Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የግንባታ ኢንዱስትሪ ሕጎች አለመተግበር ሠራተኞችን ለመብት ጥሰትና ለአደጋ እየዳረጋቸው መሆኑን ኢሰመኮ አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአገር አቀፍ ደረጃ ለግንባታው ኢንዱስትሪ ሕጎች ቢወጡም ተግባራዊ ባለመደረጋቸው፣ የግንባታ ሠራተኞች ለመብት ጥሰትና ለአደጋ እየተዳረጉ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ፡፡

ኢሰመኮ ዓርብ ሰኔ 30 ቀን 2015 ዓ.ም. ጉዳዩን በተመለከተ ባወጣው ሪፖርት፣ የሕጎች አፈጻጸም የላላ መሆን ለኮንስትራክሽን ሠራተኞች መብቶች አለመከበር ዋነኛው ምክንያት እንደሆነ በክትትል አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡ 

ኢሰመኮ አካሄድኩት ባለው ክትትል ለሴት ሠራተኞች ከባድ ወይም ለጤና ጎጂ የሆኑ ወይም የመውለድ ሁኔታን የሚያውኩ ሥራዎችን የተመለከቱ ድንጋጌዎች፣ የሴት ሠራተኞችን ጉልበት በመጠቀም የሚካሄድ ማናቸውም ክብደትን ከቦታ ቦታ የማንቀሳቀስ፣ የመሸከም፣ የማጓጓዝ፣ የማንሳት፣ የማውረድ፣ የማውጣት፣ የመጎተት፣ የመሳብና የመሳሰሉት ሥራዎችና የክብደት መጠን ጣሪያ በአብዛኛው ክትትል በተደረገባቸው የግንባታ ሥራዎች እንደሚጣሱ፣ አልያም በተሟላ መንገድ አለመተግበራቸውን አይቻለሁ ብሏል፡፡ በተመሳሳይ በክትትሉ ለመረዳት እንደተቻለው በግንባታ ሥራ ዘርፍ በብዛት የሚስተዋሉ የሥራ ላይ አደጋዎች መቀጥቀጥ፣ በሹል ነገሮች መወጋት፣ መቆረጥ፣ ስብራት፣ መላጥ፣ መፈንከትና የኤሌክትሪክ አደጋዎች የመሳሰሉት ሲሆኑ ቋሚ አካል ጉዳትና ሞትም የሚስተዋሉ ከባድ አደጋዎች መሆናቸውን አስታውቋል፡፡

በአንዳንድ አካባቢዎች ለመከላከያ ቁሳቁሶች የሚወጡ ወጪዎች እንደ ኪሳራና የቅንጦት ወጪ የመቁጠር ሁኔታም ስለመኖሩ የመረጃ ምንጮች ገልጸውልኛል ሲሉ ኮሚሽኑ በሪፖርቱ ገልጿል፡፡

ኮሚሽኑ ደኅንነቱና ጤንነቱ የተጠበቀ የሥራ ሁኔታ የማግኘት መብት ያለምንም መድልዎ በማንኛውም የሥራ ዘርፍና የቅጥር ዓይነት ለሚሠሩ ሠራተኞች የተሰጠ መብት በመሆኑ፣ ከፍትሐዊና ምቹ የሥራ ሁኔታዎች መብት መሠረታዊ ክፍሎች መካከል አንዱና ከሌሎች መብቶች በተለይም ከአካላዊና አዕምሯዊ ጤና መብት ጋር የተቆራኘ መሆኑን በሪፖርቱ አብራርቷል፡፡

ኢሰመኮ የግንባታ ኢንዱስትሪ ከፍተኛ የሥራ ላይ አደጋዎች የሚከሰቱበትና ለደኅንነትና ለጤንነት አስጊ ከሆኑ ዘርፎች መካከል በመሆኑ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀና ጤናማ የሥራ ሁኔታ መብት ላይ አገር አቀፍ የሕግና ፖሊሲ ማዕቀፎችንና አተገባበራቸውን መፈተሽ እንደሚያስፈልግ አስታውቋል፡፡ 

ደኅንነቱ የተጠበቀና ጤናማ የሥራ ከባቢ የማግኘት መብትን የተመለከቱ ድንጋጌዎችን የመተግበር ኃላፊነት ያለባቸው ተቋማት ተቋማዊ ችግሮች፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላትን አስተባብሮና አቀናጅቶ የሚመራ ጠንካራ ሥርዓት አለመኖርና ደካማ የመረጃ አያያዝ ስለመኖሩ በክትትሉ ማረጋገጡን ኮሚሽኑ አክሏል፡፡

በግንባታ ሥራ ዘርፍ ደኅንነቱ የተጠበቀና ጤናማ የሥራ ሁኔታ መብት በተሻለ መንገድ እንዲተገበር፣ የፖሊሲና የሕግ ማሻሻያ ምክረ ሐሳቦችንና ሕጎችን ማስተዋወቅ፣ እንዲሁም የመብቱን ተፈጻሚነት ለማረጋገጥ የሚረዱ ሥርዓቶችን መዘርጋትና የሙያ ደኅንነትና ከጤንነት ጋር ተያያዥነት ያላቸውን የዓለም የሥራ ድርጅት ስምምነቶችን በማፅደቅ ሥራ ላይ ማዋል እንደሚስፈልግ ኮሚሽኑ አሳስቧል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች