የዛሬው ጉዞ ከመሳለሚያ ወደ ምኒልክ ሆስፒታል ነው፡፡ ለፍቶ አዳሪዎች ጎዳውን ሞልተውት ይርመሰመሱበታል፡፡ አንዱን ጉዳይ ፈጽመው ወደ ሌላ ጉዳያቸው የሚራወጡ መንገዱን አጨናንቀውታል፡፡ የሚኒ ባስ ታክሲው ወያላ ወጪና ወራጁን አልሞላ ያለው ታክሲ ውስጥ ለማጨቅ ድምፁን ከፍ አድርጎ፣ ‹‹የሞላ ጊዮርጊስ፣ ስድስት ኪሎ፣ ምኒልክ የአራዶቹ ሠፈር…›› እያለ ይጮሃል፡፡ ከመንገዱ አካፋይ ላይ ሆኖ ቁራጭ ሲጋራውን እያጨሰ ወጪና ወራጁን የሚታዘብ ወፈፌ ቢጤ፣ ‹‹አራዳ ድሮ ቀረ… ምድረ ሰገጤ አገሩን አጨናንቆት መላ ቅጡን እያጠፋ የምን አራዳ እያሉ መቀባጠር ነው… አራዳማ ሁሉንም እንደ አመሉ ችሎ፣ ሲርብህ አብልቶ ሲጠማህ አጠጥቶ፣ ሲሰርቅህ እንኳ በጥበብ ኪስህን እንጂ አናትህን ወይም ወገብህን ብሎ አይገልህም… አሁንማ ጭካኔው በዝቶ እንኳን ገንዘብህ ሕይወትህ ለማንም ግድ አይሰጥም… አታዩም እንዴ እንደ ኮሎምቢያና ብራዚል የድራግ ጋንጎች እያገቱ የሚዘርፉና የሚገድሉ ፋራዎች ያለ ከልካይ ሲጫወቱብን… ድንቄም አራዳ እያሉ እርስ በርስ መፎጋገር…›› እያለ በረዥሙ ዲስኩሩን ሲለቀው፣ ወያላውን ጨምሮ ወጪና ወራጁ እንደ አንድ ታላቅ ፈላስፋ ነበር ከበው ያዳመጡት፡፡ ተገኝቶ ነው አትሉም ታዲያ!
ታክሲው ሞልቶ ወያላው ‹‹ሳብ!›› ብሎ ጉዞ እንደተጀመረ መሀል ወንበር ላይ የተቀመጠ ጎልማሳ የእጅ ስልክ ጮኸ፡፡ የአምቡላንስ ጩኸት የመሰለው ጥሪ ጆሮ የሚጠልዝ ስለነበር ታክሲዋ ተርገፈገፈች ቢባል ማጋነን አይደለም፡፡ ‹‹ኧረ በፈጠረህ አምቡላንስህን አስቁምልን… ምን ዓይነት የአደጋ ጥሪ ነው…›› አንዱ ከማለቱ ጎልማሳው ስልኩን አንስቶ እያናገረ በከፍተኛ ድንጋጤ፣ ‹‹ወይኔ ወንድሜን ገደሉት ነው የምትለኝ… እኛ እኮ ገንዘብ አሰባስቡለት ተብለን ይኸው ለማሟላት ትንሽ ብቻ ነው የቀረን… ወይኔ ወንድሜ ምን ዓይነት ጊዜ ላይ ደረስን… የማንም ጨምላቃ ወንበዴ መጫወቻ እንሁን እንዴ… ሾፌር እባክህ አቁምልኝና ልውረድ…›› ብሎ ዕንባው በጉንጮቹ ላይ እንደ ጎርፍ እየወረደ እየጮኸ ተለየን፡፡ ‹‹ወይ እናት አገሬ ኢትዮጵያ ምን ዓይነት ዘመን ላይ ደረስን… መንግሥት ባለበት አገር ውስጥ እንደ ወጡ መቅረት ተራ ነገር ሲሆን መድረሻችን የት ሊሆን ነው…›› ብለው አንዲት እናት ዕንባቸውን ሲያዘሩ የሁላችንም ስሜት ጎሸ፡፡ ምርር ይላል እኮ!
በዝምታ ድባብ ውስጥ ሆነን ሳናውቀው ሀብተ ጊዮርጊስ ድልድይን አልፈን ዳገቱን ስንይዝ፣ ‹‹ልጆቼ እኔ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ ብዙ መከራዎችን ያሳለፍኩ ሰው ነኝ፡፡ ያኔ በተማሪዎች እንቅስቃሴ ጊዜ ተማሪዎች ለተቃውሞ ወጥተው ሲደበደቡና ሲታሰሩ ጠበሉ ደርሶኛል… በደርግ ጊዜ ደግሞ ለስድስት ዓመታት ታስሬያለሁ… በዘመነ ኢሕአዴግ በምርጫ 97 ማግሥት በነበረው ሕዝባዊ ተቃውሞ አስተባብረሃል ተብዬ ታስሬ እስኪበቃኝ ድረስ ተደብድቤያለሁ፣ የአካል ጉዳትም ደርሶብኛል… አሁን በስተርጅና ዘመኔ ደግሞ የወገኖቼን ሰቆቃ እየሰማሁ ለጉድ ተጎልቻለሁ… ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የምሰማው ግን ከምታገሰው በላይ እየሆነብኝ ነው…›› እያሉ ዝምታችንን ሰበሩት፡፡ አንዲት በሃያዎቹ አጋማሽ ውስጥ የምትገኝ ቁጡ ገጽታ የሚነበብባት ወጣት፣ ‹‹አሁንስ በዛ ማለት ብቻ ሳይሆን መንግሥትን ራሱን ሕግ ፊት ገትረን እየደረሰ ላለው መከራ ተጠያቂ ማድረግ አለብን…›› ከማለቷ፣ ‹‹በሕግ አምላክ ብያለሁ… ይኼ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት መስጫ እንጂ የፖለቲካ መድረክ አይደለም… ብላችሁ ብላችሁ መንግሥትን እንክሰስ እያላችሁ አድማ ስትመቱ እኔ ተባባሪ አይደለሁም…›› ብሎ አንድ ድንጉጥ መሳይ ጎልማሳ ተንጨረጨረ፡፡ ምን ያድርግ እንበል እንዴ!
‹‹…እባክህ አንተን የጠራህ የለም… ድሮም እንደ አንተ ዓይነቶቹ ፈሪዎች ናችሁ አገር የምታስበሉት… ይህ ጉዳይ የማይመለከትህ ከሆነ አርፈህ ተቀመጥ እንጂ ተንጰርጵረህ ወጋችንን አታደነቃቅፍ…›› ብላ ያቺ ቁጡ መሳይ ስትገስፀው፣ ‹‹ማነህ ወያላው ወራጅ አለ… እኔ ከአድመኞች ጋር አንድ ላይ ተፈርጄ እስር ቤት መበስበስ አልፈልግም…›› ብሎ ሲወርድ ድንጋጤው ግንባሩ ላይ ይነበብ ነበር፡፡ ‹‹አይ አገሬ ኢትዮጵያ… ሁሉንም በየዓይነቱ አደባልቀሽ መኖርሽ ሳያንስ፣ ልዩነትን አለማክበር ለምን ባህልሽ እንዳልሆነ ሁሌም ይገርመኛል…›› የሚሉት እኚያ እናት ናቸው፡፡ ‹‹እማማ ይህ እኮ የልዩነት ማክበርና አለማክበር ሳይሆን የመብት ጉዳይ ነው…›› ሲላቸው አንድ ቀልቀል ያለ ወጣት፣ ‹‹እሱማ መቼ ጠፋኝ ልጄ… አገር እኮ የደፋሩም የፈሪውም፣ የቀዥቃዣውም የሰከነውም፣ የበሰለውም የጥሬውም፣ የጨዋውም የባለጌውም፣ የታማኙም የሌባውም፣ የእውነተኛውም የዋሾውም ማደሪያ ጎጆ እንደሆነች መገንዘብ አለብን ለማለት ያህል ነው…›› ሲሉ ዕድሜ የሚሉት ፀጋ ምን ያህል እንደሚያበስል ጥሩ ማሳያ ነበር፡፡ እንዲያ ነው እንጂ!
ታክሲያችን የአፍንጮ በርን ዳገት ስትያያዝ በርካቶች ወርደው በርካቶች ተተክተው ስለነበር፣ ወጉም ከወጪዎቹና ከወራጆቹ ስሜትና ፍላጎት ጋር እየተሰናሰለ ቀጥሏል፡፡ ‹‹አንተ ተማርክ አልተማርክ ምን ፋይዳ ይኖርሃል…›› የሚል ድምፅ ከበስተኋላ ወንበር ሰምተን ዞር ስንል፣ ‹‹…እንኳን አንተ አይደለህም ገና ለቢኤ ዲግሪ የምትፍገመገም ማስተርስና ዶክትሬት ዲግሪዎችን የደራረቡትን እኮ አየናቸው… ያልተማሩት እናቶቻችንና አባቶቻችንን ሩብ ያህል የረባ ብስለትና አስተዋይነት የሌላቸው ማይማን ምሁራን የበዙበት አገር ውስጥ አንተ ተጨምረህ ምን ትፈይዳለህ ነው የምለው…›› እያለ አንድ ረዥም ቀጭን ተሳፋሪ በስልኩ ሲያወራ ደነገጥን፡፡ ሰውየው በስልኩ ሲያወራ የነበረውን ሲጨርስ፣ ‹‹ሰውየው እንዴት ያለ ነገር ነው የምታወራው… አገሪቱ ሃምሳ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎችን ገንብታ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ወደ ሥራ አስገብታ ምሁራኑን እንዲህ መዘርጠጥ ተገቢ ነው እንዴ…›› ሲሉት አዛውንቱ፣ ‹‹አባቴ ከእርስዎ ባላውቅም ይህ ሁሉ ምሁር የሚርመሰመስባት አገር ውስጥ ረሃብ፣ ግጭት፣ መፈናል፣ አፈና፣ ዕገታ፣ ግድያ ለምን መፍትሔ አያገኙም ነበር… አባቴ እኔ እኮ ትምህርት ችግር ሲፈታ እንጂ ሲያባብስ ስለማላውቅ ነው…›› ሲላቸው ፀጥታ እረጭ አደረገን፡፡ ጉድ እኮ ነው!
ወደ መዳረሻችን እየተቃረብን ነው፡፡ ወያላችን የዛሬው ወግ አስደምሞት ነው መሰል፣ ‹‹እንዴት ነው ሾፌር የዛሬ ተሳፋሪዎች እኮ ዙሩን አከረሩት…›› ሲለው፣ ‹‹በዝምታ ከመታፈን ይውጣላቸው እባክህ… ዘንድሮ እንኳን ብሶት መተንፈስ ጨርቅ ተጥሎ ቢታበድ ምን ይገርማል…›› ብሎ ሾፌሩ ሲመልስለት፣ ‹‹እኛማ በአበዱት ስንስቅ ዕብደታችን በአሥር ተባዝቶ ምን እንደምንሆን እንጃ… እስቲ ልብ ብላችሁ እዩ መንገድ ላይ እኮ ብቻውን የሚያወራው እየበዛ ነው… በቀደም ዕለት አንዲት የሥነ ልቦና ባለሙያ በቴሌቪዥን ስትናገር እንደሰማሁት ከአራት ሰዎች አንዱ የጭንቅላቱን ብሎን ፈቷል፡፡ ይህ ማለት ከ120 ሚሊዮን ሕዝብ ውስጥ 30 ሚሊዮኑ በቅርቡ ለይቶለት የዕብደት ፌስቲቫል ላይ መሪ ተዋናይ ሆኖ ይቀርብ ይሆናል… ማን ያውቃል… ማን ያውቃል አሉ አብዬ መንግሥቱ…›› ብሎ ያ ቀጭን ረዥም ሰውዬ ሲስቅ የምፅዓት ቀን የቀረበ ይመስል ነበር፡፡ ‹‹አንቺ ይህ ነገር እውነት ሳይሆን አይቀርም… እኔ ሰሞኑን ምን እንደነካኝ እንጃ ልቤን እየነሳኝ የማልረሳው ነገር የለም…›› እያለች ከሾፌሩ ጀርባ ያለው ወንበር ላይ የተቀመጠች ቆንጆ አጠገቧ ላለችው ጓደኛዋ ስትናገር ሰማናት፡፡ ወይ የዘንድሮ ሥጋት!
የስድስት ኪሎን መንገድ እያገባደደች ወደ ምኒልክ ሆስፒታል የተቃረበችው ታክሲያችን እየከነፈች ሳለ፣ ‹‹ወይ ዘንድሮ… ወይ ዘንድሮ… አያልቅም ተነግሮ…›› የሚለው የኤፍሬም ታምሩ ውብ ዘፈን ከቴፑ ስፒከር እየተንቆረቆረ ነበር፡፡ ‹‹ወይ ኤፍሬም ይህንን ዘፈን ያኔ ሳይሆን ዘንድሮ ነበር መዝፈን የነበረበት… ለነገሩ ብዙዎቹ ዘፋኞቻችን የዘፈኑዋቸውን ሳዳምጥ ለያኔ ሳይሆን ለአሁኑ ጊዜ የዘፈኑ ነቢያት ይመስሉኛል…›› የሚለው እስካሁን ትንፍሽ ሳይል የነበረው አንድ ትሁት ወጣት ነው፡፡ ወጣቱ ከአነጋገሩ ለሙዚቃ ያደላ ስሜት ያለው ቢመስልም ረጋ ያለና አስተዋይ ነው፡፡ ‹‹ሙዚቃ የሕይወታችን ነፀብራቅ በመሆኑ ብዙ መልዕክቶች የሚተላለፉበት ነው… የአሁኑ ዘመን ሙዚቀኞች ውጣ ውረዶቻችንን ከሽነው ሲያቀርቡዋቸው ደስ ይለኛል… ስሜትን ከማጋል በተጨማሪ ስክነትንና አስተዋይነትን እያዋዙ ቢያቀርቡ ደግሞ ይበልጥ መልካም ይሆን ነበር… እንደ እሬት የመረረውን ሕይወታችንን ማጣፈጥና ለተሻለ ዓላማ መነሳት የሚቻለው ስሜት በማጋል ላይ ጊዜን በማጥፋት ሳይሆን፣ ትውልድ ቀራፂ የሆነ የዕውቀት መሠረት በማስጨበጥ ነው…›› እያለን ጉዞአችን ተጠናቆ ተለያየን፡፡ መልካም ጉዞ!