Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምበፈረንሣይ ፖሊስ የፈጸመው ግድያ ያስነሳው ተቃውሞ

በፈረንሣይ ፖሊስ የፈጸመው ግድያ ያስነሳው ተቃውሞ

ቀን:

በፈረንሣይ ፓሪስ በፖሊስ በተተኮሰ ጥይት የ17 ዓመቱ ናህል መርዞክ የተገደለው ባለፈው ሳምንት ሰኔ 22 ቀን 2015 ዓ.ም. ነበር፡፡ ይህም ፓሪስን ጨምሮ በመላ ፈረንሣይ ተቃውሞና ቁጣን ቀስቅሷል፡፡

ግድያውን ተከትሎ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ለተከታታይ አራት ቀናት የተካሄደ ሲሆን፣ እስከ ትላንት ድረስም ሙሉ ለሙሉ አላባራም ነበር፡፡ የፈረንሣይ መንግሥት በአንዳንድ ከተሞች ተቃውሞ መውጣትን ቢያግድም፣ አሻፈረን ያሉ ዜጎች ወጥተው ተቃውሞ ከማሰማትና ታዳጊውን ወጣት ከመዘከር አልተመለሱም፡፡

የናህልን መሞት አስመልክቶ ቀድሞ መግለጫ የሰጠው ፖሊስ ቢሆንም፣ በኋላ በበይነ መረብ የተለቀቀ ተንቀሳቃሽ ምስል ፖሊስ ከሰጠው መግለጫ ጋር የተቃረነ መሆኑ ሕዝቡን ለተቃውሞ እንዲወጣ አድርጓል፡፡

እንደ ሲኤንኤን ዘገባ፣ የከተሞች መለያ የሆኑ ሕንፃዎች፣ ትምህርት ቤቶች የፖሊስ ጣቢያዎችና ሌሎች ሕንፃዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ መኪኖችም ተቃጥለዋል፡፡ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ከዋሉ ዜጎች በተጨማሪ በፖሊስና በተቃውሞ አድራጊዎችም ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡

‹‹ፖሊስ ገድሏል››፣ ‹‹ፍትሕ ለናህል›› የሚል መፈክር የያዙ ዜጎች ለተቃውሞ እንዲወጡ፣ 40 ሺሕ ፖሊሶች የተለያዩ ከተሞችን እንዲጠብቁ፣ ከሁለት ሺሕ በላይ የተቃውሞ ሠልፈኞች እንዲታሰሩ፣ ከ500 በላይ ፖሊሶች እንዲጎዱ ያደረገው ተቃውሞ ያባባሰው በፈረንሣይ ዘርን መሠረት ያደረገ አድልኦ አለ የሚለው ነው፡፡

የአሁኑ ተቃውሞ ለማክሮን አገዛዝ ምን ማለት ነው?

የፈረንሣይ መንግሥት የጡረታ መውጫ ጊዜን አስመልክቶ ያሻሻለው ሕግ በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት የተነፈገውና ተቃውሞም ያስነሳ ነበር፡፡ ለሳምንታት ተካሂዶ የነበረውን ሠልፍ ተከትሎም ፕሬዚዳንቱ ኢማኑኤል ማክሮን አገራቸውን ከገባችበት ቀውስ ለማውጣት የ100 ቀናት ዕቅድ ይዘው ነበር፡፡ ሆኖም ይህ ፈረንሣይን ለመጠገን ተስፋ የጣሉበት ዕቅዳቸው ዳግም በሌላ ተቃውሞ ታጅቧል፡፡

በፈረንሣይ እ.ኤ.አ. በ2005 ታዳጊ ወንዶች፣ ከፖሊስ ለመደበቅ ብለው በደረሰባቸው የኤሌክትሪክ አደጋ ሲሞቱ እንደተከሰተው ዓይነት ተቃውሞ እንዳይነሳ ማድረጉ ላይም ተጠምደዋል፡፡ በወቅቱ ፈረንሣይ ለሦስት ሳምንታት በተቃውሞ ተንጣና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም ታውጆ ነበር፡፡

በአሁኑ ተቃውሞ ተመሳሳይ ሁኔታ እንዳይፈጠርም በፈረንሣይ ዝነኞችን ጨምሮ በተለያዩ አካላት የሚደረጉ ዝግጅቶች እንዲሰረዙ ተደርገዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱም ወላጆች ልጆቻቸውን በቤት ውስጥ እንዲይዙ መክረው፣ በተቃውሞ ከተሳተፉት በብዛት የታሰሩት ወጣቶች መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎች ተቃውሞውን ለማርገብ እንዲሠሩ ጥሪ ያቀረቡት ማክሮን፣ በቲክቶክና በስናፕቻት ስሜታዊ የሚያደርጉ ይዘቶችን እንዳይጠቀሙና በፈረንሣይ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ የሚያባብሱና ሥርዓት አልበኝነት እንዲሰፍን የሚቀሰቅሱትን እንዲለዩም አሳስበዋል፡፡

የተቃውሞው ገፊ ምክንያት ምንድነው?

የ17 ዓመቱ ታዳጊ ወጣት በፖሊስ መገደል ለተቃውሞው መነሻ ቢሆንም፣ ዋና መሠረቱ ከዚህ ቀደምም በአገሪቱ የሚስተዋለው ዘርን መሠረት ያደረገ አድልኦ እንደሆነ የአገሪቱ ወትዋቾች ይገልጻሉ፡፡

ዓለማዊ (ሴኪዩላሪዝም) የፈረንሣይ ቁልፍ የባህል መሠረት ነው ቢባልም፣ የዘርን ጨምሮ ልዩነቶችን መሠረት ያደረጉ ተፅዕኖዎች ይተገበራሉ፣ በርካታ ክልስ ፈረንሣውያንም ከነጮች ይልቅ በፖሊስ አድልኦ ይፈጸምባቸዋል ይላሉ፡፡

በፈረንሣይ በሰብዓዊ መብት ላይ የሚሠራው ‹‹ራይትስ ዲፊንደርስ›› በ2017 ያወጣው ጥናት እንደሚያሳየውም፣ ጥቁር ወይም ዓረብ ወጣቶች ከሌሎች ዜጎች ይልቅ በ20 እጥፍ በፖሊስ እንዲቆሙ ይገደዳሉ፡፡

በፈረንሣይ ፖሊስ ላይ የሚሰነዘሩ ወቀሳዎች ጥቁሮችን፣ ዓረቦችን ወይም ክልሶችን ማሸማቀቃቸው ብቻ አይደለም፣ ያልተገባ ኃይል የሚጠቀሙ በመሆናቸውም ነው፡፡

የአውሮፓ ምክር ቤት በዓመቱ መጀመርያ ላይ እንዳለውም፣ የማክሮንን የጡረታ ሪፎርም ተከትሎ በነበረው የተቃውሞ ሠልፍ ላይ ፖሊስ ያልተመጣጠነ ኃይል ተጠቅሞ ነበር፡፡

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችም፣ የፈረንሣይ ፖሊሶች ዘርን መሠረት ያደረገ አሠራራቸውን ለመቀየርና አድልኦን ለማስቀረት ጥልቅና መዋቅራዊ ለውጥ ማድረግ እንደሚኖርባቸው መክረዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታትም፣ ፈረንሣይ በሕግ አስፈጻሚ አካላቷ በኩል የሚፈጸሙ ዘረኝነትንና አድሏዊ አሠራርን ለመቅረፍ መሥራት አለባት ብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...