በአበበ ፍቅር
መንግሥት በጣለባቸው ከፍተኛ ቀረጥ ሳቢያ ፋብሪካዎቻቸውን ሙሉ በሙሉና በከፊል ለመዝጋት መገደዳቸውን፣ የኢንዱስትሪ ባለቤቶች አስታወቁ፡፡
የኢንዱስትሪ ባለቤቶቹ ይህንን የተናገሩት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥራ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ከግል ባለሀብቶችና ከአምራች ኢንዱስትሪዎች ጋር፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ ባለፈው ሳምንት በተደረገ የውይይት መድረክ ነው፡፡
ከሦስት ዓመት በፊት ከቻይና ከቀረጥ ነፃ ሲገቡ የነበሩ የመለዋወጫ ዕቃዎች በአሁኑ ወቅት እንደ ቅንጦት ዕቃ ተቆጥረው ከ200 እስከ 300 በመቶ ቀረጥ ክፈሉ መባላቸውን፣ ይህም ከአቅማቸው በላይ በመሆኑ ሥራቸውን ለማቆም መገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡
በርካታ የሥራ ዕድሎችን መፍጠር የሚያስችሉ ኢንዱስትሪዎች እየተዘጉና ሠራተኞቻቸውም ከሥራ እየተሰናበቱ እንደሆነ ባለሀብቶቹ አስታውቀዋል፡፡ እያጋጠመ ካለው የዶላር እጥረት በተጨማሪ፣ ከአቅም በላይ የሆነ የቀረጥ ክፍያና ሌሎች መሠረታዊ ችግሮች ለፋብሪካዎቹ መዘጋትና ለሠራተኞች መሰናበት እንደ ምክንያት አቅርበዋል፡፡
‹‹በጉምሩክ በኩል በምናስገባው የመለዋወጫ ማሽን ከአቅም በላይ የሆነ ቀረጥ ስለተጣለብን፣ ካሉን አራት ፋብሪካዎች መካከል ሦስቱን ለመዝጋት ተገደናል፤›› ሲሉ የፍርቄ ፋብሪካ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ሥራ አስኪያጀ አቶ ሲሳይ እሸቴ ተናግረዋል፡፡
በዚህም 560 ማሽኖች በመለዋወጫ እጥረት ሳቢያ ሥራ ማቆማቸውን፣ እንዲሁም መሥራት የሚችሉ 220 ማሽኖችም በአቅርቦት እጥረት ሥራ እንዳቆሙ ገልጸዋል፡፡ ‹‹መለዋወጫ ያጡ ነገር ግን መለዋወጫ ሲያገኙ አገልግሎት መስጠት የሚችሉ 560 ማሽኖችን መለዋወጫቸው ከቀረጥ ነፃ እንዲገባ መሟላት ያለበት መሥፈርት አሟልተን በጣም ብዙ መንገድ ሄደናል ነገር ግን ምላሽ አላገኘነም፤›› ብለዋል።
‹‹መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ መፍትሔ ካላበጀለት እንደ አገር ዋጋ ያስከፍለናል፤›› ብለው፣ ‹‹የዶላር እጥረት መኖሩን እንገነዘባለን፣ ነገር ግን መንግሥት በተቻለው መጠን በሚገቡ ጥሬ ዕቃዎች ላይ ያሉ ክፍተቶችን ቢያመቻችልን የተዘጉ ፋብሪካዎችን በመክፈት እየታየ ያለውን የሥራ አጥ ክፍተት ለማሟላት ዝግጁ ነን፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ከነበሩት አራት የተለያዩ ፋብሪካዎች ሦስቱ በመዘጋታቸው 900 ሠራተኞች ከሥራ መሰናበታቸውን፣ በአንድ ፋብሪካ ግን 150 ሠራተኞች በሥራ ላይ መሆናቸውን አቶ ሲሳይ ገልጸዋል፡፡፡
የኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ የገቡት ቻይናውያን ጥሬ ዕቃዎችን ከቀረጥ ነፃ እንደሚያስገቡ፣ ክር በማስመሰል የተሰፉ ልብሶችን አስገብተው እንደሚሸጡ ጥቆማዎች እንደ ደረሷቸው ተናግረዋል፡፡
