Saturday, September 30, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አዋሽ  ኢንሹራንስ ከ2.4 ቢሊዮን ብር በላይ ዓረቦን  ማሰባሰብ መቻሉን ገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ከወለድ ነፃ የኢንሹራንስ ያገኘው ዓረቦን በ357 በመቶ አድጓል

አዋሽ ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር በተጠናቀቀው የ2015 ሒሳብ ዓመት ከሦስት የመድን ሥራ ዘርፎች በአጠቃላይ 2.4 ቢሊዮን ብር ዓረቦን ማሰባሰብ መቻሉንና ከወለድ ነፃ የኢንሹራንስ ዘርፍ ያሰባሰበው የዓረቦን መጠን በ357 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን ገለጸ፡፡

ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ ያሰባሰበው የዓረቦን መጠን ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከ650 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ እንዳለውም አስታውቋል፡፡ እንደ ኩባንያው መረጃ ከሦስቱ የኢንሹራንስ ዘርፎች ካሰባሰበው ዓረቦን ውስጥ ሕይወት ነክ ካልሆነው የኢንሹራስ ዘርፍ ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ፣ ሕይወት ነክ ከሆነው የኢንሹራስ ዘርፍ ደግሞ 275 ሚሊዮን ብር ዓረቦን መሰብሰብ ችሏል፡፡

የሕይወት ነክ ያልሆነው የኢንሹራንስ ዘርፍ ያገኘው ገቢ በ66 በመቶ፣ የሕይወት ነክ ኢንሹራንስ ዘርፍ ያሰባሰበው የዓረቦን መጠን ደግሞ 47 በመቶ ዕድገት አስመዝግቧል፡፡ እንዲሁም በሒሳብ ዓመቱ ከፍተኛ ዕድገት የታየበት ከወለድ ነፃ (ታካፉል) የኢንሹራንስ ዘርፍ ያሰባሰበው ዓረቦን ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑ ታውቋል፡፡

በሒሳብ ዓመቱ ከወለድ ነፃ የኢንሹራንስ ዘርፍ (ታካፉል) የተሰባሰበው የዓረቦን መጠን ከቀዳሚ ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ357 በመቶ ዕድገት ያሳየ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

ኩባንያው ከወለድ ነፃ የኢንሹራስ ኢንሹራንስ አገልግሎት የጀመረው ባለፈው ዓመት ሲሆን፣ የዘንድሮ አፈጻጸሙ ትልቅ እመርታ የታየበት እንደሆነም ተገልጿል፡፡

የአዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ የማርኬቲንግ ኮሙዩኒኬሸን ሥራ አስኪያጅ አቶ ቢኒያም ፈንታዬ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በሒሳብ ዓመቱ ማሰባሰብ የቻለው አጠቃላይ የዓረቦን ገቢ መጠን አሁንም ከግል የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከፍተኛው እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ አዋሽ ኢንሹራንስ የዓረቦን ገቢውን በየዓመቱ እያሳደገ ሲሆን፣ በ2013 የሒሳብ ዓመት አሰባስቦት የነበረው የዓረቦን መጠን 1.28 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ ይህንን የዓረቦን መጠን በ2014 የሒሳብ ዓመት ወደ 1.75 ቢሊዮን ብር በማሳደግ ዘንድሮ 2.4 ቢሊዮን ብር ሊደርስ ችሏል፡፡  

ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ ላስመዘገበው ውጤት ከፍተኛ መሆን አንዱ ምክንያት ከሁለት ዓመታት በፊት ዓለም አቀፍ አማካሪ በሆነው ዲሎይት የተባለ ኩባንያ የአሥር ዓመት መሪ ዕቅዱን አስጠንቶ ተግባር ላይ ማዋል በመጀመሩ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ አቶ ቢኒያም እንደገለጹትም የአሥር ዓመቱን መሪ ዕቅድ በአግባቡ መተግበር መቻሉ በኢንዱስትሪው በተለይ ከግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ቀዳሚ የሚባለውን ውጤት ማዝመዝገብ ችሏል፡፡ 

በቅርቡ የድርጅት መለያ ለውጥ (Rebrand) ያደረገው አዋሽ ኢንሹራንስ፣ በኢንዱስትሪው ውስጥ ያለውን የገበያ ድርሻ ይዞ ለመቀጠልና በኢንቨስትመንት ዘርፉ ተሳትፎውን ለማጠናከር የሀብት መጠኑን ለማሳደግ ይረዳኛል ያለውን የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ግንባታ በማካሄድ ላይ እንደሚገኝም አመልክቷል፡፡

ይህንንም በአዲስ አበባ የፋይናንስ ተቋማቱ ማዕከል በሆነው ሠንጋ ተራ አካባቢ አዲስ የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ  ለመገንባት እንቅስቃሴ የጀመረ ሲሆን፣ ጂ+35 ወለል የሚኖረው የዚህ ሕንፃ ግንባታ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡ አዋሽ ኢንሹራንስ ባለፈው ዓመት የተፈረመ ካፒታሉን ወደ አራት ቢሊዮን ብር ያሳደገ ሲሆን፣ በ2015 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ የተከፈለ ካፒታሉን ሁለት ቢሊዮን ብር ማድረስ ችሏል፡፡ ታኅሳስ 1987 ዓ.ም. ወደ ሥራ የገባው አዋሽ ኢንሹራንስ በአሁኑ ወቅት ከ1,700 በላይ ባለአክሲዮኖች አሉት፡፡

ኩባንያው የሀብት መጠን በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ ወደ አምስት ቢሊዮን ብር ማድረስ ችሏል፡፡ አዲስ አበባን ጨምሮ በክልል ከተሞች ያሉትን ቅርንጫፎች ብዛት ቁጥር ደግሞ 66 አድርሷል፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች