Sunday, July 14, 2024

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርላማ ውሎ በባለሙያዎች ዕይታ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በየዓመቱ ሰኔ ወር መጨረሻ ላይ የሚካሄደውና ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፌዴራል መንግሥትን ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም አስመልክተው ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡ ጥያቄዎች ማብራሪያ የሰጡበት መድረክ፣ ሐሙስ ሰኔ 29 ቀን 2015 ዓ.ም. በነበረ የፓርላማው ሦስተኛ ዓመት 28ኛ መደበኛ ስብሰባ ተካሂዶ ነበር፡፡

በመደበኛ ስብሰባው ከበርካታ የምክር ቤት አባላት ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን፣ በአመዛኙ የመንግሥት አፈጻጸም ሪፖርትን በተመለከተ በጥያቄም ያልተነሱና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መልስ ሳይሰጡ ያለፏቸው ጉዳዮች ተስተውለዋል፡፡

በምክር ቤቱ አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተነሱ በርካታ ጥያቄዎች መካከል የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት፣ የውጭ ንግድ ሚዛን፣ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የዕዳ አከፋፈል፣ የአፈር ማዳበሪያ ሥርጭት፣ የህዳሴ ግድብ አሁናዊ ሁኔታ፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አመራር የሚከናወኑ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም፣ ሥራ አጥነት፣ የዜጎች መፈናቀልና የመሳሰሉ ጉዳዮች ተነስተዋል፡፡

በተጨማሪም የሰላምና የፀጥታ ዘርፍን በተመለከተ፣ አስተዳደራዊ በደሎች፣ የክልል ልዩ ኃይል መፍረስና አፈጻጸሙ፣ የፌዴራል መንግሥትና የትግራይ ክልልን ወቅታዊ ሁኔታ፣ የዜጎች ዕገታ፣ የመልካም አስተዳደርና የሙስና ጉዳይ፣ በአማራና በኦሮሚያ የሚካሄዱ የሕግ ማስከር ዘመቻዎች፣ እንዲሁም ከጎረቤት አገሮች ጋር ያለውን ግንኙነት የሚመለከቱ ጥያቄዎች ይገኙበታል፡፡

ለሦስት ሰዓታት የተጠጋ ጊዜ በፈጀው በምክር ቤቱ 28ኛ መደበኛ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአባላቱ ለተነሱት ጥያቄዎች በአመዛኙ መልስ የሰጡ ቢሆንም፣ በዚያው ልክ ደግሞ የውጭ ግንኙነትን፣ ከኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ጋር ተጀምሮ የነበረውን ድርድር፣ የሰዎችን ዕገታ፣ ከሕወሓት ጋር ያለውን ግንኙነቶችን በተመለከተ ለተነሱ ጥያቄዎች በተጠየቁት መጠን መልስ አልሰጡባቸውም፡፡

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የፓርላማ ተወካይ ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) ባቀረቡት ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ መንበረ ሥልጣን ከመጡበት ከመጋቢት 2010 ዓ.ም. ማግሥት ጀምሮ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮች ወደ ተወሳሰበ ሁኔታ ገብተው አሁን ወደ ሁለንተናዊ አገራዊ ቀውስ መሸጋገራቸውን መሸፋፈን የማይቻልበት ደረጃ ላይ መድረሱን ተናግረዋል፡፡

‹‹ብልፅግና መራሹ መንግሥት የኢትዮጵያን ሕዝብ በሰላም ወጥቶ የሚገባበት፣ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ ሠርቶና ነግዶ የሚኖርበት፣ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ በወቅቱ አግኝቶ አርሶ ወደ የማይበላበት፣ እንዲሁም ከተሜውን መቀለብ የማይችልበት ደረጃ›› መድረሱን አብራርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ በችጋርና በረሃብ እየተሰቃየ መሆኑን፣ የኑሮ ውድነቱ በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሕዝብ ከእጅ ወደ አፍ የነበረውን ኑሮውን መግፋት የማይችልበት ደረጃ መድረሱን፣ ኢኮኖሚው መታመሙን፣ መካከለኛ ነዋሪ የነበረው ተመቶ ወደ ድህነት ወለል መውረዱንና ሥራ አጥነት መስፋፋቱን ደሳለኝ (ዶ/ር) አክለዋል፡፡

በሌላ በኩል ዜጎች በጠራራ ፀሐይ እንደሚታገቱና በሚሊዮን ብር እንደሚጠየቅባቸው፣ በመንግሥት መዋቅር በተለይም በፖሊስ አማራዎችንና የአማራ ልሂቃንን የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎችን በማንሳታቸውና መንግሥትን በማኅበራዊ ሚዲያ በመተቸታቸው ብቻ የሌለ ወንጀል እየተሰጣቸው በማንነታቸው በጅምላ እየታሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ገጽታ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የደም ምድር ሆኗል ያሉት የምክር ቤት አባሉ፣ ሙሉ አማራ ክልልና ከፊል ኦሮሚያ ክልል የጦርነት ቀጣና መሆናቸውን ጠቅሰው ትግራይ፣ አማራና አፋር ፋይዳ ባልነበረው የብልፅግናና የሕወሓት ጦርነት ደቀዋል ብለዋል፡

‹‹ለዚህ ሁለንተናዊ አገራዊ ምስቅልቅልና ቀውስ ዋነኛ ተጠያቂው ብልፅግና መራሹ መንግሥትና የእርስዎ የወደቀ አመራር (Failed Leadership) ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ በነቢብ ብልፅግናን አመጣለሁ እያለ ቢምልና ቢገዘትም፣ በተግባር ለኢትዮጵያ ሕዝብ የመጣለት ግን ጉስቁልና ሆኗል፤›› ብለው፣ ‹‹ብልፅግና አገርን ከቀውስ ማውጣት ካልቻለና ዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም የብልፅግና ከዳሚና የችግሩም አካል በመሆናቸው፣ ከፓርቲዎቹ የሚጠበቅ መፍትሔ ባለመኖሩ ለወደቀው የእርስዎና የብልፅግና አመራር መፍትሔው ምንድነው? አገራዊ የቀውስ መፍትሔ አዘጋጅ ጉባዔ እንዲዘጋጅ አድርገው ሳይረፍድ መፍትሔ መላ ቢባል አይበጅም ወይ?›› ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

ደሳለኝ (ዶ/ር) እንደ አንድ የሕዝብ ተወካይ መንግሥትም ሆነ ብልፅግና፣ እንዲሁም አገሪቱ ከገባችበት የፖለቲካ ቅርቃር ማውጣት ስለማይችሉ፣ ‹‹ሥልጣንዎን ለጊዜያዊ ሲቪል አስተዳድር እንዲያስረክቡ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 60 ንዑስ አንድ መሠረት በምክር ቤቱ ፈቃድ ፓርላማውን እንዲበትኑና ለአዲስ ምርጫ መንገዱን እንዲጠርጉ መጠየቅ እፈልጋለሁ፤›› ብለዋል፡፡

ከደሳለኝ (ዶ/ር) በተጨማሪ ሌሎች የምክር ቤት አባላት ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ መንግሥት ለዚህ ዓመት ብቻ ለማዳበሪያ 21 ቢሊዮን ብር ቢደጎምም ለ2015 ዓ.ም. ምርት ዘመን መቅረብ የነበረበት የአፈር ማዳበሪያ ጊዜውን ጠብቆ ባለመቅረቡ፣ እንዲሁም የቀረበውም ቢሆን በወቅቱ ባለመሠራጨቱ በተለይ በአማራ፣ በኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች አርሶ አደሮች በከፍተኛ ሁኔታ ስለመማረራቸው የተናገሩት ሌላዋ የምክር ቤት አባል ወ/ሮ ገነት ከተማ ናቸው፡፡

የምርታማነት መቀነስ አሁን እየታየ ያለውን የኑሮ ውድነት እንደሚያባብሰው እየታወቀ፣ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦትና ወቅታዊነት ለምን ትኩረት እንዳልተሰጠው ጠይቀው፣ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚስተዋለውን ሌብነትና አሻጥር መቆጣጠር ያልተቻለው ለምንድነው? ሲሉ ወ/ሮ ገነት አክለው ጠየቀዋል፡፡ በቀጣይ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ችግር በአጭር ጊዜ ይፈታል ወይ?  በዘላቂነትስ ችግሩን ለመፍታት በአገር ውስጥ የማዳበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት ምን ታስቧል? ሲሉ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

