Tuesday, October 3, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ምርታማነትን ለማሳደግ ከተመድ የንግድና ልማት ጉባዔ ጋር የተወጠነው ትብብር

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ ምርታማነትን ለማሳደግ በርካታ የሕግ ማዕቀፎችና ሥርዓቶች በየጊዜው ቢወጡም፣ የሚመዘገበው ውጤት ግን ከዚህ በተቃራኒው ነው፡፡

ለአገሪቱ አጠቃላይ ምርት (ጂዲፒ) ትልቁን ድርሻ የሚያበረክተው የግብርና ዘርፍ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ኅብረተሰብ የሚሳተፍበት ቢሆንም እነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚያመርቱት ምርት ከዕለት ጉርሻቸው አልፎ ለሰፊው ሕዝብ ለማቅረብ በቂ አይደለም፡፡ ለዚህ ችግር እንደ ምክንያት የሚነሳው ደግሞ ዘርፉ ከሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች ጋር የተሳሰረና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ አለመሆኑ፣ የግብርና ምርት ከዕለት ጉርስ ባለፈ አገሪቱ ራሷን በምግብ እንድትችል አላስቻለም፡፡

በግብርናው ዘርፍ ብቻ ያላበቃው የአገሪቱ የኢኮኖሚ መሰናክልና ችግሮች ሌሎች ዘርፎችንም በታቀደውና በታሰበው መንገድ ዕድገት ከማስመዝገብ እንዲታቀቡ ያደረገ ይመስላል፡፡  

ይህን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የተለያዩ ተቋሞችን ከማስተሳሰር በዘለለ የምርታማነት አቅም ማሳደግ በእጅጉ እንደሚያስፈልግ የተረዳው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በየዘርፎቹ ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ ከተባበሩት መንግሥታት የንግድና ልማት ጉባዔ ጋር በመተባበር ከፍተኛ የሆነ ‹‹ሁሉን አቀፍ የምርታማነት አቅም ማሳደጊያ›› ፕሮግራም ለመጀመር ማቀዱን ሰኔ 27 ቀን 2015 ዓ.ም. በነበረው የጋራ መድረክ  ገልጿል፡፡

ይህ የምርታማነት አቅም ማሳደጊያ ፕሮግራም በሌሎች የዓለም አገሮች ተግባራዊ ተደርጎ ውጤታማ መሆኑ ተገለጿል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል፣ በአገሮች መካከል ያለው ልዩነት በዋናነት ከምርታማነት ጋር እንደሚያያዝ፣ ምርታማነት ደግሞ ከቴክኖሎጂና የተቋማትን አቅምና ትብብር የሚሻ መሆኑ ጠቁመዋል፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ የሚታየውን የምርታማነት ችግር ለመቅረፍ መንግሥት አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አዘጋጅቶች እየተገበረ እንደሚገኝ የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ከእነዚህ ጥረቶች መካከል የማኑክቸሪንግ ኢንዱስትሪን ምርታማነት ማሳደግ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት የንግድና ልማት ኮንፈረንስ የአፍሪካ ዳይሬክተር ሚስተር ፓወል አኪው ሚ በበኩላቸው፣ ሁሉን አቀፍ የምርታማነት አቅምን የማሳደግ ፕሮግራም የተዘጋጀው በኢትዮጵያ ምርታማነት ላይ ያሉ ማነቆዎችን በጥናት በመለየትና መፍትሔ በማመላከት ላይ ያተኮረ ነው፡፡

ጥናቱ በዋናነት ካለፈው ኅዳር ወር ጀምሮ ሲከናወን መቆየቱን ዳይሬክተሩ ገልጸው፣ ስድስት ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን በዋናነት መለየቱን ገልጸዋል፡፡

ግብርናን ማዘመንና እሴት መጨመር አንዱ መሆኑን በመጠቆም፣ ለዚህ  ተግባር ደግሞ ዘርፉን ከሌሎች ዘርፎች ጋር ማስተሳሰርና የግብርና ውጤቶች ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ማስፋፋትና የገበያ ሥርዓት መፍጠር ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡

በሁለተኛነት ያስቀመጡት ደግሞ ዓለም አቀፍ የንግድ ትስስርን ሲሆን ወጪ ንግድ ላይ ያተኮሩ ልዩ ዞኖችን በማቋቋም የወጪ ንግድን ማሳደግ እንዲሁም ቀጣናዊ ትስስርን በይበልጥ ማጠናከር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ከተለዩት ስድስት የትኩረት ጉዳዮች ሦስተኛ የሆነው የመሠረተ ልማት (መንገድ፣ የመብራትና ውኃ) ከአገር ውስጥ ባለፈ ከሌሎች አገሮች ጋር በትራንስፖርት ማስተሳሰር እንደሚገባ ጠቁመው፣ ለዚህ ደግሞ ዘርፉን የሚያሳደግ የፋይናንስ አቅርቦት መፍጠር ይገባል ብለዋል፡፡

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ልማትን ማሳደግ፣ ብቁ የሰው ኃይል የማሳደግና የግሉ ዘርፍ በተለያየ መንገድ መደገፍ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ውስጥ ተካተዋል፡፡

ለእነዚህ ሁሉ ተግባራት በትክክል ተፈጻሚ እንዲሆኑ የተቋማት ግንባታና ቅንጅታዊ አሠራር አስፈላጊ መሆኑን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፣ ለዚህ ደግሞ ክህሎት ያለው የሰው ኃይል ማፍራት ትልቁን ድርሻ ይይዛል ብለዋል፡፡

ከዓለም አቀፍና አኅጉር ጋር ስምምነት በመፍጠር የጋራ ሥራ መሥራት አስፈላጊ መሆኑን የጠቆሙት ሚስተር ፓወል፣ ለዚህ ደግሞ ጠንካራ ተቋም አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ በእነዚህ ስድስት ጉዳዮች ኢትዮጵያ ትኩረት አድርጋ መሥራት ከቻለች የኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ሽግግር ዕውን ማድረግ ትችላለች፡፡

በኢትዮጵያ ተግባራዊ ይደረጋል የተባለው ፕሮጀክት በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ማለትም አንጎላ፣ ናይጄሪያ፣ ዛምቢያና ሌሎች ላቲን አሜሪካ ላይ ሲተገበር መቆየቱን ተገልጿል፡፡

በተወሰኑ ምርቶች ወይም ማዕድናት ላይ ብቻ ጥገኛ የሆነው የታዳጊ አገሮች ምርታማነት በሌሎች ዘርፎች በማስፋት ዓለም አቀፍ የእሴት ሰንሰለት ተሳታፊ እንዲሆኑ ማስቻል የፕሮጀክቱ ዓላማ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በቅድሚያ ምርታማነትን ለማሻሻል የተቋማት ቅንጅት ወሳኝ ሚና እንዳለው መለየቱን፣ በመሆኑም ሁሉም ባለድርሻ ተቋማት ተቀናጅተው መሥራት የሚያስችላቸው አሰራር ገቢራዊ ማድረግ እንደሚገባ  ጠቁመዋል። ቅንጅታዊ አሠራሩ  በሁለት መልኩ ሊመራ ይችላል ያሉት ዳይሬክተሩ፣ የሚኒስትሮች ኮሚቴ  ወይም በከፍተኛ መሪዎች  ማሠራት እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ቀጣይነት ያለውና ተገማች የልማት ፈንድና የልማት አጋሮች ትብበር አንዱ መሆኑን፣ ይህን የልማት ፈንድን ቀጣይነት ባለውና ተገማች በሆነ መንገድ ማሰቀጠል ከተቻለ  ስኬቶችን መሠረት ያደረጉት ዕቅዶችን ለመተግበርና የምርታማነት ዕድገት ፍጥነትን ለማስቀጠል ያግዛል ብለዋል።

ሁሉን አቀፍና የተቀናጀ ፖሊሲ በማዘጋጀት፣ የተሻለ የተወዳዳሪነት አቅምን የሚፈጥሩ ጉዳዮችን በመለየት የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግርን ለማረጋገጥ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ሎጂስቲክስ፣ መሠረተ ልማትና የሰው ኃይልን በመቀየር ረገድ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡ የንግድ ሥርዓትን ሊደገፉ የሚችሉ አቅምና ብቃት ያላቸው ተቋማት፣ የኃይል አቅርቦትና ተዓማኒ የሆነ የአይሲቲ ዘርፍ መገንባት ለኢኮኖሚ ማዋቅራዊ ሽግግር ወሳኝ ሚና እንዳለው አስረድትዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት የንግድና ልማት ኮንፈረንስ የዘላቂ ልማት ንዑስ መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙሴ ደሳለኝ በበኩላቸው፣ ፕሮግራሙ ተግባራዊ የሚደረገው ለስምንት ዓመታት ነው፡፡

ላለፉት አምስት ዓመታት ፕሮጀክቱ አንጎላ፣ ቦትስዋናና ሩዋንዳን ጨምሮ ላቲን አሜሪካና ኤዥያ ላይ እየተተገበረ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት የንግድና ልማት ኮንፈረንስ ለስምንት ዓመት በዓይነት ከሚያደርገው አስተዋጽኦ በተጨማሪ፣ ከ15 ሚሊዮን እስከ 17 ሚሊዮን ዶላር በተለያየ መንገድ ይጋፋል ብለዋል፡፡

ለዚህ ፕሮጀክት መሳካትም ለጋሾች ሃያ ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንዲያደርጉ መጠየቃቸውን ገልጸዋል፡፡

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው
የኢትዮጵያ መንግሥት ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ  ሲተገበር የቆየው አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሦስት ቁልፍ ጉዳዮችን መያዙን ገልጸዋል፡፡

የመጀመርያው ማክሮ ኢኮኖሚውንና የፋይናንስ ዘርፉን ማረጋጋት፣ ሁለተኛው ንግድ ለመጀመር እንቅፋት የሚሆኑ አሠራሮችን ማሻሻል መሆኑን፣ በዚህም የግሉን ሴክተር በስፋት ወደ ሥራ ማስገባት፣ ሦስተኛው ደግሞ በተለየ መልኩ በተለያዩ ዘርፎች ያሉ ችግሮችን ለይቶ መቅረፍ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው ብለዋል፡፡

ከዚህ አኳያ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን ምርታማነት የማሳደግ ጉዳይ በሦስተኛው የትኩረት አቅጣጫ ውስጥ ተካቶ እየተሠራበት ያለ መሆኑን፣ ከማኑፋክቸሪንግ በተጨማሪ ግብርና፣ ማዕድን፣ ቱሪዝምና አይሲቲም ልዩ ትኩረት የተሰጣቸው ዘርፎች መሆናቸውን  ተናግረዋል፡፡

እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ የመጀመርያው አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያም የአሥር ዓመቱን መሪ የልማት ዕቅድ በማዘጋጀት ረገድ ቁልፍ ግብዓት ሆኖ አገልግሏል።

ይሁን እንጂ ድርቅ፣ግጭት፣ ጎርፍና የአንበጣ መንጋ የመሳሰሉ የአገር ውስጥ ፈተናዎችና እንደ ኮቪድ-19 እና ወረርሽኝ የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት የመሰሉ የውጭ ተፅዕኖች የትግበራ ምዕራፍ ፈተናዎች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

እነዚህ ፈተናዎች በተለይ በኢንዱስትሪ ዘርፉ ምርታማነት ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድረው ማለፋቸውን ጠቁመዋል፡፡ የተመድ የንግድና ልማት ጉባዔ እ.ኤ.አ. በ2018 የአገሮች ምርታማነት ምዘናው ከተካተቱ 193 አገሮች መካከል ኢትዮጵያ 169 ደረጃ ማግኘቷን አስታውሰዋል፡፡  

ምርታማነትን ይበልጥ ለማሻሻል የባለድርሻ ተቋማት የተናበበ ቅንጅት በእጅጉን እንደሚያስፈልግ፣ ከዚህ አኳያ የቀረበው ‹‹ሁሉን አቀፍ  የምርታማነት ምጣኔ›› ኢትዮጵያ ያላችበትን ሁኔታ በማመላከት በቀጣይ የተሻለ ሥራ ለማከናወን ትልቅ ዕድል የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡

መንግሥት በዛሬው መድረክ የቀረበው ጥናት ያመላከታቸውን ጉዳዮች በመውሰድ ለተግባራዊነቱ እንደሚሠራ ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡ ፕሮግራሙ በኢትዮጵያ ምርታማነት ላይ ያሉ ማነቆዎችን በጥልቀት ጥናት በማድርግ የለየ መሆኑን፣ በኢትዮጵያ የአሥር ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ ውስጥ የተካተቱ ቁልፍ ጉዳዮች ጋር በተጣጣመ መልኩ እንደሚተገበር ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ፕሮግራሙ የኢትዮጵያን ምርታማነት ከማሻሻል በላይ ያልተነኩ አቅሞችን ጥቅም ላይ እንዲውሉ ዕድል የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች