የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሰኞ ሐምሌ 3 ቀን 2015 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ፣ በሦስት ጉዳዮች ውሳኔዎችን ማስተላለፉን ይፋ አድርጓል፡፡
ውሳኔ ከተላለፈባቸው ጉዳዮች መካከል የኢትዮጵያ ክለቦች የጥሎ ማለፍ ውድድር፣ የክለቦች መውጣትና መውረድ እንዲሁም የትግራይ እግር ኳስ ክለቦች ጉዳይ ይገኝበታል፡፡
በዚህም መሠረት ላለፉት ዓመታት ተቋርጦ የቆየው የኢትዮጵያ ክለቦች የጥሎ ማለፍ ውድድር እንደገና ጀምሯል፡፡
ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ላለፉት ዓመታት ውድድሩ ተቋርጦ በመቆየቱ ምክንያት ክለቦች በዓመት ውስጥ ሊያከናውኗቸው የሚገባቸው ጨዋታዎች መጠን ከማሳነሱ በተጨማሪ በጥሎ ማለፍ ውድድር የሚገኘውን የፉክክር ስሜትና ባህሪን መጥፋቱን ያትታል፡፡ ከዚህም ባሻገር ፌዴሬሽኑ ሊያገኘው የሚገባውን ገቢ እንዳሳጣው ጠቅሷል፡፡
በሌላ በኩል ውድድሩ መካሄድ ባለመቻሉም በፕሪሚየር ሊጉ ሁለተኛ ደረጃኝ ይዞ የሚያጠናቅቅ ክለብ፣ በቀጥታ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ እንዲሳተፍ ማድረጉን አንስቷል፡፡
የፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ቀደም ሲል ‹‹የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የጥሎ ማለፍ ዋንጫ›› በመባል የሚታወቀው ውድድር ወደነበረበት እንዲመለስና ማሻሻያዎች ተደርገውበት ከ2ዐ16 ዓ.ም. ጀምሮ ‹‹የኢትዮጵያ ዋንጫ›› በሚል እንደገና እንዲጀምር መወሰኑን አብራርቷል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ በውድድሩ የከፍተኛና የፕሪሚየር ሊጎች ክለቦች ተሳታፊ እንዲሆኑበት፣ አሸናፊውም በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ እንዲካፈል የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መወሰኑ ተገልጿል፡፡
ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ዝርዝር አፈጻጸሙ ወደ ፊት ለሁሉም ክለቦች ይገለጻል ብሏል፡፡
በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበርና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የውድድር ዳይሬክቶሬት የ2016 ዓ.ም. የውድድር ዘመን ካላንደርን ጥሎ ማለፉን ታሳቢ ባደረገና በተጣጣመ መልኩ የውድድር መርሐ ግብራቸውን እንዲዘጋጁ ውሳኔ አሳስቧል፡፡
በሌላ በኩል የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ካስተላለፈባቸው ውሳኔዎች መካከል በ2016 ዓ.ም. የሚመጡና የሚወርዱ ክለቦችን ጉዳይ ይገኝበታል፡፡ ፌዴሬሽኑ የውድድሮቹን ጥራት ለመጠበቅና በተለይ ከከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪሚየር ሊግ የሚያድጉ ክለቦች በውድድር አቅምና በአደረጃጀት የተሻሉና ተፎካካሪ እንዲሆኑ አሳስቧል፡፡
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 84 ንዑስ አንቀጽ 3 ለሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት፣ በ2016 የውድድር ዘመን ከከፍተኛ ሊግ የሚያድጉ ክለቦች ሁለት እንዲሁም ከፕሪሚየር ሊግ የሚወርዱ ክለቦች በተመሳሳይ ሁለት ብቻ እንዲሆኑ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡
ሦስተኛው ውሳኔ ደግሞ የትግራይ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን በተመለከተ ያስተላለፈው ውሳኔ ይጠቀሳል፡፡ በዚህም የትግራይ ፌዴሬሽን በተለያዩ ቀናት በጻፋቸው ደብዳቤዎች በብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ሥር በሚካሄዱ ውድድሮች ተሳታፊ የነበሩ የክልሉ ክለቦች በሰሜን በነበረው ጦርነት ምክንያት ላለፉት ሦስት ዓመታት ሳይሳተፉ መቅረታቸውን ጠቅሶ፣ ከ2016 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ውድድሩ እንዲመለሱ ጠይቋል፡፡
ይህንን ተከትሎ የፌዴሬሽን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በፌዴሬሽኑ መተዳደሪያ ደንብ ክፍል 11 ማጠቃለያ ድንጋጌዎች አንቀጽ 91 መሠረት፣ ያልተጠበቁ ድንገተኛና ከአቅም በላይ አስገዳጅ ሁኔታዎች በሚለው አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 መሠረት፣ ‹‹ያልተጠበቀ፣ ድንገተኛና ሊመልሱት የማይቻል ሁኔታ ሲያጋጥም ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በጉዳዩ ላይ የመወሰን ሥልጣን ይኖረዋል›› እንደሚል ይጠቅሳል፡፡
ውሳኔዎች የፊፋና የካፍ አግባብነት ያላቸውን ደንቦችን እንዲሁም የሚመለከታቸው አስገዳጅ ሕጎችን ከግምት ያስገባ እንደሆነ ያስቀምጣል፡፡
በዚህም መሠረት ‹‹አንድ ክለብ በዚህ አንቀጽ 1 በተመለከተው መሠረት በውድድር ዓመቱ ከውድድሩ ውጪ ከሆነ በውድድሩ ላይ የሚሳተፍ ከሆነ ብቻ ነው›› የሚል ሲሆን፣ የትግራይ ክልል ክለቦች ደንቡ ላይ ከተጠቀሰው ጊዜ በላይ ከውድድር ውጪ የነበሩ በመሆኑ እንደ አዲስ ከክልል ክለቦች ሻምፒዮና መጀመር እንዳለባቸው ያስቀምጣል፡፡
ሆኖም ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው፣ የትግራይ ክልል ክለቦች በደንቡ ከተቀመጠው ጊዜ ገደብ ውጪ የሆኑ ቢሆንም፣ የክልሉን እግር ኳስ ለማነቃቃትና ወደ ቀደመው ተፎካካሪነት ለመመለስ በፌዴሬሽን መተዳደሪያ ደንብ ክፍል 9፣ ውድድሮችና በውድድሮች ውስጥ ያሉ መብቶች በሚለው ክፍል አንቀፅ 84 ንዑስ አንቀፅ 3 መሠረት፣ የትግራይ ክልል ክለቦች አንድ ደረጃ ዝቅ ብለው እንዲወዳደሩ ወስኗል፡፡ ይህም ተፈጻሚ የሚሆነው ለ2016 ዓ.ም. የውድድር ዘመን መሆኑን ተጠቅሷል፡፡
በዚሁ መሠረት በፕሪሚየር ሊግ ሲወዳደሩ የነበሩ ክለቦች ወደ ከፍተኛ ሊግ፣ በከፍተኛ ሊግ ሲወዳደሩ የነበሩ ክለቦች ወደ አንደኛ ሊግ፣ በአንደኛ ሊግ ሲወዳደሩ የነበሩ ክለቦች ወደ ትግራይ ክልል የሊግ ውድድር አንድ ደረጃ ዝቅ ብለው እንዲወዳደሩ ወስኗል፡፡