Saturday, September 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ከዚያስ?›› – የጥበብና የዕውቀት መንገድ

ልጆች በዕውቀትና በሥነ ምግባር ታንጸው እንዲያድጉ፣ በፈጠራ ሥራም የዳበሩ እንዲሆኑ ብሎም የነገ አገር ተረካቢ በማድረግ ረገድ ወላጆች፣ ማኅበረሰቦች፣ ትምህርት ቤቶች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ትልቁን ድርሻ ይይዛሉ፡፡ በዚህም የተነሳ አንዳንዶቹም የየድርሻዎቻቸውን ለመወጣት ደፋ ቀና ሲሉ ይስተዋላሉ፡፡ ይህን መሰል እንቅስቃሴ ከሚያደርጉትም መካከል ‹‹ሴጅ ኢትዮጵያ›› የተባለው አገር በቀል ተቋም አንዱ ነው፡፡ የተቋሙ መሥራችና ኃላፊ ወጣት ዘሪሁን ላቀው ሲሆን፣ በተቋሙ እንቅስቃሴና ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች በተመለከተ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሮታል፡፡

ሪፖርተር፡- ሴጅ ምን ማለት ነው? ‹‹ሴጅ ኢትዮጵያ›› መቼ ተቋቋመ? ለማቋቋም መንስዔ የሆነው ምክንያት ምንድነው?

ወጣት ዘሪሁን፡- ሴጅ በእንግሊዝኛ ፍችው ዕውቀት፣ ጥበብ ማለት ነው፡፡ ‹‹ሴጅ ኢትዮጵያ›› ከተቋቋመ ሁለት ዓመት ሆኖታል፡፡ በተለያዩ ትምህርትና በልዩ ልዩ ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራ አገር በቀል ተቋም ነው፡፡ ለማቋቋም መንስዔ የሆነው ዋነኛ ምክንያት በቀደሙትና በአሁኑ ትውልዶች መካከል የተሞክሮና የዕውቀት ክፍተት መኖሩን በመገንዘብ ነው፡፡ ይህም ማለት አባቶች በሕይወት ዘመናቸው የቀሰሙትን አገር በቀል ዕውቀትና በሥራ ያዳበሩትን ተሞክሮ ለአዲስ ትውልድ የሚያስተላልፉበት፣ አዲሱም ትውልድ የአባቶችን ዕውቀትና ተሞክሮ የሚቀስምበት ምቹ መድረክ አለመኖሩ ለተቋሙ መቋቋም ሌላው የመንስዔ ምክንያት ነው፡፡ በዚህም ተቋም አማካይነት ከቀደሙት አባቶች የሚተላለፉትን ዕውቀቶች ልጆቹም ሆኑ አዋቂዎች ቤታቸው ሆነው እንዲያገኙ ለማድረግ የሚያስችሉ መንገዶች ከተመቻቹ በኋላ ከልጆች አስተዳደግ ጋር የተያያዘ ለወላጆች ሥልጠናና የሙያ ድጋፍ ለማስተላለፍ ተችሏል፡፡ ለዚህም ዕውን መሆን ዘመኑ ያፈራቸውን የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም ለስኬት በቅተናል፡፡ ይህን መሰሉ የሙያ ድጋፍ ሥልጠናና ዕውቀት የተላለፈው በቴሌግራም ሲሆን የተላለፈውም ሁልጊዜ ከሰኞ እስከ ሰኞ ከምሽቱ ሦስት ሰዓት በኋላ ወይም ለአንድ ሰዓት ተኩል ነው፡፡ በዚህም ከ2,800 በላይ ሰዎችን ደርሰናል፡፡ በልዩ ልዩ የሙያ ዘርፎች ብቃትና ችሎታ ያላቸው 560 የሚሆኑ ዕውቀት ለጋሾች ዕውቀታቸውን በነፃ አስተላልፈዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ከተጠቃሚዎች ምን ግብረ መልስ አገኛችሁ?

ወጣት ዘሪሁን፡- በመጀመርያ ሳልጠቅሰው የማላልፈው ነገር ቢኖር ትምህርቱ የተላለፈው በቀጥታ መስመር (ላይቭ) ነው፡፡ በተረፈ ትምህርት አዘል የሆኑ መልዕክቶች በተላለፉ ቁጥር ከተከታታዮች ወይም ከታዳሚዎች ባልገባቸው መልዕክቶች ላይ ማብራሪያና መልስ የሚሹ ጥያቄዎች በብዛት ይቀርባሉ፡፡ ይህም የሚሆነው ጠያቂዎች በቅድሚያ ራሳቸውን ካስተዋወቁና አድራሻቸውን ከገለጹ በኋላ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ የተላለፉት ትምህርቶች በሰዎች ዘንድ ምን ያህል ተደራሽ ሆነዋል በሚለው ዙሪያም በየሁለት ወሩ የዳሰሳ ጥናት ተካሂዷል፡፡ በዚህ ዓይነት እንቅስቃሴ ምን ያህል ሰዎች ተጠቃሚ እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ አሁን ደግሞ ወደ መድረክ መጥተናል፡፡

ሪፖርተር፡- ‹‹ወደ መድረክ መጥተናል›› ስትል ምን ማለትህ ነው?

ወጣት ዘሪሁን፡- ወደ መድረክ መጥተናል ስንል ‹‹ኑ ትውልድ ላይ በጋራ እንሥራ!!›› በሚል መሪ ቃል መጪውን የክረምት ወራት ምክንያት በማድረግ በልጆች፣ በቤተሰብ፣ በነገው አገር ተረካቢ ትውልድ ጉዳይ ላይ የተለያዩ ሥራዎችን ለማከናወን የሚያስችል ‹‹ከዚያስ?›› የተሰኘ አዲስ ፕሮጀክት ቀርጸን ወደ ተግባር መግባታችንን ለመግለጽ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የፕሮጀክቱ ዋና ዓላማ ምንድነው?

ወጣት ዘሪሁን፡- ዋናው ዓላማ ወላጆች በልጆቻቸው ላይ ሁለንተናዊ የሆነ ለውጥ እንዲያመጡና መጪው ትውልድም በሥነ ምግባርና በዕውቀት የታነጸ እንዲሆን ለማስቻል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አንድ ፕሮጀክት ሲቀረጽ የራሱ የሆኑ ግቦች ይኖሩታል፡፡ ከዚህ አኳያ ግቦቹን በተመለከተ ማብራሪያ ብትሰጠን፤

ወጣት ዘሪሁን፡- ፕሮጀክቱ ሰባት ግቦች አሉት፡፡ ቀዳሚው ሁሉም ወላጆች በልጆች አስተዳደግ ጉዳይ ላይ የሚገጥማቸውን ችግሮች በውይይት፣ በሥልጠና፣ በምክር አገልግሎትና በፓናል ውይይት እንዲፈቱ ማድረግ፣ በዘርፉ የሚሠሩ ባለሙያዎችም በልጆች ሁለንተናዊ ዕድገት ላይ የሠሩትን የምርምርና የጥናት ውጤቶቻቸውን የሚያቀርቡበትን መድረኮችን በማዘጋጀትና በዘርፉ የሚሠሩ ባለሙያዎችን በጋራ በማሰባሰብ ትውልድ ላይ ሁሉም የየድርሻውን እንዲወጣ ማድረግ የሚሉ ይገኝበታል፡፡ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የነገ አገር ተረካቢ ልጆች አስተዳደግን በዕውቀትና በኃላፊነት መንፈስ እንዲሠራ፣ መደበኛ ያልሆነ የማስተማር ዘዴ በመጠቀም በልጆች ሁለንተናዊ ዕድገታቸው ላይ በጎ ተፅዕኖን በመፍጠር የፈጠራ ብቃታቸውን መጨመር፣ ችሎታውን የሚያዳብሩባቸውን ዕድሎች ማመቻቸት ሳይጠቀሱ መታለፍ የሌለባቸው ግቦች ናቸው፡፡ ከዚህም ሌላ ልጆች የሠሯቸውን የፈጠራ ውጤቶች በሙሉ ዓውደ ርዕይ በማዘጋጀት ልጆቹን በማበረታታትና ዕድሎች እንዲያገኙ ማመቻቸት፣ በተጨማሪም በዚህ ዘመን ላሉ ልጆች ሊመጥን በሚችል መልኩና ሁሉንም ሕፃናት ባማከለ በተረት መጽሐፍ፣ በፊልም፣ በሙዚቃና ወዘተ ልጆቹ ሊማሩባቸው የሚችሉባቸውን የጋራ ጀግኖቻቸውን በመፍጠርና በብዛት በማሳተም ለሁሉም ተደራሽ ማድረግ፣ ሁሉም አካላት በጋራ በመጪው ትውልድ ላይ ባልተከፋፈለና ባልተለያየ መንፈስ በአብሮነት ልጆች የነገው ኢትዮጵያዊ መልካም ዜጎች እንዲሆኑ መሥራትና ለተለያዩ ፖሊሲ አውጪዎች እንዲሁም አስፈጻሚ አካላት የሕግ ድጋፎችንና ምክረ ሐሳቦችን ማስገኘት ከግቦቹ መካከል ተጠቃሾች ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- የፕሮጀክቱ ቆይታንና ተግባራዊ የሚሆንበትን አካሄድ በተመለከተ ዘርዘር ያለ ማብሪሪያ ቢቀርብበት?

ወጣት ዘሪሁን፡- የፕሮጀክቱ ቆይታ ለሦስት ተከታታይ ወራት ነው፡፡ ልዩ ልዩ ተግባራትን ያካተቱ ሁለት ምዕራፎች ያሉትና ዘወትር በሳምንት ሦስት ቀናት ማለትም ማክሰኞ፣ ሐሙስና ቅዳሜ በቀጥታ ሥርጭት ከስቱዲዮ የሚተላለፍ መርሐ ግብር አለው፡፡ በዚህም ዓይነት በሚተላለፈው ፕሮግራም ልዩ ትኩረቱን በወላጆች ላይ በማድረግ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላትን ባሳተፈ መልኩ የሚደረግ የውይይት፣ ሥልጠና እንዲሁም የምርምር ውጤቶች የሚቀርብበት አሳታፊ ፕሮግራም ነው፡፡ እያንዳንዱ ምዕራፍ የአንድ ወር ከ15 ቀናት የሚቆይ ፕሮግራም ያለው ሲሆን የመጀመርያው ምዕራፍ ተግባራት ከወላጆችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው፡፡ ሁለተኛው ምዕራፍ ተግባራት ደግሞ ሁሉንም ልጆች ብቻ ያካተተ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በሁለቱም ምዕራፎች ውስጥ የተካተቱት ተግባራት ምንድን ናቸው?

ወጣት ዘሪሁን፡- በመጀመርያው ምዕራፍ ውስጥ ከተካተቱት ተግባራት መካከል ‹‹ሴጅ ኢትዮጵያ ከእናቶች ወግ ጋር በመሆን ስለልጆች አስተዳደግ በዓይነቱ የመጀመርያ የሆነው እናቶችን ብቻ ተሳታፊ ያደረገ የግማሽ ቀን የውይይት መድረክ፣ አስተማሪ የሆኑ ታሪኮቻቸውን የሚያቀርቡበት መርሐ ግብር፣ የእርስ በርስ ግንኙነታቸውን የሚያጠናክሩበትና ስለልጆቻቸው የሚመክሩበት መድረክ ይመቻቻል፡፡ ይህም በእናቶች ብቻ የሚመራ ይሆናል፡፡ እንዲሁም ከመንግሥት፣ ከሃይማኖት ተቋማት፣ ከንግዱ ማኅበረሰብ፣ ወላጆችና በውጭ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ሌሎችም አካላት በተገኙበት ‹‹የልጆች ጉዳይ›› በሚል የመድረክ ውይይቶች ይከናወናሉ፡፡ በሁለተኛው ምዕራፍ ውስጥ ከተያዙትም ተግባራት ውስጥ ከተለያዩ በጎ ፈቃደኛ ሰዎች ጋር በመሆን ልጆች ተሰጥዖአቸውን እንዲለዩ የሚደረግበት፣ የንባብ ባህልን እንዲያዳብሩ፣ በምናብ የማሰብ ችሎታቸው እንዲጨምር በተለያየ መንገድ የተለያዩ ቦታዎች ታዋቂ ግለሰቦችን በመጠቀም ልጆች ላይ የተሠሩ ተረትና የታሪክ መጻሕፍትን እንዲያነቡላቸው የማድረግ ሥራ ይገኙበታል፡፡ ለአንድ ሳምንት በልዩነት የተለያዩ የሳይንስ፣ የሒሳብ፣ የቴክኖሎጂ ተግባር ሥልጠናዎችን መስጠትም የተግባራቱ አካል ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- የፕሮጀክቱ መጠርያ ‹‹ከዚያስ?›› የሚል ጥያቄ አዘል ያለበት ቃል መሆኑ ምንን የሚያመለክት ነው?

ወጣት ዘሪሁን፡- ሰዎች ከውልደታቸው የሚፈልጓቸውን ነገሮች ካሳኩ በኋላ የሚጠይቁት ጥያቄ ነው፡፡ ስለዚህም ሰዎች በግልም ሆነ በጋራ በጥረታቸው ከደከሙለት ጉዳይ በላይ የገነቡት ነገር ለትውልድ እንዲተላለፍ፣ ትውልድ ላይ በጋራ መንፈስ እንዲሠሩ ለማስቻል የተጠቀምንበት መነሻ ቃል ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች