Saturday, September 30, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የግብር አሰባሰብ ሒደት ላይ ያሉ ችግሮች በዘላቂነት እንዲፈቱ ግብር ከፋዮች ጠየቁ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአዲስ አበባ ከተማ በግብር አሰባሰብ ሒደት ላይ የሚስተዋሉ በርካታ ችግሮች በዘላቂነት እንዲፈቱ ግብር ከፋዮች ጥያቄ አቀረቡ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ የ2015 በጀት ዓመት አፈጻጸም የ2016 በጀት ዓመት ግብር የመሰብሰብ ሒደት በተመለከተ፣ ማክሰኞ ሐምሌ 4 ቀን 2015 ዓ.ም. በማዘጋጃ ቤት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል፡፡

በውይይቱ ከተገኙት ግብር ከፋዮች መካከል ወ/ሮ ሳውራ መሐሪ የ2015 በጀት ዓመት ግብር አሰባሰብን ሒደት ጥሩ መሆኑን አመላክተው፣ ነገር ግን በግብር አሰባሰብ ላይ የሚታዩ ችግሮት ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ተናግረዋል አሳስበዋል፡፡

የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ነጋዴዎች ማኅበርን ወክዬ ተገኝቼያለሁ ያሉት ወ/ሮ ሳውራ እንደገለጹት፣ በተለይ ግብር ለመክፈል ወደ ሰብሳቢዎች ሲያቀኑ ‹‹አንድ ሚሊዮን ብር ለመንግሥት ከምትከፍሉ 200 ሺሕ ብር ለባለሙያ ሰጥታችሁ፣ 200 ሺሕ ለመንግሥት ከፍላችሁ የተቀረውን 600,000 ብር ለምን አታተርፉም?›› የሚሉ ግብር ሰብሳቢዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ ቀደም እንዲህ ዓይነት አሠራር በድብቅ እንደሚካሄድ ገልጸው፣ ነገር ግን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በጠራራ ፀሐይ የሚሠራ ወንጀልና የአደባባይ ሚስጥር መሆኑን አስረድተዋል፡፡

እንዲህ ዓይነት ሥነ ምግባር የጎደላቸው ነጋዴዎችና የግብር ሰብሳቢ ባለሙያዎች፣ ስለግብር ምንነት ግንዛቤ ቢሰጣቸውና አለፍ ሲልም ተጠያቂነት ማስፈን ቢቻል ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማና ወረዳ ሦስት ነዋሪና ግብር ከፋይ መሆናቸውን የተናገሩ አንድ አባት የግብር ከፋይ ደረጃ እንዲሻሻል ጠይቀዋል፡፡

ለዚህ እንደ ምክንያት ያነሱት ደግሞ ከዛሬ አምስትና ስድስት ዓመታት በፊት አሥር ብር የነበረው የመግዛት አቅም ከአሁኑ ጋር ሲነፃፀር እንደሚለያይ ጠቅሰው፣ ለዚህም ከብር የመግዛት አቅም ጋር የሚጣጣም የግብር ከፋይ ደረጃ በድጋሚ መውጣት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

የአዲስ አበባ ነጋዴዎችን ወክለው እንደተገኙ የተናገሩ አንድ ግብር ከፋይ በበኩላቸው፣ ካለፈው ሥርዓት ወይም ከለውጡ በፊት የነበሩና የተላለፉት ችግሮች አሁንም አሉ ብለዋል፡፡

በተለይ በግብር ሰብሳቢዎች በኩል ግብር ከፋዮችን ያለማክበር ችግር መኖሩን ጠቁመው፣ ከዚህ ባለፈ በዕውቀት ያልተመሠረተ የግብር አሰባሰብ ሒደት ለሥራቸው እንቅፋት እንደሆነባቸው ገልጸዋል፡፡

ግብር ሰብሳቢዎች ግብር ከፋዮችን ከማስተማርና ከማሳየት ይልቅ የማስፈራራትና ዛቻ ጭምር እንደሚያደርሱባቸው በመግለጽ፣ ለመንግሥት ገቢ ከመሰብሰብ ይልቅ የግል ኪሳቸውን ለማደለብ የሚጠቀሙ መሆናቸውን አክለዋል፡፡ 

ከዚህ በተጨማሪ ሕገወጥ የንግድ ግብር ያሳንሳል ያሉት ግብር ከፋዩ፣ መንግሥት ሕገወጦችን ወደ መስመር ለማስገባት አሠራር መዘርጋት እንዳለበት ሐሳባቸውን አካፍለዋል፡፡

መርካቶ ራጉኤል አካባቢ ነጋዴ መሆናቸውን የገለጹት አንድ ነጋዴ ከዚህ ቀደም ሕገወጥ ንግድ መርካቶ እንዳለ በመግለጽ፣ በሌሎች የንግድ ማዕከላት ብዙ መርካቶዎች መፈጠራቸውን ተናግረዋል፡፡ መንግሥት መርካ’ቶ ገበያ ላይ ብቻ ትኩረት ከማድረግ በተጨማሪ፣ ሌሎች የገበያ ቦታዎችንም አሠራር ቢፈትሽ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ መንግሥት መርካቶ ገበያ ላይ ትኩረት ሲያደርግ፣ በሌሎች ከመርካቶ የበለጠ ብዙ ሕገወጥ ቦታዎች ሕገወጥ የንግድ ሰንሰለት መስፋፋቱን ጠቁመዋል፡፡  

ገቢዎች ቢሮና ነጋዴዎች ሲባል የዓይጥና የድመት ጨዋታ የሚሆንበት ምክንያት ትክክል አይደለም ያሉት ግብር ከፋዩ፣ በግብር ሰብሳቢው በኩል ከማስተማር ይልቅ ነጋዴውን የሚያስጨንቅበት ሁኔታ መሻሻል አለበት ብለዋል፡፡

የገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ አደም ኑር ከግብር ከፋዮች የተነሱ ሐሳቦች ትክክል መሆናቸውን ገልጸው፣ በየደረጃው የሚፈቱ ችግሮች ናቸው ብለዋል፡፡

የተነሱትን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ቢሮው ባለሙያዎችን ከማሠልጠን በተጨማሪ፣ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እያከናወነ ይገኛል ብለዋል፡፡

በ2015 በጀት ዓመት 100 ቢሊዮን ግብር ለመሰብሰብ ታቅዶ፣ 107.5 ቢሊዮን ብር ከልዩ ልዩ የገቢ ዓይነቶች መሰብሰቡን ገልጸዋል፡፡ በተያዘው ዓመት ዕቅዱ መቶ በመቶ መሳካቱንና ከ2014 ዓ.ም. ጋር ሲነፃፀር 37.83 ቢሊዮን ብር ወይም 53 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን ገልጸዋል፡፡

በ2015 በጀት ዓመት 3.7 ቢሊዮን ብር ከዕርዳታና ከብድር፣ 77.3 ቢሊዮን ብር ከታክስ ገቢ፣ 11.3 ቢሊዮን ብር ታክስ ካልሆኑ ገቢዎች መሰብሰቡን ተናግረዋል፡፡

ከማዘጋጃ ቤት አገልግሎት ገቢ ከዚህ ቀደም ዝቅተኛ እንደነበር ገልጸው፣ በተያዘው ዓመት ግን 13.6 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡ ከማዘጋጃ ቤት አገልግሎት፣ ከክፍላተ ከተሞች፣ ከገቢዎች ቢሮና ቅርንጫፎች፣ ከመሬት ሊዝ፣ ከመሬት ይዞታና ምዝገባ፣ ከመሬት ልማት አስተዳደርና ከሌሎችም ዘርፎች የተሰበሰብ መሆኑን በመድረኩ ተገልጿል፡፡

በ2016 በጀት ዓመት ከተለያዩ የገቢ ዓይነቶች ወደ 140.29 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን የቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ በዚህም የገቢ ማሰባሰብ ድልድል መሠረት 105 ቢሊዮን ብር ከገቢዎች፣ ከክፍላተ ከተሞች ደግሞ 13.6 ቢሊዮን ብር፣ ከማዕከል ተቋማት ደግሞ 26.31 ቢሊዮን ብር፣ በድምሩ ከ140 ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ መታቀዱን አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች