Saturday, September 23, 2023

ኢትዮጵያ በማዕቀብ ማግሥት በብሪክስ ዋዜማ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ከአምስት ቀናት ቀደም ብሎ የሩሲያ ስፑትኒክ የዜና ምንጭ በአፍሮ ቨርዲክት ፕሮግራሙ እንግዳ አድርጎ ያቀረባቸው በሞስኮ የኢትዮጵያ አምባሳደር ኡሪያት ቻም ኡጋላ፣ ጠቃሚ ነጥቦችን በኢትዮጵያ አቋም ዙሪያ አንስተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከሩሲያ ጋር ስላላት ግንኙነት ብቻ ሳይሆን፣ ብሪክስ (BRICS) እየተባለ ስለሚጠራው የአገሮች ማኅበር ዲፕሎማሲያዊ ብስለት የሚታይበት ሐሳብ ሰንዝረዋል፡፡

ሩሲያ ለአፍሪካ ከፀረ ቅኝ አገዛዝ ትግል አጋርነት ጀምሮ በኢኮኖሚ፣ በወታደራዊና በልማት ዘርፎች የአኅጉሩ ሁነኛ አጋር ሆና ስለመዝለቋ አምባሳደሩ ተናግረዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ጋርም በተናጠል ዘመናትን የተሻገረ አጋርነት እንዳበጀች የጠቀሱት አምባሳደሩ ይህ በንግድ፣ በኢኮኖሚ፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ (የኑክሌር ስምምነትን ጨምሮ) ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል፡፡

ሩሲያ በፈጠረችው ሚር (Mir) በተባለው ዓለም አቀፍ መገበያያ የንግድ ልውውጣችሁን ለማድረግ አስባችኋል? ተብለው አምባሳደሩ ሲጠየቁ፣ ለዚህ የሰጡት ምላሽ ጥንቃቄ የተሞላበት ነበር፡፡ ‹‹በሩሲያ ላይ በተጣለው ማዕቀብ ሳቢያ ከሩሲያ ጋር ለመገበያየት ፈተና ሆኖብናል፡፡ የሁለትዮሽ የንግድ ልውውጣችን እንዲያድግ እንፈልጋለን፡፡ ሁለቱ አገሮች አሁን ባለው የዓለም የግብይት ሁኔታ የተቀላጠፈ ግብይት ማድረግ ተቸግረዋል፡፡ ስለሆነም የተቀላጠፈ የመገበያያ አማራጭ መፈለግ ግድ ይላቸዋል፤›› በማለት ነበር ኡሪያት ቻም ኡጋላ (አምባሳደር) መልስ የሰጡት፡፡

ብሪክስ የሚባለውን ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ህንድ፣ ቻይናና ደቡብ አፍሪካ የተጣመሩበትን የአገሮች ማኅበር ለመቀላቀል እንደ ኢትዮጵያ፣ ግብፅ፣ አልጄሪያና ቱኒዚያ ያሉ የአፍሪካ አገሮችን ጨምሮ ሌሎች አገሮች ጥያቄ እያቀረቡ ነው፡፡ ብሪክስን የመቀላቀል ፍላጎት የጨመረው ለምን ይመስልዎታል ተብለውም አምባሳደሩ ተጠይቀዋል፡፡

‹‹ብሪክስን የመቀላቀሉ ፍላጎት የሚመነጨው ለኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ብቻ አይደለም፣ ፖለቲካዊ አማራጭም ይሰጣል፡፡ ዓለም እየተለወጠ ነው፣ በተናጠል ልዕለ ኃያል የሚዘወር ዓለምን ማንም አይፈልግም፡፡ ዘርፈ ብዙ የግንኙነት አማራጭ ዓለም እንዲኖረው በመሻት ነው አገሮች ወደ ብሪክስ የሚቀላቀሉት፡፡ ኢትዮጵያም ብሪክስን ከመቀላቀል የሚያግዳት ነገር የለም፤›› በማለት ነበር አምባሳደሩ በዲፕሎማሲያዊ አገላለጽ ያብራሩት፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብሪክስ ወደሚባለው የፈጣን አዳጊ አገሮች ማኅበር ለመቀላቀል ብዙ አገሮች እየጠየቁ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ 19 አገሮች ማኅበሩ ደጃፍ ተሠልፈው ምላሽ እየተጠባበቁ መሆናቸው ተሰምቷል፡፡

