Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየውጭ አገር ሕክምና ጉዞን የመቀነስ ትልም

የውጭ አገር ሕክምና ጉዞን የመቀነስ ትልም

ቀን:

‹‹እኔ ነኝ ደራሽ ለወገኔ፣ እኔ ነኝ፣

እሱ ነው እኔን ሰው ያደረገኝ ያቆመኝ፤›› ይህን ስንኝ በውስጡ የያዘው ሙዚቃ በአዲስ አበባ ሕዝብ በሚተራመስባቸው ጎዳናዎች፣ የታክሲ መነሻዎችና መድረሻዎች እንዲሁም በመገበያያ ቦታዎች ማዳመጥ የተለመደ ነው፡፡

ለልመና የዋለውና በብዙዎች አዕምሮ ውስጥ ተቀርፆ የቀረው ሙዚቃ፣ በአዲስ አበባ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን በክልል ከተሞችም እየተለመደ ከመጣ ሰነባብቷል፡፡

ከሙዚቃው ጀርባ አንድ በሕመም እየተሰቃየ የሚገኝ ሰው መኖሩን የሚያመለክቱ ወጣች ካርቶን ይዘው ገንዘብ ሲለምኑም ማየት ተለምዷል፡፡ እነዚህ ለዕርዳታ እጃቸውን የሰጡ ሰዎች ቀሪ ዘመናቸውን ለመኖር ውጭ ሄዶ መታከምን የሚሹ ናቸው፡፡

ሕክምናን በአገር ውስጥ ማገኘት ባለመቻላቸው፣ ወደ ውጪ አገር አምርተው ለመታከም ደግሞ አቅም ስለሚያጥራቸው ለልመና ወደ ጎዳና እንደሚወጡም በማስረጃ አስደግፈው የሚገልጹ አሉ፡፡

ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ተይዘው የውጭ ሕክምናን ከሚሹና ልመና ከሚደረግላቸው መካከል የልብ ሕሙማንም ይጉኙበታል፡፡

ጤናማ ካልሆነ የአኗኗር ዘይቤ፣ ከታይፕ 2 ዳያቤቲክ ከጭንቀት፣ ከፍተኛ የደም ግፊት፣ በደም ውስጥ ከሚገኝ ከፍተኛ የስብ መጠን፣ ከማጨስና በተለያዩ ምክንያቶች የሚከሰተው የልብ ሕመም ሕፃናትንም የሚያጠቃ ነው፡፡

በኢትዮጵያ የልብ ሕመም በሕፃናት ላይ ሳይቀር እየጠናና አሳሳቢ ደረጃ ላይ እየደረሰ ቢሆንም፣ በአገሪቱ በቂ ሕክምና አለመኖሩና ዘመናዊ ሕክምና መስጠት የሚያስችሉ ሆስፒታሎች ውስን መሆናቸው ችግሩን ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› አድርጎታል፡፡

በመንግሥት በኩል በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሚገኘው የሕፃናት ልብ ሕሙማን መርጃ ማዕከልም በአላቂ ዕቃዎች እጥረት ምክንያት የዕቅዱን ያህል መሄድ አልቻለም፡፡ በግል ለማሳካም ደግሞ ወጪው የሚቻል አይደለም፡፡

ሆኖም ሕክምናውን በአገር ውስጥ ማግኘት እንዲቻልና ወደ ውጪ አገር የሚደረገውን የሕክምና ጉዞ ለመቀነስ ዘመናዊ ሆስፒታሎችን በአገር ውስጥ የሚገነቡ ባለሀብቶችም አሉ፡፡

ከእነዚህ ውስጥ በቅርቡ በ400 ሚሊዮን ብር የተገነባው የኢትዮ ኢስታንቡል አጠቃላይ ሆስፒታል አንዱ ነው፡፡ ሆስፒታሉ ለልብ ሕክምና ቅድሚያ በመስጠት የአገር ውስጥና የውጭ ባለሙያዎችን በማቀናጀት አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡ ወደ ውጭ አገሮች አምርተው በከፍተኛ ወጪ ሕክምና የሚያደርጉ ዜጎች በአገር ውስጥ መታከም እንዲችሉ ዓላማ አድርጎ መመሥረቱንም ሆስፒታሉ አስታውቋል፡፡

ሆስፒታሉ የልብ ቀዶ ሕክምናን ጨምሮ የተለያዩ ከፍተኛ ሕክምናዎችን እንደሚሰጥም የሆስፒታሉ መሥራችና ባለቤት አቶ ብርሃን ተድላ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

ከሕፃናት እስከ አዋቂ የልብ ሕክምና ለማግኘት ወረፋ የሚጠብቅ ሲሆን፣ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የልብ ማዕከል በኢትዮጵያ ብቻ ከዓመት በፊት ከሰባት ሺሕ በላይ ሕፃናት የልብ ሕክምና ለማግኘት ተራ እየተጠባበቁ እንደነበር ማዕከሉ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡

በኢትዮጵያ ከታማሚው ጋር ተመጣጣኝ የሆነ የሕክምና አገልግሎት ባለመኖሩም፣ በየዓመቱ በርካታ ሕፃናት ይሞታሉ፡፡

የታካሚዎችን ቁጥር ለማቃለልና ወደ ወጭ አገር የሚደረገውን ቁጥር ለመቀነስ ይረዳ ዘንድ፣ የኢትዮ ኢስታንቡል አጠቃላይ ሆስፒታል በየዓመቱ ለ300 ሕፃናት ነፃ የልብ ሕክምና ለመስጠት ማቀዱን አቶ ብርሃን ገልጸዋል፡፡

ከሁሉም የሕክምና ባለሙያዎች ጋር ከስምምነት በመድረስም በሳምንት ከአራት እስከ ሰባት ለሚሆኑ ሕፃናት ነፃ የልብ ሕክምና ለመስጠት መታቀዱን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ነፃ የልብ ሕክምናውን የሚያገኙ ሕፃናትን ለመለየት ሆስፒታሉ ከኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ማኅበር ጋር አብሮ ለመሥራት ከስምምነት መድረሱንም አክለዋል፡፡

አንድ የልብ ቀዶ ሕክምና ለማከናወን አሁን ባለው ገበያ እስከ 1.5 ሚሊዮን ብር እንደሚፈጅ የሚያስረዱት አቶ ብርሃን፣ ሆስፒታሉ በየዓመቱ እስከ 300 ሚሊዮን ብር ድረስ በማውጣት ወጪውን ለመሸፈን ማቀዱን ጠቁመዋል፡፡

‹‹ሆስፒታላችን ቀዳሚ ዓላማው ወደ ውጭ አገር ሄደው የሚታከሙ ሕሙማንን ቁጥር መቀነስ ነው፡፡ በአገር ውስጥ በርካታ ብቁ ባለሙያዎች እያሉ ዜጎች ለእንግልትና ለከፍተኛ ወጪ መዳረግ የለባቸውም፤›› የሚሉት አቶ ብርሃን፣ በዚህ የውጭ ምንዛሪን ማዳን እንደሚቻልም ያክላሉ፡፡

በዓመት በርካታ ታካሚዎች ወደ ውጪ አገር ለመታከም ሲያመሩ፣ የውጭ ምንዛሪ የሚፈልጉ መሆናቸው፣ አገሪቷ ባለባት የምንዛሪ እጥረት ላይ ችግሩን የከፋ እንደሚያደርገው ይናገራሉ፡፡

ኢትዮጵያ ብቁ የሕክምና ባለሙያዎች ያላት በመሆኑ፣ ዘመናዊ የሕክምና መሣሪያ ወደ አገር ውስጥ በማስገባት መሥራት የተሻለ አማራጭ መሆኑንም ያነሳሉ፡፡

ሆስፒታሉ ከ30 በላይ ልዩና ንዑስ ስፔሻሊቲ አገልግሎቶችን እንደሚሰጥ፣ ከእነዚህም መካከል የልብ ቀዶ ሕክምና፣ የውስጥ ደዌ፣ የሕፃናት፣ የማሕፀንና የፅንስ፣ የጠቅላላ ቀዶ ሕክምና፣ የጨጓራ እንዲሁም የአንጎልና የነርቭ እንደሚኙበት ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ለተለያዩ ሆስፒታሎች ችግር የሆነውን የኦክስጅን እጥረት ለመቅረፍ፣ የኦክስጅን አገልግሎት ማቅረብ የሚችል (Central Oxygen Plant) እንዳለው አቶ ብርሃን ያስረዳሉ፡፡ እንደ አቶ ብርሃን ማብራሪያ፣ የኦክስጅን ፕላንቱ ለሌሎችም ሆስፒታሎች ለማከፋፈል የሚያስችል አቅም አለው፡፡

በኢትዮጵያ የሚገኙ ከ24 በላይ የሕክምና ባለሙያዎችና ከእሥራኤል፣ ከቱርክ፣ ከህንድና ከኮሪያ የሚመጡ የሕክምና ባለሙያዎች በሆስፒታሉ አገልግሎት እንደሚሰጡ ተገልጿል፡፡

ሆስፒታሉ በተለይ በአፍሪካ ጭምር ብቁ የሕክምና አገልግሎት ለማይገኝለት የሚጥል በሽታ ሕክምና ከሚሰጡ የእሥራኤል የሕክምና ተቋማት ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ ሕክምናው እንዲሰጥ ከስምምነት መድረሳቸውንም አቶ ብርሃን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

‹‹የሚጥል በሽታ ሕክምና በኢትዮጵያ እንዲሰጥ ከእሥራኤል ከፍተኛ የሕክምና ባለሙያዎች፣ ከጤና ሚኒስቴር እንዲሁም ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ጋር ስምምነት ላይ ደርሰናል፡፡ ከሕክምና አገልግሎቱ ባሻገር የትምህርት ማዕከልም ይኖረናል፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡ ሕክምናው በ2016 ዓ.ም. ከጥር ወር ጀምሮ እንደሚሰጥም አስታውቀዋል፡፡

ጠቅላላ የሕክምና አገልግሎት የሚሰጠው ሆስፒታሉ፣ የኩላሊት እጥበትና የኩላሊት ንቅለ ተከላ ሕክምና አገልግሎት የሚሰጡ ዘመናዊ መሣሪያዎችን ያካተተ ነው፡፡

በዓለም የአኗኗር ዘይቤ በመለወጡ የተለያዩ በሽታዎች እየተበራከቱ መምጣታቸውን ተክተሎ፣ በተለያዩ አገሮች የግሉ ዘርፍ በሕክምና ተሰማርቶ ዘመናዊ የሕክምና አገልግሎቶችን ማቅረብ እንዲችልና አቅም እንዲኖረው መንግሥታቸው ሁኔታዎችን ያመቻቻል፡፡

በአንፃሩ በኢትዮጵያ ችግሩ እየተባባሰ ቢመጣም፣ ለዘርፉ ምቹ ሁኔታን መፍጠር አለመቻሉ ይነሳል፡፡ አቶ ብርሃን እንደ አብነት ያነሱትም፣ በውጭ አገር ጥራቱ የተረጋገጠ የሕክምና መሣሪያ ወደ አገር ውስጥ ሲገባ፣ የጥራት ደረጃው መረጋገጥ አለበት በሚል ከስድስት ወር እስከ አንድ ዓመት ጊዜ የሚወስድ መሆኑን ነው፡፡

‹‹ዋነኛው የዚህ አገር ችግር ደረጃው ተረጋግጦ የመጣ የሕክምና ቁሳቁስን ለመመዝገብና በአገር ውስጥ ለማረጋገጥ የሚወሰደው ጊዜ ነው፡፡ ይህ የሕክምናውን ሒደት የሚያጓትትና ታካሚዎች በአገር ውስጥ የሚፈልጉትን ሕክምና እንዳያገኙ እንቅፋት ነው፤›› ሲሉ አቶ ብርሃን ስለሁኔታው ያስረዳሉ፡፡

እንደ አቶ ብርሃን፣ የሕክምና ቁሳቁሱ መመዝገብ ካለበትም ጊዜውን ማሳጠር ይገባል፡፡ በተለይ ለልብ ሕሙማን ወሳኝ የሆነውና በርካታ ታካሚዎች ወደ ውጪ አገር እንዲያመሩ የሚያስገድደው የልብ ባትሪ (Pacemaker) ለማስገባት ረዥም ጊዜ ይወስዳል፡፡

ኢትዮ ኢስታንቡል ጠቅላላ ሆስፒታል ለአሥር ዓመት በሊዝ በተከራየው ቦታ እየተባባሰ የመጣውን የልብ ሕመም ለማከም እንደሚሠራ ገልጸውም፣ ሆስፒታሉ የሕክምና አገልግሎቱን ለማስፋፋት ዕቅድ እንዳለው፣ መንግሥት ዘርፉን ለማሳደግና ከመሬት አቅርቦት ጀምሮ ያለውን ውስብስብ ሒደት ለማቃለል መሥራት እንደሚገባው ጠቁመዋል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው፣ በዓለም በየዓመቱ 18 ሚሊዮን ሰዎች በልብ ነክ በሽታዎች ይሞታሉ፡፡ በተለይም ከ30 እስከ 50 ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ለበሽታው ተጋላጭ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እ.ኤ.አ. በ2017 ያወጣው ሪፖርት እንደሚሳየውም፣ በኢትዮጵያ ከ2.8 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በልብና በልብ ደም ሥር በሽታዎች ተጠቅተዋል፡፡

 ከእነዚህም ውስጥ 33.7 በመቶ የሚሆኑት የጉሮሮ ሕመምን ተክትሎ በሚመጣ የልብ ሕመም የተጠቁ ሲሆን፣ 22.5 በመቶ የሚሆኑት በልብ የደም ቧንቧ ጥበት በሽታና 11.4 በመቶ ደግሞ በ‹‹ስትሮክ›› በሽታ የተጠቁ ናቸው፡፡

የልብ ሕክምና አገልግሎትን ለመስጠት በርካታ ችግሮች እንዳሉና በተለይ የግብዓት፣ የመድኃኒትና ሌሎች ነገሮች ባለመኖራቸው የተነሳ አብዛኛዎቹ ሕሙማን በጊዜው የሕክምና አገልግሎትን ማግኘት ባለመቻላቸው የተነሳም ለሞት ይዳረጋሉ፡፡ የልብና የልብ ደም ቧንቧ በሽታዎች ዋነኛ የሞት መንስዔ መሆናቸውና ይህንንም ተከትሎ በየቀኑ 170 ሰዎች በልብና በልብ ደም ቧንቧ በሽታዎች እንደሚሞቱ መስከረም 19 ቀን 2015 ዓ.ም. የዓለም የልብ ቀን በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሲከበር መነገሩ ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...