Wednesday, October 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየሸገር ከተማ ስፖርት ምክር ቤት ክለቦችን እንደ አዲስ ሊያዋቅር መሆኑን አስታወቀ

የሸገር ከተማ ስፖርት ምክር ቤት ክለቦችን እንደ አዲስ ሊያዋቅር መሆኑን አስታወቀ

ቀን:

  • በክፍለ ከተሞቹ ለሚገነቡ ስታዲየሞች የግንባታ ቦታዎች ተለይተዋል

በኦሮሚያ ክልል አዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ አምስት ከተሞች ተዋቅሮ የተመሠረተው የሸገር ከተማ፣ የስፖርት ምክር ቤትን ማቋቋሙ ይፋ አድርጓል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ ከዚህ ቀደም በኦሮሚያ ክልል ሥር የነበሩ የአምስት ከተማ የስፖርት ክለቦችን እንደ አዲስ ማዋቀሩን አስታውቋል፡፡

የስፖርት ምክር ቤቱን ሰኔ 26 ቀን 2015 ዓ.ም. ማቋቋሙን ያስታወቀው የከተማ አስተዳደሩ የእግር ኳስ፣ አትሌቲክስ እንዲሁም ቅርጫት ኳስ ስፖርቶችን በአዲስ መልክ እንዲደራጁ መወሰኑን፣ የሸገር ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ናስር ሁሴን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ምክር ቤቱ ውሳኔ ካስተላለፈባቸው ጉዳዮች መካከል፣ በክፍለ ከተሞች የሚገኙ እግር ኳስ ክለቦች ጉዳይ ይጠቀሳል፡፡ ከተማው ከክልል ሊግ እስከ ሱፐር ሊግ እየተሳተፉ የሚገኙ 11 የእግር ኳስ ክለቦች አሉት፡፡ ምክር ቤቱ ባፀደቀው ውሳኔ መሠረት ክለቦቹ የበጀት ድጋፍ ተደርጎላቸው እንደ አዲስ እንዲዋቀሩ መወሰኑም ተገልጿል፡፡

በሌላ በኩል ምክር ቤቱ የሸገር ከተማ አስተዳደር የወንዶችና ሴቶች እግር ኳስ ቡድኖች እንዲቋቋሙ፣ በዚህም መሠረት በከተማ ውስጥ የሚገኙ በሱፐር ሊግ ደረጃ እየተሳተፉ የሚገኙ እግር ኳስ ቡድኖች የሸገር ከተማ ክለብ ሆነው እንዲዋቀሩ ለማድረግ መወሰኑ ተጠቅሷል፡፡

ከዚያም ባሻገር የከተማው ክለብ የሆኑና በመጀመርያ ሊግና በክልል ሊጎች እየተሳተፉ የሚገኙትን ክለቦች ደግሞ በክፍለ ከተማ ደረጃ እንዲደራጁ መደረጉን አቶ ናስር ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

እንደ ቢሮ ኃላፊ ማብራሪያ ከሆነ፣ በከተማ አስተዳደሩ የሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች የሴቶችንና የወንዶች የስፖርት ፕሮጀክቶችን ማዋቀር እንዳለባቸው ተወስኗል፡፡ በሌላ በኩል በከተማ አስተዳደሩ ሥር አምስት የአትሌቲክስ ክለቦች የነበሩ ሲሆን፣ ያሉባቸው ክፍቶች ተገምግሞ፣ ድጋፍ እየተደረገላቸው ባሉበት እንዲቀጥሉ መወሰኑም ተገልጿል፡፡

የከተማውን ስም ይዞ የሚቋቋመው የአትሌቲክስ ክለብ በሥሩ 120 አትሌቶችን ያቅፋል ተብሏል፡፡

ምክር ቤቱ ውሳኔ ካስተላለፈባቸው የስፖርት ዓይነቶች መካከል የቅርጫት ኳስ አንዱ ነው፡፡ በፕሪሚየር ሊግ ላይ እየተሳተፈ የሚገኘው ክለቡ የዘንድሮ ሻምፒዮና መሆን ችሏል፡፡ የቅርጫት ኳስ ክለቡ ከቀጣይ ዓመት ጀምሮ የሸገር ከተማ ስፖርት ክለብ ሆኖ ይቀጥላል ተብሏል፡፡

በሌላ በኩል ከተማ አስተዳደሩ የስፖርት ምክር ቤቱ ምሥረታ ዕለት ከስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ጋር በተያያዘ ውሳኔ ያስተላለፈ ሲሆን፣ ያሉት የማዘውተሪያ ሥፍራዎች የባለቤትነት ማረጋገጫ እንዲያገኙ እንዲሁም አዲስ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች በሁሉም የከተማዋ ወረዳዎች በሕዝቡ አሠፋፈር ልክ እንዲገነቡ መወሰኑ አቶ ናስር ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘም የከተማ አስተዳደሩ ከ12 ክፍለ ከተሞች፣ በአምስቱ ዘመናዊ ስታዲየሞችን ለመገንባት ጥናት ማድረጉን በማኅበራዊ ገጹ ይፋ አድርጓል፡፡

በዚህም መሠረት ደረጃቸውን የጠበቁ ስታዲየሞች ለመገንባት የመጀመርያ ጥናት መደረጉን የተገለጸ ሲሆን፣ ከ10 እስከ 20 ዓመታት ውስጥ በማከፋፈል ተራ በተራ ለመገንባት መታቀዱን አቶ ናስር ገልጸዋል፡፡

እንደ ቢሮ ኃላፊው ከሆነ ስታዲየሞቹ የሚገነቡበት ቦታ በመለየት የመጀመርያ ምዕራፍ ጥናት ተጀምሯል፡፡ በቀጣይ ስታዲየሞቹ የሚገነቡባቸው ቦታዎችን ማካለሉ ይሠራል፡፡

በሸገር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ የሚመራው የስፖርት ምክር ቤቱ፣ የከተማ ካቢኔ አባላት፣ የክፍለ ከተሞች ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች፣ የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አመራሮች እንዲሁም በክፍለ ከተሞቹ ሥር የሚገኙ 36 ወረዳ አስተዳዳሪዎች ድምፅ ይሰጣሉ፡፡

ከዚህ ባሻገር በከተማዋ የሚኖሩ ባለሀብቶች፣ በስፖርቱ ንቁ ተሳትፎ ያላቸው ግለሰቦች እንዲሁም የተለያዩ የትምህርት ተቋማት ድምፅ የሌላቸው የምክር ቤቱ አባል ናቸው፡፡ ምክር ቤቱ መቋቋሙን ተከትሎ የተለያዩ ውሳኔዎች የተላለፉ ሲሆን፣ በቀጣይ ዓመት በከተማ አስተዳደሩ ሊተገበሩ የታሰቡ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ በዚህም ምክር ቤቱ የሚተዳደርበት ደንብ፣ የደንብ ማስፈጸሚያ መመርያ እንዲሁም የምክር ቤት ገቢ ማሰባሰቢያ መመርያ መፅደቁን አቶ ናስር አክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...