ሕይወቱ ከመርካቶ ጋር የተቆራኘው የልዑል መኰንን ኃይለ ሥላሴ ት/ቤት አገራቸውን በተለያያ መስክ ያገለገሉና በማገልገል ላይ የሚገኙ አያሌ ምሩቃንን አፍርቷል። አውሮፕላን አብራሪዎች (የሴት አብራሪ ሳትቀር)፣ አርኪቴክቶች፣ ምክትል ሚኒስትሮች፣ የመምሪያ ኃላፊዎች፣ ፕሮፌሰሮች፣ ወዘተ …። በግሌ በአካዳሚው ዓለም ስኬታማ እየሆንኩ ስሄድ ብዙ ጊዜ ሰዎች ይጠይቁኝ የነበረው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን የት እንዳጠናቀቅኩ ነበር። አጠያየቃቸው ዊንጌት ወይ ተፈሪ መኰንን ወይ ኮተቤ ብዬ እንድመልስላቸው እንደ ሆነ ይገባኛል። እኔም “ልዑል መኰንን” ብዬ ስመልስላቸው በመገረም መርካቶ?! ብለው መልሰው ይጠይቁኛል። እኔም ደረቴን ነፍቼ “ አዎ! መርካቶ!” እላቸዋለሁ። አዎ! መርካቶ የሸቀጥ መቸርቸሪያ ብቻ ሳትሆን የዕውቀት አምባም ነበረች፤ ነችም።
– ባሕሩ ዘውዴ “ኅብር ሕይወቴ ግለ ታሪክ” (2015)