Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ተሟገትኢቢሲን ‹ቤት ለእንቦሳ!›

ኢቢሲን ‹ቤት ለእንቦሳ!›

ቀን:

በገነት ዓለሙ

ባለፈው ሳምንት፣ በፈረንጆቹ የጁን ወር የመጨረሻ ሳምንትና የመጨረሻ ቀናት ውስጥ (ጁን 29፣ በእኛ ሰኔ 20 ቀን 2015 ዓ.ም.) ፎሬን ፖሊሲ የተባለው የአሜሪካ መጽሔት፣ ‹‹U.S. Lifts Human Rights Violations Designation on Ethiopia ›› የሚል ዜና ይዞ ወጥቷል፡፡

እዚህ ፎሬን ፖሊሲ የተባለው መጽሔትም እንደ ፍጥርጥሩና እንደ ልቡ ጭምር ያለበት/የተናገረበት በሰላም ስምምነቱ የቆመ ጦርነት ውስጥ ሳንገባ በፊት የመንግሥት አውታራትን፣ የዴሞክራሲ ተቋማትን ገለልተኛ አድርጎ እንደገና መገንባትን፣ ሕግ፣ የአገር ሕግ፣ መንግሥትን ራሱን ወደሚገዛበት ሥርዓትና አሠራር እንገባለን ማለትን ወደ ጀመረ ለውጥና ሽግግር ውስጥ ጉዞ ጀምረን ነበር፡፡ ጦርነቱም የተጫረውና የተነሳው ይህንን የለውጥ ጉዞ በመቃወምና በመጠናወት ነው፡፡ ጦርነቱ ውስጥ ስንገባ ከባዱና ልዩ ልዩ ዓይነት የውጭ ጣልቃ ገብነት፣ ተፅዕኖ፣ የማዕቀብና የጭቆና ዕርምጃ ጭምር የተደባለቀበትና የተረባረበበት ከባድና ብዙ አደጋ ያለበት ጦርነት ውስጥ የገባነውም ደረጃውና የግዳጁ መጠን ቢለያይም፣ የመንግሥት አውታራትንና የዴሞክራሲ ተቋማትን ግንባታ ሥራ አገርን ከማዳን የህልውና ጉዳይ ጋር አንድ ላይ ደርበን ነበር፡፡ በመንግሥትና በሕወሓት መካከል ግጭትን በቋሚነት በመግታት አማካይነት ለዘላቂ ሰላም የተደረገው ስምምነት (ይህ የስምምነቱ ይፋዊ መጠሪያ ስም ነው) መያዝና መዝለቁ፣ እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች መረን እየለቀቀ የመጣውን የውስጥ ፀጥታና ሰላምን የማስተማመን የአገርና የመንግሥት ግዳጅ ላይ እየተሳለቀ የሚያሳጣን የውስጥ ሰላም ገመናችንን ልክና መልክ ከማስያዝ ዋና መደበኛ ሥራችን ጋር፣ ተቋማትን የመገንባት ጉዳይ ምን ጊዜም ችላ የማይባልና የማይዘነጋ አደራና ግዳጅ ነው፡፡

- Advertisement -

ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላምን የማስፈንና ዴሞክራሲን በፅኑ መሠረት ላይ የመገንባት ሥራ፣ በአጠቃላይ አገሪቱን ወደ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር የመቀየር ሥራ መሠረታዊ ቁምነገር፣ ከየትኛውም ፓርቲ ወገናዊነት ነፃ የሆኑ የተቋማት ግንባታ የግድ የሚፈልግ መሆኑ ነው፡፡ መንግሥታዊ አውታራትን ከገዥው ፓርቲ መለየት እስኪሳነን ድረስ የአንድ ፓርቲ/ቡድን አገዛዝ ተንሰራፍቶ በኖረበት አገር፣ ከዚህም የተነሳ የመንግሥት አውታራትና ዓምዶች የገዥው ቡድን አሻንጉሊትና መጫወቻ፣ እንዲሁም የተቃውሞ እልህ መውጫ ሆነው ባገለገሉበት አገር፣ ለዴሞክራሲና ለሕግ የበላይነት የሚደረግ ትግል ከቡድን/ከፓርቲ ይዞታነት፣ ባለቤትነትና ተቀፅላነት ነፃ የሆነ የአገዛዝ አውታር የመገንባት ተቀዳሚ ሥራ አለበት፡፡  የቡድኖች መንግሥታዊ ገዥነት ከነፃና ከትክክለኛ ምርጫ የሚመነጭበት አዲስ ምዕራፍ የሚከፈተው ገለልተኛ ተቋማት ሲገነቡ ነው፡፡

