Wednesday, October 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊወደ መካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ለሥራ የሚሄዱ ዜጎች የፓስፖርት አገልግሎት ማግኘት አለመቻላቸው ተነገረ

ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ለሥራ የሚሄዱ ዜጎች የፓስፖርት አገልግሎት ማግኘት አለመቻላቸው ተነገረ

ቀን:

በአበበ ፍቅር

ለሥራ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አገሮች የሚሄዱ ዜጎች የፓስፖርት አገልግሎት ማግኘት አልቻሉም ሲል፣ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት  አስታወቀ፡፡

‹‹የተጠቃሚዎች ቁጥር መጨመርና የፓስፖርት ወረቀቱን የሚያመርቱ የውጭ አገር ኩባንያዎች ውስን መሆን፣ በተለይ ከሚያዝያ ወር መጨረሻ ጀምሮ ከፍተኛ የሆነ የፓስፖርት እጥረት መከሰቱን፣ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ብሩህተስፋ ሙሉጌታ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

‹‹ከሚያዝያ ወር መጨረሻ ጀምሮ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ለሥራ የሚሄዱ ሠራተኞችን ጨምሮ፣ ቅድሚያ ለመስጠት የሚያስችል ምክንያት ለሌላቸው ዜጎች አገልግሎት መስጠት አቁመናል፤›› ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡ 

በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አማካይነት 60 ሺሕ ዜጎች ወደ ዓረብ አገሮች ለመሄድ ተመዝግበው ፓስፖርት በመጠባበቅ ላይ እንደሆኑ የተናገሩት አቶ ብሩህተስፋ፣ ነገር ግን  ተቋማቸው ባጋጠመው የግብዓት እጥረት በአሁኑ ወቅት የቅድሚያ ቅድሚያ ለሚያስፈልጋቸው ብቻ እየተሰጠ መሆኑን እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ 

‹‹ችግሩን ለመፍታት ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴርና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር እየሠራን ነው፤›› ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ‹‹በዚህም ለሥራ ወደ ውጭ አገር የሚሄዱትን ጨምሮ ሌሎች አገልግሎቱን ለሚፈልጉ ዜጎች ከአንድ ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ አገልግሎት ይሰጣል የሚል ተስፋ አለን፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ባለፈው ኅዳር ወር ተቋማችን ከፓስፖርት ግብዓት አቅራቢዎች ጋር የስምምነት ክፍያ የፈጸመ ቢሆንም፣ የኅትመት ኩባንያዎች ካለባቸው ችግር አንፃር ከአንድም ሁለት ጊዜ ውላቸውን አራዝመውብናል፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹በቀጣይ ግን በፍጥነት እንዲያስገቡልን ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣ ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመሆን ግፊት እያደረግን ነው፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

  አገልግሎቱን ለማግኘት ተመዝግበው ከአራት ወራት በላይ እየጠበቁ ባሉ ደንበኞች ላይ እየደረሰ ባለው መጉላላት ተቋሙ ይቅርታ ይጠይቃል ብለዋል፡፡

‹‹ከፍተኛ የሆነ የፓስፖርት እጥረት ገጥሞናል፤›› ካሉ በኋላ፣ ‹‹በተፈጠረው የግብዓት እጥረት ምክንያት ለደንበኞች እናደርሳለን ብለን በገባነው ቃል መሠረት ባለማድረሳችንና ደንበኞቻችንን ከአራት ወራት በላይ በማስጠበቃችን ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡ አሁንም ካለው የግብዓት እጥረት አንፃር አገልግሎቱን በአስቸኳይ ለመስጠት ውስንነቶች ይኖሩብናል፤›› ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ አክለዋል፡፡

‹‹አሁን ተቋሙ ማስተናገድ ባለበት ልክ እያስተናገደ አይደለም፤›› ያሉት አቶ ብሩህተስፋ፣ ነገር ግን አስገዳጅ ሁኔታዎች ለሚያጋጥሟቸው ዜጎች እንደ ችግራቸው የቅድሚያ ቅድሚያ በመስጠት እያስተናገዱ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

‹‹ለሕክምና፣ ከሁለተኛ ዲግሪ በላይ የትምህርት ዕድል ላገኙ ዜጎችና የመኖሪያ ፈቃዳቸው መታደሻ ለደረሰባቸው ቅድሚያ ሰጥተን እየሠራን ነው፤›› ብለዋል፡፡

ለሰባት ተከታታይ ሳምንታት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ፓስፖርት ለሚፈልግ ሁሉ ሲሰጥ እንደነበር የተናገሩት ኃላፊው፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የፓስፖርት ፈላጊዎች ቁጥር መጨመር፣ እንዲሁም መንግሥት ከዓረብ አገሮች ጋር በገባው ስምምነት መሠረት ለሥራ ወደ ውጭ የሚሄዱ ዜጎች ቁጥር መጨመሩ አሁን ለተከሰተው መጉላላት እንደ ምክንያት አቅርበዋል፡፡

በዚህም እስከ ሚያዝያ ወር መጨረሻ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ሲሰጥ የነበረው ፓስፖርት መቆሙን ተናግረው፣ በአሁኑ ወቅት ቅድሚያ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ብቻ እየተሰጠ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

‹‹መንግሥት በልዩ ሁኔታ በከፈተው የሥራ ዕድል መሠረት ከፍተኛ ቁጥር ላላቸው ተጠቃሚዎች አገልግሎት ስንሰጥ ቆይተናል፡፡ በዚህም ባለፉት ሦስት ወራት 34 ሺሕ የሚሆኑ ዜጎች ከሥራና ክህሎት በደብዳቤ ተልከው አገልግሎት አግኝተዋል፤›› ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡

 በሌላ በኩል አገልግሎቱን ለማግኘት በርከት ያለ ገንዘብ ተገልጋዮች ለእጅ መንሻ እየከፈሉ ነው ስለሚባል፣ ይህንን ጉዳይ ተቋማችሁ እንዴት ይመለከተዋል ሲል ሪፖርተር ለቀረበላቸው፣ ጥያቄ፣ ‹‹ከመልካም ሥነ ምግባር ዕጦት አኳያ አንድ የማናልፈው ነገር ሁልጊዜም እጥረት ሲኖር፣ ሌሎች በተቃራኒ የሚቆሙ እንዳሉ ዕሙን ነው፤›› ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ‹‹ትልቁ ችግር ግን ዜጎች አገልግሎት ማግኘት ያለባቸውን ቦታ መለየት አለመቻላቸው ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹በተቋማችን ተሰጡ የተባሉ ፓስፖርቶችን ለማረጋገጥ ሞክረናል፡፡ ነገር ግን ሁሉም ሐሰተኛ ሰነድ ሆነው ተገኝተዋል፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡

ከ200 በላይ በሚሆኑ ሐሰተኛ ሰነድ ሰጪዎች ላይ የሕግ ዕርምጃ እንደተወሰደባቸው የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፣ 33 የተቋሙ ሠራተኞች ከሥራ መሰናበታቸውን አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...