በኦሮሚያ ክልል የሚገኘው የሉሜ ወረዳ የበይነ መረብ ማኅበረሰብ የጤና መረጃ ሥርዓትን (ኤሌክትሮኒክ ሄልዝ ኢንፎርሜሽን ሲስተም) ተግባራዊ ካደረጉ ቀደምት ወረዳዎች አንዱ ነው።
በሉሜ ወረዳ 35 የጤና ኬላዎችና ሰባት የጤና ጣቢያዎች የሚገኙ ሲሆን፣ በቀጣይ ጤና ተቋማቱ አገልግሎታቸውን ሙሉ በሙሉ ኤሌክትሮኒክ የመረጃ ሥርዓትን መሠረት ባደረገ መልኩ የሚሰጡ ይሆናል።
የጤና ሚኒስቴር፣ በኤሌክትሮኒክ የማኅበረሰብ መረጃ ሥርዓት በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም የተቀመጡ የሥነ ተዋልዶ፣ የእናቶችና የጨቅላ ሕፃናት ጤና አገልግሎቶችን ለማሻሻል እንዲሁም ጥራትን ለማስጠበቅ ዓይነተኛ መንገድ እንደሆነ ያምናል።
ይህ የመረጃ ሥርዓት ማኅበረሰቡን በማገልገል ግንባር ቀደም የሆኑ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችን በተለያዩ የዲጂታል የመረጃ አማራጮች የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ ያስችላል። ሥርዓቱ የወረቀት የጤና አገልግሎት መስጫ ካርዶችና የሪፖርት መረጃዎችን ወደ ዲጂታል መቀየር ያስችላል።
የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች ይህን ማድረግ የሚችሉት ደግሞ በታብሌት በቋሚነት ማሻሻያ (አፕግሬድ በሚደረግበት የሞባይል የጤና መተግበሪያ አማካይነት ነው።
በዚህ መሠረት የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በየቤቱ የቤተሰብ አባላትን የጤና መረጃ በቀላሉ በማውጣት፣ የአገልግሎት ቀጣይነትን ማረጋገጥ ይችላሉ። የጤና ምክር አገልግሎት መመርያንም መጠቀም ይችላሉ። እንዲሁም አድካሚ ከሆነ የወረቀት የሪፖርት (ሪፖርቲንግ) ሥርዓት በተሻለ ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት ይችላሉ።
የኤሌክትሮኒክ ሄልዝ ኢንፎርሜሽን ሲስተም ፕሮጀክት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ደሳለው እማዋይ ስለ ፕሮጀክቱ (የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ታብሌት በመጠቀም በሞባይል መተግበሪያ በቀላሉ ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲሰጡና መረጃ እንዲይዙ ያስችላል፤›› ይላሉ።
እሳቸው እንደሚሉት፣ ይህ ጥራት ያለው የጤና መረጃ እንዲኖርና ከጥቅም እንዲውል ብቻ ሳይሆን ባለሙያዎች አገልግሎት በሚሰጡበት ወቅት የአገልግሎት አሰጣጥ መመርያዎችን እንዲሁም ሪፖርት ማድረጊያ መሣሪያዎችንም ይሰጣቸዋል። ሥርዓቱ ጥራት ያለው የመጀመርያ ደረጃ የጤና አገልግሎት እንዲሰጥም ያስችላል ሲሉ አብራርተዋል።
በርካታ የልማት አጋሮች ጤና ሚኒስቴርን በዚህ የኤሌክትሮኒክስ የጤና መረጃ ሥርዓት ዝርጋት ሲደግፉ የቆዩ ሲሆን፣ ጄኤስአይም በቺልድረንስ ኢንቨስትመንት ፈንድ ፋውንዴሽን (ሲአይኤፍኤፍ) ድጋፍ ተግባራዊ በሚደረገው ፕሮጀክቱ እ.ኤ.አ. ከ2020 ጀምሮ የጤና ሚኒስቴር እንቅስቃሴን በመደገፍ ላይ ይገኛል።
ፕሮጀክቱ በተመረጡ ወረዳዎች ላይ አዳዲስ የጤና አገልግሎት መተግበሪያዎች፣ ጂኦ ስፓሻል ካርታዎችን የሚያሳዩ ዳሽ ቦርዶችን፣ በአሻራ የጤና መረጃ አያያዝን እንዲሁም የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችን የሥራ አፈጻጸም የተሻለ የሚያደርጉ አካሄዶችን ሲተገብር ቆይቷል።
በዚህ መሠረት ጤና ሚኒስቴር ከአጋሮቹ ጋር በመሆን እስካሁን ፕሮጀክቱን በ7,500 የጤና ኬላዎች ተግባራዊ አድርጓል።
የሉሜ ወረዳ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ገመቹ ታፈሰ፣ ‹‹ሉሜ የሙከራ ትግበራ የሚደረግበት ወረዳ ብቻ ሳይሆን፣ የጤና አገልግሎት ሥርዓትን ሙሉ በሙሉ ዲጂታል የማድረግን ጠቀሜታ እውን አድርጎ ያሳየም ነው፤›› በማለት ሉሜ ለሌሎች ወረዳዎች አስተማሪ እንደሆነ ይገልጻሉ።
ምንም እንኳ የኢንተርኔት መሠረተ ልማት (ኮኔክቲቪቲን)፣ የመረጃ አያያዝን እንዲሁም የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን በማሻሻል ረገድ ሊሠሩ የሚገባቸው በርካታ ሥራዎች ቢኖሩም፣ እስከዛሬ የማኅበረሰቡን ጤና አገልግሎት ዲጂታላይዝ በማድረግ ረገድ የተከናወኑ ተግባራት ጠንካራ ናቸው።
ቀጠሮ ከመድረሱ በፊት የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችን በሚያስታውሰው የኤሌክትሮኒክ የመረጃ ሥርዓት አማካይነት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ነፍሰ ጡሮች የቅድመ ወሊድ ክትትል ሊያደርጉ ችለዋል። ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ጨቅላዎችና ሕፃናት ወሳኝ የሕክምና ክትትል እንዲያደርጉ፣ አስፈላጊ ክትባቶችንም እንዲወስዱ አስችሏል።
ስለዚህም ሉሜ የእናቶችና ሕፃናት ጤና አገልግሎትን በማሻሻል ረገድ ከፍተኛ ውጤት እየታየበት ያለ ወረዳ መሆኑ ተገልጿል። ጄኤስአይ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመሆን ቀሪዎቹ ወረዳዎች ሙሉ በሙሉ ወደ ዲጂታል ጤና አገልግሎት አሰጣጥ እንዲሻገሩ ድጋፍ ማድረጉን ይቀጥላል።
ጄኤስ አይ
የማኅበረሰብና የግለሰቦችን ጤና ማሻሻል ላይ አትኩሮ የሚሠራ ዓለም አቀፍ ድርጅት ነው። የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራምን የማሻሻል የኤሌክትሮኒክ የማኅበረሰብ ጤና መረጃ ሥርዓት የአምስት ዓመት ፕሮጀክት ሲሆን፣ መንግሥት ዲጂታል ቴክኖሎጂን መሠረት አድርጎ የጤና አገልግሎት ሽፋንና ጥራትን ለማሻሻል የሚያደርገውን ጥረት የሚደግፍ ነው። ፕሮጀክቱ እስከ ዛሬ የነበረውን ወረቀት መሠረት ያደረገ የጤና አገልግሎት ዲጂታላይዝ ማድረግ የሚያስችል በጄኤስአይ የሚተገበርና በሲአይኤፍኤፍ CIFF የሚደገፍ ነው።