Saturday, September 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና‹‹በአሁኑ ወቅት ለኢትዮጵያ ሙሉ የሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲ ውጤታማ ይሆናል ብዬ አላምንም›› የቀድሞ...

‹‹በአሁኑ ወቅት ለኢትዮጵያ ሙሉ የሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲ ውጤታማ ይሆናል ብዬ አላምንም›› የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ

ቀን:

ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ሁኔታ ሙሉ የሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲን መከተል ውጤታማ ሊሆን እንደማይችል፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር  አቶ  ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ገለጹ። መንግሥት በተመረጠ ሁኔታ ኢኮኖሚው ውስጥ ጣልቃ እየገባ የሚሠራበት ሁኔታ መቀጠል አለበት ብለው እንደሚያምኑ አስረድተዋል። 

አግራ (AGRA) እና የአፍሪካ ኅብረትን ጨምሮ በ12 ተቋማት በቦርድ ሊቀመንበርነትና በተለያዩ ኃላፊነቶች እያገለገሉ የሚገኙት አቶ ኃይለ ማርያም፣ ሥልጣን ላይ በነበሩት የኢሕአዴግ ጊዜም ሆነ አሁን ከመንግሥት ሥልጣን ከራቁ በኋላ በልማታዊ መንግሥት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ከልባቸው እንደሚያምኑ ከሪፖርተር ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል። 

‹‹ምንም ጥያቄ የሌለው በደምና በአጥንቴ ጭምር በልማታዊ መንግሥት ላይ እምነት አለኝ፤›› ብለዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሚመራው መንግሥት በይፋ የልማታዊ መንግሥት ርዕዮተ ዓለምን ትቻለሁ ባይልም፣ ወደ ነፃ ኢኮኖሚ ሥርዓት የሚያመሩ ዕርምጃዎችን ሲወስድ ይታያል። የቴሌኮምና የባንክን ጨምሮ የተለያዩ ዘርፎችን ለመጀመሪያ ጊዜ ለውጭ ከባንያዎችና ኢንቨስተሮች እየከፈተ መሆኑም ይታወቃል። 

በድኅረ ጦርነት ወቅት የምትገኘው ኢትዮጵያ አብዛኛውን የመልሶ ግንባታና ማገገሚያ የልማት ሥራዎችን ለመከወን የመንግሥትን ወሳኝ ድርሻ የምትጠብቅ ቢሆንም፣ የመንግሥት ካዝና መራቆትን ለመሸፈን የውጭ ድጋፍና የግሉ ዘርፍ አስፈላጊነት ምርጫ አይደለም ሲሉ ባለሙያዎች ያሳስባሉ።

ስለኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነትና የዲፕሎማሲ አቅጣጫ የተጠየቁት አቶ ኃይለ ማርያም የዓለም አቀፍ ምጣኔ ሀብት፣ የፖለቲካ ምኅዳር (Landscape) እና የጂኦ ፖለቲካ ትኩረት በየጊዜው ስለሚቀያየር ኢትዮጵያም ከሁኔታዎች ጋር የሚሄዱና የሚቀያየሩ ፖሊሲዎች ያስፈልጓታል ብለዋል።

‹‹የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ አቅጣጫ በድንብ የተጠና ሊሆን ይገባል። ዓለም አቀፍ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ምኅዳሩ አንዳንዴ አዎንታዊ ሊሆን ይችላል፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ጉዳት ሊያመጣ ይችላል። የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አቅጣጫ በጥናት ላይ የተመሠረተና ነገሮች ሲቀያየሩ የሚቀያየር ሊሆን ይገባል ብዬ አምናለሁ። አሁን በደንብ የተጠና ነገር በሌለበት አስተያየት ለመስጠት ይከብዳል፤›› ሲሉም አስረድተዋል።

በእሳቸው ጊዜ በንፅፅር በቁጥጥር ሥር የነበረውን የዋጋ ንረትና ይህም በማኅረሰቡ ላይ የፈጠረውን አስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታን በተመለከተ አቶ ኃይለ ማርያም ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፣ የዋጋ ንረቱ ለእሳቸውም እንደሚሰማቸውና በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ነዋሪዎች ፈተና መሆኑን ገልጸዋል።

‹‹በአገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ የኑሮ ውድነት አለ። እኔ ለቤቴ የማወጣውን አውቃለሁ፣ ኑሮ እየከበደ ነው። ደመወዝተኛውም በኑሮ ውድነት እየተቸገረ ነው። እኔ በቤቴ ውስጥ የማወጣውን አውቃለሁ። እኔ እንዲህ የማወጣ ከሆነ ሌላው (ዝቅተኛ ገቢ ያለው የማኅበረሰብ ክፍል) ምን ሊያወጣ ይችላል ብዬ አስባለሁ፤›› ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት የዋጋ ንረት ሰማይ ያልደረሰበትና የማይሰቃይ የዓለም አገር እንደሌለ የጠቀሱት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር፣ አሁን በኢትዮጵያ የሚስተዋለው ከፍተኛ የዋጋ ንረት ውስጣዊ ምክንያት ቢኖረውም ችግሩ ግን ዓለም አቀፋዊ ይዘት እንዳለው ገልጸዋል። 

‹‹ጦርነት ባለበት አገር የዋጋ ንረት መከሰቱ አይቀርም፤›› ያሉት አቶ ኃይለ ማሪያም፣ ነገር ግን መንግሥት የምግብ ዋጋ ንረትን ለማረጋጋት ጥረት እያደረገ ስለመሆኑ በስፋት እየተካሄደ ያለውን የስንዴ ልማት በዋቢነት ጠቁመዋል።

እሳቸው በሥልጣን ላይ ቢቆዩ አገሪቱ ባለፉት ዓመታት ያየችው ጦርነትና የእርስ በርስ ግጭት ውስጥ ትገባ ነበር ወይ ተብለው የተጠየቁት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር፣ በዚህ ጉዳይ ላይ መተንበይ እንደማይፈልጉ ተናግረዋል።

‹‹እኔ ሥልጣን ላይ ብቆይ አገሪቱ አሁን ያለችበት ግጭት ውስጥ አትገባም ብዬ መተንበይ አልፈልግም።  ለምን እተነብያለሁ? እኔ የነበርኩበት ዓውድና አሁን ያለው የተለየ ነው። እኔም በሥልጣን ብቀጥል ችግር ውስጥ እንገባ ነበር፣ ወይም ችግር ላይፈጠር ይችል ይሆናል። ያንን የሚወስነው የፖለቲካ ዓውዱ ነው። እዚህ ቁጭ ብዬ እንዲህ አደርግ ነበር ማለት አልችልም፤›› ብለዋል።

‹‹ኢትዮጵያ ውስብስብ አገር ናት፤›› የሚሉት አቶ ኃይለ ማሪያም፣ ከችግር መውጣት የሚቻለው ጠብመንጃ አስቀምጦ መፍትሔ ለመፈለግ በመወያየት መሆኑን እንደሚያምኑ ተናግረዋል። 

‹‹ወደ እርስ በእርስ ግጭት ተሳስተን ገብተን ይህ ሁሉ ሆኗል። አሜሪካም ሆነ አውሮፓ ውስጥ በሽግግር ወቅት መሰል ችግሮች ተፈጥረዋል፣ በመቶ ሺዎች አልቀዋል። እነሱ ግን በቃ ብለው ወደ ዴሞክራሲ ተሻግረዋል። በሽግግር ጊዜ ግጭቶች ይፈጠራሉ፣ እኛም አሁን በቃን ብለን መመለስ አለብን። አለበለዚያ የዕልቂቱ ጊዜ ይራዘማል ብዬ እሠጋለሁ። ይህ እንዳይሆንም እፀልያለሁ፤›› ብለዋል።

በኢትዮጵያ የነበሩ ሁሉም ሥርዓቶች አገሪቱ አሁን ላለችበት ውጥንቅጥ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን የጠቀሱት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ አገሪቱ የተጠራቀመ ችግር ያለባት መሆኑን ተገንዝቦ ከዚህ መውጫ መፍትሔውን ለማመላከት ትኩረት ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል።

‹‹እኔም ሥልጣን ላይ በነበርኩበት ወቅት ያጠፋሁት ነገር አለ፡፡ በግሌ ሳይሆን እንደ ፓርቲና መንግሥት የተሳሳትነውና ያጠፋነው ነገር አለ። ንፁህ የሆነ ሥርዓት የለም፤›› ያሉት አቶ ኃይለ ማርያም፣ ‹‹በእኔ ጊዜ ኢትዮጵያን ወደፊት የወሰዱ ነገሮች አሉ፣ ወደኋላ የጎተቱም አሉ። ዋናው ነገር የወደፊቱን እንዴት እናድርግ ብለን የሚጠቅመንን ይዘን መሄድ ነው ያለብን። ቁጭ ብለን ተወያይተን የተስማማንበትን የጋራ ሕገ መንግሥት አድርገን መሄድ ነው የሚገባን፤›› ሲሉ አክለዋል።

   

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...