Saturday, September 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበራያ ቆቦ ወረዳ በመከላከያና በፋኖ መካከል በተቀሰቀሰ ግጭት በነዋሪዎች ላይ የሞትና የአካል...

በራያ ቆቦ ወረዳ በመከላከያና በፋኖ መካከል በተቀሰቀሰ ግጭት በነዋሪዎች ላይ የሞትና የአካል ጉዳት ደረሰ

ቀን:

  • የጉሙዝ ታጣቂዎች የሰላም ስምምነቱ አልተተገበረም በማለት ጉዳት አደረሱ

በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ራያ ቆቦ ወረዳ በቆቦ ከተማና በዙሪያው በመከላከያ ሠራዊትና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በተቀሰቀሰ ግጭት በሰዎች ላይ ሞትና ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን፣ የአካባቢው ነዋሪዎችና የወረዳው የሥራ ኃላፊዎች ለሪፖርተር ገለጹ።

ሐሙስ ሐምሌ 6 ቀን 2015 ዓ.ም. የተቀሰቀሰው ግጭት በማግሥቱ ዓርብ ዕለትም ቀጥሎ መዋሉን የአካባቢው ነዋሪዎች አስረድተዋል። እስከ ዓርብ ምሽት ድረስ በተሰባሰበ መረጃ መሠረት በመከላከያና በፋኖ ታጣቂዎች የተኩስ ልውውጥ ሦስት ንፁኃን ሰዎች ሲገደሉ፣ በርካቶች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። 

ስለግጭቱ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የቆቦ ከተማ ከንቲባ አቶ ሰዒድ አባተ፣ በተቀሰቀሰው ግጭት እስከ ዓርብ ምሽት ድረስ ሦስት ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸው ተረጋግጧል ብለዋል።

ሕይወታቸው አልፏል ከተባሉት ነዋሪዎች በተጨማሪ፣ በሰባት ያህል ነዋሪዎች ላይ ከባድ የአካል ጉዳት ከመድረሱም በላይ የሟቾችና የተጎጂዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ገልጸዋል።

የቆቦ ከተማ ጤና ጣቢያ ኃላፊ አቶ ብርሃኔ ተንሳው በበኩላቸው፣ ሐሙስ ሐምሌ 6 ቀን 2015 ዓ.ም. በመከላከያ ሠራዊትና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት ሦስት ሰዎች በጥይት ተመተው ሕይወታቸው ማለፉን ለሪፖርተር አረጋግጠዋል።

‹‹ወደ ጤና ጣቢያው የመጡት ታጣቂዎች ሳይሆኑ የተጎዱ ነዋሪዎች ናቸው፤›› ያሉት ኃላፊው፣ ‹‹እኛም መርዳት የምንችለውን አክመናል። ከእኛ አቅም በላይ የሆኑትን ደግሞ ወደ ሌሎች የሕክምና ተቋማት ልከናል፤›› ብለዋል።

አምስት ሰዎች በተተኮሰ ጥይት ተመተው ወደ ጤና ጣቢያው ለሕክምና መምጣታቸውን የተናገሩት ኃላፊው፣ ሁለቱ ሰዎች ያጋጠማቸው ጉዳት ቀላል ስለነበረ በጤና ጣቢያው ሕክምና እንዲያገኙ መደረጉን ገልጸዋል። ሦስቱ ሰዎች ላይ የደረሰው ጉዳት ከባድና ከጤና ጣቢያው አቅም በላይ በመሆኑ ወደ አካባቢው ሆስፒታል መላካቸውን አስረድተዋል።

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ባለፈው ሳምንት በጅማ ከተማ በነበረው የሠራዊቱ ማዕከላዊ ዕዝ ዓመታዊ ክብረ በዓል ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር የሚያዋጋ አጀንዳ እንደሌለ ተናግረው ነበር።

‹‹ፋኖ በሚል አማራ ክልል ላይ የነበረውን እንቅስቃሴ በአብዛኛው በሰላም ወደ ቤተሰቡ እንዲመለስ ያደረገው መከላከያ ነው፤›› ያሉት ኤታ ማዦር ሹሙ፣ በጫካ ከነበሩ የፋኖ ታጣቂዎች መካከል በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩት በአገር ሽማግሌዎችና በሃይማኖት አባቶች ዕገዛ ወደ ሰላማዊ ሕይወት እንዲመለሱ መደረጋቸውን ገልጸው ነበር።

‹‹የቀሩት ፋኖዎችም ወደ ሰላሚዊ ሕይወታቸው እንዲመለሱ ነው እኛ የምንፈልገው። ከፋኖ ጋር መዋጋት አንፈልግም። ከፋኖ ጋር የሚያዋጋ ምንም አጀንዳ የለንም፤›› ነበር ያሉት።

ሪፖርተር ያነጋገራቸው ሦስት የቆቦ ከተማ ነዋሪዎች ሐሙስ ረፋድ ላይ በከተማው መሀል በሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ ላይ ተኩስ ከተከፈተ በኋላ ግጭቱ መቀጣጠሉን፣ ፖሊስ ጣቢያው ላይ በተከፈተው ተኩስም ሰዎች መገደላቸውን ተናግረዋል።

የተኩስ ልውውጡ በአካባቢው በሚገኘው የመከላከያ ሠራዊትና የምሥራቅ አማራ ፋኖ ተብሎ በሚጠራው ታጣቂ ቡድን መካከል መሆኑን የገለጹት ነዋሪዎቹ፣ ግጭቱ ተስፋፍቶ በርካታ አካባቢዎችን ማዳረሱን ጠቁመዋል።

ግጭቱ በራያ ቆቦ ከተማና በከተማው ዙሪያ በሦስት አቅጣጫዎች ማለትም ከከተማው ወጣ ብሎ በስተ ምዕራብ በኩል ካራይላ፣ ቀመሌ፣ ጠዘጠዛ፣ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን አካባቢዎችን ማዳረሱን፣ በስተ ደቡብ በኩል ደግሞ አራዱም፣ ሮቢትና ጎብዬ ከተማዎችና በዙሪያቸው፣ እንዲሁም በስተ ምሥራቅ በኩል በዞብል ተራራ ላይ መካሄዱን ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የቆቦ ሆስፒታል አንድ ሠራተኛ፣ ‹‹በብዛት የተጎዱት ሲቪሎች ናቸው። ሪፈር የተባሉ አሉ። ሪፈር ተብለው የሞቱ አሉ። በሆስፓታሉ የሞቱም አሉ። ሪፈር ተጽፎላቸው መንገድ በመዘጋቱ መሄድ ያልቻሉም አሉ፤›› ሲሉ አስረድተዋል።

ሆስፒታሉ ከመጡት ነዋሪዎች መካከል ሕፃናትና እናቶች እንዳሉበትም እኚሁ ሠራተኛ ተናግረዋል።

የተጎዱት ሰዎች ምን ያህል እንደሆኑ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹አሁን በቁጥር መግለጽ እቸገራለሁ፣ ወደ አለማጣና ወልዲያ ከተማ ሆስፒታል ሪፈር የተጻፈላቸው ተጎጂዎች አሉ፡፡ ወደ ወልዲያ ከተማ ሆስፒታል ሪፈር የተጻፈላቸውም አሉ፣ ነገር ግን መንገድ በመዘጋቱ መሄድ አልቻሉም፤›› ብለዋል።

ሪፈር ተጽፎላቸው ወደ አላማጣ ከተማ ከተላኩት ተጎጂዎች መካከል አንድ ሰው መሞቱን፣ በቆቦ ሆስፒታል በሕክምና ላይ የነበረ ሌላ አንድ ