Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርኦዲትን ከማስተማር ባለፈ መተግበር የተሳናቸው የአገራችን ዩኒቨርሲቲዎች

ኦዲትን ከማስተማር ባለፈ መተግበር የተሳናቸው የአገራችን ዩኒቨርሲቲዎች

ቀን:

በቶፊቅ ተማም

ኦዲት የሚለው ቃል “Audire” ከሚለው የላቲን ቃል የመጣ ሲሆን፣ ትርጉሙም ይሰማል (He Hears) ማለት ነው፡፡ በጥንት ዘመን መንግሥት ወይም የመሬት ባለሀብቶች የሾሟቸው ባለሥልጣናት የሀብቱን ብዛትና ይዘት የሚያጣሩ ሰዎች መድበው፣ ያጠናቀሩትን መረጃ አስቀርበው በቃል ይሰሙ እንደነበር ይነገራል፡፡ የኦዲት አጀማመር በጥቂትም ቢሆን ራቅ ባለ ጊዜ ከሒሳብ አያያዝ እንደሚቀድም የሥልጣኔ ዕድገትን ተከትሎም፣ አንድ ሰው በተወሰነ ደረጃ በሌላ ሰው ንብረት ላይ የመታመን አስፈላጊነትን ሲያመለክት ይህንኑ ታማኝነት የሚያረጋግጥ መቆጣጠርያ ሥርዓት እንዲኖር በማስፈለጉ ነበር ኦዲት መተግበር የተጀመረው፡፡ በኦዲት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሚጠቀሙባቸው ሥርዓቶች፣ ሒደቶችና ያስገኟቸው ወይም ያላስገኟቸው ውጤቶች ይፈተሻሉ፣ ግኝቱም ይፋ ይደረጋል፡፡

የሥራ እንቅስቃሴዎችና ክንውኖች ከታወቁ ግቦች፣ ከበጀትና ከደንቡ አኳያ ይፈተሻሉ፡፡ ይኼንን ተግባር ለመወጣት ደግሞ አገሮች የኦዲት ተቋም ይኖራቸው ዘንድ ግድ ነው፡፡ ኦዲት መተግበር ያለባቸው ሥራዎች መከበራቸውን ማረጋገጫም ነው፡፡ በመሆኑም ሕጋዊነትና ሙያዊ መሥፈርቶች አለመሸራረፋቸውን፣ አለመጣሳቸውን፣ ብሎም በትክክል ሥራ ላይ መዋላቸውን የማረጋገጥ ሚና ይጫወታል፡፡ እርግጥ ነው ዋና ዓላማው ለወደፊት እየታረሙ፣ እየተማሩ በተሻለ ሁኔታ ተቋማቱ የተቋቋሙበትን ተልዕኮ ለማሳካት በተገቢው መንገድ መሥራታቸውን፣ እንዲሁም የተመደበላቸውን በጀት በሕጉ መሠረት እየተጠቀሙ መሆናቸውን ማረጋገጥ ነው፡፡ ይህ ማለት ግን ዓላማው ማስተማር ነው በማለት አጥፊዎችና መዝባሪዎችን ዕርምጃ ሳይወስዱ መተው ፍጹም ሊሆን አይችልም፡፡ እንዲህ ከሆነ መዝባሪዎችን ማበረታታት ነው፡፡

ኦዲት አንድም ፋይናንስን የሚመለከት ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ክንውንን ሊመለከት ይችላል፡፡ ድርጅቶች የተቋቋሙበትን ዓላማ በትክክል እያሳኩ መሆናቸው በኦዲት ይፈተሻል፡፡ ስለሆነም ወጪ ቆጣቢነታቸውን፣ ብቃታቸውን፣ ውጤታማነታቸውን ለማረጋገጥ ሲባል ኦዲት ይደረጋል፡፡ የመንግሥትን ውጤታማነትን ለመለካት የኦዲት ሥርዓት ወሳኝነት አለው፡፡ ሲጀመር የኦዲት ሥርዓትን ማጠናከር መንግሥት አገሪቱን ኢኮኖሚ በትክክል ለማስተዳደር እንዲችል መረጃ ያገኝበታል፡፡ ከዚህ ሌላም መሥሪያ ቤቶች የተጣለባቸውን ተልዕኮ ለመወጣት የገንዘብና የንብረት አስተዳደር ሥርዓት ሕግን የተከተለ መሆኑን አለመሆኑን ለማረጋገጥ ይረዳል፡፡ ኦዲት በመንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ ግልጽነት፣ ተጠያቂነትና መልካም አስተዳደርን ለማስፈንም ዓይነተኛ መሣሪያ ነው፡፡

ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች በአግባቡ የተሰጣቸውን በጀት (የሕዝብ ሀብት) በሚገባው አኳኋን ሥራ ላይ መዋል አለማዋላቸውን በመከታተል የፋይናንስ ሕጋዊነት የክዋኔ ኦዲት በመተግበር፣ ለኅብረተሰቡ በመንግሥት ተቋማት ስለተፈጸሙ የሕግ ጥሰቶች የአፈጻጸም ድክመት በማስረጃ ላይ የተደገፉ ሪፖርቶች ማቅረብና የመፍትሔ አቅጣጫ ማሳየት ኃላፊነት የተሰጠው ተቋም ደግሞ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ነው፡፡ በፌዴራሉ ዋና ኦዲተር የኦዲት ጉድለት አለባቸው በሚል ስማቸው በተደጋጋሚ ከሚጠቀሱ ተቋማት መካከል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግንባር ቀደም ናቸው፡፡ በእርግጥ ዩኒቨርሲቲዎች የአንድ መጠነኛ ከተማ ያህል ማኅበረሰብ የሚመሩ ውስብስብ የዕውቀት ማዕከላት ሲሆኑ፣ ይህም ከሌሎች የተለየ ባህሪ እንዲኖራቸው አድርጓል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች በተለያዩ ወቅቶች ለሚነሳባቸው የኦዲት ግኝት መንስዔዎች የሕግ ማዕቀፍ መጣረስ በዋነኛነት ይጠቀሳል፡፡ በአገሪቱ የሚታዩ የኦዲት ጉድለቶች ከዓመት ወደ ዓመት እንዲስተካካሉ አቅጣጫ ቢሰጥም፣ በሚገባው ልክ መታረም እንዳልቻሉ በየዓመቱ የፌዴራል ዋና ኦዲተር በሚያቀርበው ሪፖርት መረዳት ይቻላል፡፡ መንግሥት ያሉ አማራጮችን በሙሉ በመጠቀም ከአገር ውስጥ የሚሰበስበውን ገቢ ለማሳደግ እንደሚጥረው ሁሉ፣ ይህ የሕዝብ ሀብት በየዓመቱ በቢሊዮን ብሮች ለሚመደብላቸው ተቋማት በአግባቡ ሥራ ላይ መዋሉን የማረጋገጥ ሥራ በመሥራት ከደሃው ኅብረተሰብ የተሰበሰበው ጥሪት ባክኖ እንዳይቀር ተገቢውን የቁጥጥር ሥርዓት በመዘርጋት ከጥፋት ሊታደገው ይገባል፡፡

ወደ ዋናው ነጥቤ ስመለስ ዩኒቨርሲቲዎች ላይ ትኩረት እንዳደርግ ያደረገኝ ምክንያት ማክሰኞ ግንቦት 15 ቀን 2015 ዓ.ም. በተካሄደው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ የሚኒስቴሩን የዘጠኝ ወራት ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት ኦዲትን አስመልክተው ያቀረቡትን መነሻ በማድረግ ነው፡፡ እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ ከሆነ የ2013 ዓ.ም. ሒሳባቸው ኦዲት ከተደረጉ 37 የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ምንም ጉድለት ያልተገኘባቸው (Un qualified Opinion) ሁለት ብቻ ሲሆኑ፣ 17 ዩኒቨርሲቲዎች ‹‹ጥቂት ጉድለት›› (Qualified Opinion) ሲገኝባቸው፣ 18 ዩኒቨርሲቲዎች ተቀባይነት የሚያሳጣ (Adverse Opinion) የኦዲት ጉድለት ተገኝቶባቸዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲዎቹ ላይ ለታዩ ዋና ዋና ጉድለቶች ምክንያቶችን በተመለከተ በፌዴራል ዋና ኦዲተር ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበ የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች የ2013 በጀት ዓመት ሒሳብ፣ የፋይናንስና ሕጋዊነት ኦዲትና የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ላይ የተወሰኑትን እንመልከት፡፡

በሕጋዊነት ኦዲት ወቅት የታዩ ዋና ዋና ግኝቶች

የፌዴራል ዋና ኦዲተር የ2013 በጀት ዓመት የፀደቀው በጀት የፋይናንስ አስተዳደር አዋጅ፣ ደንብና መመርያ በሚፈቅደው መሠረት በትክክል ሥራ ላይ መዋሉን ለማረጋገጥ ባከናወነው ኦዲት፣ በርካታ የሒሳብ አያያዝ ግድፈቶችና የውስጥ ቁጥጥር ድክመቶች፣ እንዲሁም አፈጻጸማቸው ከሕግና ከተዘረጋው አሠራር ውጪ የሆኑ ሁኔታዎች ተገኝተዋል፡፡ የምክር ቤቱን ትኩረት ሊያገኙ የሚገቡ አንኳር ግኝቶች ብቻ ተለይተው የቀረቡ ሲሆን፣ በሪፖርቱ የቀረቡ የተወሰኑ የኦዲት ግኝቶች በጥቂቱ ለማሳያ ያህል እንመልከት፡፡

የጥሬ ገንዘብ ጉድለት

በጥሬ ገንዘብና በባንክ ሒሳቦች ላይ ተገቢ ቁጥጥር አለማድረግ የገንዘብ ብክነትና ጉድለት የሚያጋልጥ በመሆኑ፣ የጥሬ ገንዘብ ሒሳብ አያያዝና አጠባበቅን ለማረጋገጥ ኦዲት ሲደረግ ጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ 1,491,901.91 ብር እና ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ 21,749.54 ብር በአጠቃላይ 1,513,651 ብር የጥሬ ገንዘብ ጉድለት ተገኝቷል፡፡ በተጨማሪም በሐዋሳ፣ በሚዛን ቴፒና በቀብሪ ደሀር ዩኒቨርሲቲ 1,051,318 ብር በክፍያ ከተወሰነው ገንዘብ መጠን በላይ በጥሬ ገንዘብ ወይም በቼክ ወጪ የተደረገ ሒሳብ ሊገኝባቸው ችሏል፡፡

በሚኒስትሮች ምክር ቤት የፋይናንስ አስተዳደር ደንብ ቁጥር 190/2002 አንቀጽ 32 እስከ 35 በተደነገገው መሠረት የሰነድ ሒሳብ በወቅቱ መወራረድ ሲጣራ፣ በወቅቱ ያልተወራረደ ውዝፍ ተሰብሳቢ ሒሳብ ከተገኘባቸው ተቋማት መካከል ቀድሞ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር 1,019,438 ብር፣ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ 428,571, 375.86 ብር፣ ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ 421,584,874 ብር ይገኙበታል፡፡

መሰብሰብ ሲገባው ያልተሰበሰበ የጉዳት ካሳ ቅጣትና ውል ማስከበሪያ ሒሳብ

መሰብሰብ ሲገባው ያልተሰበሰበ የጉዳት ከሳ ቅጣትና ውል ማስከበሪያ (bid bond) በፌዴራል መንግሥት የግዥ አፈጸጸም መመርያ አንቀጽ 16 ንዑስ አንቀጽ 27/4 (ሀ) እና (ለ) መሠረት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በየቀኑ 0.1 በመቶ ወይም ከውሉ ዋጋ አሥር በመቶ ሳይበልጥ የጉዳት ካሳ ሊሰበስቡ እንደሚገባ ያመለክታል፡፡ የጉዳት ካሳ ካልሰበሰቡ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል መቱ ዩኒቨርሲቲ 6,907,003.36 ብር፣ የውል ማስከበሪያ ካልሰበሰቡ መካከል አሶሳ ዩኒቨርሲቲ 14,770,258 ብር፣ አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ 6,226,798.77 ብር የውል ማስከበሪያ ያልሰበሰቡ ሆነው ተገኝተዋል፡፡

በገቢ ሒሳብ ሪፖርት ውስጥ ያልተካተተ ገቢ

የተሰብሳቢ ገቢ በትክክል ተመዝግቦና በሒሳብ ሪፖርታቸው ተካቶ መቅረቡን ለማረጋገጥ ኦዲት ሲደረግ፣ የገቢ ሒሳብ ያልመዘገቡና በገቢ ሒሳብ ሪፖርት ካላካተቱ ተቋማት መካከል ጅማ ዩኒቨርሲቲ 93,546,705.55 ብር፣ አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ 36,831,811.45 ብር፣ ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ 16,749,006.84 ብር፣ ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ 16,690,944.18 ብር እና ጂንካ ዩኒቨርሲቲ 10,009,460.05 ብር በገቢ ሒሳብ ሪፖርታቸው ሳይካተት ቀርቷል፡፡

ደንብና መመርያን ሳይከተሉ ያላግባብ የተፈጸሙ ክፍያዎች

ከደንብና ከመመርያ ውጪ ያለአግባብ ክፍያ ከፈጸሙ ተቋማት መካከል ዩኒቨርሲቲዎች ሲሆኑ ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ 12,205,748.26 ብር፣ አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ 7,351,862 ብር፣ እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ 7,097,200 ብር፣ ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ 4,949,923 ብር፣ ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ 3,636,820 ብር ያላግባብ ደንብና መመርያ ሳይከተሉ ክፍያዎች ፈጽመዋል፡፡

የግዥ መመርያ ሳይከተሉ የተፈጸሙ ግዥዎች

የዕቃና የአገልግሎት ግዥ በመንግሥት ግዥ አዋጅና መመርያ መሠረት የተፈጸመ መሆኑን ለማጣራት በተደረገ ኦዲት ከተገኙ ግኝቶች መካከል፣ ያለ ጨረታ በቀጥታ ግዥ መፈጸም መሥፈርት ሳያሟላ በውስጥ ጨረታ ግዥ ሒደት አለመከተል የታየ ሲሆን፣ ከእነዚህ ተቋማት መካከል ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ 73,028,431 ብር፣ ጂንካ ዩኒቨርሲቲ 49,493,614.66 ብር፣ ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ 29,701,889 ብር፣ ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ 26,524,332 ብር በማውጣት የግዥ መመርያን ሳይከተሉ ግዥ ፈጽመዋል፡፡

በተሰብሳቢ ሒሳብ መመዝገብ ሲገባው በወጪ የተመዘገበ የቅድሚያ ክፍያ ሒሳብ

በተሰብሳቡ ሒሳብ መመዝገብ ሲገባው በወጪ የተመዘገበ የቅድሚያ ክፍያ ሒሳብ በተመለከተ ቅድመ ከፍያዎች በተሰብሳቢ ሒሳብነት ተይዘው ሥራው መሠራቱ ሲረጋገጥና ተገቢው ማስረጃ ተሟልቶ ሲቀርብ ብቻ በወጪነት መመዝገብ ቢገባውም፣ ቅድመ ክፍያ በወጪ ከተመዘገቡ ተቋማት መካከል የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሰቲ 5,799,901 ብር መዝግቦ ተገኝቷል፡፡

ማስረጃ ሳይኖር በወጪ የተመዘገበና ትክክለኛነቱን ለማረጋገጥ ያልተቻለ የወጪ ሒሳብ

ተገቢው ማስረጃ ሳይቀርብ የመንግሥትን ገንዘብ ወጪ ማድረግ ሕግና አሠራርን መጣስ ከመሆኑም በላይ፣ የሕዝብንና የመንግሥትን ገንዘብ ለጥፋትና ለብክነት የሚዳርግ በመሆኑ ማንኛውም ወጪ ከመመዝገቡ በፊት ተገቢው ማስረጃ መቅረቡን በማረጋገጥ እንዲመዘገብ ሆኖ፣ የወጪ ማስረጃ ያልቀረበበት ሒሳብ በቂ ማስረጃ እንዲቀርብበት ቢጠበቅም በወጪ የተመዘገቡ ክፍያዎች ሕጋዊ ማስረጃ የቀረበላቸውና ትክክለኛ ወጪ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ኦዲት ሲደረግ፣ በ22 ተቋማት ብር 4,083,767,754 ብር ማስረጃ ሳይኖረው በወጪ የተመዘገበ ሒሳብ የተገኘባቸው ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል ጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ 1,991,230 ብር በማስረጃ ሳይረጋገጥ በወጪ ተመዝግቦ ተገኝቷል፡፡

በወቅቱ ያልተከፈለ ተከፋይ ሒሳብን በተመለከተ

በበጀት ዓመቱ በተከፋይ ሒሳብ የተያዙት ሒሳቦች በተገቢው ጊዜ ውስጥ መከፈላቸውንና ሒሳባቸውም በተከፋይ መያዝ የሚገባቸው መሆኑን ለማረጋገጥ በተደረገ ኦዲት፣ በወቅቱ ያልተከፈለ ተከፋይ ሒሳብ ከታየባቸው ተቋማት መካከከል የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ 63,837,450 ብር፣ እንዲሁም አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ 45,473,305.97 ብር በወቅቱ ያልተከፈለ ተከፋይ ሒሳብ ተገኝቶባቸዋል፡፡

የበጀት አጠቃቀም

መሥሪያ ቤቶች የተፈቀደላቸውን በጀት በአግባቡ መጠቀማቸውን ለማረጋገጥ ኦዲት ሲደረግ፣ በ24 ተቋማት በልዩ ልዩ የሒሳብ መደቦች በደንቡ መሠረት ሳያስፈቅዱና በጀት ሳያዘዋውሩ ከመደበኛ በጀት ከውስጥ ገቢና ከካፒታል በጀት በድምሩ 645,198,927 ብር ከተደለደለው በጀት በላይ ወጨ የሆነ ሒሳብ ተገኝቷል፡፡ በልዩ ልዩ የሒሳብ መደቦች ከተፈቀደላቸው በጀት በላይ ከተጠቀሙ ተቋማት መካከል ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ 159,474,595 ብር፣ ወለጋ ዩኒቨርሲቲ 47,651,241 ብር፣ ጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ 31,419,378 ብር፣ ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ 25,565,165 ብር፣ እንዲሁም ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ 25,808,529 ብር በዋነኛነት ተጠቅሰዋል፡፡

ከላይ ለአብነት ያህል በዋና ኦዲተር ሪፖርት የቀረቡ ለኦዲት ግኝት ምክንያት የሆኑ ጉዳዮችን ካየን ዘንዳ፣ ዋና ኦዲተር ላለፉት ሦስት ዓመታት የተደረጉ የፋይናንስ ሕጋዊነት ኦዲት ሁኔታ ምን እንደሚመስል ያስቀመጠው መረጃ ምንም እንኳ ዩኒቨርሲቲዎቹ ለአገሪቱ ላሉ ተቋማት በኦዲት ዙሪያ ሞዴል ሊሆኑ ቢገባም፣ በተቃራኒው በእነሱ የሚታየው የኦዲት ጉድለት ምን ያህል አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንዳለ የሚያሳይ ሲሆን መረጃውም ከዚህ በታች በሰንጠረዥ ተመላክቷል፡፡

በ2013 በጀት ዓመት ሒሳብ ኦዲትና ባለፉት ተከታታይ ሁለት ኦዲቶች

ሒሳባቸው የጎላ ችግር ያለበት በመሆኑ ተቀባይነት የሚያሳጣ አስተያየት  የተሰጣቸው /Adverse opinion/

    x

አስተያየት ለመስጠት ያልተቻለባቸው መሥሪያ ቤቶች /Disclaimer Opinion/

xx

ከጥቂት ስህተቶች በስተቀር በአጠቃላይ ሒሳባቸው አጥጋቢ በመሆኑ ነቀፌታ ያለበት (Except for) የተሰጣቸው

E

 

ተ.ቁ

የመሥሪያ ቤት ስም

ኦዲት የተደረገበት ዓመት በጀት ዓመት

2011

012

2013

 

ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት

 

 

 

1

ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ

x

x

x

2

ጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ    

 

 

x

3

ጂንካ ዩኒቨርሲቲ

X

x

x

4

ጅማ ዩኒቨርሲቲ

X

x

x

5

ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ 

X

x

x

6

ሚዛን  ዩኒቨርሲቲ

X

x

x

7

መደወላቡ ዩኒቨርሲቲ

 

 

x

8

ሀረማያ ዩኒቨርሲቲ 

X

x

x

9

ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ

X

x

x

10

ወለጋ ዩኒቨርሲቲ    

 

 

x

11

የኢትዮጵያ ቴክኒካል ዩኒቨርስቲ     

 

 

xx

12

መቱ ዩኒቨርሲቲ

X

x

x

13

የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ

X

x

x

14

ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ

Xx

x

x

15

አዲማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ

X

x

x

16

ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ

Xx

x

x

17

ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ 

X

x

x

 

ከላይ ለኦዲት ግኝት መነሻ ከሆኑ ምክንያቶች በተጨማሪ ሌሎች ለኦዲት ግኝት የሆኑ ምክንያቶች ስንመለከት በሀብትና ዕዳ መግለጫ (Balance Sheet) የተመለከቱ ሒሳቦች ትከክለኛነቱ አስተማማኝ ማረጋገጫ ያልተሰጠበት መሆኑ፣ የጥሬ ገንዘብ ቆጠራና የባንክ ሒሳብ ማስታረቂያ ባለመዘጋጀቱ ስለትክክለኛነቱ ለማረጋገጥ አለመቻሉ፣ በዩኒቨርሲቲና በተባባሪ ተቋማት መካከል ስለሚድረጉ የሒሳብ እንቅስቃሴዎች የመረጃ ልውውጥ ግልጽ አለመሆኑ፣ በእነዚህ ተቋማት አለ ተብሎ በሒሳብ መግለጫ (Financial Statement) የተመለከተው ተሰብሳቢና ተከፋይ ሒሳብ ሚዛን ትክክለኛነቱ ማረጋገጫ ማግኘት አለመቻሉ፣ በሒሳብ መግለጫ የተመለከቱ ተሰብሳቢና ተከፋይ ሒሳቦች ተቀፅላ ሌጀር ባለመዘገጀቱ የተሰብሳቢና የተከፋይ ሒሳቦች ትክክለኛነት አለመረጋገጥ፣ በሀብትና ዕዳ መግለጫ የተመለከተ ተከፋይ ሒሳብ ለረዥም ጊዜ የቆዩና በቀጣይ መከፈል የሚገባው ቢሆንም ያልተከፈለ መሆኑ፣ ከተለያዩ ለጋሽ ድርጅቶች የተገኘ ብር በገቢ አለመያዝ፣ በፋይናንስና በጀት አስተዳደር የተከለከለ የበጀት ዝውውር ማድረግ ማለትም በጀት ሳይፈቀድ ወይም ዝውውር ሳይደረግ ወጪ ማድረግ  በዋነኛነት ይጠቀሳሉ፡፡

ለማጠቃለል ያህል ይህ ቀላል ሊባል የማይችል የኦዲት ግኝት ይታረም ዘንድ በዋነኛነት የሚታዩ የሕግ ማዕቀፎች ችግሮችን ማስተካከል የዩኒቨርሲቲዎች የፋይናንስ አያያዝና አስተደዳር ማዘመን፣ የሰው ኃይልን ማብቃት፣ በዋና ኦዲተር የሚሰጡ የኦዲት ግኝቶችን በአግባቡ ማረም፣ የበጀት አጠቃቀምና አስተዳደርን ከነባራዊ ሁኔታ ጋር ማዘመን የዩኒቨርሰቲዎች የራሱ የሆነ የግዥ መመርያ ማዘጋጀት፣ ዩኒቨርሲቲዎችን የሚመስሉ የሕግ ማዕቀፎችን ማዘጋጀት፣ የግዥና ንብረት አስተዳደር የሥራ ተግባራትን ለሚያከናውኑ ባለሙያዎች ለሥራቸው በሚያስፈልጉ የፌዴራል መንግሥት አዋጆች፣ መመርያዎችና ማንዋሎች ላይ ሥልጠና መስጠት በዋነኛነት ይጠቀሳሉ፡፡

የታዩትን የአሠራር ግድፈቶችን በማረም ረገድ አብዛኞቹ ዩኒቨርሲቲዎች በሚጠበቀው ልክ ለውጥ እያሳዩ እንዳልሆነ በፌዴራል ዋና ኦዲተር ተደጋግሞ የሚገለጽ ቢሆንም፣ እነዚህ የኦዲት ግኝቶች ትኩረት ተሰጥቷቸው ተገቢው ዕርምጃ ተወስዶ ሊስተካከሉና ሊታረሙ ይገባል፡፡ ይህንን ያላደረጉ ተቋማት ደግሞ ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት ተጠያቂ የሚያደርግ አሠራር መዘርጋት የሚገባ ሲሆን፣ በየዓመቱ ተደጋግመው እየታዩ ለሚገኙ የኦዲት ግኝቶች የተከበረው ምክር ቤት፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ የገንዘብ ሚኒስቴር፣ እንዲሁም የዩኒቨርሲቲዎችና ተጠሪ የሆኑባቸው ተቋማት፣ በተጨማሪም የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አግባብ የሆነውን የተጠያቂነት ዕርምጃ ሊወስዱ ይገባል እያልኩ፣ ይህን ታላቅ አገራዊ ጉዳይ በማስመልከት የበለጠ እንነጋገርበት ዘንድ በማሰብ ያዘጋጀሁትን መነሻ ሐሳብ በዚህ ላብቃ፡፡ ሰላም!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመላከከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...