Thursday, July 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹በርካታ ጠቃሚ ነገሮችን ለመሞከርና ለመሥራት የሎጂስቲክስ ዘርፍን መጫወቻ ሜዳ ማስፋትና ነፃነት መስጠት ያስፈልጋል›› አቶ ዳዊት ውብሸት፣ የሎጂስቲክስ ዘርፍ ባለሙያና ኢንቨስተር

የኢትዮጵያ ፍሬት ፎርዋርደርስ አሶሴሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ የዓለም አቀፉ ፍሬት ፎርዋርደርስ አሶሴሽን የአንደኛው ቦርድ አባልና የአየር ጭነት አገልግሎቱን በዳይሬክተርነት ይመራሉ፡፡ በሎጂስቲክስ ሥራ በተለይ በአበባ ጭነት ማጓጓዝ ሰፊ ድርሻ ያለው ውብጌት ሆልዲንግ መሥራችና ኃላፊ የሆኑት አቶ ዳዊት ውብሸት፣ በሎጂስቲክስ ዘርፍ ከ20 ዓመታት በላይ መሥራታቸውን ይናገራሉ፡፡ ዘርፉ በአገሪቱ ካለው የፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ እየገጠመው ስላለው ተግዳሮትና መልካም ዕድሎቹን በተመለከተ ዮናስ አማረ ከእሳቸው ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ዕቃ አስተላላፊዎች/አጓጓዦች አሶሴሽን ምን እየሠራ ነው?

አቶ ዳዊት፡- የፍሬት ፎርዋርደርስ አሶሴሽኑ ብዙ ሥራዎችን ይሠራል፡፡ በዋናነት የምንሠራቸውን በሦስት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ አንዱ ሥራ የአድቮኬሲ ሥራ ነው፡፡ ዘርፉ ማለትም ሎጂስቲክስ ለአገር ያለው አስተዋጽኦ እንዲታወቅ የማድረግ ሥራ ይሠራል፡፡ ሁለተኛው ለዘርፉ ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር ከመንግሥት ጋር በመተባበር ጥረት ያደርጋል፡፡ የዕቃ አመላላሾች ድምፅ በመሆን ያገለግላል፡፡ ከእኛ ወገን ብቻ ሳይሆን ከመንግሥትም በኩል የሚፈለግ ነገር ሲኖር የዘርፉን አንቀሳቃሾች እናማክራለን፣ እናስተባብራለን፣ ብሎም ለጋራ ጥቅም የሚሆኑ ጉዳዮችን እናስፈጽማለን፡፡ ሌላኛው የሎጂስቲክስ ሥራ መስክ በትምህርት፣ በዕውቀትና በሳይንስ እንዲመራ ዕገዛ እናደርጋለን፡፡ ሥልጠናዎች በማዘጋጀት፣ ጉብኝት በማድረግ፣ የልምድ ልውውጥ በማካሄድና ሌሎች ልምድ የሚገኙባቸውን ዕድሎች በመፍጠር በዘርፉ የልምድና የዕውቀት ሽግግር እንዲፈጠር እንሠራለን፡፡ የውጭ አገሮች ልምዶች የሚገኝባቸውን ዕድሎች በመፍጠር፣ ትልልቅና ስመጥር ከሆኑ የውጭ የሎጂስቲክስ ዘርፎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር በአገራችን የተሻለ የአሠራር ክህሎት እንዲፈጠር ጥረት እናደርጋለን፡፡

ሌላው የአሶሴሽናችን ወሳኝ ሥራ ደግሞ ኢንዱስትሪውን በዓለም አቀፍ ደረጃ ማስተሳሰር ነው፡፡ ከውጭ አገሮች ዕቃ አጓጓዦች፣ ዕቃ አስተላላፊዎች ወይም የዕቃ አመላላሾች ማኅበራት ጋር ትስስር መፍጠር፣ ለዘርፉ ማደግ ዕገዛ ያላቸው ስብሰባዎች፣ ኮንፍረንሶች፣ ፓናል ውይይቶችና ማስተዋወቂያ መድረኮችን መካፈልና ማዘጋጀት አንዱ ሥራ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሥራ ትስስር ለመፍጠርም እንሠራለን፡፡ ለምሳሌ አንድ አበባ ላኪ አበባውን ወደ ውጭ ሲሸጥ፣ እዚህ አበባውን የሚልክለት ብቻ ሳይሆን ሄዶ የሚሸጥበት አገርም አበባውን ተረክቦ የሚያቀርብለት አካል ያስፈልጋል፡፡ እንዲህ ዓይነት አገልግሎት ሲፈለግ እኛ የምንፈጥረው ግንኙነት ወሳኝ ነው፡፡ ለምሳሌ አምስተርዳም ያለ ፍሬት ፎርዋርደር ኢትዮጵያ ካለ ፍሬት ፎርዋርደር ጋር አብሮ እንዲሠራ ግንኙነት እንፈጥራለን፡፡ በተለያዩ የዓለም ማዕዘናት የተፈጠሩ የፍሬት ፎርዋርደሮች ጥምረቶች አሉ፣ ከእነሱ ጋር ትብብሮች እንዲፈጠሩ ዕገዛ እናደርጋለን፡፡

ዓለም አቀፍ ኔትወርክ መፍጠር አንዱ የአሶሴሽናችን ሥራ ነው፡፡ ለምሳሌ የአፍሪካ አኅጉር ነፃ የንግድ ቀጣና እየተፈጠረ ነው፡፡ ለምሳሌ ጋና ከኢትዮጵያ ዕቃ ለመጫን ብትፈልግ፣ ጋና የሚገኙ ፍሬት ፎርዋርደሮችን ካላወቅን ሥራው አይቀላጠፍም፡፡ በዓለም ደረጃ ትልልቅ ማኅበራት አሉ፡፡ ከአሶሴሽናችንም ሆነ በተናጠል ከእነሱም ጋር ግንኙነት መመሥረት የአሶሴሽናችን ትልቁ አስተዋጽኦ ነው የሚሆነው፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ የሚሳተፉበት የዓለም አቀፉ ፍሬት ፎርዋርደርስ አሶሴሽን ሚናስ ምንድነው?

አቶ ዳዊት፡- ዓለም አቀፉ ፍሬት ፎርዋርደርስ አሶሴሽን (ፊያታ) (International Federation of Freight Forwarders Associations – FIATA) ወደ 46 ሺሕ አባላትን የያዘ ትልቅ ማኅበር ነው፡፡ እኔ በዚያ ውስጥ የአንድ ቦርድ አባልና የአየር ጭነት አገልግሎቱን በዳይሬክተርነት እመራለሁ፡፡ ይህ ሥራ ክፍል ከተመሠረተ በ50 ዓመት ታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚባል ደረጃ ነው አንድ አፍሪካዊ ወይም ጥቁር በዚህ ኃላፊነት የተሰየመው፡፡ ጥቁሮች አያውቁም፣ አይችሉም፣ ወይም ያነሱ ናቸው ተብሎ ስለሚታመን ነው ይህን ሁሉ ጊዜ ከፍ ላለ ቦታ በድርጅቱ ሳይታጩ የቆዩት፡፡ ፊያታ የተጀመረው በኦስትሪያ ቬና ከተማ ሲሆን፣ መቶ ዓመት ለመድፈን ሁለት የቀሩት የ98 ዓመት ድርጅት ነው፡፡ ድርጅቱ በዋናነት የተመሠረተው አውሮፓዎቹን ለማገልገል ቢሆንም በሒደት ግን አሜሪካንም፣ እስያንም ሆነ አፍሪካንም ለማካተት ተገዷል፡፡ ምሥራቅ እስያና አፍሪካ ሰፊ ቁጥር ያለው ሕዝብና ገበያ ያላቸው አገሮች ሆነው ሳለ ተገቢውን ቦታ በድርጅቱ ሳያገኙ ነው የዘለቁት፡፡ እኛ ይህን አስተሳሰብ ሰብረን ነው የገባነው፡፡ ሁሌም በምዕራባዊያኑ ተፅዕኖ ሥር የቆየውን ተቋም አንኳኩተን ገብተን ብዙ ነገሮችን ለመቀየር ችለናል፡፡ ለምሳሌ ዓለም አቀፍ ፕሮግራሞች እንዲጀመሩ አድርገናል፡፡ ከእኛ አልፎ ዓለምም እንዲጠቀም አድርገናል፡፡ ግሎባል ፕሮግራሙ ኢትዮጵያ ውስጥም እንዲጀመር አድርገናል፡፡ እ.ኤ.አ. በሐምሌ ወር እዚህ አዲስ አበባችን ላይ ኤር ካርጎ ግሎባል ፕሮግራም ጉባዔ ይካሄዳል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ይህን ዕድል ኢትዮጵያ ያገኘችው፡፡ በርካታ የፊያታ ሰዎችና ዓለም አቀፍ እንግዶች መጥተው የሚካሄድ ፕሮግራም ነው፡፡    

ሪፖርተር፡- በፀጥታ ችግር ሳቢያ ከቦታ ቦታ ዕቃ ለማጓጓዝ ዘርፉ ጉዳት አልገጠመውም?

አቶ ዳዊት፡- ጉዳት ገጥሞናል፡፡ ዘርፉ በፀጥታ ችግር እየተጎዳ ነው፡፡ ለምሳሌ ከዝዋይ በሌሊት መኪኖቻችን ጭነው የሚወጡት፡፡ ዝዋይ ማታ ገብተው ማደር ደግሞ አለባቸው፡፡ በዝዋይና በአካባቢው ያለውን ሥራ በአጠቃላይ በሚባል ደረጃ የምንሠራው እኛ ነን፡፡ በየቀኑ ከ100 እስከ 110 ቶን ጭነት እናመላልሳለን፡፡ በየቀኑ በትንሹ አንድ ካርጎ አውሮፕላን ጭነት እናመላልሳለን ማለት ነው፡፡ የምናመላልሰው በአብዛኛው አበባ እንደመሆኑ መጠን ከፍተኛ ጥንቃቄ ይጠይቃል፡፡ ጠባቂዎች ይመደቡልናል፣ ጭነቱ ታጅቦ ነው የሚመጣው፡፡ ነገር ግን ሥራው ብዙ ምልልስ ያለው በመሆኑ፣ በተለይ መኪኖቻችን አራግፈው ምሽት ወደ ዝዋይ ሲመለሱ ችግር እየገጠማቸው ነው፡፡ በወቅቱ ባለው የፀጥታ ችግር ሁለት ልጆች ሞተውብናል፡፡ መኪና ውስጥ እንዳሉ በጥይት ተመተው ሞተዋል፡፡ አንድ መኪና ደግሞ ሹፌሩ ተኩስ ሲሰማ ደንግጦ ተገልብጦብናል፡፡ ከአንድ ወር ቀደም ብሎ ጓደኛው በዚያው መንገድ ሲያልፍ መገደሉ ገና ያልወጣለት በመሆኑ በድንጋጤ ነው አደጋው የደረሰበት፡፡ ማታ ማታ መኪኖቻችን ወደ ዝዋይ ሲመለሱ ከባድ ችግር ነው እየገጠማቸው ያለው፡፡ ተኩስና የፀጥታ ሥጋት መንገድ ላይ አለ፡፡ በሃጫሉ ግድያ ማግሥት በተፈጠረው ረብሻ ደግሞ ሁለት መኪኖች በእሳት ተቃጥለውብናል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ከደረሰብን ችግር በላይ አሁን ያለው የፀጥታ ሥጋት ከባድ ፈተና ሆኖብናል፡፡

መንግሥት የፀጥታ ችግሩን ለመቅረፍ ብዙ ጥረት እያደረገ እንደሆነ ብናውቅም፣ ነገር ግን ከእስካሁኑ የበለጠ ጥረት ችግሩ ይጠይቃል፡፡ ሾፌሮቻችን በተደጋጋሚ በሚፈጠሩ ችግሮች የተነሳ ሥራውን በነፃነት ለመሥራት እየተቸገሩ ነው፡፡ መንገዱ ተሠርቷል፣ በአጭር ጊዜ በፈጣን መንገድ ተጉዞ መድረስ ይቻላል፡፡ ነገር ግን አንዳንዴ በተለያዩ ምክንያቶች ለምሳሌ በፀሐይ ዕጦት፣ በማሸጊያ ዕጦት፣ ወይም በሠራተኛ እጥረት ሊሆን ይችላል ወደ ውጭ የሚላከው አበባ በአግባቡ ተዘጋጅቶ ላያልቅ ይችላል፡፡ እኛ እንዲህ ዓይነት ችግር ሲፈጠር ሁለቴ ተመላልሰን ማንሳት እንችላለን፡፡ የተመረተው ምርት ኤክስፖርት ሳይደረግ እንዳይቀር ከታሰበ ሁለቴ ምልልስ አድርገን መጫን እንችላለን፡፡ ነገር ግን ተመላልሶ አገልግሎት ለመስጠት በፀጥታው ችግር የተነሳ ከባድ ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ መኪኖቻችን በቀን አንዴ ብቻ ነው የሚሠሩት፡፡ ምክንያቱም ይመሻል፣ በመሸ ሰዓት ደግሞ ደኅንነት የለም፡፡ ችግሩን ለመንግሥት በተደጋጋሚ አቅርበናል፡፡ የሚመለከተው አካል ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቅ በመሆኑ የቅርብ ክትትልም እያደረገ ይገኛል፡፡ በተቻለ መጠን በአጭር ጊዜ ችግሩ ተፈቶ የተሻለ ሥራ መሥራት የሚቻልበት ዕድል ይፈጠራል ብለን እንጠብቃለን፡፡

ሪፖርተር፡- ለዘርፉ የኢንሹራንስ ሽፋን በቂ ነው?

አቶ ዳዊት፡- ኢንሹራንስ የሚሸፍናቸውና የማይሸፍናቸው አደጋዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ በጥቃት የሚደርስ ጉዳትን ኢንሹራንሶች አይሸፍኑም፡፡ በሁከት ለሚቃጠል ዕቃ ወይ ለሚደርስ ጉዳት አብዛኛውን ጊዜ ኢንሹራንስ የለውም፡፡ ለመኪኖቹና ለሚጫነው ዕቃ ኢንሹራንስ አለ፡፡ ከእነዚህ ውጭ ግን ኢንሹራንሱ የማይሸፍናቸው አደጋዎችም አሉ፡፡ 

ሪፖርተር፡- ፍራፍሬ ማመላለስም ሊጀመር መሆኑ ተነግሯል፡፡ ወደ እዚህ ሥራ ለመግባት እየተዘጋጃችሁ ነው?

አቶ ዳዊት፡- ፍራፍሬን በተመለከተ ኦሞራቴ የሚባል ቦታ፣ አርባምንጭና ጂማም አካባቢ በሙዝ የተሸፈነ ብዙ ሔክታር እርሻ አለ፡፡ ባለን መረጃ መሠረት ከ300 እስከ 400 ሔክታር መሬትና ከዚያም የሚበልጥ የሙዝ እርሻ አለ፡፡ አቮካዶ ደግሞ ከ7,000 እስከ 8,000 ሔክታር የሚሆን እርሻ አለ፡፡ አቮካዶው በኦሮሚያ፣ በደቡብና በአማራ ክልሎች በክላስተር እርሻ የተተከለ ነው፡፡ የክላስተር እርሻ ደግሞ ማለት በአንድ አካባቢ ያሉ ገበሬዎችን አስተባብሮ የሚሠራ ልማት እንጂ፣ ልክ እንደ አግሮ ኢንዱስትሪዎች ሁሉ ነገር በተሟላበት የሚሠራ እርሻ አይደለም፡፡ አርሶ አደሮቹ ምርታቸውን በአግባቡ ተረክቦ፣ አሽጎ፣ ወስዶ ኤክስፖርት የሚያደርግላቸው ሰው ይፈልጋሉ፡፡ ትልልቅ ኢንዱስትሪዎች ዘንድ ይህ በራሳቸው ነው የሚያልቀው፡፡ አሁን እኛ ለመሥራት ያሰብነው በክላስተር እርሻ ከሚያመርቱ አርሶ አደሮች ምርቱን በመረከብ ለኤክስፖርት የማዘጋጀቱን ሥራ ለመሥራት ነው፡፡ አንድ ማቀዝቀዣ ያለው ግዙፍ የማቆያ ቦታ በመገንባት ምርቱን ከተለያዩ ገበሬዎች በመረከብ ለኤክስፖርት ማዘጋጀት ሥራውን ያቀለዋል፡፡ አቮካዶ ለምሳሌ ተቆርጦ ብቻ አይላክም፡፡ ራሱን የቻለ ልክ እንደ ፋብሪካ የሚሠራ የእጥበት፣ የማድረቅና ዋክስ የማድረግ ሥራ ተሠርቶለት ነው ለኤክስፖርት የሚዘጋጀው፡፡ ቻይና ልላክ ብትል ዋክስ የተደረገ አቮካዶ ነው የምንፈልገው ሊሉ ይችላሉ፡፡ አውሮፓ ደግሞ ሌላ ፍላጎት ሊኖረው ይችላል፡፡     

ከምርት በኋላ ምርቱን ለውጭ ገበያ የማዘጋጀት ሥራ በፍራፍሬ በኩል ራሱን የቻለ ንዑስ የሥራ ዘርፍ ነው፡፡ እኔ እስከማውቀው ይህን በተመለከተ ታስቦበት እየተሠራ ያለ ነገር የለም፡፡ አቮካዶው እየተመረተ ነው፣ ምርቱም መላክ እየተጀመረ ነው፡፡ በሚቀጥሉት ወራት ይህ ምርት በሰፊው መመረት ሲጀምር ደግሞ፣ ለኤክስፖርት የሚያዘጋጅ ማዕከል በሰፊው ካልተዘጋጀ ጥራቱም ላይ ሆነ ገበያው ላይ ክፍተት መፍጠሩ አይቀርም የሚል ግምት አለኝ፡፡ ምርቱንም በሰፊው ለመላክ ብቻ ሳይሆን በጥራት ለመላክ ካልተቻለ የምንፈልገውን ዓይነት ዶላር ከውጭ ገበያው ላናገኝ እንችላለን፡፡ በሰዓቱ፣ በሚፈለገው መጠንና ጥራት ምርትህን ካላቀረብክ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ አትሆንም፡፡ ኬንያ ለምሳሌ አቮካዶ በመላክ ብቻ በገቢ እስከ አንድ ቢሊዮን ዶላር ደርሳለች፡፡ ከኬንያ በተጨማሪ ኡጋንዳ፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛኒያና ዚምባብዌም በሰፊው እየሠሩበት ነው፡፡ በእኛ አኅጉራዊ መስመር ያሉ በሙሉ ገብተውበታል፡፡ በኢትዮጵያ ልዩ ትኩረት ስለተሰጠው አቮካዶ በሰፊው እየተመረተ ነው፡፡ ሰፊ መሬትም ለአቮካዶ የሚሆን አለ፡፡ በዚህ ዘርፍ አገራችን ጠንካራ ተወዳዳሪ እንድትሆን መዘጋጀት አስፈላጊ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- መሥሪያ ቦታ ጠይቃችሁ ነበር ጉዳዩ የት ደረሰ?

አቶ ዳዊት፡- ኢትዮጵያ ውስጥ በአበባ ጭነት በብቸኝነት ማለት በሚቻል ሁኔታ የእኛ ድርጅት ሲሠራ ቆይቷል፡፡ የእኛ ድርጅትም እንደ አንዱ የሴክተር አንቀሳቃሽ የራሱን ሥራ ይሠራል፡፡ በቀን አንድ ተኩል ወይም ሁለት ካርጎ አውሮፕላን ነው አገሪቱ የምትልከው፡፡ የአንድ አውሮፕላን ጭነት እኛ ካመላለስን በዘርፉ ያለን ድርሻ ከፍተኛ ነው ማለት ነው፡፡ አንዳንድ ባለእርሻዎች የማመላለሱን ሥራም ደርበው ይሠራሉ፡፡ በዘርፉ በቂ ምርት የማጓጓዝ አገልግሎት ሰጪ ባለመኖሩ ነው አምራቾቹ ተገደው የገቡበት፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ ችግር አለው፡፡ አምራቾቹ አንደኛ ማጓጓዙ ዋና ሥራቸው አይደለም፡፡ መኪና ብልሽትና ሌላም ችግር ሊያጋጥማቸው ይችላል፡፡ የአንደኛው ፍሪጁ ሲሠራ የሌላኛው ደግሞ ላይሠራ ይችላል፡፡ ይህ ሲሆን ኤክስፖርት ምርት አቅርቦቱ በጊዜ፣ በመጠንም ሆነ በጥራት ወጥነት ይጎድለዋል፡፡ ለምሳሌ አበባ በተለያየ መንገድ ተጓጉዞ ይመጣና ወደ አውሮፕላን ለመጫን አንድ ላይ ተሰብስቦ ይዘጋጃል፡፡ ነገር ግን ሕይወት ያለው ተክል በመሆኑ አንዱ አበባ ሌላው ላይ ይተነፍሳል፡፡ ሞቆ የመጣው አበባ በትክክል የመጣውን አበባ ያበላሸዋል፡፡ የአበባው ጥራት ቀነሰ ማለት ደግሞ ከምርቱ የምናገኘውን ገቢም ይቀንሰዋል፡፡ ስለዚህ የመጓጓዣ ሙቀት አጠባበቅ ሥራ ለኢትዮጵያ እጅግ በጣም አስፈላጊ ሥራ በመሆኑ በጥንቃቄ መያዝ አለበት፡፡ አሁን ደግሞ አቮካዶ፣ ሙዝና አናናስ የመሳሰሉ ምርቶች ሊመጡ ነው፡፡ ወደ እነዚህ ከመገባቱ ቀድሞ የምርቶቹ አላላክ ሥራ በቅጡ ዝግጅት ይፈልጋል፡፡

እኛ ለዚህ መፍትሔ እንዲሆን በማሰብ ሞጆ ግዙፍ የማቆያ መጋዘን ለመገንቢያ የሚሆን 30 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ጠይቀን ነበር፡፡ ከ5,000 እስከ 7,000 ካሬ ሜትር ላይ እየታየ የሚሰፋ ለሙዝ፣ ለአቮካዶም ሆነ ለአናናስና ለአበባም የሚሆን ቀዝቃዛ መጋዘን ለመገንባት ዕቅድ ይዘናል፡፡ መኪኖችን በመጨመር ገበሬው ያመረተውን ምርት ከየቦታው በአግባቡ በመሰብሰብ ምርቶቹን ለኤክስፖርት የማዘጋጀት ሥራም በዚያው በአንድ ማዕከል ለመሥራት ነበር ያሰብነው፡፡ ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳዩ ዘግይቶብናል፡፡

እኛ ለሚበላሹ ምርቶች ሎጂስቲክስ የበለጠ ማዘመንና የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲሰጥ ማሳደግ ነው የምንፈልገው፡፡ አበባም በ2004 ዓ.ም. ስንጀምር እንደ አገር ተመሳሳይ ችግር ነበር የገጠመን፡፡ ከዚያ ተነስተን አበባ እንዴት እንደሚሠራ በደንብ አጠናን፡፡ ከአቀጣጠፉ ጀምሮ አስፈላጊነቱን በመረዳት አቀማመጡ፣ የመኪና ቅዝቃዜ አጠባበቁ፣ አስተሻሸጉና ሌላውንም የኤክስፖርት ዝግጅት ላለፉት 20 ዓመታት እያሳደግን መጥተናል፡፡

አበባ ያኔ ከነበረበት 50 ሚሊዮን ዶላር አሁን የሚገኝበት 570 ሚሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡ ዘርፉ ይህን ሁሉ ዕድገት ሲያመጣ የእኛ አስተዋጽኦም ነበረበት፡፡ አበባውን የሚያመርቱት ሌሎች ቢሆኑም ምርቱ እስኪላክ ድረስ ያለውን የእሴት ሰንሰለት በሚፈለገው መንገድ በመጠበቅ ብዙ ሥራ ሠርተናል፡፡ በነገራችን ላይ አንድ አበባ 60 በመቶው ወጪው ከተመረተ በኋላ ለሽያጭ እስኪቀርብ ባለው የሎጂስቲክስ እሴት ሰንሰለት ላይ የሚፈስ ነው፡፡ ምርቱ እስኪቀጠፍ ያለው ወጪ 40 በመቶ ብቻ ነው፡፡ በአውሮፕላንና በመኪና ይጫናል፣ ይታሸጋል፣ ሌላም ሒደትን ያልፋል፡፡ ወደ አቮካዶም ሆነ ሙዝ ሲገባ ተመሳሳይ ውጣ ውረድ የሚጠይቅ የእሴት ሰንሰለትን መፍጠር ይጠይቃል፡፡ የእኛ ድርጅት ጥናቱን ለልማት ባንክ አቅርቦ ፀድቆለታል፣ ብድርም ሊፈቀድለት ፈቃድ አግኝቷል፡፡ ነገር ግን ሥራው ከዚያ ፈቅ እንዳይል ያደረገው የቦታ ማግኘት ጉዳይ ነው፡፡ ሞጆ ላይ የጠየቅነው ቦታ ቢሰጠን በሦስት ወይም በአራት ወራት ግንባታውን ጨርሰን ወደ ሥራው መግባት እንችላለን፡፡ ቦታ የሚሰጠን ግን ጠፍቷል፡፡ ቦታው ወደ ሞጆ እንዲጠጋ የፈለግነው ለሎጂስቲክስ ሥራ ባለው አመቺነት ነው፡፡ ወደፊት በኮንቴይነር (በመርከብ) ኤክስፖርት ለማድረግ የኢትዮ ጂቡቲ ባቡር መስመር ወዳለበት ሞጆ መጠጋት አመቺ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የወደፊት የማስፋፊያ ሥራም ወደ ሞጆ የተጠጋ ነው፡፡ ሞጆ ሁሉንም አቅጣጫ ለማገናኘት የተመቸች ናት፡፡ ከአማራ ክልል፣ ከኦሮሚያም ሆነ ከደቡብ የሚመረት ምርትን ለማሰባሰብና አቀነባብሮ ለመላክ እጅግ የተመቸች ናት፡፡ ማቀነባበሪያውን ሞጆ ለመገንባት ያሰብነው በብዙ መመዘኛዎች ቦታው የተመቸ በመሆኑ ነው፡፡

ኤክስፖርት የሚደረጉ ፍራፍሬዎችን ማቀዝቀዝና ማዘጋጀት ብቻ አይደለም ፕሮጀክቱ ታሳቢ ያደረገው፡፡ ለምሳሌ በአገሪቱ የድንች ጥብስ አምራቾች እየበዙ ነው፡፡ ሎሊ ቺፕስ፣ ሰን ቺፕስ፣ ዋን ቺፕስ የተባሉ በትንሹ ሦስት ትልልቅ የድንች ጥብስ አምራች ድርጅቶች አሉ፣ ሌሎችም እየመጡ ነው፡፡ እነዚህ ከአርሶ አደሮች ነው ምርት የሚሰበስቡት፡፡ ነገር ግን የድንች ምርት በሰፊው የሚመረትበት ጊዜ እንዳለ ሁሉ የምርቱ እጥረት የሚፈጠርበት ወቅትም አለ፡፡ ይህን ክፍተት ለመሙላት ድንቹን ሳይበላሽ ማቆየት የሚችል ማዕከል መገንባት አስፈላጊ ይሆናል፡፡ እነዚህ ድንች ጥብስ አምራቾች ተፎካካሪነታቸውን ለማሳደግም ሆነ ሥራቸውን ለማስፋት ድንች ሳይበላሽ ማቆያ ማዕከል ያስፈልጋቸዋል፡፡ መንግሥት ከዚህ በፊት ይህን ነገር አስቦ ፉድ ቼን አዲስ በሚል ፕሮጀክት ከሆላንድ መንግሥት ጋር በትብብር ለመገንባት አቅዶ ነበር፡፡ ሐሳቡ አራት ዓመታት ያለፈው ቢሆንም እስካሁን ግን አልተጀመረም፡፡ እንዲህ ያሉ ሥራዎች በግል ዘርፍ ቢሠሩ የበለጠ ውጤታማ ይሆናሉ፡፡ በመጋቢት ወር የአበባና የፍራፍሬ ዘርፍ አንቀሳቃሾች በተገኙበት ለከፍተኛ ባለሥልጣናት የዘርፉ ችግሮች ቀርበዋል፡፡ መንግሥት የመጓጓዣ መኪኖችን ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ፈቅዷል፡፡ ነገር ግን አበባና ፍራፍሬ መጫኛ መኪኖችን መግዣው ውድ ነው፡፡ ከዚያ በተጨማሪም አንድ ሥራ ብቻ ነው የምትሠራባቸው፡፡ አንድ መኪና እስከ 15 ሚሊዮን ብር ይጠይቃል፡፡ መኪናውን የሚበላሹ ምርቶችን ብቻ ነው የምትጭንበት፡፡ ሌላ መኪና ብትገዛ ግን ቡናው ቢጠፋ እህሉ፣ እህሉ ቢጠፋ ሌላ ነገር ትጭንበታለህ፡፡ ብዙ ሰው ኪሳራን ስለሚፈራ ወደ ሆርቲካልቸር ጭነት መጓጓዣ ብዙም ደፍሮ አይገባም፡፡ ዘርፉ ግን ከተበረታታና ከታገዘ ለሁሉም የሚበቃ ሰፊ ዕድል አለው፡፡

ሪፖርተር፡- በዘርፉ እንቅፋት የሆኑ የፖሊሲ፣ የሕግ ወይም አሠራር ችግሮች የምትሏቸው ምንድናቸው?