ሕገ መንግሥቱ ለምሳሌ በምዕራፍ ሦስት የመሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ድንጋጌዎች፣

(4) ለዴሞክራሲ ሥርዓት አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎች፣ ሐሳቦችና አመለካከቶች በነፃ መንሸራሸራቸውን ለማረጋገጥ ሲባል ፕሬስ በተቋምነቱ የአሠራር ነፃነትና የተለያዩ  አስተያየቶችን የማስተናገድ ችሎታ እንዲኖረው የሕግ ጥበቃ ይደረግለታል፡፡

(5) በመንግሥት ገንዘብ የሚካሄድ ወይም በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያለ መገናኛ ብዙኃን የተለያዩ አስተያየቶችን ለማስተናገድ በሚያስችለው ሁኔታ እንዲመራ ያደረጋል ይላል፡፡

ከተቋም ግንባታ፣ ተቋማትን ከፓርቲ ወገናዊነት ነፃ አድርጎ ከመገንባት ሥራዎች መካከል አንዱ የተጠቀሰው ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ በተቋምነት (ኢንስቲትዩሽን ብሎ) የጠራው ፕሬስ ወይም ሚዲያ አንዱ ነው፡፡

መሰንበቻችንን የኢትዮጵያን ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) የራሱን የአየር ሞገድ ያጨናነቀው ዜናና ፕሮግራም ላይ ተጠምዶ የቆየው፣ ብሮድካስተሩ ወደ ሸጎሌ አዲሱ ኮምፕሌክስ በመግባቱ/በመዛወሩ ጉዳይ ምክንያት ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ከሁለትና ከሦስት ወራት በፊት በብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ/ቋሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ እንደተናገሩትና እንዳስተዋወቁት አዲሱ የኢቢሲ የሥራ ቦታ/መሥሪያ ቤት፣ ‹‹…ወደ 10 ገደማ ስቱዲዮዎች አሉት፣ እየተሠራበት [ያለው] ሳይዝ፣ ጥራትና የቴክኖሎጂ ብቃት በዓለም ላይ ካሉት ትልልቅ ሚዲያዎች ያስመድበዋል፡፡ የናሬሽን ፓወር ጅማሮው ደግሞ… ከአራት፣ ከአምስት ዓመት በኋላ ኢቢሲ የአፍሪካን ወሬ የሚያወራ ነው፡፡ ይህንን ሥራ የሠሩ ብርቱ እጆች ሰው ፈጥረው የኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ሁነኛ ናሬሽን መፍጠሪያ ቱል ይሆናሉ፤›› ሲሉ ሰምተናል፡፡ ይህም ንግግር የመሰንበቻችን የኢቲቪ የአዲሱ የሸጎሌ ዋና መሥሪያ ቤቱ ወይም ጠቅላይ መምርያው ምርቃት ማጀቢያው ሲሆን ደጋግመን መስክረናል፡፡ የመንግሥት የሥልጣን አካላት፣ ባለሥልናትን ጨምሮ አቻና ሌሎች የመንግሥትም የግልም የሚዲያ ተቋማት ኃላፊዎች የደስታው ተካፋይ ሲሆኑ፣ ኢቢሲን እንኳን ደስ አለህ ሲሉ፣ የደስታው ተካፋይ ሲሆኑ ዓይተናል፡፡ የራሱ የተቋሙ ሠራተኞችም በፕሮግራሞቻቸውም በዜናዎቻቸውም ጭምር ሳይቀር የደስታ ሲቃቸውን ሲያሳዩ ተመልክተናል፡፡

ማዘጋጃ ቤት ሕንፃ ውስጥ ደባል ሆኖ የኖረው፣ ላለፉት 29 ዓመታት ደግሞ ‹‹ሰው›› ሌላ ድርጅት በሠራው ከቡናና ሻይ ባለሥልጣን በተወሰደው ሕንፃ ውስጥ ሲሠራ ለቆየው ኢቢሲ፣ ይህን በሰፊው የተነገረለትን የመሰለ በቦታም፣ በድርጅትም፣ በቴክኖሎጂም ግዙፍ ‹‹ኮምሌክስ›› ማግኘቱ ሁሉንም የሚያስደስት ነው፡፡ ይህ ደስታ ግን ትርጉም የሚኖረው፣ በተለይም በአሁኑ ጊዜ የለውጡንና የሽግግሩን ዋነኛ አደራና ግዳጅ የማከናወን ተግባር የሚሆነው ለብዙ ጊዜ (ከለውጡም በፊት፣ ከለውጡም በኋላ በነበሩት አምስት ዓመታት) ተወዝፎ የኖረው የሕገ መንግሥቱ የአንቀጽ 29 (4) እና (5) ድንጋጌዎች ተጨባጭ ማስፈጸሚያ አካል ሲሆን ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አቋቁመናል ካልንበት ጊዜ ጀምሮ ‹‹…ፕሬስ በተቋምነቱ አሠራር ነፃነትና የተለያዩ አስተያየቶችን የማስተናገድ ችሎታ (ባህርይና ፍጥርጥር ማለት ነው) እንዲኖረው [ሆኖ ይደራጃል] የሕግ ጥበቃ ይደረግለታል›› ብሎ አዞናል፣ አስዳጅ ትዕዛዝ ሰጥቶናል፡፡ በተለይ፣ በተለይ ‹‹በመንግሥት ገንዘብ የሚካሄድ ወይም በመንግሥት ቁጥጥር ያለ የመገናኛ ብዙኃን የተለያዩ አስተያየቶችን ለማስተናገድ በሚያስችው ሁኔታ እንዲመራ ይደረጋል›› የሚል ግዳጅና ትዕዛዝ አሸክሞናል፡፡

ሕገ መንግሥቱ ገና በረቂቅነት ደረጃና ኋላም ከፀደቀ በኋላ በነበረው አፍላ ወቅት፣ በተለይ ዓለም አቀፋዊ ሐሳብን የመግለጽና የንግግር ነፃነት ዋና ዋና አቀንቃኞች ይህንን የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 29 ድንጋጌ፣ በተለይም በመንግሥት ገንዘብ ስለሚካሄድ ሚዲያ፣ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ስላለ ሚዲያ የሚናገረውን ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ ሲበዛና አጥብቀው የጠሉትና የተቃወሙት፣ እንዴት ይህንን በመሰለ ሰነድ ላይ በመንግሥት ይዞታ/ባለቤትነት ሥር ስለሚቆይ/ስለሚዘልቅ ሚዲያ ይናገራል ብለው ነበር፡፡ የእኛ ሕመም ግን እነዚህ ሚዲያዎች (ነባሮችም፣ ኋላ የመጡትም) የተለያዩ አስተያየቶችን ለማስተናገድ በሚያስችላቸው ሁኔታ አሁንም ገና እንዲደራጁና እንዲመሩ አለመደረጉ ነው፡፡ እግረ መንገዴን ስለ‹‹የመንግሥት ሚዲያ›› አንድ ተጨማሪ ነገር ላክል፡፡ የሸጎሌው ኮምፕሌክስ በተመረቀበትና የመጀመሪያው የዜና ሥርጭት በተላለፈበት ዕለት (ሰኔ 26 ቀን 2015 ዓ.ም. ምሽት በቀረበው የኢቲቪ ‹‹አጀንዳ›› ዜና ላይ ሪፖርተሩ፣ ‹‹የመንግሥትና የሕዝብ እንደሆኑ [ስለ] የሚነገርላቸው ሚዲያዎች›› የሠራው ዜና ይሰማል፡፡ ይህ ዘገባ በያዘው በዋነኛው ጉዳይ ላይ፣ ማለትም እነዚህ ሚዲያዎች ለገዥው ፓርቲ ያደላሉ፣ ለሌሎች ፓርቲዎች ዝግ ናቸው የሚለውን ስሞታና ክስ ‹‹አጀንዳ›› አድርገው እንዲያብራሩ የተጋበዙት የዕለቱ እንግዳ (የኢትዮጵያ ሚዲያ ባለሥልጣን ዋና ኃላፊ) በሰጡት ማብራሪያ ውስጥ ስለዋናው ጉዳይ ከተናገሩትና ካብራሩት ይልቅ፣ ‹‹የመንግሥት ሚዲያ የሚባል የለም፤›› ያሉት ይበልጥ ገርሞኛል፡፡ ዕውን ‹‹የመንግሥት ብሮድካስት አገልግሎት›› የሚባል ነገር የለም? ብለን እናጠያይቅ እናመራምር ብንል ችግሩ ያለው ቋንቋው ላይ ነው፡፡ በእንግሊዝኛው የሕጉ ቅጅ (በሕጎች በሙሉ) የምንነጋገርበት የሚዲያ ዓይነት ፐብሊክ ብሮድካስቲንግ ሰርቪስ ይባላል፡፡ ይህ የብሮድካስት አገልግሎት ዓይነት ከ1999 ዓ.ም. ጀምሮ የፀናው ሕግ ‹‹ሥራ ላይ›› በኖረበት ጊዜ ሁሉ በአማርኛ የመንግሥት ብሮድካስት አገልግሎት ሲባል ኖሯል፡፡ ፐብሊክ ማለት ‹‹መንግሥት›› ሳይሆን ‹‹ሕዝብ›› ነው ያለው፣ ኧረ ፐብሊክ ብሮድካስቲንግን የመንግሥት ብለን የጠራነው ትክክል አይደለም፣ ‹‹የሕዝብ ቢባል ይሻላል፣ የሕዝብ ነው መባል ያለበት›› ተብሎ ከመጋቢት 27 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ የፀናው የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 ሲወጣ ነው፡፡

ይህንን የመሰለ የትራንስፎርሜሽን ሳይሆን በስም ብቻ፣ በቃላት ጨዋታ ብቻ የተሽሞነሞነ ለውጥ የገፋፋው፣ ገፋፍቶ ያመጣው ከዚያ ቀደም ሲል በ1999 ዓ.ም. የብሮድካስት አዋጅ የተፈጻሚነት ዘመን ውስጥ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ባለሥልጣን ከ2010 ዓ.ም. በፊት ባወጣው መመርያ፣ ፐብሊክ ማለት መንግሥት ሳይሆን ሕዝብ ነው ብሎ በመመርያ ነው፡፡ መጀመርያ የኢትዮጵያ የብሮድካስት ባለሥልጣን ያወጣው ከሰኔ 1 ቀን 2003 ዓ.ም. ጀምሮ የፀናው፣ ‹‹የመንግሥት ወይም የሕዝብ ብሮድካስት ፈቃድ አሰጣጥ መመርያ ቁጥር 1/2003›› በብሮድካስት አገልግሎት አዋጅ ቁጥር 533/99 በአንቀጽ 2/9 ፐብሊክ ብሮድካስቲንግ በአማርኛ የመንግሥት ብሮድካስት የሚባለውን፣ ‹‹የመንግሥት ወይም የሕዝብ ብሮድካስት አገልግሎት›› ብሎ ጠራ፣ ወሰነ፡፡ የመንግሥት ብሮድካስት አገልግሎት ወይም የሕዝብ ብሮድካስት አገልግሎት ማለት የአንድ ነገር፣ የዚያው የፐብሊክ ብሮድካስት ተለዋዋጭ/ተወራራሽ ስሞች/መጠሪያዎች ሆኑ፡፡ ቀስ እያለ… ግን ‹‹የሕዝብ ወይም የመንግሥት›› ቀረና አሁን ላይ ደግሞ፣ ‹‹የመንግሥት ሚዲያ የሚባል የለም›› ሲባል ሰማን፡፡

ይህ ሁሉ ሲሆን በፀናው፣ ፀንቶ በሚገኘው ከሐምሌ 16 ቀን 1999 ዓ.ም.  ጀምሮ ሥራ ላይ በዋለው የአገር የብሮድካስት ሕግ መሠረት (Public Broadcasting Service) ማለት የመንግሥት ብሮድካስት አገልግሎት ማለት ነው፣ ነበር፡፡ የሚገርመው ግን 2010 ዓ.ም. ላይ የመጣው ለውጥና የተጀመረው ሽግግር ከዴሞክራሲ አልባነት ወደ ዴሞክራሲ የመሸጋገር ትልምን መርጦ፣ የአገሪቱን የሥልጣን ዓምዶችና የዴሞክራሲ ተቋማት ከፓርቲ ታማኝነትና መዳፍ የማላቀቅ ማሻሻያዎችን የማካሄድ ሒደት ውስጥ ከገባ በኋላ፣ ለዚህ ዓላማ በወጡ ሕጎች ውስጥ በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 ፐብሊክ ሰርቪስ ብሮድካስቲንግ ‹‹የሕዝብ ብሮድካስት አገልግሎት ነው›› ተባለ፡፡ በዚህም አማካይነት የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ፐብሊክ ማለት ሕዝብ እንጂ መንግሥት አይደለም፣ የቆየ ትግልና ‹‹መመርያ›› በማውጣት የተቀጣጠለ ‹‹አመፅ›› በግርግር ውስጥ አሸናፊነት አገኘ፡፡ መንግሥትም፣ የመንግሥት የሥልጣን አካላትም በጉልበትና በሸፍጥ መንገድ ሁሉ የመዋደቅ ትግል ውስጥ ገብተው በነበረበት በዚያ ወቅት ነበር፣ ብሮድካስት ባለሥልጣን በመመርያ ፐብሊክ ሰርቪስ ብሮድካስቲንግ ማለት የሕዝብ ብሮድካስት አገልግሎት ነው ብሎ የለወጠው፡፡

‹‹ፐብሊክ›› ማለት ሕዝብ ነው? መንግሥት የተለያዩ ዘርፎችና አገባቦች ላይ አንዱ ወይም ሌላው ውስጥ ሲፈረጅ ማየት የተለመደ ነው፡፡ ለምሳሌ ፐብሊክ ቦዲ፣ ፐብሊክ መኒ፣ ፐብሊክ ፕሮፐርቲ፣ ፐብሊክ ዴት፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤት፣ የመንግሥት ገንዘብ፣ የመንግሥት ንብረት፣ የመንግሥት ዕዳ ናቸው፡፡ ፐብሊክ ትራንስፖርት፣ ፐብሊክ ኸልዝ፣ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ፣ እንዲሁም ፐብሊክ ኢንተረስት፣ ፐብሊክ ፓርቲሲፔሽን ደግሞ የሕዝብ ይባላሉ፡፡ ጥያቄውና ክርክሩ ፐብሊክ ሰርቪስ፣ ፐብሊክ ሴክተር፣ ወዘተ ማለትም አብዛኛው (?) መንግሥት እየተባለ ለምን ፐብሊክ ብሮድካስቲንግ የመንግሥት ሲባል ቆይቶ ለዚያውም በሸርና በመሰሪ መንገድ ወደ ‹‹ሕዝብ›› ተለወጠ የሚል የ‹‹ብሽቀት››፣ የመቆርቆር፣ የመብከንከን ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ ከዚህ የበለጠ የተቋም ግንባታ፣ ነፃ ተቋም የመገንባት፣ ኢወገናዊ በሆነ ተቋማት ላይ ዴሞክራሲን የማቋቋም ተግባር አካል ነው፡፡ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 29 (4) እና (5) ተግባራዊ አድርገናል ወይ ብሎ የመተሳሰብ፣ የመጠያየቅ ጉዳይ ነው፡፡ ‹‹በመንግሥት ገንዘብ የሚካሄድ ወይም በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያለ የመገናኛ ብዙኃን››፣ በሌላ ቋንቋ የመንግሥት ሚዲያ ወደ ሕዝብ ሚዲያ መለወጥ ያለበት መሆኑ ሕገ መንግሥቱ የጣለብን ግዳጅና ዕዳ ነው፡፡ የዚህ ትራንስፎርሜሽን ይዘት ዝርዝሩ፣ አጠቃላይ መልክና ልኩ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ገና አዲስ አስሰን (ፈልገን አፈላልገን) እንድረስበት የምንለው አይደለም፡፡ ተደጋግሞ የተጠቀሰው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 (4) እና (5)፣ እንዲሁም የዚሁ የበላይ ሕግ አንቀጽ 13 መሠረታዊ መንገድን ያስይዛል፣ ያስጨብጣል፡፡ በዚህ ብቻ ሳይወሰን በርካታ ሞዴል ሕጎችና የአሠራር መመርያዎች በዓለም ዙሪያ አሉ፡፡ በአፍሪካ ውስጥ የአፍሪካ የሰብዓዊና የሕዝቦች መብቶች ኮሚሽን የነደፋቸው መሠረታዊ መርሆዎች ሐሳብን በመግለጽ ነፃነት ሰፊ ማዕቀፍ ውስጥ የስቴት ብሮድካስተሮች ወደ ፐብሊክ ብሮድካስተርነት መለወጥ/ትራንስፎርም ስለሚደረጉበት ሁኔታና አኳኋን ሞዴል አሠራርና ሕግና ደንቦችን ያበጃሉ፡፡ በዚህ ምክንያት የ‹መንግሥትን› ሬዲዮና ቴሌቪዥን ‹‹የሕዝብ›› የማድረግ ወግና ባህል አለ፡፡ ኢትዮጵያም ውስጥ መከናወን ያለበት ለውጥ ይኼው ነው፡፡ ለውጡና በአገር የበላይ ሕግ የተደነገገው ግዴታ ግን ስምን በመለወጥ፣ በስያሜ ላይ ለውጥ በማምጣት የትራንስፎርሜሽን ሥራ አይሠራም፡፡ እከሌን በሌላ ስም በመጥራት አካሉንና ይዘቱን አንለውጠውም፡፡ ለዚህ ነው የብሮድካስት አገልግሎት አዋጅ ቁጥር 533/1999 ፀንቶ በኖረበት ዘመን ውስጥ በራሱ ፐብሊክ ሰርቪስ ብሮድካስቲንግን በመመርያ የብሮድካስት ባለሥልጣን የሕዝብ ብሎ ሲጠራና የሕዝብም አደረግኩት ሲል፣ የለም አይሆንም የምንለው ለዚህ ነው የኢትዮጵያ/ሚዲያ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር በሰኔ 26 ቀን 2105 ዓ.ም. የኢቲቪ ዜና ላይ ‹‹የመንግሥት ሚዲያ የሚባል የለም›› ሲሉ፣ ኧረ በሕግ የምንለው፡፡

ወደ ዋናው ጉዳይ ገብተን የመንግሥት ሚዲያዎችን ዕውን ወደ ‹‹ሕዝብ›› ሚዲያ አሸጋግረናቸዋል ወይ የሚለው ጥያቄ ላይ ከምር መነጋገር ከተፈለገ መልሱ አዎንታዊ አይደለም፡፡ እንኳንስ ኢቢሲ የኢቢሲንና የሌሎችንም መገናኛ ብዙኃን ነፃነትና ገለልተኛነት ከአደጋ በበላይነት ለመጠበቅ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 (4) እና (5) የተወሰነ ባህርያቸው አለኝታ፣ ጋሻና መከታ ሆኖ ለማገልገል የተቋቋመው የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን እንኳ በተቋቋመበት የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ መሠረት ‹‹የባለሥልጣኑ ገለልተኛትና ነፃነት›› (አንቀጽ 7) ለስሙ መጠሪያ ታህል እንኳን ማሟላት አቅቶት ሲወድቅ ያየነው በይፋና በአደባባይ ሕጉን ራሱን ባወጣው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ላይ ነው (መጋቢት 29 ቀን 2014 ዓ.ም.)፡፡  የሕጉ ድንጋጌዎች በአጠቃላይ (አንቀጽ 7) ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ፓርቲ አባል የቦርድ አባል አይሆንም (አንቀጽ 11)፣ የሚሉት ተጥሰው ሲሾሙ አይተናል፡፡ ወደ ‹‹ሕዝብ›› ወይም ፐብሊክ ብሮድካስተርነት ሽግግር አደረገ ለማለት ኢቢሲም እዚህ ዓይነት የአመራርና የአስተዳደር ለውጥ ውስጥ መግባት አለበት፡፡ ከፖለቲካም ሆነ ከኢኮኖሚ ተፅዕኖ የተጋረዱ፣ የተከለሉና የተመሸጉ ሥራ አስፈጻሚዎችና የቦርድ አባላት ሊመሩት ይገባል፡፡

ከመንግሥት ሚዲያነት ወደ ፐብሊክ ሚዲያነት መሸገጋር፣ ይህንን ዕውን ማድረግ ለውጥና ማሻሻያዎችን ማድረግ ማለት ቀላል ግዳጅ አይደለም፡፡ ሕግ ከማውጣትም በላይ ለሕግ የመገዛትን የመሰለ አዲስ ባህልና መጠበቂያ ይሻል፡፡ የጋዜጠኛነት ሙያ ወይም የሚዲያ ሥራ በአገራችን ሲጀመር የመንግሥት ቃል አቀባይና አወዳሽ ሆኖ የተቃኘ ነው፡፡ የመንግሥት ባለሟልና አገልጋይ ሆኖ የተሠራ ነው፡፡ ዋናው ጉዳያችን የመንግሥት ሚዲያ ሆኖ ነው እንጂ ነፃነት የሚዲያ ነፃነት የአንዱ ወይም የሌላው ብቻ የሚባል ‹‹ባህርይ›› አይደለም፡፡ የአገሪቱን ሰላም ከሚነሱ/ከሚያባብሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት ብዙ የሚለፋበት፣ የሚለፉበት ብቻ ሳይሆን የሚከላከሉትና ከፍተኛ ኃላፊነት የሚያሸክም ነው፡፡ በተለይም የሁሉም ሚዲያዎች ተቀዳሚ ተግባር (የመንግሥት ነኝ አይደለሁም ሳይሉ) የመናገር ነፃነታቸውን የሚያጎናፅፋቸውን ሰላምና ዴሞክራሲ ሥር እንዲይዝና እንዲፀና መታገል ነው፡፡ መብቴ ነው፣ ነፃነቴ ነው የምንለውን ያህል የአገራችን የፖለቲካ ምኅዳር የተለያዩ ሐሳቦችን፣ የሐሳብ ውድድሮችን የማስተናገድና የማስተናበር ልምምድ ኖሮት የማያውቅ መሆኑን ጭምር ከመረዳት መነሳት አለብን፡፡

መረጃዎች፣ ሐሳቦችና አመለካከቶች በነፃና በኃላፊነት የሚንሸራሸሩበት፣ በሰላማዊና በሕጋዊነት የሚፋተጉበትና የሚብላሉበት የፖለቲካ ምኅዳር መኖሩን ለማረጋገጥ ሲባል ነው፣ ‹‹ፕሬስ በተቋምነት የአሠራር ነፃነትና የተለያዩ አስተያየቶች የማስተናገድ ችሎታ እንዲኖረው የሕግ ጥበቃ ይደረግለታል›› የተባለው፡፡ ይህ ለሁሉም ፕሬስ እውነት ነው፡፡ ወጪውን በቻለላቸው፣ በገንዘብ አዋጮቻቸው፣ በፈጠሯቸው፣ ጠፍጥፈው በሠሯው ሰዎች/ተቋማት የፖለቲካ ዝንባሌ ውስጥ የማርገድ ወገንተኛነት ውስጥ ‹‹እንሞታታለን›› የሚሉ ሚዲያ ይዞ ስለፕሬስ ነፃነት መናገር እንደማይቻል ሁሉ፣ ኢቢሲም ነፃ ሚዲያ ሆነ የምንለው የሚፆመው ዜና ወይም ጭብጥ ‹‹እርም የሰው ገላ›› ብሎ የሚተወው ጉዳይ የለም ሲባልና በተግባር ሲገለጽ ነው፡፡

አንዳንድ ሆቴሎችና ሌሎች ገበያዎች ውስጥ የሆነ ዕቃ ወይም የሸቀጥ ዓይነት እሱን እኛ ‹አናወርደውም››፣ እሱን እኛ አንሸጥም ሲሉ እንሰማለን፡፡ ምክንያታቸውም ‹‹ፈላጊ የለውም›› ከሚል ጀምሮ በቃ እሱን አንሸጥም፣ መሸጥ አንፈልግም የሚል ዓይነት ሊሆን ይችላል፡፡ እዚህም ውስጥ እንኳን ተፈጻሚ የሚሆን ይህንን የሚከላከል የሸማቾች ጥበቃ ሕግ ያለ ይመስለኛል፡፡ ሚዲያው ውስጥ ግን ከዚህ የበለጠ ጥበቃ አለ፣ መኖርም አለበት፡፡ ወደ ሕግ ከመሄዳችን በፊት መጀመሪያ ነገር አንድ ሚዲያ ውስጥ (ለምሳሌ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ያወጣው የኢንፎርስድ ዲስአፒራንስ ዜና ኢቪቲ ላይ አይነገርም ማለት፣ እዚያው ኢቲቪ ውስጥ) ነውር መደረግ አለበት፡፡ የኢቢሲን አዲስ የሥራ ቦታ ምረቃ ምክንያት በማድረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ጉዳይ አማካሪ ሚኒስትር ዳንኤል ክብረት ኢቲቪ የማያወራው ወሬ፣ ኢቲቪ ጋ የማይደርስ ጉዳይ የሚባል ነገር የለም ሲሉ ሰምቻለሁ፡፡ ሚዲያው ከዚህ ሁሉ መፅዳት፣ ይህንን ሁሉ መዳን አለበት፡፡

በአጠቃላይ የአገራችንን ሚዲያዎች እንኳን ደስ አላችሁ የምንላቸው የሕዝብ ብሶት ዘጋቢ፣ መዝጋቢና አስተጋቢ፣ የእውነት ማጣሪያና የጭብጦች ማብላያ መሆን በሚያስችል ሁኔታ ሲደራጁ ጭምር ነው፡፡ ዝጉርጉር/የተለያዩ አመለካከቶችና ዕይታዎች፣ ትንታኔዎች እየተፋጩ የሚነጥሩባቸው መድረኮች ጭምር ሲሆኑ ነው፡፡

ከዚህ ጋር ሚዲያዎች ሁሉ የጥበብ መጀመሪያቸው ሊያደርጉት የሚገባ አንድ እውነት አለ፡፡ ቀደም ብዬም ጠቅሼዋለሁ፣ የሚዲያዎች ተቀዳሚ ተግባር የመናገር/ሐሳብን የመግለጽ ነፃነታቸውን የሚያጎናፅፋቸውን ሰላምና ዴሞክራሲ ራሱን የሚያጠፋ መሆን የለበትም፡፡ ዛሬ መብቴ ነው፣ ነፃነቴ ነው ማለት ሁሉም ቦታ የሚሰማ መፈክር፣ የሙገት ዓይነትና የ‹‹ዘራፍ!›› ፋሽን ነው፡፡ ቁምነገሩ ግን ገና መብቶቻችንንና ነፃነቶቻችንን ከእርጥባን በዘለለና ከጉልበተኛ ጥቃት ነፃ በሆነ ደረጃ መኖር ላይ በጭራሽ አልደረስንም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...