አሜሪካ ለዩክሬን ክላስተር ቦምብ እንደምትሰጥ ያሳወቀችው ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ነበር፡፡ በሩሲያና ዩክሬን መካከል እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ተከትሎ አሜሪካና አጋሮቿ የጦር መሣሪያ ድጋፍ እያደረጉ የሚገኙ ቢሆንም፣ አሜሪካ ለዩክሬን ከምትሰጠው የ800 ሚሊዮን ዶላር የጦር መሣሪያ ፓኬጅ ውስጥ የክላስተር ቦምብን ማካተቷን ኮንነዋል፡፡
ዓርብ ሰኔ 30 ቀን 2015 ዓ.ም. አሜሪካ ለዩክሬን ከምታደርገው የጦር መሣሪያ ድጋፍ ውስጥ የክላስተር ቦምብ መካተቱን ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ያረጋገጡ ሲሆን፣ እንግሊዝ፣ ስፔን፣ ጀርመን፣ ካናዳ፣ ካምቦዲያ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ)፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ሂዩማን ራይትስ ዎች በተለይም ደግሞ በአሜሪካ ከግማሽ ምዕት ዓመት በፊት በዘነበባት ክላስተር ቦምብ ዛሬም ድረስ ዜጎቿን እያጣች የምትገኘው ላኦስ የአሜሪካን ውሳኔ ተቃውመዋል፡፡
የዩክሬን መከላከያ ሚኒስትር ኦሊክሲ ሬዝኒኮቭ ክላስተር ቦምቡ በሩሲያ ግዛት ውስጥ ጥቅም ላይ አይውልም፣ ይልቁንም በሩሲያ የተያዙ የዩክሬን ግዛቶችን ለማስለቀቅ የምንጠቀምበት ይሆናል ቢሉም፣ የአሜሪካ ውሳኔ በበርካቶች ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም፡፡
እንግሊዝ፣ ፈረንሣይና ጀርመንን ጨምሮ ከ120 በላይ አገሮች ክላስተር ቦምብን ላለማምረት፣ ላለመጠቀም፣ ላለማከማቸትና ለሌሎች አገሮች ላለማስተላለፍ ዓለም አቀፍ ስምምነት እ.ኤ.አ. በ2008 ፈርመዋል፡፡
በየካቲት 2022 በዩክሬንና ሩሲያ መካከል ጦርነት መጀመሩን ተከትሎ ሁለቱም አገሮች ክላስተር ቦምብ መጠቀማቸው የሚገር ሲሆን አሜሪካን ጨምሮ ሦስቱም አገሮች የክላስተር ቦምብ አለመጠቀም ስምምነትን ያልፈረሙ ናቸው፡፡
ለዩክሬን የጦር መሣሪያ ድጋፍ መደረግ አለበት፣ ነገር ግን ክላስተር ቦምብ አይደለም ከሚሉት አገሮች መካከል ስፔን አንዷ ናት፡፡
የስፔን መከላከያ ሚኒስትሯ ማርጋሬታ ሮቤልን ጠቅሶ ኤቢሲኒውስ እንዳሰፈረው፣ ስፔን በማንኛውም ሁኔታ ቢሆን ክላስተር ቦምብ ለዩክሬን መሰጠቱን አትስማማበትም፡፡
የስምምነቱ ፈራሚ የሆነችው ብሪታንያም፣ በአሜሪካ የክላስተር ቦምብ አቅርቦት ውሳኔ አትስማማበትም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ረሺ ሱናክ እንዳሉትም፣ አገራቸው ክላስተር ቦምብን ማምረትና መጠቀም አትደግፍም፡፡
ብሪታኒያ ዩክሬን ራሷን ከሩሲያ ወረራ ለመታደግ የምታደርገውን ትግል ደግፋ የምትቀጥል ቢሆንም፣ የክላስተር ቦምቡን አቅርቦት ግን አትስማማበትም ብለዋል፡፡
የካናዳ መንግሥት፣ የፈረመውን ስምምነት አጥብቆ እንደሚጠብቅ ሲገልጽ፣ ተመድ በበኩሉ ክላስተር ቦምብ ጥቅም ላይ እየዋለ መቀጠሉን ኮንኗል፡፡
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ሂዩማን ራይትስ ዎች ሩሲያና ዩክሬን ክላስተር ቦምብ ከመጠቀም እንዲቆጠቡ ጥሪ ያቀረበ ሲሆን፣ አሜሪካም ክላስተር ቦምብ ለዩክሬን እንዳትልክ ጠይቋል፡፡
ቡድኑ ሩሲያና ዩክሬን ክላስተር ቦምብ እየተጠቀሙ መሆናቸውንና በዚህም ምክንያት በዩክሬን በርካታ ሲቪሎች መገደላቸውን ኮንኗል፡፡
እ.ኤ.አ. ከ1964 እስከ 1975 በነበረው የቬትናም ጦርነት ከአሜሪካ ከሁለት ሚሊዮን ቶን በላይ ክላስተር ቦምብ የወረደባት ላኦስ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ መግለጫ አውጥታለች፡፡
በዓለም ላይ እንደ ላኦስ ሕዝብ የክላስተር ብምብ ሰለባ የለም ያለው መግለጫው፣ ክስተቱ 50 ዓመታት አስቆጥሮም ዛሬም በአገሪቱ ባልፈነዱ ቦምቦች ምክንያት ሕዝቡ እየተጎዳ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ላኦስ ጦርነቱ ካበቃ በኋላ 20 ሺሕ ዜጎቿን በየጊዜው በሚፈነዱ ቦምቦች ያጣች ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 45 በመቶው ሕፃናት ናቸው፡፡
ላኦስ እንደምትለውም፣ በዓለም ማንኛውም ሕዝብ በክላስተር ቦምብ መጎዳት የለበትም፣ በመሆኑም ክላስተር ቦምብ በሁሉም አገሮች መታገድ አለበት፡፡
የባይደን ውሳኔ አገሮችና ተቋማት ብቻ ሳይሆኑ ወትዋቾችም ተቃውመውታል፡፡ የአሜሪካ ኮንግረስ የባይደንን ውሳኔ እንዲያስቀለብስ ጥሪ ማቅረባቸውንም ዘኔሽን በድረገጹ አስፍሯል፡፡
የኢንተርናሽናል ካምፔይን ቱ ባን ላንድማይንስ ኤንድ ክላስተር ሚውኔሽን ኮአሊዥን ምክትል ፕሬዚዳንት ፖል ሃኖን፣ የባይደን ውሳኔ ዩክሬናውያንን አሁንና ወደፊትም ተጎጂ እንዲሆኑ የሚያደርግ ነው፡፡
ክላስተር ቦምብ መቀጠም የጦር ወንጀል ነው የሚሉት ወትዋቾች፣ የአሜሪካ ውሳኔ ልጆችን አደጋ ላይ መጣል ነው፡፡ ጦርነትን ማስቆም አይችልም ብለዋል፡፡
በዩክሬን፣ የኔቶ አባል አገሮችን በሚቀላቀሉ አገሮች ሌሎች አጀንዳዎችን ይዞ ከሐምሌ 4 እስከ 5 ቀን 2015 ዓ.ም. እየመከረ በሚገኘው የሰሜን ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) እየተሳተፉ የሚገኙት የፈረንሣይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፣ ለዩክሬን የሚያደርጉትን የጦር መሣሪያ ድጋፍ እንደሚያጠናክሩ ተናግረዋል፡፡
በኔቶ ጉባዔ የተሳተፈው የጀርመን መከላከያ ሚኒስቴርም፣ የ700 ሚሊዮን ዩሮ የጦር ድጋፍ ለማድረግ መወሰኑን አስታውቋል፡፡
ቱርክ የስዊድንን ወደ ኔቶ መቀላቀል በፓርላማዋ ለማስወሰን በተስማማችበት የሉቲኒያው የኔቶ ጉባዔ፣ የዩክሬን የአባልነት ጥያቄ ጦርነት ላይ በመሆኗ አሁን ላይ የማይቻል ቢሆንም፣ ወደፊት የሚታይበት አግባብ አለ መባሉን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
አባል አገሮቹ ለዩክሬን በሚደረግ የጦር መሣሪያ ድጋፍ ስምምነታቸውን ሲያጠናክሩ፣ ሩሲያ ኔቶ ሩሲያን እንደ ጠላት ማየቱን ኮንናለች፡፡
የክሪምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮፍ፣ ‹‹የኔቶ መሪዎች ሩሲያን እንደ ጠላት ያዩዋታል፡፡ በዚህ ስሜት ውስጥ ሆነው ነው ጉባዔያቸውን እያካሄዱ ያሉት›› ብለዋል፡፡
‹‹ሩሲያ የራሷን ደኅንነት ለማስጠበቅ እያንዳንዱን እንቅስቃሴ ትመረምራች፤›› ያሉት ቃል አቀባዩ፣ የተወሰዱ ዕርምጃዎችም የኔቶን መስፋፋት ተከትለው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ቀድሞውንም ከአሜሪካ ጋር ስምምነት የሌላት ሰሜን ኮሪያ የፕሬዚዳንት ጆ ባይደንን ውሳኔ፣ ‹‹የወንጀል ድርጊት›› ነው ስትል ገልጻዋለች፡፡
የአሜሪካ ለዩክሬን ክላስተር ቦምብ መላክ፣ ዓለምን ወደ ሌላ ሥጋት የሚጨምር እንደሆነ በመግለጽ፣ አሜሪካ ውሳኔዋን እንድትቀለብስ አስሳስባለች፡፡
የኔቶ አባል አገሮች ለዩክሬን የአባልነት ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ ካሳዩ እንዲሁም ጦርነቱ ከተስፋፋ አውሮፓ አሰቃቂ ውጤት ይገጥማታል ስትልም ሩሲያ አስጠንቅቃለች፡፡
‹‹አሜሪካ ለዩክሬን የጦር መሣሪያ ማቅረቧም ለዲፕሎማሲ ዋጋ ካለመስጠት የመነጨ ነው›› ያለችው ሩሲያ፣ የጦርነቱ መስፋፋት ይበልጥ አውሮፓን ይጎዳል ብላለች፡፡