በመጪው ወር በደቡብ አፍሪካ በሚደረገው የብሪክስ መሪዎች ስብሰባ ላይ ማኅበሩ የሚወስነው ውሳኔ በጉጉት ይጠበቃል፡፡ ምዕራባውያኑ ከወዲሁ የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ማዕቀብ ሳይፈሩ፣ ደቡብ አፍሪካ ይገኛሉ/አይገኙም? ስለሚለው ጉዳይ ሰፊ ክርክር ይዘዋል፡፡ ይሁን እንጂ ብዙኃኑ የዓለም ማኅበረሰብ ስለብሪክስ መጠናከር እያወጋ ነው፡፡

ብሪክስ በመጪው ወር ስብሰባው የጋራ መገበያያ ገንዘብ ሥራ ላይ ማዋል ስለሚቻለበት ሁኔታ፣ እንዲሁም የአባልነት ጥያቄዎችን በተመለከተ እንደሚመክር ይጠበቃል፡፡

እ.ኤ.አ. 2006 የተመሠረተው ብሪክስ ከአራት ዓመታት በኋላ ደቡብ አፍሪካን በማከል የአምስት አገሮች ማኅበር መሆኑ ይታወሳል፡፡ ማኅበሩ ዛሬ የዓለምን ጥቅል ምርት (ጂዲፒ) 1/3ኛ የሚሸፍኑና የዓለምን 3.2 ቢሊዮን ሕዝብ የያዙ አገሮች ስብስብ ነው፡፡ ወደ እዚህ የኢኮኖሚ ማኅበር እንደ ኢራን፣ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስና የመሳሰሉት አገሮች ቀድመው ለመቀላቀል ጠይቀዋል፡፡ አሁን ደግሞ ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ አገሮችም አስገቡን እያሉ ነው፡፡

የብሪክስ ማኅበር ማደግና መፈጠርም ለምዕራባውያኑ ከባድ ፈተና እንደሆነ ይነገራል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1944 ጀምሮ እንደ ‹‹አይኤምኤፍ›› እና ‹‹የዓለም ባንክ›› ያሉ ተቋማትን በመገንባት ዓለም አቀፍ ተፅዕኖውን አፈርጥሞ የቆየው አሜሪካ መራሹ፣ ምዕራቡ ዓለም ዛሬ ላይ ከባድ ተገዳዳሪ መጥቶበታል፡፡ የብሪክስ ማኅበር የፈጠረው ኒው ዴቨሎፕመንት ባንክ (New Development Bank) አዲሱ የዓለም ሚዛን አስጠባቂ እየተባለ ይገኛል፡፡

ከዚህ የከፋው የምዕራባውያን ፈተና ደግሞ የዶላር ጥገኝነትን የመቀነስ ዝንባሌ በዓለም ላይ እየጨመረ መምጣቱ እንደሆነ ይነገራል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ወደ ሁለት ትሪሊዮን ዶላር በሥርጭት ላይ አለ ይባላል፡፡ ከዚህ ውስጥ ግማሹ አሜሪካ ውስጥ የተሠራጨ ሲሆን፣ ቀሪው ግማሽ ግን በመላው ዓለም ተሠራጭቶ ዓለም አቀፍ ግብይት እንደሚካሄድበት ይነገራል፡፡ አሜሪካ የዓለም አገሮች በዶላር በመገበያየታቸው ብቻ ሳይሆን፣ ተቀማጭ ሀብታቸውን በዶላር በማድረጋቸው ስታተርፍ ቆይታለች ይባላል፡፡  

ለምሳሌ ኢትዮጵያና ሳዑዲ ዓረቢያ ሲገበያዩ ዶላርን ለመግዛት ይገደዳሉ፡፡ ከሳዑዲ ነዳጅ ለማምጣት ኢትዮጵያ በብር ዶላርን መጀመርያ መግዛት እንዳለባት ሁሉ፣ ሳዑዲ ከኢትዮጵያ ቡና ለመግዛት ዶላር ቀድማ መግዛት ይኖርባታል፡፡ ይህ ማለት አሜሪካ ባሳተመችው የዶላር ኖት ብቻ ግብይቱ ውስጥ ባትኖርም ታተርፋለች እንደ ማለት ነው፡፡

ይህንን ዓይነቱን የምዕራባውያኑን ጡንቻ የሚያፈረጥም ግብይት በርካታ አገሮች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያስቀሩ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2022 ቻይና ከሩሲያ ጋር በቻይና መገበያያ ገንዘብ ዩዋን መነገድ ጀምረዋል፡፡

በአንድ ዓመትም 88 ቢሊዮን ዶላር ግምት ያለውን የንግድ ልውውጥ ያለ ዶላር ማካሄድ ችለዋል፡፡ የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም ድረ ገጽ እንዳስነበበው ከሆነ ቻይና ከሩሲያ በተጨማሪ ከብራዚል፣ ከአርጀንቲና፣ ከዓረብ ኤምሬትስና ከፈረንሣይ ጭምር ያለ ዶላር መነገድ ጀምራለች፡፡

እ.ኤ.አ. በ1999 የአሜሪካ ዶላር እስከ 73 በመቶ አገሮች ሀብታቸውን ተቀማጭ ያደረጉበት ገንዘብ ነበር፡፡ ዛሬ ግን በዶላር ተቀማጭ የሆነው የዓለም አገሮች ሀብት 59 በመቶ ብቻ ነው፡፡ የዓለም አገሮች የአሜሪካ ዶላር ላይ ጥገኛ መሆንን ቀንሰዋል፡፡ በተለይም ከሩሲያና ከዩክሬን ጦርነት ወዲህ ዶላር እየተገፉ ነው፡፡

ምዕራባውያኑ ለዩክሬን አግዘው ወደ 300 ቢሊዮን የሚጠጋ የሩሲያን ተቀማጭ ሀብት ማገዳቸው ሳያንስ፣ ለዩክሬን የጦርነት ካሳ አድርገን እንሰጠዋለን ሲሉ መሰማታቸው ዓለምን ማስደንገጡ ይነገራል፡፡ ምዕራባውያኑ ሩሲያ ስዊፍትን ጨምሮ በዓለም አቀፍ መገበያያዎች እንዳትጠቀም ማድረጋቸው፣ ሌሎች አገሮች ‹‹ነገ በእኔ›› እንዲሉ አድርጓቸዋል ይባላል፡፡ እነዚህ ሁሉ መነሻ ምክንያቶች ተደራርበው እንደ ብሪክስ ያሉ አማራጭ ማኅበራትን የማጠናከሩና ከዶላር ጥገኝነት ራስን የማላቀቁ ፍላጎት መጠናከሩ በሰፊው እየተዘገበ ነው፡፡

ኡሪያት ቻም ኡጋላ (አምባሳደር) እንደተናገሩትም፣ ኢትዮጵያ ሊኖራት የሚችለውን ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ተጠቃሚነትን አሥልታ የብሪክስ አባል የመሆን ፍላጎት እንዳሳየች ነው የተነገረው፡፡

ከሰሞኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ መለስ ዓለም (አምባሳደር)፣ ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ለመሆን ጥያቄ እንዳቀረበች ይፋ አድርገዋል፡፡ መግለጫውን ተከትሎ ከደቡበ አፍሪካ ግማሽ ኢኮኖሚ ያነሰ ኢኮኖሚ ያላትና ጥቅል ምርቷ ከ156 ቢሊዮን ዶላር ያልበለጠው ኢትዮጵያ፣ ‹‹ብሪክስን ልቀላቀል አለች›› በማለት የዓለም መገናኛ ብዙኃን በስላቅ ዘግበዋል፡፡ ጩጬ ኢኮኖሚ ይዛ ብሪክስን የምትቀላቀለዋ ኢትዮጵያ ‹‹ጩጬዋ የብሪክስ አባል ልትሆን ነው፤›› ሲሉም ተሳልቀዋል፡፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሁለተኛዋ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ እንዳላት የዘነጉ ሚዲያዎች፣ ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ለመሆን እንደማትመጥን ጠቅሰዋል፡፡ ይሁን እንጂ ሰፊ የሰው ኃይልና ሰፊ ገበያን ብቻ ሳይሆን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገትንም ይዛ ኢትዮጵያ ማኅበሩን እንደምትቀላቀል በመጥቀስ፣ የኢትዮጵያ ወደ ብሪክስ መግባት ለራሷ ብቻ ሳይሆን ለማኅበሩም ጥንካሬ መሆኑን የተናገሩት ወገኖች በርካታ ናቸው፡፡ አሁን ቡድን ሰባት ከሚባለው ሰብስብ በሕዝብም በጥቅል ምርትም በልጧል የሚባለው ብሪክስ ኢትዮጵያን መቀላቀሉ ትልቅ ዕድል እንደሆነ ነው እየተነገረ ያለው፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን ኢትዮጵያ እንደ ብሪክስ ያሉ አማራጮችን ለማማተር የተገደደችው በምዕራባውያኑ በደረሰባትና ሊደርስባት በሚችል ግፊት መሆኑ በሰፊው እየተነገረ ይገኛል፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ጋር ተያይዞ አገሪቱ ያላት የውጭ ግንኙነት ሻክሮ ነው የቆየው፡፡ ምዕራባውያኑ በተለይ አሜሪካና የአውሮፓ ኅብረት ተከታታይ ማዕቀቦችን በኢትዮጵያ ላይ ጥለዋል፡፡ ይህንን ማዕቀብ ለማንሳት አሜሪካ ከሰሞኑ እንደወሰነች በሰፊው ቢነገርም፣ ማዕቀቡ አስከትሎት የቆየው ጫና ለኢትዮጵያ ትምህርት ሰጪ እንደሆነ ነው የሚነገረው፡፡

ይህንኑ የሚያጠናክር አስተያየት የሰጡት የኢኮኖሚው አማካሪ ቆስጠንጢኖስ በርሄተስፋ (ዶ/ር)፣ የማዕቀቡ መነሳት በሁለት መንገድ ሊታይ እንደሚችል ይናገራሉ፡፡

‹‹አሜሪካኖቹ ማዕቀቡን ማንሳታቸው ከፖለቲካ አንፃር የሚታይ ነው፡፡ አንዳንዶች አሁንም ቢሆን በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ ቀጥሏልና ማዕቀቡ መነሳት የለበትም እያሉ ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን እነሱ ከፖለቲካ አንፃር ነው ይህንን የወሰኑት ተብሎ ይገመታል፡፡ ኢትዮጵያ አንደኛም የአፍሪካ ኅብረት፣ እንዲሁም የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን መቀመጫ ናት፡፡ ኢትዮጵያን በማዕቀብ ከማራቅ ይልቅ ቀርበን አጋር ብናደርጋትና ብናነጋግር ልታሻሽል ትችላለች በሚል ነው ወደ እዚህ ዕርምጃ የገቡት፤›› በማለት ያስረዳሉ፡፡

አሜሪካኖቹ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቋርጠናል ቢሉም ሆነ የአጎዋ ንግድ ዕድልን ቢከለክሉም፣ ዘንድሮ ወደ 1.8 ቢሊዮን ዶላር የሰብዓዊ ረድዔት መስጠታቸውን ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር) ይጠቅሳሉ፡፡

‹‹አሜሪካኖቹ ማዕቀብ ጣልን ቢሉም ኢትዮጵያን መርዳት ግን ፈጽሞ አልተውም፡፡ አሁን ማዕቀቡን አነሳን ማለት የፈለጉት ከሰብዓዊ መብት ይልቅ ፖለቲካዊ አንድምታ ያለው ዕርምጃ ነው፡፡ ወደ ቻይና የተፅዕኖ ቀጣና ጭልጥ ብለን እንዳንገባ የወሰዱት ነው የሚመስለው፤›› ብለዋል፡፡

