Friday, May 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

መንግሥት ቁልፍ ባላቸው ፕሮጀክቶች ላይ ለሚሰማሩ የውጭ ኩባንያዎች የውጭ ምንዛሪ ዋስትና ፈቀደ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ቁልፍ ወይም ስትራቴጂካዊ ተብለው በሚለዩ ፕሮጀክቶች ላይ ከመንግሥት ወይም ከግል ኩባንያዎች ጋር ተጣምረው ለሚሰማሩ የውጭ ኩባንያዎች፣ የውጭ ምንዛሪ ዋስትና ተፈቀደ።

የተፈቀደው የውጭ ምንዛሪ ዋስትና ቁልፍ ተብለው በሚለዩ ፕሮጀክቶች ላይ ኢንቨስት የሚያደርጉ የውጭ ኩባንያዎች ከፕሮጀክቱ ትግበራ የሚያገኙትን ትርፍ በውጭ ምንዛሪ ከኢትዮጵያ ለማውጣት፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ ለሚተገብሩት ፕሮጀክት ከውጭ የፋይናንስ ተቋማት የወሰዱትን ብድር ሳይቸገሩ ለመክፈል እንዲያስችላቸው ነው።

ውሳኔውን ያሳለፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሲሆን፣ ዓላማውም መንግሥት ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ አላቸው ብሎ በሚለያቸው ዘርፎች ኢንቨስት ለማድረግ ተስማምተው ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ የውጭ ኩባንያዎች ትርፋቸውን ለመውሰድ በሚፈልጉበት ወቅት፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ ለሚተገብሩት ፕሮጀክት ከውጭ ፋይናንስ ተቋማት የወሰዱት ብድር መክፈያ ጊዜ ደርሶባቸው በአገር ውስጥ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ባይችሉ መንግሥት የውጭ ምንዛሪ እንደሚያቀርብላቸው፣ የብሔራዊ ባንክ ምክት ገዥ አቶ ፍቃዱ ደግፌ ለሪፖርተር ገልጸዋል።

አሁን ባለው አሠራር በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ የውጭ ኩባንያዎች ትርፋቸውን በውጭ ምንዛሪ መውሰድ የሚችሉበት አሠራር መኖሩን፣ ነገር ግን ኩባንያዎቹ በብር ያገኙትን ትርፍ በውጭ ምንዛሪ ቀይረው ለማስወጣት ሲፈልጉ የሚስተናገዱት እንደ ማንኛውም የውጭ ምንዛሪ ፍላጊ መሆኑን አስረድተዋል።

የብሔራዊ ባንክ ቦርድ በቅርቡ ባሳለፈው ውሳኔ የውጭ ምንዛሪ ዋስትና እንዲያገኙ የተፈቀደላቸው መንግሥት በሚለያቸውና አገራዊ ፋይዳ ባላቸው ቁልፍ ልማቶች ላይ፣ በተለይም በመንግሥት ለመንግሥት አጋርነት እንዲሁም በግልና በመንግሥት አጋርነት (Public Private Partnership) ማዕቀፍ ለማልማት ተስማምተው በኢትዮጵያ ለሚሰማሩ የውጭ ኩባንያዎች ብቻ መሆኑን አቶ ፍቃዱ ጠቁመዋል።

በዚህም የውጭ ኩባንያዎቹ ዓመታዊ ትርፋቸውን ጨምሮ ከውጭ የፋይናንስ ተቋማት በኢትዮጵያ ለተሰማሩበት ኢንቨስትመንት በብድር ያገኙትን ካፒታል ለመክፈል የውጭ ምንዛሪ እንዳይቸገሩ መንግሥት የሚሰጠው መሆኑን የገለጹት አቶ ፍቃዱ፣ ዋስትናውን የሚያገኙ ኩባንያዎች በተመረጡ ስትራቴጂካዊ ልማቶች ከመሳተፋቸው ባሻገር ሌሎች መሥፈርቶችም እንደሚታዩ አብራርተዋል፡፡

ለአብነትም ልማቱን በጀመሩ በአጭር ዓመታት ውስጥ የውጭ ምንዛሪ ይዘው ለመውጣት የማይጠይቁ መሆናቸው፣ ቁልፍ በሆኑና ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ሊያስገኙ በሚችሉ ፕሮጀክቶች የተሰማሩ መሆናቸውና ከገንዘብ ሚኒስቴር ወይም ከሌሎች የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት ጋር ስምምነት ፈጽመው ወደ ኢትዮጵያ የገቡ መሆን እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።

ቁልፍ ከሚባሉት ፕሮጀክቶች መካከል የኃይል ማመንጫ፣ የማዕድንና የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች እንደሚገኙበትም አክለዋል፡፡

የውጭ ምንዛሪ እጥረት በኢትዮጵያ ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት ያላቸው የውጭ ኩባንያዎች ላይ ተፅዕኖ እያደረሰ በመሆኑ መንግሥት የውጭ ምንዛሪ ዋስትና ለመስጠት ከመወሰኑም በተጨማሪ፣ ይህንኑ የዋስትና ጥያቄ በግልጽ ያቀረቡ የውጭ ኩባንያዎች መኖራቸውን የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት ሪፖርት ገልጸው ነበር።

ጥያቄውን በግልጽ ካቀረቡት ኩባንያዎች መካከል ማስዳር (MASDAR) የተሰኘው የአቡዳቢ ኩባንያ መሆኑን አቶ አህመድ የገለጹ ሲሆን፣ ኩባንያው ከመንግሥት ጋር ባደረገው ስምምነት መሠረት ከፀሐይ ኃይል 500 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ስምምነቱ እ.ኤ.አ. በ2021 የተፈረመ ሲሆን፣ ማስዳር የተባለው ኩባንያ ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልገውን ፋይናንስ ራሱ ይዞ በመምጣት ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቱን ጨምሮ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችን በመገንባት፣ እንዲሁም ግንባታው ከተጠናቀቀ በኋላ የኃይል ማመንጫውን ለረጅም ዓመታት በማስተዳደር ከኃይል ማመንጫው የሚመረተውን የኤሌክትሪክ ኃይል ለመንግሥት እንደሚሸጥ ታውቋል።

ተመሳሳይ ስምምነት ከመንግሥት ጋር በመፈራረም ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ያሰበው ሌላው ኩባንያ ደግሞ አሚአ ፓወር (AMEA Power) የተሰኘ ኩባንያ ሲሆን፣ ኩባንያው በሶማሌ ክልል አይሻ በተባለ አካባቢ የንፋስ ኃይልን በመጠቀም 300 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ለማከናውን ያለመ መሆኑን ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡

ሁለቱም ኩባንያዎች ከፕሮጀክቱ የሚያገኙትን ትርፍ ከአገር ለማስወጣትና ለፕሮጀክቱ ያገኙትን የውጭ ብድር ለመክፈል መንግሥት የውጭ ምንዛሪ ዋስትና እንዲሰጣቸው የጠየቁ ሲሆን፣ የብሔራዊ ባንክ ቦርድ ባሳለፈው ውሳኔ መሠረትም የውጭ ምንዛሪ ዋስትና ከመንግሥት የሚያገኙ የመጀመርያዎቹ ኩባንያዎች ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች