በአበበ ፍቅር
ለኩላሊት ታማሚዎች የተለያዩ ዕገዛዎችን ሲያደርግ የነበረው የቀድሞው ‹‹ሞት በኩላሊት ይብቃ›› በአሁኑ ሰላም ጤና ለኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ማኅበር ለአብ የኩላሊት እጥበት ማዕበል ተሰጠ፡፡
ርክክቡን ‹‹የራዕይ ሽግግር ወይም የኃላፊነት ሽግግር እንደሆነ ነው የማስበው›› ያሉት የሞት በኩላሊት ይብቃ ማኅበር መሥራችና ኃላፊ አቶ ኢዮብ ተክለአረጋይ፣ ማኅበሩ ላለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ የኩላሊት ሕክምና እንዲስፋፋ እንዲሁም መሣሪያዎቹ በነፃ እንዲገቡ ሲታገል መቆየቱን ተናግረዋል።
‹‹በፊትም የኩላሊት ሕመምተኛ ነበርኩ አሁን ብሶብኝ አካል ጉዳተኛ እስከመሆን ደርሻለሁ›› ያሉት አቶ ኢዮብ፣ በአሁኑ ወቅት ድርጅቱን ከዚህ በላይ ለማስኬድ አቅሙ የለም ብለዋል።
በአዳዲስና በብቁ ባለሙያዎች ታግዞ ለሕሙማን የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጥ በማሰብ፣ ፕሮጀክቱን ለአብ ሜዲካል ማኅበር ማስረከባቸውን፣ የዛሬ አራት ዓመት ፕሮጀክቱ ተቋቁሞ ወደ ሥራ ሲገባ፣ የገንዘብ እጥረት እንዳለ ሆኖ በእውቀትም ባለሙያዎች ስላልነበሩ ለሕሙማን ተመጣጣኝና የተሻለ አገልግሎት መስጠት እንዳልተቻለ ገልጸዋል፡፡
በበላይነት ሲያስተዳድሩ የነበረውን ድርጅት ያስተላለፉትም፣ ጅምራቸው በኩላሊት ሕክምናው መሻሻል ስላሳየ የታየውን ጅማሮ ሊያሰፋ ስለሚችልና በባለሙያዎች ታግዞ ቢተገበር የበለጠ ውጤታማ ሊሆን ይችላል ብለው በማሰብ እንደሆነ አቶ ኢዮብ ተናግረዋል።
የኩላሊት ሕመምተኞች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በእጅጉ እየጨመረ መምጣቱን የሚናገሩት ኃላፊው፣ አገልግሎቱን በነፃ የሚያገኙት በጣም ጥቂት መሆናቸውም ያክላሉ።
ብዙዎቹ የኩላሊት ታማሚዎች በግል ሆስፒታል በከፍተኛ ወጪ እየተሰቃዩ እንደሆነ፣ በኢትዮጵያ የኩላሊት እጥበት በቀላሉ የሚገኝ ባለመሆኑም ብዙዎች ሕይወታቸው እንደሚያልፍ ተናግረዋል፡፡
አንድ ሰው ሙሉ የኩላሊት እጥበት ሕክምና ማድረግ ቢኖርበት በቀን እስከ 3000 ብር ወጪ ማድረግ ይጠበቅበታል፣ ገንዘብ መክፈል ቢቻል እንኳን አገልግሎት ለማግኘት ብዙ ወጣ ውረድን ማለፍ እንደሚጠበቅ አክለዋል፡፡
ሕክምናው በቅዱስ ጳውሎስ፣ በዘውዲቱና በዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታሎች በነፃ ቢሰጥም፣ ያለው ቦታ ውስን በመሆኑ በሚፈለገው ልክ አገልግሎት ማግኘት እንደማይቻል ገልጸዋል።
የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብና ራሳቸውም የችግሩ ተጠቂ በመሆናቸው የቀድሞው ስያሜ ሞት በኩላሊት ይብቃ በጎ አድራጎት ማኅበርን በመመሥረት በችግሩ ዙሪያ ብዙ ሥራዎችን ሲሠሩ መቆየታቸውን አቶ ኢዮብ ተናግረዋል።
የአብ ሜዲካል መሥራች ሲስተር ትዕግስት አበበ በበኩላቸው፣ የኩላሊት ሕክምና ከመቼውም በበለጠ ችግር ላይ ይገኛል ብለዋል።
በተለይ ለሕክምና አገልግሎት የሚያገለግሉ ግብዓቶች በአገር ውስጥ አለመገኘታቸው ችግሩን የበለጠ እንደሚያከብደው፣ የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና የሚሰጥበት መሣሪያ ገበያ ውስጥ በመጥፋቱ ሞት እንደሚከሰት ሲስተር ትዕግስት ተናግረዋል።
የድርጅታቸው ዋና ዓላማ ለኩላሊት ሕሙማን የሚደረገውን ልመና ማስቆምና መንግሥትም ለሁኔታው ከዚህ የተሻለ እንቅስቃሴ እንዲያደርግ መወትወት ይሆናል ያሉት ኃላፊዋ፣ መለመን እንኳን ቢኖርበት በግለሰብ ደረጃ ሳይሆን በተቋም ደረጃ እንዲሆን እናደርጋለን ብለዋል።
‹‹ታካሚ አልጋ ላይ ተኝቶ በየመንገዱ በመኪና ከሚለመንለት፣ እኔ እንደ ተቋም ብለምን ይሻላል በማለት ወስኜ ነው የገባሁት፤›› ያሉት ሲስተር ትዕግስት፣ በማዕከሉ ዕድሜአቸው ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ከ12 በላይ ታካሚዎች እንዳሉ ሕክምናቸውን በአግባቡና በወቅቱ ካገኙ ጤነኛ መሆን ይችላሉ የሚል እምነት እንዳላቸው አክለዋል፡፡
ድርጅታቸው ወጪዎችን በመሸፈን አንድ የኩላሊት ታካሚ በሳምንት ሦስት ጊዜ እንዲታከም እያደረጉ እንደሆነ፣ አሁን በኢትዮጵያ ካለው የዶላር እጥረት ጋር ተያይዞ በተለይ አላቂ ዕቃዎች ላይ ከፍተኛ ጭማሪ መኖሩን፣ ሥራውን ሲጀምሩ 42 ብር የነበረው መድኃኒት በአሁኑ ወቅት 250 ብር መግባቱን አብራርተዋል።
በሦስት ፈረቃ 93 ሕሙማንን በቀን ሦስት ጊዜ ሕክምና እየሰጠ የሚገኘው አብ ሜዲካል በጎ አድራጎት ድርጅት፣ ካለው የአገልግሎት ውስንነት አኳያ ከአቅም በላይ ታማሚዎችን እያስተናገደ መሆኑን የተናገሩት ሲስተር ትዕግስት፣ በሳምንት 240 ሕሙማንን ማክሰኞ፣ ሐሙስና ቅዳሜ በፈረቃ እያስተናገደ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ፕሮጀክታቸው የኩላሊት ሕክምናን በኢትዮጵያ ተደራሽ ለማድረግ እየሠራ እንደሆነ፣ በቀጣይ ከዚህ በተሻለ ለመሥራት በጎ አድራጎት ድርጅቶችና የሚመለከታቸው ሁሉ ርብርብ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
የሚለግሱ ሰዎችም በግለሰብ ደረጃ ከመለገስ ወደ ማኅበሩ በማምጣት ቢረዱ እንደተቋም የተሻለ ሥራን እንደሚሠሩም አክለዋል፡፡
በቀጣይም ከአዲስ አበባ ውጪ በጎንደር፣ ባህር ዳር፣ ደሴ፣ ጅማና አፋር እንዲሁም በሀዋሳ ከተሞች ሥራ እንደሚያስጀምሩ ገልጸዋል፡፡
ያለምንም ወጪ ለብዙ ዓመታት ሕክምና ሳደርግ ቆይቻለሁ ሲል አንድ አስተያየት ሰጪ ምስክርነቱን ተናግሯል።
‹‹አሁን በሕይወት ለመቆየቴ የማኅበሮች ሚና ከፈጣሪ በታች ከፍተኛ ነው››ም ብሏል፡፡