ምዕራባውያኑ በተለይ አሜሪካኖች ከሰሞኑ በኢትዮጵያ ላይ የጣሉትን ማዕቀብ ለማንሳት የተገደዱት በተዘዋዋሪ በኢትዮጵያ ጫና የመጣ ነው ብሎ መናገር ይቻል እንደሆነ የተጠየቁት ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር)፣ በተወሰነ መንገድ ማለት እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡

‹‹ኢትዮጵያን ዝም ብሎ መቀጥቀጥ አያዋጣም ብለው ያሰቡ ይመስላል፡፡ ሙሉ ለሙሉ በእኛ ዲፕሎማሲያዊ ጫና የመጣ ላይሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን የሰሜኑ ጦርነት ስለቆመ ማዕቀቡን መቀጠሉ አስፈላጊ እንዳልሆነ አመዛዝነው ለማንሳት የወሰኑ ይመስላል፤›› በማለት ይናገራሉ፡፡

በዩክሬን ጦርነት አፍሪካዊያን የያዙትን አቋም ምዕራባውያኑ ብዙም የተደሰቱበት አይመስሉም፡፡ አፍሪካዊያኑ ከቻይና ጋር ከመሻረክ በተጨማሪ ወደ ሩሲያ ካምፕ እንዳያዘነብሉ በማሰብ፣ ምዕራባውያኑ በተቻለ መጠን አፍሪካዊያኑን ወደ ራሳቸው መሳብን አማራጭ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ነው ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር) ያብራሩት፡፡

በዘ ኢፖች ታይምስ የዜና ምንጭ ‹‹Has the West already lost control of its most vital sea route?›› በሚል ርዕስ ሰፋ ያለ ሐተታ ያስነበቡት ግሪጎሪ ኮፕሊ፣ አሜሪካና ምዕራባውያኑ የቀይ ባህር ብሎም ኢትዮጵያ የምትጎራበትበትን የምሥራቅ አፍሪካ ቀንድ ቀጣና ቀስ በቀስ እያጡት ስለመሆኑ ይናገራሉ፡፡ በሰፊው የቀይ ባህር አዋሳኝ ቀጣና የተፈጠሩ የቅርብ ጊዜ ጂኦ ፖለቲካዊ ለውጦችን አንድ በአንድ የሚጠቃቅሱት ጸሐፊው፣ ምዕራባውያኑ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮችን ለማቅረብ ጥረት የጀመሩባቸውን አስገዳጅ ሁኔታዎች አስረድተዋል፡፡

የሩሲያና የቻይና በቀይ ባህር ብሎም በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና እንቅስቃሴ መጨመር ምዕራባውያኑን እንደሚያሠጋ ዘገባው ይጠቅሳል፡፡ የመካከለኛው ምሥራቅ ፖለቲካ መለዋወጥንም ያወሳል፡፡ የሳዑዲና ኢራን መታረቅ ብቻ ሳይሆን፣ እስራኤል ከዓረብ አገሮች ጋር ያላት ግንኙነት መለወጡ ለምዕራባውያኑ የቆየ ፖሊሲ አመቺ አለመሆኑን ይዳስሳል፡፡

ከሁሉም በላይ ደግም ምዕራባውያኑ የሚጠሏቸው የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ፣ የቀይ ባህርና አዋሳኝ የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ቁልፍ ተፅዕኖ ፈጣሪ እየሆኑ መምጣታቸውን ዘገባው በሰፊው ይተነትናል፡፡

የቻይና የቀድሞ ተማሪ ኢሳያስ አፈወርቂ በቀይ ምንጣፍ እየተራመዱ እ.ኤ.አ. ከግንቦት 14 እስከ 19 2023 በቤጂንግ ጉብኝት ሲያደርጉ መክረማቸው ከፍ ያለ አንድምታ ያለው መሆኑን ያክላል፡፡ ቻይና አሥር ቢሊዮን ዶላር ለኤርትራ ተጨማሪ ድጋፍ አቀርባለሁ ማለቷ ዝም ብሎ የመጣ አለመሆኑን ዘገባው አመልክቷል፡፡

ከቤጂንግ መልስ ወደ ሩሲያ ሞስኮ ኢሳያስ የማምራታቸውን አጋጣሚ፣ እንዲሁም ግንቦት 31 ቀን ቭላድሚር ፑቲን ከኤርትራ ጋር አገራቸው ዘርፈ ብዙ የትብብር ስምምነቶች መፈራረሟን ማስታወቃቸውን አክሎ የሚያወሳው ዘገባው፣ የኢሳያስን አጋርነት ሁለቱም እየፈለጉት መሆኑን አስረጂ አድርጎ ያቀርበዋል፡፡ ቤጂንግም ሆነች ሞስኮ ከዚህ ቀደም በምሥራቅ አፍሪካ በነበራቸው አጋርነት፣ ኢትዮጵያን ከኤርትራ ሳያበላልጡ መወዳጀትን ይከተሉ እንደነበር ጸሐፊው ያስታውሳሉ፡፡

ኤርትራና ኢትዮጵያ ታርቀው የቆየ ጠላትነታቸውን መተዋቸውን የሚናገሩት ጸሐፊው፣ ምዕራባውያኑ ግን በኢሳያስ ላይ ያላቸውን ቂምና ቁርሾ በማስቀደማቸው የተነሳ ቀጣናው ከእነሱ ጆኦ ፖለቲካዊ ተፅዕኖ ተገፍቶ እንዲወጣ አድርገዋል በማለት የአካባቢውን ሁኔታ ተንትነዋል፡፡

ምዕራባውያኑ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከኤርትራም አልፈው የረዥም ጊዜ ወዳጃቸውን ኢትዮጵያን ጭምር ሲጫኑና በማዕቀብ ሲቀጡ ኖረዋል፡፡ አሁን ግን ይህንን አካሄድ ማለዘብ ወይም መለወጥ ፈልገዋል እየተባለ ነው፡፡ ይህ የምዕራባውያኑ አቋም መቀየር ደግሞ የአፍሪካ ቀንድ አገሮች ፊታቸውን ወደ እነ ቻይና አቅጣጫ ከማዞራቸው ጋር ይገናኛል እየተባለ ነው፡፡

የኢትዮጵያ የብሪክስ ማኅበርን የመቀላቀል ጉዳይ የቆየ መሆኑን የሚያወሱት የኢኮኖሚ አማካሪው ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር)፣ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በነበሩ ጊዜ ጀምሮ ንግግሮች እንደነበሩ እንደሚያስታወሱ ጠቁመዋል፡፡

‹‹የእኛ የብሪክስ አባል መሆን ብዙ ዓይነት ጠቀሜታ አለው፡፡ የብሪክስ አባል አገሮች ከፍተኛ የልማት ሀብት ያላቸው ናቸው፡፡ የብሪክስ ባንክ ራሱን የቻለ ብዙ ብድር ሊገኝበት የሚችል ነው፡፡ ከቻይና የተበደርነው እጅግ ከፍተኛ ብድር እንደመሆኑ የዕዳ ቅናሽ (ስረዛ) ለማግኘትም ይረዳናል፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

ከ15 ዓመታት በፊት አካባቢ ቻይናውያን ራሳቸው በጠየቁት መሠረት የዓለም ባንክና አይኤምኤፍን ለመቋቋም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በተደረገ ጥናት መካፈላቸውን ያስታወሱት ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር)፣ ራሱን የቻለ ባንክ እንዲጀምሩ በጊዜው ለቻይናውያን ምክር እንደቀረበላቸው ጠቅሰዋል፡፡

የእስያ ኢንፍራስትራክቸር ልማት ባንክ የተባለው በዚህ መነሻነት እንደጀመሩና ከዓለም ባንክ በላይ ካፒታል የሚያንቀሳቀስ ባንክ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

‹‹ኢትዮጵያ ከምዕራባውያኑ ጥገኝነት ለመላቀቅ ብቻ ሳይሆን፣ ከሁለቱም ማለትም ከምዕራቡ ዓለምም ሆነ ከእነ ቻይና ጋር ሚዛን የጠበቀ ግንኙነት መሥርቶ ለመቀጠል ብሪክስን መቀላቀሏ ጠቃሚ ዕርምጃ ነው፤›› በማለትም ሐሳባቸውን አጠቃለዋል፡፡       

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -