Saturday, September 23, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትበአምስተኛው የግራንድ አፍሪካ ሩጫ በርካታ ኢትዮጵያውያን ይጠበቃሉ

በአምስተኛው የግራንድ አፍሪካ ሩጫ በርካታ ኢትዮጵያውያን ይጠበቃሉ

ቀን:

በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ በየዓመቱ የሚከናወነው የግራንድ አፍሪካ የጎዳና ሩጫ፣ በርካታ ኢትዮጵያውያን እንደሚሳተፉ ተገለጸ፡፡ ጥቅምት 3 ቀን 2016 ዓ.ም. በሚካሄደው የጎዳና ሩጫ በአሜሪካና በተለያዩ አኅጉሮች የሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያን እንደሚሳተፉ አዘጋጁ ገልጿል፡፡

የጎዳና ሩጫውን በተመለከተ ኖቫ ኮኔክሽን ሐምሌ 3 ቀን 2015 ዓ.ም. ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጠ ሲሆን፣ በዝግጅቱ ከ20 በላይ ታዋቂ ኦሊምፒያኖችና የዓለም ሻምፒዮን የሆኑ ባለውለታዎች ተሳታፊዎችን ለማበረታታት እንደሚካፈሉ ተገልጿል፡፡

በዓመታዊ የጎዳና ሩጫው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ምክትል ኮሚሽነር ደራርቱ ቱንሉ ጨምሮ በርካታ ስመ ጥር አትሌቶች፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች እንዲሁም ዝነኞች በክብር እንግድነት እንደሚገኙበት ተገልጿል።

ግራንድ አፍሪካ ሩጫ ‹‹አብሮነት መሻል ነው›› በሚል መሪ ቃል በየዓመቱ እየተሰናዳ ይገኛል፡፡ ዓመታዊ ውድድሩ ኢትዮጵያውያንን ማሰባሰብ፣ የመጀመርያው ትውልድ ልጆችን ከባህላቸው ጋር የበለጠ ማቀራረብና ለተለያዩ በጎ ሥራዎች ገቢ ማሰባሰብን ዓላማው አድርጎ እየተከናወነ እንደሚገኝ በጋዜጣዊ መግለጫው ተብራርቷል፡፡

በዓመታዊ የጎዳና ሩጫው በሺዎች የሚቆጠሩ የዳያስፖራው ማኅበረሰብ አባላት እንደሚሳተፉ ተጠቁሟል፡፡ ደራርቱ ከመጀመርያው ውድድር ጀምሮ በአካል በመገኘት አዘጋጆቹን ስትደግፍ የቆየች መሆኗን የገለጸው አዘጋጁ፣ ዓመታዊ ሕዝባዊ ውድድሩ እያሳየ ያለውን ዕድገት አድንቃለች ብሏል። 

ሕዝባዊ ውድድሩ ኢትዮጵያ በምትታወቅበት አትሌቲክስ ከአገር ውጭ ያሉ ወገኖችን የሚያሰባስቡበት መድረክ በመሆኑ ልዩ ትርጉም አለው ስትል ደራርቱ አስተያየቷን ሰንዝራለች፡፡

በሌላ በኩል የኦሊምፒክና የዓለም ሻምፒዮኑ ቀነኒሳ በቀለ በበኩሉ፣ ኢትዮጵያን በበጎ መልክ ለማሳወቅ ጉልህ ድርሻ ባለው በዚህ መድረክ መሳተፍ በመቻሉ ደስተኛ መሆኑን ጠቅሶ፣ ቀኑን በአብሮነት እንዲሁም በደማቅ ሁኔታ ለማሳለፍ ለኅብረተሰቡ ጥሪ አቅርቧል።

የግራንድ አፍሪካን ሩጫ ዋና አዘጋጅ ጋሻው አብዛ (ዶ/ር) ዓመታዊ ውድድሩ የአምስት ኪሎ ሜትር የቤተሰብ ሩጫ የበለጠ ፋይዳ ያለው መርሐ ግብር መሆኑን ጠቁመው፣ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያንን በማቀራረብ ረገድ ጉልህ ሚና አለው ብለዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር ከሩጫው ጎን ለጎን ኑሯቸውን በአሜሪካ ያደረጉ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለሚኖሩበት የአሜሪካ ማኅበረሰብና ለትውልድ አገራችው ኢትዮጵያ የጎላ አስተዋፅኦ ላደረጉ የዳያስፖራ ወገኖች ሽልማት የሚሰጥበት መድረክ እንደሆነም አብራርተዋል።

ባለፉት የውድድር ዓመታት፣ የኢትዮጵያ ብርቅዬ አትሌቶች ደራርቱ ቱሉ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ገንዘቤ ዲባባ፣ ሚሊዮን ወልዴ፣ ፋጡማ ሮባ፣ ብርሃኔ አደሬ፣ ስለሺ ስህን፣ ቁጥሬ ዱለቻና ሌሎችም በክብር እንግድነት ተገኝተውበታል።

በአምስተኛው የቤተሰብ የ5 ኪሎ ሜትር ውድድር ለመሳተፍ ከሐምሌ 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ምዝገባ እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡

በሌላ በኩል በውድድሩ ማግሥት (ጥቅምት 4) ምሽት የሽልማት መርሐ ግብር የሚከናወን ሲሆን በዚህም በሕይወት እያሉ ለማኅበረሰባቸው አስተዋጽኦ ያደረጉ ግለሰቦች የሚዘከሩበት፣ የሚወደሱበት መድረክ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

በዓምናው ሽልማት የምንጊዜም ምርጥ የረዥም ርቀት አትሌቱ ቀነኒሳ በቀለ የግራንድ አፍሪካ ሩጫ የ‹‹ኢምፓክት አዋርድ›› ተሸላሚ መሆኑ ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...