እነሆ፤ ስለጥበቤ ሐሳብ ገባኝ፤ ብዙ ማር እንዳከማቸ ንብ ለመውሰድ የተዘረጉ እጆች አስፈለጉኝ። ወዲያ ለመስጠትና ለማደል እፈልጋለሁ። በሰዎች መካከል ያሉት ጠቢባን በሞኝነታቸው፤ ድሆችም በሀብታቸው እስኪደሰቱ ድረስ። በዚህ ዓላማ ምክንያት አሁን ቁልቁል መውረድ አለብኝ። በየምሽቱ እንደምታደርጊው፤ በባሕሩ ማዶ አልፈሽ በታችኛው ዓለም ላሉት ብርሃን ሰመስጠት እንደምትሄጅ፤ እጅግ ባለጸጋዋ ኮከብ ሆይ። እኔም እንዳንቺ ወደታች “መጥለቅ” አለብኝ፤ የምወርድላቸው ሰዎች እንደሚሉት። ከመጠን በላይ የሆነውን ደስታ እንኳ ያለቅናት የምታይ፤ ሰላምን የተመላሽ ዐይን ሆይ፤ እንግዲህ መርቂኝ። ተርፎ ለመፍሰስ የሚፈልገውን ዋንጫ መርቂ፤ ውሀው ከሱ እንደ ወርቅ ይፈስ ዘንድ፤ የደስታሽንም ማንጸባረቅ (ሪፍሌክሽን) ወደመላው ዓለም ይሸከምልሽ ዘንድ። እነሆ ይህ ዋንጫ እንደገና ባዶ ለመሆን ፈለገ፤ ዘራቱስትራም ዳግመኛ ሰው ለመሆን ተመኘ። የዛራቱስትራ ወደታች መውረድ እንደዚህጀመረ።» ኒቼ የሚባለው ትልቅ የሐሳብ ሰው የቀረጸው የአስተማሪ ምሳሌ ነው። ደራሲው ለፈለገው ትልቅ ዓላማ አንድ እንዲህ ያለ ሰው አስፈላጊው ነበር። በመጀመሪያ ይህንን እንመልከት። የሰውን ልጅ በአስተማሪነት የረዱት የዓለም ታላላቅ ሰዎች ሁሉ ከቀድሞ ዘመን ነቢያት፤ ፈላስፎችና መምህራን ጀምሮ እስከ ዛሬዎቹ ፕሮፌሰሮችና አስተማሪዎች ድረስ አንድ የሚደነቅ የሕይወት ምልክት እናይባቸዋለን። ይህም ብቸኝነት ፤ ብሕትውና ነው። የትልቅነት መገኛው ምንጭ ብቸኝነት ነው። ከገዛ ራሱ ውስጥ በገዛ ራሱ ጥረት አንድ ትልቅ ነገር የሚያስገኝ ሰው እሱ ትልቅ ይባላል። ዘዴው በብሕትውና ወይም በብቸኝነት ከገዛ መንፈስ ጋር መታግል ነው። ኦሆ በሐሊ፤ ያርጋጅ አናጓጅ ፤በደመቀበት ቦታ ሁሉ የሚያበጭብ አንድም የተለየ ነገር ለማስገኘት አይችልም።
– እጓለ ገብረ ዮሐንስ “የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ” (1955)