Saturday, September 23, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበቀጣዩ አገራዊ ምርጫ ተመጣጣኝ የምርጫ ሥርዓት እንዲተገበር ፓርቲዎች ጠየቁ

በቀጣዩ አገራዊ ምርጫ ተመጣጣኝ የምርጫ ሥርዓት እንዲተገበር ፓርቲዎች ጠየቁ

ቀን:

ከመጪዎቹ ሦስት ዓመታት በኋላ ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው ሰባተኛው አገራዊ ምርጫ፣ ተመጣጣኝ የምርጫ ሥርዓት ተግባራዊ እንዲደረግበት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠየቁ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በተለያዩ የተመረጡ አጀንዳዎች ላይ የሚያደርገውን ሁለተኛ ዙር ምክክር፣ ማክሰኞ ሐምሌ 4 ቀን 2015 ዓ.ም. አካሂዷል፡፡

በውይይቱ በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ የነበሩ ተግዳሮቶችና ስኬቶች፣ የምርጫ አፈጻጸም ብቃትና ገለልተኝነት፣ ተመጣጣኝ የፖለቲካ ሥርዓት ስለመዘርጋት፣ በምርጫ አፈጻጸም ቴክኖሎጂን ስለመጠቀም፣ የሕዝብ ቆጠራ፣ የአካባቢ ምርጫን የሚመለከቱ የሕግና የአሠራር ማሻሻያዎችና የምርጫ ክልል አከላከል ጉዳዮች የተመለከቱ አጀንዳዎች ቀርበው ነበር፡፡

በውይይቱ ከተሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የገዳ ፓርቲን የወከሉት አቶ ሮቤል ታደሰ፣ በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያ ክልል እየተዋጉ ያሉ ኃይሎች ዋነኛ ችግር የሥልጣን ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው ይህንን ችግር የሚፈታ አሳታፊና ፍቱን ይሆናል ያሉትን የተመጣጣኝ የምርጫ ሥርዓት እንዲተገበር ጠይቀዋል፡፡

በተመሳሳይ ከቅማንት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የተወከሉት አቶ አውግቸው ማለደ፣ በቀጣይ ለሚካሄደው አገራዊ ምርጫ የተመጣጣኝ የምርጫ ሥርዓት ሊከናወን የሚችልበት መንገድ ለመፍጠር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራ ይገባል ብለዋል፡፡ ‹‹ልሙጥ የሆነ ምክር ቤት ለመፍጠር የሚደረገውን አዝማሚያ መቅረፍ አለብን፤›› ብለዋል፡፡

የነፃነትና እኩልነት ፓርቲ ፕሬዚዳንት አብዱልቃድር መሐመድ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ከዚህ በፊት ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ከመካሄዱ በፊት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በነበረ ውይይት በፓርቲዎች የምርጫ ሥርዓቱ ተመጣጣኝ እንዲሆን ቀርቦ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ በወቅቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጊዜው ስለማይበቃ መቀየር አልችልም ማለቱን አስታውሰዋል፡፡ አሁንም የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ካልተደረገ በቀጣይ በሚካሄደው ምርጫም ተመሳሳይ ውጤት ይገኛል ብለዋል፡፡

የጋሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ጋሕዴፓ) ሊቀመንበር አቶ ዳሮት ጉምኢ ተመጣጣኝ የምርጫ ሥርዓትን ሥራ ላይ ለማዋል መንግሥት ቁርጠኛ ከሆነ በቀጣዩ የምርጫ ዘመን ይደርሳል በማለት፣ ‹‹ነገር ግን ለገዥው ፓርቲ ፍላጎት ሲባል ሕገ መንግሥት የሚጥስ፣ ለሕዝብ ፍላጎት ሲባል ደግሞ ሕጉን የሚጣረስ ከሆነ የሚያስኬድ ባለመሆኑ፣ የምርጫ ሥርዓቱን ለመቀየር ሕገ መንግሥት የሚባለው ጉዳይ ከሕዝብ ጥቅም አንፃር ሊታይ ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

በውይይቱ የተሳተፉት የብልፅግና ፓርቲ ተወካይ አቶ ዛዲግ አብርሃ፣ በጉዳዩ ላይ ዕውቀት ያላቸው ሰዎች ጥልቅ ጥናት አድርገውበትና በውይይት ዳብሮ እንጂ እንዲያው በቀላሉ ወደ ተመጣጣኝ የምርጫ ሥርዓትን ይቀየር አይቀየር ተብሎ የሚወሰን አይደለም ብለዋል፡፡ የሕገ መንግሥት ትንታኔ የሚፈልጉ ጉዳዮች መኖራቸውን አክለዋል፡፡

የምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ፣ ቦርዱ የምርጫ ዓይነት ይህ ይሁን ማለት እንደማይችል ገልጸው፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች በራሳቸው አቋም ይዘው የሚነጋገሩበት ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 54 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በአንድ የምርጫ ክልል ውስጥ ከሌሎች ተወዳዳሪዎች መካከል አብላጫ ድምፅ ያገኘ ተወዳዳሪ አሸናፊ በሚሆንበት የምርጫ ሥርዓት ይመረጣሉ ይላል፡፡

ኢትዮጵያ የምትከተለው የምርጫ ሥርዓት የአብላጫ ድምፅ የምርጫ ሥርዓት ሲሆን፣ የዚህ ዓይነቱ ሥርዓት በፓርቲ የተወከሉ ወይም የግል ዕጩዎች ለፌዴራሉ የሕዝብ ተወካዮች ወይም ለክልል ምክር ቤቶች የሚወዳደሩበት ሲሆን፣ በዚህ የምርጫ ሥርዓት አብላጫ ድምፅ ያገኘው ዕጩ አሸናፊ ሆኖ የምክር ቤት ወንበር ያገኛል፡፡

በሌላ በኩል የተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓት በአንፃሩ የተለያየ አተገባበር ቢኖረውም ግለሰቦች ሳይሆኑ ፓርቲዎች የሚወዳደሩበት ሲሆን፣ ድምፅ ሰጪዎች ለፓርቲዎች በሰጡት የድምፅ መጠን ልክ እያንዳንዱ ፓርቲ የተወዳደረበትን የምክር ቤት ወንበር ይከፋፈላል፡፡

በመድረኩ የምርጫ ቦርድ የድጋፍ ሰጪ የባለሙያዎች ኮሚቴ አባል ፍሬሕይወት ስንታየሁ (ዶ/ር)፣ ፓርቲዎች የምርጫ ሥርዓቱን የመምረጥ ጉዳይ ላይ በጥንቃቄ እንዲያዩ አሳስበዋል፡፡ ፓርቲዎች የተመጣጣኝ የምርጫ ሥርዓትን መርጠናል ብለው ቢወስኑና ይሁን ተብሎ ወደ ሥራ ቢገባ፣ ውጤቱ የተፈለገውን የአካባቢ ውክልና ላያመጣ ይችላል ብለዋል፡፡  ጉዳዩ ግን የሕገ መንግሥት ማሻሻልና የመንግሥት ድጋፍም የሚያስፈልገው ነው ብለው፣ ይሁን እንጂ የምርጫ ሥርዓቱ የአብላጫ ድምፅና የተመጣጣኝ የምርጫ ሥርዓቱን በአንድ ያካተተ ቅይጥ ሥርዓት ቢሆን ይመረጣል ሲሉ አስረድተዋል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...