አቶ ዳዊት፡- መንግሥት ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ላይ በብዙ ዘርፎች ይሠራል፡፡ ጨርቃ ጨርቁም ሆነ የእርሻ ምርቱ በሰፊው እንዲመረት ድጋፍ ይደረጋል፡፡ ይሁን እንጂ ለሁሉም ዘርፍ ወሳኝ አከርካሪ አጥንት የሆነው ሎጂስቲክስ ከእነ ማነቆው ይገኛል፡፡ ከሰሞኑ ለምሳሌ ማዳበሪያ ዘገየ የሚል ቅሬታ በሰፊው ይነሳል፡፡ ከመርከቡ ጀምሮ፣ ከጂቡቲ ማንሳት፣ ወደ መኪና መጫን፣ ወደ ተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ማሠራጨቱ ሁሉ ብዙ ችግር ያለበት ሒደት ነው፡፡ ሎጂስቲክስ ዘርፍ ጠቀሜታው ትልቅ መሆኑ ታይቶ፣ አሁን የሚገኝበት ማነቆም ታይቶ አገሪቱ ባላት አቅም የተቀላጠፈ የሎጂስቲክስ አሠራር የምትዘረጋበት ሁኔታ መመቻቸት አለበት፡፡ ሴክተሩን ለማገዝ የባንክ ብድርን ጨምሮ ብዙ ዕገዛዎች በመንግሥት ይደረጋሉ፡፡ ነገር ግን እሱ ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ የዘርፉ ችግር በአብዛኛው የሚመነጨው በመንግሥት አቅም ማነስ ወይ በሀብት እጥረት ብቻ አይደለም፡፡ በዘርፉ የሚመደቡ አመራሮች ዘርፉ ስለሚጠይቀው ጉዳይም ሆነ በአጠቃላይ ስለሎጂስቲክስ በቂ መረዳትና ግንዛቤ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ላይ ያሉ አመራሮች ለዘርፉ ቅርበት ያላቸው ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ወደ መካከለኛና ወደ ታችኛው እርከን አመራሮች ሲወረድ የግንዛቤ ክፍተት ካለ ዘርፉ በቂ ዕገዛ አያገኝም፡፡ ሎጂስቲክስ ለአገር ዕድገት ወሳኝ ሴክተር መሆኑን በተመለከተ በየደረጃው ወጥነት ያለው ግንዛቤ መፍጠር አስፈላጊ ነው፡፡

ለምሳሌ ባለፉት አሥር ዓመታት ካልተጀመረ በሚል ከመንግሥት ጋር ሲያጨቃጭቅ የዘለቀ መልቲሞዳል የተባለ ፕሮጀክት አለ፡፡ የማሪታይምና የመርከብ ድርጅቱ ብቻ ሳይሆን ሌሎች የግል አንቀሳቃሾችም ወደ ዘርፉ ገብተው መሥራት አለባቸው ተብሎ ነው መልቲሞዳል የተዘጋጀው፡፡ ወደ ሥራው ለመግባት ብዙዎች ፍላጎት አሳይተዋል፡፡ ጨረታ ወጥቶ ሲሰረዝ ቆየ፡፡ አሁንም ለሦስተኛ ጊዜ ጨረታ እየወጣ ነው፡፡ የግሉ ሎጂስቲክስ ዘርፍ ዕውቀት አለው፣ የመሥሪያ መኪናን ጨምሮ ዘርፉን የሚያሳድግ ሀብት አለው፡፡ ነገር ግን የመሥራት ዕድል በደንብ እየተሰጠው አይደለም፡፡ ቦታ ስጡኝ ስትልም መሬት በአግባቡ የሚያቀርብ የለም፡፡ መልቲሞዳሉ ቢቀር እንኳ የመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነት (ፐብሊክ ኤንድ ፕራይቬት ፓርትነርሺፕ) ተፈጥሮ ወደ ሥራ ግቡ ተባለ፡፡ በዚህ መንገድም ለመሥራት ከመንግሥት ድርጅቶች ጋር ትስስር ፈጠርን፡፡ ነገር ግን ሥራው እስካሁንም አልተጀመረም፡፡

የኢትዮጵያ የግል ሎጂስቲክስ ዘርፍ ገና አላደገም፡፡ እኛ ዘንድ ከ200 ብዙም ያልበለጡ ፍሬት ፎርዋርደሮች ናቸው ያሉት፡፡ ሌሎች አገሮችን ትተን በአፍሪካ ደረጃ እንኳ ብናይ 1,000 እና 2,000 ፍሬት ፎርዋርደር ያላቸው አገሮች ብዙ ናቸው፡፡ እንዳለን የሕዝብ ቁጥርና የቆዳ ስፋት በቁጥር ማደግ አለብን፡፡ በጥራት ማገልገልና ዘመናዊ አሠራር መከተል አለብን፡፡ ዘመኑ የሚጠይቀው ደረጃ ላይ ለመድረስ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ማደግ አለብን፡፡ ዘመኑም ሆነ ዓለም በዘርፉ ብዙ ቀድሞናል፡፡ በዚህ ዘርፍ በዓለም ላይ ብዙ ሥራ እንደሚሠራ ጥቂት በመሥራት ዓይተናል፡፡ ነገር ግን እኔ ብቻ 80 ነገር ባውቅ አምጥቼ በአገሬ ልሠራው ካልቻልኩኝ ምን አደርገዋለሁ? በርካታ ጠቃሚ ነገሮችን ለመሞከርና ለመሥራት የሎጂስቲክስ ዘርፍን መጫወቻ ሜዳ ማስፋትና ነፃነት መስጠት ያስፈልጋል፡፡ በተለያዩ አገሮች በተለያዩ አጋጣሚዎች የሆነ ነገር ባየን ቁጥር ኢትዮጵያማ እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረስ ገና ብዙ ይቀራታል እያልን በተስፋ መቁረጥ የምንመለስ ከሆነ አስቸጋሪ ነው፡፡ አገራችን ከዚህ ምን ትጠቀማለች የሚል ስሜት ነው መፈጠር ያለበት፡፡

አኅጉራዊው የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ሊጀመር ነው፡፡ እኛ ለዚህ ምን ያህል ተዘጋጅተናል? የረባ አገር አቋራጭ የመጓጓዣ አገልግሎት መስጠት የሚችል አቅም አልገነባንም፡፡ አሁን ወደ ጂቡቲ መስመር ካልሆነ የተጠናከረ የሎጂስቲክስ ኔትወርክ አልተገነባም፡፡ ከሌሎች አገሮች ጋር በቅብብል ለመሥራት ብዙ ዝግጅት ያስፈልገናል፡፡ አየር መንገዳችንን በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችል ቁመና መፍጠር አለብን፡፡ በአፍሪካ ግዙፉ አየር መንገድ ነው ያለን፡፡ ብቻውን ሁሉንም ነገር መሥራት ግን ስለማይችል እየመጣ ካለው ዕድል ለመጠቀም የሚያስችል ዝግጅት ሊኖረን ይገባል፡፡ ዘመኑ የፉክክር ብቻ ሳይሆን የትብብር ነው፡፡ ተጋግዘንና ተረዳድተን መሥራት እንጂ በትብብር ዘመን እኔ ብቻ ሁሉን አውቃለሁ ወይም ሁሉን አሟላለሁ የሚል አስተሳሰብ መቅረት አለበት፡፡ ዘመኑ የሰፕላይ ቼን/የአቅርቦት ሰንሰለት ሳይሆን የዲማንድ ቼን/የፍላጎት ሰንሰለት ነው፡፡ ድሮ እንደፈለግህ አምርተህና በመሰለህ አዘጋጅተህ አቅርቦትህን ሞላሁ ትላለህ፡፡ አሁን ግን ቀርቷል፡፡ ፍላጎትን መሠረት አድርጎ ነው ሁሉ ነገር የሚመረተው፡፡

ሞዴሉ ሲቀየር እኛም ራሳችንን መቀየር አለብን፣ አለበለዚያ ጊዜ አይጠብቀንም፡፡ በዓለም ላይ ጠንካራ ተወዳዳሪ መሆን የምንችለው እነሱ የሚፈልጉትን ነገር ችለን ስንገኝ ነው፡፡ ገዥዎቻችን የሚጠይቁንን ነገር ስናሟላ ነው በዓለም ገበያ የምንፎካከረው፡፡ ኢትዮጵያ አቮካዶ አለሽ ወይ ተብሎ ሲጠየቅ አዎ ብሎ በሚፈለገው ሰዓት፣ መጠንና ጥራት ማቅረብ ይጠይቃል፡፡ ምርቱ አለኝ፣ ነገር ግን መጓጓዣው ጎደለኝ፣ ወይ ማሸጊያ ቸገረኝ የምትል ከሆነ ተወው ብሎ ከኬንያ ሊገዛ ይሄዳል፡፡ ምክንያቱም በአልቲቲዩድ፣ በአየር ንብረት፣ በአመራረት፣ በጥራትና በሌላም የሚፎካከሩ አገሮች ናቸው በገበያው የተሠለፉት፡፡ ከኬንያ፣ ዩጋንዳና ከሌሎችም የቀጣናችን አገሮች ጋር መፎካከር በዚህ መንገድ ከባድ ነው የሚሆንብን፡፡

በዓለም ገበያ የሆርቲካልቸር ምርት ሰፊ ፍላጎት አለው፡፡ ሁላችንም ብንሠራና በሚፈለገው መንገድ ብናቀርብ ለሁላችንም የሚተርፍ ዕድል አለ፡፡ በኢትዮጵያ አሁን ምርት እየመጣ ነው፡፡ ነገር ግን በዓለም ገበያ ውጤታማ የሚሆነው በጥሩ ሁኔታ ለገበያ ስናቀርበው ነው፡፡ ለዚህ ሁሉ ደግሞ ሎጂስቲክስ መሠረታዊ ነው፡፡

የውጭው ገበያ አገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ስለሚያስፈልጋት በሚል የሚሠራ ነው፡፡ ነገር ግን አገር ውስጥም ቢሆን ዘርፉ ሰፊ ገበያ እንዳለው መረሳት የለበትም፡፡ ለምሳሌ 40 በመቶ ምርት የሚበላሸው በኢትዮጵያ በሎጂስቲክስ አቅርቦት መጓደል ነው፡፡ ብርቱካን በለው ሙዝና ሌላም ማስቀመጫ፣ ማጓጓዛና መጫኛ ባለመኖሩ 40 በመቶ ይበላሻል፡፡ በአያያዝ ጉድለት የተነሳ ግማሹ ምርታችን ይበላሻል፡፡ ብርቱካንና ሙዝ እዚህ አዲስ አበባ በኪሎ የሚሸጥበት ዋጋ እጅግ ውድ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሌላው ቀርቶ አያያዛችንን አሻሽለን 20 በመቶውን የሚበላሽ ምርት ማዳን ብንችል እንኳን የሚመጣው ውጤት ከፍተኛ ነው፡፡ አትክልትና ፍራፍሬ የሀብታም ምግብ ብቻ አይደለም፡፡ ሁሉም ሰው በአቅሙ ሊበላው የሚገባ መሆን መቻል አለበት፡፡ ነገር ግን ከአምራቹ ወደ ተጠቃሚው በአግባቡ የሚደርስበት ሎጂስቲክሱ መስተካከል አለበት፡፡

ሪፖርተር፡– የሎጂስቲክስ ዘርፍ ውጤታማ በሆነ መንገድ ቢያዝ ከውጭም ሆነ ከአገር ውስጥ ምን ዓይነት ሀብት ማመንጨት የሚችል ዘርፍ ነው ይባላል፡፡ የውጭ አገሮችን ተሞክሮ ማነፃፀሪያ በማድረግ ቢያነሱልን?

አቶ ዳዊት፡- ቀላል ምሳሌ የኢትዮጵያ አየር መንገድን እንወሰድ፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዕቃ ማጓጓዣ ያደገው ለኢትዮጵያ ብቻ በሚሰጠው አገልግሎት አይደለም፡፡ ከኢትዮጵያ አንድ ወይ ሁለት አውሮፕላን አበባ ጭኖ ይወጣል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግን ከ11 በላይ ዕቃ ጫኝ አውሮፕላኖች ያሉት ትልቅ አየር መንገድ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኢምፖርትና ኤክስፖርት ንግድ ተመጣጣኝ ሚዛን የለውም፡፡ አየር መንገዱ ብዙ ዕቃ ጭኖ ያመጣል፡፡ ወደ ውጭ ሲልክ ግን ባዶ አውሮፕላን መላኩ አክሳሪ ነው፡፡ ይህ ትልቅ ችግር በመሆኑ ኢትዮጵያን ማዕከል በማድረግ የሌሎች የአፍሪካ አገሮችን ዕቃ የማጓጓዝ ሥራ ትስስር ፈጥሯል፡፡ በዚህ መካከል እኛ ልንሠራቸው የሚችሉ ብዙ የሥራ ዕድሎች ይፈጠራሉ፡፡ ፕሮሰሲንግ፣ ፓኬቺንግ፣ ኮንሶሊዴሽን፣ ዲኮንሶሊዴሽን ሌላም ሥራ አለ፡፡ ይህ እያደገ የሚሄድ ሥራ ደግሞ በአየር መንገዱ ብቻ የሚሠራ ባለመሆኑ የግል ጭነት አጓጓዥ ድርጅቶች በትብብር የመሥራት ዕድል ቢመቻችላቸው የተሻለ ይሆናል የምንለው ለዚያ ነው፡፡ ኢንዱስትሪው አልተነካም፡፡ ዓለም የሚመካበት ገና ያልተነካ ኢንዱስትሪ ነው፡፡ እነ ሆላንድና ቤልጂየም ሌላ ምን አላቸው? በሎጂስቲክስ ነው የሚኖሩት፡፡ እኛ ለምሳሌ ቡናችንን ልከን አንደኛ ደረጃ ገበያ እንዲያገኝ ሙቀቱ፣ እርጥበቱ፣ አስተሻሸጉና አላላኩ ሁሉ ጥራቱን የጠበቀ ሆኖ መላክ አለበት፡፡

ሎጂስቲክስ በተለይ አገራችን በደንብ ያልተሠራበት ዘርፍ ነው፡፡ ይህ የሆነው በመሠረታዊነት ደግሞ የተማረ የሰው ኃይል በዘርፉ ባለመኖሩ ነው፡፡ የተማረ የሰው ኃይል ለመገንባት ሥልጠና መስጫ ተቋማት ውስን ናቸው፡፡ አየር መንገዱ ብቻ ነው የተሻለ ማሠልጠኛ ያለው፣ የራሱን ሰዎች ብቻ ያሠለጥንበታል፡፡ ኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ማሠልጠኛ አለ፡፡ እርሱም ቢሆን የሚወስደው ሰው በቂ አይደለም፡፡ ከዚያ ውጭ የእኛ የፍሬት ፎርዋርደርስ አሶሴሽን ሥልጠና አለ፡፡ በዚህም ቢሆን የማታና የቀን ሁሉ ሥልጠና እየሰጠን በዓመት ከ150 ሰዎች በላይ ማውጣት አልተቻለም፡፡ እነሱም በቀለም የተማሩትን ወጥተው በተግባር እየሠሩ ካልተማሩት ውጤታማ መሆን ይከብዳቸዋል፡፡ ስለዚህ የተማረ ሰው ኃይል ክፍተትን ለመሙላት የተሻለ ተቋም ያስፈልገናል፡፡ ለመንግሥት ተቋም የመገንባት ጥያቄ አቅርበናል፡፡ ቦታ እንደሚሰጠን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቃል ተገብቶልናል፡፡ ይህ የሚቀላጠፍ ከሆነና ተቋሙ ከተገነባ የሰው ኃይል ክፍተቱ ይሞላል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ወደ 120 ሚሊዮን ሕዝብ ላላት አገር አሁን ባሉ አነስተኛ የሎጂስቲክስ ዘርፍ አንቀሳቃሾች አገልግሎት ማዳረስ አይቻልም፡፡

ሪፖርተር፡- በዘርፉ ውስጥ ያለው ተናቦ መሥራት እንዴት ይገለጻል? ዘርፉን የሚመራው አካልና በዘርፉ የተሰማሩ አንቀሳቃሾች ተግባብቶ የመሥራት ሁኔታ ተፈጥሯል?

አቶ ዳዊት፡- ለብዙ ዓመታት ይህ ችግር ነበር፡፡ የሚያዳምጥ የጠፋበት ሁኔታ ይታይ ነበር፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን የሴክተሩ ጠቀሜታ እየታወቀ በመምጣቱ በመንግሥት በኩል ለዘርፉ የሚሰጠው ትኩረት ጨምሯል፡፡ ሥልጠና ማዕከል መገንቢያ ቦታ በቶሎ ይሰጣቸው ተብሏል፡፡ ሕጎች ሲወጡ፣ ፕሮጀክቶች ሲመቱ ወይም ለውጦች ሲመጡ ጠርተው ያማክሩናል፡፡ ከሞላ ጎደል ባለፉት ጥቂት ዓመታት ጥሩ ትኩረት አግኝተናል፡፡ ወደ ዘርፉ የሚመጡ አመራሮችም ጥሩዎች ናቸው፡፡ ዘርፉን ቀረብ ብለው የሚያውቁ ብቻ ሳይሆኑ የእኛ አሶሴሽን የሚሰጠውን ሥልጠና ጭምር ለመውሰድ ፍላጎት ያላቸው አመራሮች መጥተዋል፡፡

አዲሱ ዘመን ደግሞ የኢንተርኔት ግብይት ዘመን ነው፡፡ የኤሌክትሮኒክ ኮሜርሱን ለማሳደግ የክፍያ ሥርዓቱን ከማዘመን ጎን ለጎን ብዙ ሥራ ይጠይቃል፡፡ ኦንላይን ግብይት እያደገ ነው፡፡ አየር መንገዱ አፍሪካን ለማዳረስ የሚያስችል በ150 ሚሊዮን ዶላር በጀት ግዙፍ የኦንላይን ግብይት ማዕከል በራሱ እያስገነባ ይገኛል፡፡ አየር መንገዱ ይህን ሲያደርግ ሌላውም ጎን ለጎን መሥራት አለበት፡፡ አብሮ ለመሥራት የሚያስችል ዝግጅት ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ሎጂስቲክስ ዘርፍ ለመግባት ለሚፈልጉ ወገኖች ዘርፉ ምን ምቹ ዕድል አለው ይላሉ?    

አዎ ዳዊት፡- የሎጂስቲክስ ዘርፍ ትልቅ ዕድገት አለው፡፡ ወደብ አልባ አገር መሆናችን ቢጎዳንም የሎጂስቲክስ ዘርፍ ግን ትልቅ ተስፋ ያለው ነው፡፡ ለምሳሌ በርበራ ይጀመራል ተብሏል፡፡ እኔም ሄጄ እንዳየሁት በርበራ ከ250 ሺሕ ያላነሰ ኮንቴይነር በዓመት ማስተናገድ የሚችል ትልቅ አማራጭ ነው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ በርበራን መጠቀም  ትችላለች፡፡ አማራጭ ወደቦች ያስፈልጉናል፡፡ ባልተጠበቀ ጊዜ የተለያዩ ውሳኔዎች በጂቡቲ በኩል ይወሰናሉ፡፡ ባለፈው ወር ለምሳሌ አዳዲስ የኤሌክትሮኒክ ሕጎች ወጥተው ነበር፡፡ የእኛ ሰዎች ሄደው ተነጋግረው ነው ችግሩ የተቀረፈው፡፡ አማራጭ እንደሌለን ስለሚቆጠር ነው አንዳንድ ዕርምጃዎች የሚወሰዱት፡፡ የወደብ አማራጮቻችንን ብናሰፋ ግን እንደዚህ አይደረግም፡፡ ኬንያ አለ፣ ፖርት ሱዳን፣ በርበራ፣ የኤርትራ ወደብም አለ፡፡ እነዚህን እንደ አማራጭ ለመጠቀም መጣር ያስፈልጋል፡፡ አንድ ወደብ ላይ ብቻ መንጠልጠል ጥሩ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- በኮንቴይነር የሆርቲካልቸር ምርቶችን መላክ ሊጀመር ነው እንዴ?

አቶ ዳዊት፡- አዎ ሐሳቡ አለ፡፡ እነ ኬንያ በኮንቴይነር መላክ ላይ ብዙ ሄደዋል፡፡ ያስተማራቸው ደግሞ ችግር ነው፡፡ በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት የአውሮፕላን እንቅስቃሴ ብዙ ስለተገደበ ተቸግረው ነበር፡፡ እኛ የራሳችን የካርጎ አውሮፕላኖች አሉን፡፡ እነ ኬንያ ግን ተከራይተው ነበር ሥራውን ሲሠሩ የቆዩት፡፡ ኮሮና ሲዛመት የአውሮፕላን እንቅስቃሴው በመቆሙ አማራጭ አጥተው ብዙ ተቸግረዋል፡፡ ከዚህ ችግር ግን ልምድ በመቅሰም የኮንቴይነር አማራጭን ወደ መጠቀም ገቡ፡፡ አሁን በደንብ እየተጠቀሙበት ነው፡፡ ከሰሞኑ ለአንድ ኮንፍረንስ ኬንያ ነበርኩኝ፡፡ እነሱ እንዲያውም የኮንቴይነሩን ለምደውት ወደ አውሮፕላኑ ብንገባ እንደገና ብዙ ሥራ ከመርከቡ ይወስድብናል የሚል ሥጋት ነው የያዛቸው፡፡ የአበባ ኤክስፖርት በእርግጥ በአውሮፕላን ካልሆነ በስተቀር አይሞከርም፡፡ አቮካዶ፣ ሙዝና አናናስ ግን በቀዝቃዛ ኮንቴይነር መጫን ይቻላል፡፡ ትልቁ ችግራችን ግን የኮንቴይነር እጥረት አለ፣ የመኪናም ችግር አለ፣ ሌላው የመርከብ ኮኔክቲቪቲ ችግር አለ፡፡ እኛ ጋ ለሙከራ በሚል ወደ ስድስት ኮንቴይነር ሙዝ ልከን ነበር፡፡ ነገር ግን ሙዙ የተፈለገው ቦታ ሲደርስ የጥራት ችግር ገጥሞታል፡፡ ኮንቴይነሩን ከጂቡቲ አምጥቶ ወደ 800 ኪሎ ሜትር ኦሞራቴ ወስዶ፣ ከኦሞራቴ ኮንቴይነሩን ለመጫን ብቻ አራትና አምስት ቀን ይፈጃል፣ ከዚያ በተሰባበረ መንገድ ሞጆ ማድረስ አለ፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ ጂቡቲ በባቡር አድርሶ ወደ ውጭ መላክ አለ፡፡ ይህ ውጣ ውረድ ተደማምሮ ዋጋው በጣም ውድ ይሆናል፡፡ ሥራው ግን ሙያዊ በሆነና ሥርዓት ባለው መንገድ ከተመራ አዋጭ ነው፡፡ ከአውሮፕላን ውጭ ለሚጫኑ ጭነቶች በኮንቴይነር መጫኑ አዋጭ ነው፡፡ ለምሳሌ በባቡር ከሞጆ ጂቡቲ በ10 ሰዓት መድረስ ይቻላል፡፡ በመኪና ሁለት ቀንና ከዚያ በላይ ሊፈጅ የሚችልን ሥራ በቀላሉ አጠናቆ መመለስ ይቻላል፡፡ መቀናጀት ነው ለዚህ የሚያስፈልገው፡፡ ባቡሩ፣ መርከብ ድርጅቱ፣ ፍሬት ፎርዋርደሩ ከተቀናጀን ምንም የማይቆራረጥ አገልግሎት መስጠት ይቻላል፡፡ ለመቀናጀት ግን ሥራውን ማወቅና ቀናነት ያስፈልጋል፡፡

ሥራውን ካለወቅን ግን ቀናነት አስፈላጊ ነው፡፡ ሥልጣን ላይ ተቀምጠህ መርከቡ አይወጣም፣ ወይም አይሄድም ማለት የለብህም፡፡ አይቻልም በሚል አሠራርም ዘርፉ አያድግም፡፡ ሥራውን ካላወቅነው እንኳን ሌሎች እንዲሠሩት ቀናነት ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ አበባ ሲጀመር የዛሬ 20 ዓመት በቦይንግ 757 ካርጎ ስንጀምር አቶ ግርማ ዋቄ ነበሩ ዋና የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ፡፡ በወቅቱ አውሮፕላኑ ስለማይሞላና በቂ ምርት ስለሌለን እሳቸውን ማስፈቀድ ብቸኛው አማራጭ ይሆናል፡፡ እሳቸው ጋ እየገቡ ፈቃድ ከሚጠይቁት አንዱ ነበርኩና አስታውሳለሁ፡፡ አውሮፕላኑ ይውጣ ስንላቸው በቀና መንፈስ እኛን እያበረታቱ አይዟችሁ ካርጎ የኢትዮጵያ ዕዳ ከፋይ ነው ይሉን ነበር፡፡ ይውጣ እያሉ ይፈቅዱልን ነበር፡፡ ዛሬ በካርጎ አውሮፕላን ኢትዮጵያ ወደ አሥራ ምናምን ደርሳለች፡፡ አንድ ቦይንግ 757 ለመጫን የምትቸገር አገር ዛሬ ሁለት አውሮፕላኖች መላክ ላይ ደርሳለች፡፡ በትንንሽ አውሮፕላኖች ደግሞ በጣም ብዙ ዕቃ እየተጫነ ይገኛል፡፡ ከ150 እስከ 200 ሺሕ ቶን መጫን ደርሰናል፡፡ ነገር ግን አንድ ሚሊዮን ቶን የመጫን አቅም አለን፡፡ በጣም ትልቅ አቅም ስላለ ዘርፉ ማደግ ይችላል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግን ከአገር ውስጥ ይልቅ በውጭ አገሮች በአስተማማኝ አገልግሎቱ፣ በቅልጥፍናውና በተደራሽነቱ ይፈለጋል፡፡ እሱን በመጠቀም ነው ብዙ ሥራ እየተሠራ የሚገኘው፡፡ ይህን ኢትዮጵያ ውስጥ ብናመጣው ምርጥና ተደራሽ የሆነ አየር መንገድ ስላለን ብዙ ሥራ መሥራት ይቻላል፡፡ ከኬንያ የሚላክ አንድ ኪሎ አበባ 2 ዶላር ከ75 ነው የሚጫነው፡፡ እኛጋ ደግሞ ከ2 ዶላር ከ20 አይበልጥም፣ በጣም ርካሽ ነው፡፡ ይህ ልዩነት አለው፡፡ ለአየር መንገዱ ብቻ ሳይሆን ለአበባ ላኪውም ጠንካራ ተወዳዳሪነት ይፈጥርለታል፡፡ ሎጂስቲክስ በአየር ብቻ አይደለም፡፡ በባቡር፣ በመርከብ፣ በመኪናና በሌላም አለ፡፡ እነዚህን ሁሉ አሟጦ መጠቀም ይጠይቃል፡፡ አሁን ለምሳሌ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጀመረው ነገር አለ፡፡ አንድ ዕቃ ከቻይና ወደ ናይጄሪያ ለማድረስ ሁለት ወራት ይፈጃል፡፡ ጂቡቲ ቢራገፍ ግን 27 ቀናት ነው የሚፈጀው፡፡ ጂቡቲ የተራገፈውን ደግሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ናይጄሪያ ሲያደርሰው ከወር ብዙ ባልተሸገረ ቀን ይደርሳል፡፡ የእኛ አየር መንገድ ብቻ ሳይሆን የናይጄሪያ ሰዎችም ይጠቀማሉ፡፡ መርከብና አየርን በማቀናጀት የሚሠራ መልቲሞዳል አገልግሎት ነው፡፡ የግሉ የሎጂስቲክስ ዘርፍም ተበረታቶ በዚህ መሰሉ ሥራ ቢሳተፍ ደግሞ በዚህ ረገድ ትልቅ ለውጥ ይመጣል፡፡  

ሪፖርተር፡- በመጨረሻ የሚያነሱት የቀረ ሐሳብ ካለ?

አቶ ዳዊት፡- መንግሥት ለዘርፉ የሚሰጠውን ትኩረት መጨመር አለበት፡፡ ለምሳሌ አቮካዶ ይላካል ሲባል አቮካዶ የሚላከው እንዴት ነው? በምን ሁኔታ ነው? አስተሻሸጉና አጫጫኑን በተመለከተ ሲምፖዚየም፣ ኮንፍረንስ ወይ ሌላ መድረክ በመፍጠር ግንዛቤ ማስፋት ላይ መሠራት አለበት፡፡ የሌላ አገሮች ተሞክሮ መቅረብ መቻል አለበት፡፡ ከውጭ አገር ሰዎችን በማምጣትም ይሁን ሰዎችን ወደ ውጭ በመላክ በአካባቢያችን ካሉ አገሮች ጋር ተፎካካሪ ለመሆን የሚረዳ ልምድና ዕውቀት መቅሰም ያስፈልገናል፡፡ ዘመናዊ ዝግጅት ያስፈልገናል፡፡ በጥራትም፣ በመጠንም ሆነ በተመጣጣኝ ዋጋ ተፎካካሪ የሆነ ምርት ለዓለም ማቅረብ አለብን፡፡ በዚህ ረገድ ደግሞ የሎጂስቲክስ ዘርፉ መዘመን አለበት፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ሥራቸውን በነፃነት ሳይፈሩና ሳይሸማቀቁ እንዲያከናውኑ ዋስትና የሚሰጣቸው ሕግ የለም›› አቶ አመሐ መኮንን፣ የሕግ ባለሙያና የመብት ተሟጋች

ለበርካታ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች በፍርድ ቤት በመሟገት የሚታወቁት የሕግ ባለሙያ፣ ጠበቃና የመብት ተሟጋቹ አቶ አመሐ መኮንን የፈረንሣይና  የጀርመን መንግሥታት በጋራ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር የላቀ...

‹‹የአጎራባች ክልሎች የሰላም ዕጦት በእኛ ላይ ሸክምና ጫና ፈጥሮብናል›› ከአቶ ባበከር ሀሊፋ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የግብርና ቢሮ ኃላፊ

አቶ ባበከር ሀሊፋ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ወንዶ ገነት ኮሌጅ በፎረስትሪ ሠርተዋል። ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተምረው አጠናቀዋል። ከ2002 ዓ.ም. እስከ 2003 ዓ.ም....

‹‹ሥራችን ተከብሮ እየሠራን ነው ብዬ አስባለሁ›› ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ፣ የፌዴራል ዋና ኦዲተር

ቀደም ሲል በተለያዩ ተቋማት በኃላፊነቶች ሲሠሩ የቆዩትና በ2014 ዓ.ም. የፌደራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤትን በዋና ኦዲተርነት እንዲመሩ የተሾሙት  ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ፣ በኦዲት ክፍተቶች ላይ...