ኢኮኖሚው እያደገ ቢሄድም የኑሮ ውድነቱን መግታት አንዳልተቻለ፣ በየጊዜው ምክንያታዊ ባልሆነ የዋጋ ጭማሪ በሸቀጦች ላይ በሰዓታት ልዩነት ጭምር ጣሪያ በመንካቱ ሕዝቡ በእጅጉ መማረሩንና መኖር እንደከበደው ጠቅሰው፣ ይህንን የኑሮ ውድነት መቆጣጠር ወይም ማሻሻል እንዴት አልቻለም በማለት የጠየቁት ደግሞ ው/ሮ ሰናይት አስራደው የተባሉ የምክር ቤት አባል ናቸው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአባላቱ ለተነሱት ጥያቄዎች ማብራሪያ ሲሰጡ፣ ‹‹ከቀደመው ሥርዓት የወረስናቸው›› ያሏቸው ኢኮኖሚውን አንቀው የያዙና ስብራት ብለው የጠሯቸው የዋጋ ግሽበትን፣ የዕዳ ጫናና የበጀት ጉድለትን በማንሳት፣ ‹‹የፖለቲካና የሰላም ችግርን ለማስተካከል ኃላፊነት እንደሚሰማው መንግሥትና ዜጋ እያረምንና እያስተካከልን ለሚቀጥለው ትውልድ የተሻለ አገር ማሸጋገር አለብን የሚል ዓላማ አለን፤›› ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት፣ እሳቸው ወደ ሥልጣን ሲመጡ ከ59 በመቶ በላይ የአገሪቱ ጠቅላላ ብሔራዊ ምርት ዕዳ ነበር፡፡ ‹‹የወረስነው በዕዳ የተሞላ አገር በመሆኑ ይህን ዕዳ በግማሽ በማውረድ የሚቀጥለውን ትውልድ ፈተናና ተግዳሮቱን ለመቀነስ መሥራት አለብን በሚል የተዘጋጀ ዕቅድ አለ፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የዓለም የገንዘብ ድርጅትን ጠቅሰው የኢኮኖሚ ዕድገትን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ ኢትዮጵያ በ2014 ዓ.ም. 6.4 በመቶ፣ በ2015 ዓ.ም. 6.1 በመቶ፣ እንዲሁም በ2016 ዓ.ም. 6.4 በመቶ ዕድገት እንደምታስመዘግብ፣ ከሰሃራ በታች ካሉ አገሮች በኢትዮጵያ ልክ ዕድገት ያስመዘግባል ተብሎ የተተነበየ አገር የለም ብለዋል፡፡

 ‹‹በዓለም ላይ ፈጣን ዕድገት እያመጡ ካሉ ጥቂት አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ነች፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ብንፈልግም ባንፈልግም እውነቱ ይኼ ነው፡፡ የትኛውንም ፋይናንስ የሚያውቅ፣ ማንኛውም ሥራ የሚያውቅ፣ ሥራ ሠርቶ የሚያውቅ፣ ማንኛውም የተገለጠ ዓይን ያለው ሰው፣ ምንም ዓይነት አስተማሪና መረጃ ሳያገኝ አዲስ አበባ፣ ባህር ዳር፣ አርባ ምንጭ፣ ጅማ ተንቀሳቅሶ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታይ ዕድገትና የሚዳሰስ ነገር ነው፤›› ብለዋል፡፡ በሳይንስና በቁጥር ከሚቀመጠው ባሻገር የሚታይ ዕድገት በማለት፣ በዚህ ዓመት ኢትዮጵያ ቢያንስ 7.5 በመቶ ዕድገት ታስመዘግባለች ብለዋል፡፡

የዓለም የገንዘብ ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው ግን ከሰሃራ በታች ካሉ አገሮች እ.ኤ.አ. በ2023 ፈጣን ዕድገት ያስመዘገባሉ የተባሉ አገሮች ዝርዝር ሲታይ ሴኔጋል 8.3 በመቶ በአንደኛ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ 6.3 በመቶ በሁለተኛ፣ ሩዋንዳና አይቮሪኮስት እያንዳንዳቸው 6.2 በመቶ በማስመዝገብ አራተኛ፣ ኢትዮጵያ 6.1 በመቶ በማስመዝገብ በአምስተኛ ደረጃ ተቀምጠዋል፡፡ በተመሳሳይ በዓለም የገንዘብ ድርጅት እ.ኤ.አ. በ2024 ፈጣን ዕድገት ያስመዘግባሉ የተባሉ አገሮች ትንበያ መሠረት በአንደኛ ደረጃ የምትገኘው ኒጀር በ13 በመቶ፣ ሴኔጋል 10.6 በመቶ፣ ሩዋንዳ 7.7 በመቶ፣ ሞዛምቢክ 8.2 በመቶ፣ አይቮሪኮስት 6.6 በመቶና ኢትዮጵያ 6.4 በመቶ ዕድገት በስድስተኛ ደረጃ ተዘርዝረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዋጋ ግሽበትን በተመለከተ ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ በምሳሌ ሲያብራሩ በአርጀንቲና 100 በመቶ፣ ቬኒዙዌላ 400 በመቶ፣ ዚምባቡዌ 172 በመቶ፣ የዋጋ ግሽበት እንዳስመዘገቡና በብዙ አገሮች መቋቋም በማይችሉበት ደረጃ እያደገ እንደሄደ ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ የኢትዮጵያን የዋጋ ግሽበት ከ30 በመቶ እንዳይበልጥ ሥራ ተሠርቷል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ የአገር ውስጥ ምርት በ2010 ዓ.ም. 2.2 ትሪሊዮን ብር የነበረ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በ2014 ዓ.ም. ግን 6.2 ትሪሊዮን ብር ደርሷል ብለዋል፡፡ ይህ ደግሞ በውጭ ምንዛሪ ከሃምሳ በመቶ ማደጉን ገልጸው፣ ‹‹በዚህም ከሰሃራ በታች ካሉ አገሮች ሦስተኛ፣ ከምሥራቅ አፍሪካ አንደኛ ነን፣ ይህንን እውነታ መከራከር ጥሩ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

ከሰሃራ በታች ካሉ አገሮች ከናይጄሪያና ከኬንያ ቀጥሎ ሦስተኛ መሆኗን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ኢኮኖሚው ማደጉንና መለወጡን ተቀብለን ያለበትን ስብራትና ችግር ደግሞ እንዴት እንፍታ የሚለው ላይ መምከር እጅግ አስፈላጊ ነው፤›› ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ሪፖርተር በዚህ ጉዳይ ላይ ያነጋገራቸው በኢትዮጵያ የኢኮኖሚክስ አሶሴሽን የምጣኔ ሀብት ተመራማሪ አረጋ ሹመቴ (ዶ/ር)፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት ተጨባጭ የአገር ውስጥ አጠቃላይ ምርት (Real GDP) እና አሁናዊ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት ዋጋ (Nominal GDP) ነው የሚለው መጣራት አለበት፡፡ እሳቸው እንደሚሉት ‹‹ኖሚናል›› የሚባለውና አሁን ያለው ምርት ባለው አሁናዊ ዋጋ የሚሰላ በመሆኑ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደ አንድ ፖለቲከኛ ተናግሮ ማሳመን ስላለባቸው  የአገር ውስጥ ምርት በእጥፍ ጨመረ ብለው ቢናገሩ ትክክል የሚሆንበት መንገድ እንደሚኖር ጠቁመዋል፡፡ ዋናው ነገር ግን ይህ ‹‹ኖሚናል›› የሚባለው አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት ግን የዋጋ ግሽበቱ ውጤት ያመጣው ነው ይላሉ፡፡ የዋጋ ግሽበቱ ከፍተኛ መሆኑን በምሳሌ ሲያብራሩ፣ አሁን የጤፍ ዋጋ በኩንታል ወደ አሥር ሺሕ ብር ገብቷል፡፡ ይህ ማለት በኖሚናል ኢኮኖሚክስ የዘንድሮውን ምርት በዘንድሮ ዋጋ ስታበዛው የሚሰጥህ ዋጋ ሲሆን፣ ነገር ግን ይህ የጤፍ ምርት ዋጋው ጨመረ እንጂ ገበያው ውስጥ ምርት ባለመጨመሩ ተጨባጭ የአገር ውስጥ አጠቃላይ ምርት (Real GDP) የሚባለውን ውጤት አይሰጥም ብለዋል፡፡  

እውነተኛ ዕድገት የሚለካውና የመንግሥት የሥራ ውጤት የሚታውቀው መንግሥት በዕቅድና በፖሊሲ ሠርቶ ባመጣው ሥራ መሠረት ነው የሚሉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው፣ አገሮች መንግሥት ሳይኖራቸው እንኳ ሕዝቡ በራሱ በሚያደርገው የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ዕድገት መምጣቱና አጠቃላይ ሀብት ሊጨምር የሚችል በመሆኑ፣ በመንግሥት ፖሊሲ ያልተደገፈ ዕድገት ግን ጤነኛ አይደለም ሲሉ አክለዋል፡፡

ኢኮኖሚው አድጓል በሚል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያብራሩትን እንዴት አዩት ተብሎ ጥያቄ የቀረበላቸው የምጣኔ ሀብት ባለሙያው እንደሚሉት፣ በኢኮኖሚው ውስጥ ያለው የውጭ ምንዛሪና የንግድ ሚዛን እያሽቆለቆለና የዋጋ ግሽበት እያሻቀበ፣ የተማረው የሰው ኃይል ሥራ አጥ በሆነበት በዚህ ጊዜ ጤናማ ኢኮኖሚ አለ ተብሎ አይታሰብም ብለዋል፡፡ ‹‹ምናልባት ዕድገት ሊኖር ይችላል፡፡ በተለይ የኖሚናል ዓይነቱ ዕድገት የዋጋ ግሽበት የሚያመጣው በመሆኑ፣ በዚሁ ዕድገት ሊቀጥል ይችላል እንጂ አሁን ኢኮኖሚው አድጓል ለማለት ይከብዳል፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ግዙፍነት የሚለካው ለሕዝቡ በነፍስ ወከፍ ገቢ ሲከፋፈል በሚመጣው ውጤት እንደሆነ የሚናገሩት ምሁሩ፣ ለፖለቲካ ዓላማ ወይም ግዝፈትን ለማሳየት ካልሆነ በስተቀር አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት መግዘፍ ለሕዝቡ ሲከፋፈል የሚመጣው የነፍስ ወከፍ ገቢ ትልቅ ካልሆነ ትርጉም እንደማይኖረው ተናግረዋል፡፡

ዓብይ (ዶ/ር) ማዳበሪያን በተመለከተ ሲያብራሩ ወደ ሥልጣን ሲመጡና በለውጡ ወቅት አካባቢ የኢትዮጵያ መንግሥት 450 ሚሊዮን ዶላር ለማዳበሪያ ያወጣ እንደነበር ጠቅሰው፣ አሁን መንግሥት አንድ ቢሊዮን ዶላር ወጪ በማድረግ እየገዛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ይህን በማየት መንግሥት የሰጠውን ትኩረት ከሚወጣው ወጪ አንፃር በቀላሉ መገመት ይቻላል ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ የማዳበሪያ ፋብሪካ በአገር ውስጥ ለመገንባት ትልቅ ሀብት የሚጠይቅ በመሆኑ፣ አሁን ፋብሪካ ለመገንባት ቀላል ሥራ እንዳልሆነና በቀጣይ መንግሥት የጀመራቸውን ግዙፍ ፕሮጅክቶች ሲጨርስ ሊያስብበት እንደሚችል ግን ጠቁመዋል፡፡

ጠቀቅይ ሚኒስትሩ በራሳቸው የግል ጥረትና የፋይናንስ አፈላላጊነት የሚገነቡ ፕሮጀክቶችን በተመለከተ በፓርላማ በተደጋጋሚ ስለፋይናንስ ምንጫቸው በግልጽ አለመታወቅ ለሚነሳው ጥያቄ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በማብራሪያቸው የሥራው ማለቅ የሚያማቸው ሰዎች አሉ ብለዋል፡፡ ‹‹ሥራውን የተመለከቱ የአፍሪካ ወንድሞች እንዴት ዓምና ስንመጣ ያልነበረ ዘንድሮ ተሠራ? እንዴት ፈጠናችሁ? ጥራቱስ? እስኪ መንገዱን አመላክቱን በሚል ወደ ኢትዮጵያ የመጣ ማንኛውም እንግዳ ጥያቄውን ሳያነሳ ሄዶ አያውቅም፤›› ብለዋል፡፡ ዕውን ኢትዮጵያ እንዲህ ዓይነት ሥራ ትሠራለች በማለትም እንደሚጠይቁም አክለው ገልጸዋል፡፡ ገንዘብና ፍላጎቱ ኖሯቸው በዓመትና በሁለት ዓመት መሥራት አንችልም ላሉ መሪዎች የሚያግዝ ቡድን መላኩንም ተናግረዋል፡፡ ‹‹በዩኒቲ ፓርክ ላይ ጥያቄ አለኝ ለሚል ሰው፣ ይህ ቦታ እኔ ወደ ሥልጣን ስመጣ ያለምንም ማጋነን 60 እና 70 በመቶ የሚሆነው ቆሻሻ ነበር፡፡ አሁን ግን መቶ በመቶ ለምቷል፡፡ ይኼ የሆነው የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ፕሬዚዳንት ገንዘብ የለኝም ስላቸው፣ ጥያቄውን ተቀብለው ኮንትራት ሰጥተው የራሳቸውን ኩባንያ ልከው በዲዛይን ተስማምተው ሥራ ተሠራ እንጂ ገንዘቡን እንካና ሥራው አላሉኝም፡፡ ገንዘቡን ኦዲት ማድረግ የምትፈልጉ ሰዎች የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ሄዳችሁ ሼክ መሐመድን ጠይቁ፤›› ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል የብሔራዊ ቤተ መንግሥትን ለማደስ የፈረንሣይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮንን ገንዘብ ጠይቀው እንዳገኙ፣ ፕሬዚዳንት በራሳቸው ጨረታ አውጥተው ለአውሮፓ ኩባንያ ሰጥተው ሥራው የተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፣ በዚህም ፕሮጀክትም የኦዲት ጉዳይ ያለበት ሰው ፈረንሣይ ሄዶ እሳቸውን ማነጋገር ይችላል ብለዋል፡፡

‹‹በተመሳሳይ የወዳጅነት ፓርክን ለቻይና ፕሬዚዳንት ባቀረብኩላቸው ጥያቄ መሠረት እሳቸውም ጨረታ አውጥተው ነው ያሠሩት፡፡ እዚህም አካባቢ ጥያቄ ያለው ሰው ካለ ትኬት እንቆርጣለን ፕሬዚዳንቱን ሄዶ ማነጋገር ይችላል፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩ ፕሮጀክቶች የሚከናወኑት አገሮች ተለምነው ሲፈቅዱና ከኢትዮጵያውያን ተለምኖ እንደሆነ ገልጸው፣ ‹‹አንድ ብር ከዚህ ምስኪን ሕዝብ አንሰርቅም፣ ትርፋችንና ገንዘባችን ሕዝባችን ነው፣ የምንሠራውም ለዚህ ነው፣ የሠራነውን ሥራ አይቶ ያልመሰከረልን የለም፣ እናንተ ባትመሰክሩም የመጣ ዓለም በሙሉ እየመሰከረልን ነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ታዲያ ለምንድነው ይኼ ሁሉ ጉዳይ የሚነሳው ሲባል፣ ተሳካላቸው በሆነ መንገድ ሽንቁር ፈልገን ይህን ስኬት እናጠልሽ ብለው የሚሹ ምስኪን ፖለቲከኞች አሉ፤›› በማለት አብራርተዋል፡፡

ሥልጣናቸውን አስረክበው ምርጫ እንዲካሄድ ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ‹‹የቀረበውን ጥያቄ በጣም ማድነቅ እፈልጋለሁ፡፡ የተቃዋሚ ድርጅቶች ችግር ምርጫ አይፈልጉም፣ ዝም ብላችሁ ልቀቁና ሥልጣን እንያዝ ነው የሚሉት፡፡ አሁን ምርጫ ይደረግ የሚለው ሐሳብ በጣም ጠቃሚ ቢሆንም ሦስት ዓመት መታገስ አለብን፡፡ በየሳምንቱ ምርጫ አይካሄድም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ሦስት ዓመት ጠብቀንና ሐሳብ ይዘን ቀርበን የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈርደውን በፀጋ መቀበል ነው፤›› ሱሉም አክለዋል፡፡

 የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) የፓርላማ አባል አብርሃም በርታ (ዶ/ር) የፓርላማን ውሎ አሰመልክቶ ሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲያብራሩ፣ ‹‹የእኔ ዕይታ ከምክር ቤት አባላቱ ለተነሱ ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ መልስ የሰጡበት አግባብ ትክክል ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ከተጠየቁት ጥያቄዎች አንፃር ለአገር ሲባል አንዳንዴ በሚስጥር የምትይዛቸው ወይም የማታወራቸው ጉዳዮች ይኖራሉ፤›› ብለዋል፡፡

‹‹በመሆኑም የተጠየቀ ሁሉ ላይመለስ ይችላል፣ ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደ መንግሥት ማስተላለፍ ያለባቸውን አብዛኛውን ነገር የገለጹ ይመስለኛል፡፡ ይሁን እንጂ ኢኮኖሚው አደገ በሚል ለቀረበው የኅብረተሰቡ የኑሮ ሁኔታ መለወጥ ነበረበት፡፡ እዚህ ላይ አሁንም ጥያቄ ይፈጥርብኛል፤›› ብለዋል፡፡ ያም ሆኖ ግን ዓብይ (ዶ/ር) እንደ አገር መመለስ ያለባቸውንና አስታራቂ የሆነውን ሙሉ ነገር ተናግረዋል ሲሉ የምክር ቤት አባሉ አስረድተዋል፡፡

ከፓርላማ አባላት ያልተነሱ ጥያቄዎችና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ልለፋቸው ብለው መልስ ያልሰጡባቸው ጉዳዮች ምላሽ ማግኘት አልነበረባቸውም ወይ ተብለው ለተጠየቁት ሲያብራሩ፣ ‹‹ምንም የቀረ ነገር አለ ብዬ አላስብም፤›› ብለዋል፡፡  ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምክር ቤት መጥተው ማብራራት ያለባቸውን አብራሩ እንጂ፣ በእሳቸውና በፓርላማው መካከል የተለየ የመሪና ተመሪ ዓይነት ባህሪም አላየሁም፤›› ያሉት አብርሃም (ዶ/ር)፣ ‹‹በአገላለጻቸው ምንም የተለየ ችግር አላየሁበትም፡፡ ያን ያህል ጽንፍ በወጣ ሁኔታ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሥልጣን የሚያስለቅቅና ውረድ የሚያስብል ነገር አለ ብዬም አላስብም፤›› ብለዋል፡፡

ለዚህም እንደ ምክንያት ያቀረቡት፣ በዚህ ጊዜ መንግሥትን ክፍተት የምትፈጥርበትና አስገድደህ ፓርላማውንና ጠቅላይ ሚኒስትሩን ከሥልጣን እንዲወርድ የምታደርግ ከሆነ በአገር ላይ በችግር ላይ ችግር እየፈጠረ ይሄዳል ብለዋል፡፡ ስለዚህ ለመንግሥት ጊዜ መስጠትና መረጋጋቱ የተሻለ አማራጭ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

‹‹መንግሥትን ዝም ብሎ አስጨንቆ መያዙና በየጊዜው እየወጣን በቃ ልቀቅ ማለቱ የሶሻል ሚዲያ ማስተጋባት ነው የሚመስለኝ፡፡ በተደጋጋሚ ከሚሰሙት ጉዳዮች መካከል እንደ ማስረጃ የምትወስደው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሮጀክቶች ላይ ለሚነሱ ጥያቄዎች አሁን ግልጽነት ተፈጥሯል፡፡ የፈለገ ሰው ሄዶ ኦዲት ማድረግ ስለሚችል ያን ያህል ለማስጮህ የተፈለገበት ምክንያት ግልጽ አልሆነልኝም፤›› ብለው፣ አንድን ፕሮጀክት የተሠራበት ገንዘብ አላውቅምና ትክክል አይደለም ብሎ መጠየቅም ትክክል አይደለም ሲሉ አክለዋል፡፡

የእናት ፓርቲ ፕሬዚዳንት ሰይፈ ሥላሴ አያሌው (ዶ/ር) የፓርላማውን 28ኛ መደበኛ ጉባዔና የጠቅላይ ሚኒስትሩን ውሎ በምክር ቤቱ ተገኝተው ተከታትለው ነበር፡፡ እሳቸው እንደሚሉት በፓርላማው ውሎ የተነሱ ጥያቄዎችንና የጠቅላይ ሚኒስትሩን ምላሾች በማዳመጥ መረዳት የሚቻለው፣ ችግርን አለባብሶ ማለፍን ነው፡፡ ‹‹ለምሳሌ እየታመምክ እኔ አልታመምኩም ጤነኛ ነኝ ብትል በሽታህን ሳትታከመው ትሞታለህ፡፡ በመሆኑም ለአንተ የሚያስፈልግህ መታመምህን አውቀህ መድኃኒት ለመፈለግ ጥረት ስታደርግ ነው ችግርህ የሚፈታው፤›› ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምክር ቤቱ የሰጡት መልስ ግን ሁሉም ነገር ሜዳ ለሜዳ እንደሆነ፣ በተደጋጋሚ እንደሚባለው አገሪቱ በብልፅግና ጎዳናና ከፍታ ላይ መሆኗ ነው የሚነገረው እውነታው ግን ይህ አይደለም ሲሉም አስረድተዋል፡፡

የፓርላማ አባላት በአብዛኛው የአንድ ፓርቲ አባላት ቢሆኑም የአገሪቱን ሁኔታ አይተው ጠቅላይ ሚኒስትሩን አበክረው መጠየቅ ነበረባቸው የሚሉት ሰይፈ ሥላሴ (ዶ/ር)፣ እሳቸውም ፓርላማውን እንደ ተማሪዎቻቸው ሳይሆን ሪፖርት እንደሚያደርጉለት ተቋምና ተጠሪነታቸው ለዚያ ተቋም መሆኑን በመገንዘብ ማቅረብ ይጠበቅባቸው ነበር ብለዋል፡፡ ‹‹አለመታደል ሆኖ ያን አላየንም፣ አንዳንዴ ስላቅ ሁሉ ነበር፤›› ብለው፣ ማንም የሕዝብ ተወካይ ምክር ቤት አባል ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ እኩል የሕዝብ ውክልና እንዳላቸው አብራርተዋል፡፡

የተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚያነሱት ጥያቄ መሳለቂያ መሆን እንደሌለበት ጠቁመው፣ የአብን ተወካይ ያነሱት ጥያቄ አገር የምትፈልገው ትልቅ ጥያቄ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ለእኔ ፓርኮችን መሥራት፣ መዝናኛ መሥራት፣ ሆቴሎች መሥራት ትልቅ ሥራ ነው፡፡ ነገር ግን የመንግሥት ሥራ ይኼ ነው ወይ? የሚለውን ስትመለከት መልሱ የመንግሥት ዋነኛ ተግባር የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት በመጠበቅ ወጥተው እንዲገቡ፣ አጭደው እንዲወቁ፣ ነግደው እንዲመለሱ ነበር ግብር የሚሰበሰበው፡፡ ነገር ግን በዚህ ጉዳይ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰጡ መልሶች የሉም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የረሱት የእሳቸው መንግሥት የአገሪቱን ግማሽ ክፍል እየተቆጣጠረው አለመሆኑን ነው፡፡በአንዳንድ ቅርብ የአዲስ አበባ አካባቢዎች ጭምር ቀን ቀን በአዲስ አበባ መንግሥት፣ ማታ ማታ ደግሞ በጫካው የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ቁጥጥር ውስጥ ነው፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -