመሠረቱ ዝርዝር ሕጎች መሠረት ካልሆነ በስተቀር፣ የእነዚህን መብቶች አጠቃቀም ሊገድብ አይችልም፡፡  

ሕገ መንግሥቱ የበላይ ሆኖ የሚገዛውን በግለኝነት ላይ የሚደረገውን የተለየ ገደብ እዚያ ፖስታ መዘርዘሪያ ሕንፃና የቴሌኮሙዩኒኬሽን ማዞሪያ ሥርዓት ውስጥ እንዴት ሆነው ይፈጸማሉ? ብዙ ጊዜ በምንሰማቸው የከፍተኛ ጉዳዮች ክስ ሒደት ውስጥ የመገናኛ ብዙኃን፣ ዓቃቤ ሕግ (ወይ በፀረ ሙስና ወይም በሽብር፣ አለዚያም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በማፍረስ ሙከራ ክስ) የስልክ ንግግር ከቴሌ ተገልብጦ እስኪሰጠው ድረስ ቀጠሮ ጠየቀ ሲባል እናውቃለን፡፡ ‹‹ሰውም አልጠየቀ፣ ቴሌም/መንግሥትም አይናገር›› የሚባለው ግን ይህ ሥራ እንዴት እንደሚሠራ ነው፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ሲጠየቁ፣ መልስም ሲሰጥባቸው የፓርላማውም የተቆጣጣሪነት ሥልጣን ተፈጻሚ ሲሆን ማየት ያለብን ኢትዮ ቴሌኮም ወይም ፖስታ ቤት ሪፖርት የሚቀርቡበት ቋሚ ኮሚቴ የግድ ‹‹የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሲሆን ብቻ አይደለም፡፡ የልማት ድርጅቶች ቋሚ ኮሚቴም ከሌሎች ኮሚቴዎች ያልተናነሰ የቁጥጥር ሥልጣን አለው፡፡ እንዲያውም ይህ የልማት ድርጅቶች ቋሚ ኮሚቴ ሊያስተዋውቀውና የሚቆጣጠራቸው በርካታ የልማት ድርጅቶች የዓይን ብርሃን የእግር መንገድ ሊሆን የሚገባው፡፡ በአገራችን ውስጥ ብዙም የማይታወቅ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ‹‹GUIDING PRINCIPLES ON BUSINESS AND HUMAN RIGHTS›› የሚባል ሰነድ አለ፡፡ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 13 (2) ከሰብዓዊ መብቶችና ነፃነቶች አተረጓጎም ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የመንግሥትም ሆነ የግል የንግድ ሥራ ተቋማት የመንግሥታቱ ድርጅት የ‹‹Protect, Respect and Remedy›› ማዕቀፍ ነው፡፡  

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...