‹‹ለአገር መክፈል ያለባቸውን ካለመክፈላቸው ባሻገር የሚያቀርቧቸው ዕቃዎች ደረጃቸውን ያልጠበቁ በመሆናቸው በገበያችን ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረቡን፤›› ነው ብለዋል፡፡ ‹‹ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ የውጭ ኢንቨስተሮች ክር አምጥተው ልብስ ከሚሰፉ ይልቅ፣ መለዋወጫዎችን ማምረት የሚችሉ ማሽኖችን ቢያስገቡልን ያለ ምንም ዶላር መሥራት እንችላለን፤›› ሲሉም አስረድተዋል፡፡
በውይይቱ ወቅት አንድ ሌላ ባለሀብት በሰጡት አስተያየት የአቶ ሲሳይን ሐሳብ ተጋርተዋል፡፡ ‹‹እየታየ ባለው የገበያ አለመረጋጋት የብረታ ብረት ማምረቻ ጅርጅታችን እየሠራ አይደለም፤›› ብለዋል። ‹‹ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ እየተቀዛቀዘ የመጣው የሥራ እንቅስቃሴ፣ ላለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ችግሩ ተባብሶ ሥራ ለማቆም ተገደናል፤›› ሲሉ አስረድተዋል።
‹‹ችግሩ አገር አቀፋዊ ቢሆንም የከተማ አስተዳደሩ ለበርካታ ሰዎች የሥራ ዕድል ለሚፈጥሩ ፋብሪካዎች ትኩረት ሰጥቶ ዕገዛ ማድረግ ቢኖርበትም፣ የመሥሪያ ቦታ ከመስጠት ጀምሮ የተለያዩ አገልግሎቶችን ለማገኘት በጣም እየተቸገርን ነው፤›› ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርበዋል።
‹‹በድርጅታችን በሚገኝ ሰፊ መሬት ላይ ሼድ በመሥራት የሥራ ዕድል ለመፍጠር እንቅስቃሴ ስናደርግ፣ ፈቃድ የሚሰጡ አካላት የተለያዩ ምክንያቶችን እያቀረቡ አጥጋቢ ምላሽ ማግኘት አልቻልንም፤›› ሲሉ ባለሀብቱ አብራርተዋል። ‹‹አሁን ያለንበት ወቅት አስቸጋሪ በመሆኑ በከተማ አስተዳደሩ የሚቀርቡ ምክንያቶች፣ ባለው ችግር ላይ ተጨማሪ ችግር ሊፈጥሩብን አይገባም፤›› ብለዋል።
አምራች ኢንዱስትሪዎች በመዘጋታቸው ምክንያት በተለያዩ የግልና የመንግሥት የፋይናንስ ተቋማት ሳይቀር፣ ዜጎች ሥራ ለመቀጠር ከአንድ እስከ ሁለት መቶ ሺሕ ብር ክፈሉ እየተባሉ መሆናቸውን አክለዋል።
‹‹ዘርፈ ብዙ ችግሮች ባሉበት ሁኔታ የከተማ አስተዳደሩ እንዲህ አድርጉ እንደዚያ ሥሩ ማለቱ መፍትሔ አይሆንም፡፡ ይልቁንስ በጋራ በመሆን ምቹ የሥራ አካባቢን በመፍጠር ዘለቄታዊ መፍትሔ ማበጀት ይገባል፤›› ሲሉ ባለሀብቱ ሐሳባቸውን አጠቃለዋል፡፡
ከተነሱት የምንዛሪ እጥረት፣ ከአቅም በላይ የሆነ የቀረጥ ክፍያና ተያያዥ ጥያቄዎች በተጨማሪ እንደ መብራትና ውኃ የመሳሰሉት መሠረተ ልማቶች በመቆራረጣቸው ለተጨማሪ ወጪ መዳረጋቸውን ሌሎች ተሳታፊዎች በመድረኩ ላይ ቅሬታቸውን አቅርበዋል።
‹‹ተጨማሪ የሰው ኃይል እንድትፈጥሩ ጥሪ አድርገን እንወያይ፣ ችግሮች በአግባቡ ባለመፈታታቸው ምክንያት ኢንዱስትሪ ዘግተን ሠራተኞችን በትነናል የሚል ነገር መስማት በጣም ከባድ ነው፤›› ያሉት ደግሞ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የሥራና ኢንተርፕራይዝ ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር ዓባይ ናቸው፡፡ ‹‹ሰፊ የሥራ ዕድል የሚፈጥረው አምራች ኢንዱስትሪው ነው ካልን ምን ያህሎቹ ፋብሪካዎች ችግራቸው ተፈቶ ማምረት እየቻሉ ነው የሚለው ጥያቄ አብሮ ሊነሳ ይገባል፤›› ብለዋል።
‹‹የጥያቄዎቹ መነሻም ኢንዱስትሪው የውጭ ምንዛሪ ማምጣት የሚያስችል ስምምነት መፍጠር አንዱ የመንግሥት ኃላፊነት ነው የሚል ደረጃ ላይ ባለመድረሳችን፤›› ነው ሲሉም አክለዋል፡፡
በባለሀብቶቹ የተነሱት የቦታና ተያያዥ ጥያቄዎች ሕጋዊ አሠራሩን በመጠበቅ ሊፈቱ ይገባል ያሉት አቶ ጃንጥራር፣ ‹‹አንድ አምራች ኢንዱስትሪ ሲዘጋ የግለሰቡ ነው ብለን አናምንም ይልቁንስ የሚዘጋው የአገር ሀብት ነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ከ1,050 ሠራተኞች ውስጥ 150 አስቀርቶ 900 ሠራተኞችን ሲበትኑ እየከሰረ ያለው ድርጅቱ ብቻ አይደለም፡፡ እንደ አገር በጣም የሚያስደነግጥ ነው፤›› ሲሉ አብራርተዋል፡፡
የግል ባለሀብቶችና ተቋማት ተሳትፎ ካላደገ አሁን ያለውን የሥራ አጥነት ችግር ለመፍታት አዳጋች እየሆነ ነው ያሉት አቶ ጃንጥራር፣ ‹‹የግሉ ዘርፈ ለሥራ ዕድል ፈጠራ ከ80 በመቶ በላይ የሚሸፍን ሲሆን፣ በመንግሥት በኩል ደግሞ 20 በመቶ ብቻ ሚና አለው፤›› ብለዋል፡፡
መንግሥት ላለፉት አሥር ዓመታት ባስቀመጠው ዕቅድ በተለይ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን አቅም በማጎልበት 18 እና 17 በመቶ የነበረውን የሥራ አጥነት መጠን ወደ ዘጠኝና ስምንት በመቶ ዝቅ ለማድረግ አቅዶ ወደ ሥራ የገባ ቢሆንም፣ በተለያዩ ምክንያቶች የሥራ አጥነት ምጣኔው ከነበረበት 19.2 በመቶ ወደ 22.8 በመቶ ከፍ ማለቱን አቶ ጃንጥራር ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ኤጀንሲ አወጣው ባሉት መረጃ መሠረት፣ በሥራ አጥነት ከተመዘገቡት 22.8 በመቶ መካከል 80 በመቶ የሚሆኑት የትምህርት ደረጃቸው ከ12ኛ ክፍል በታችና የሥራ ፍላጎት የሌላቸው እንደሆኑ አመላክቷል ብለዋል፡፡
ምክትል ከንቲባው እንዳሉት፣ በከተማዋ እየታየ ያለው የሥራ አጥነት ከመደበኛው በላይ ማሻቀብ ከገጠር ወደ ከተማዋ የሚደረገው ፍልሰት ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ከሚታየው ከፍተኛ የሥራ አጥነት ቁጥር በተጨማሪ ከገጠር ፈልሰው የሚመጡት ሲጨመሩበት ለመዲናዋ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሆነባት ገልጸዋል፡፡ ችግሩን ለማቃለል ከኅብረተሰቡ በተነሱ ጥያቄዎች መሠረት የአዲስ አበባ ከተማ የነዋሪዎች መታወቂያ ካርድ ላላቸው ብቻ የከተማ አስተዳደሩ የሥራ ዕድል እየፈጠረ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡ በዚህም እስካሁን በአንድ አካባቢ ብቻ 90 ሺሕ ያህል ሥራ አጥ ወጣቶችን በመመልመል እያሠለጠነ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በአጠቃላይ በግል ኢንዱስትሪዎች ላይ የሚታዩ ችግሮችን በመፍታትና በተለያዩ ምክንያቶች ሥራ ያቆሙ ፋብሪካዎችን መልሶ በመክፈት፣ ሠራተኞችን ወደ ቀድሞ ሥራቸው እንዲመለሱ ጥረት ይደረጋል ብለዋል፡፡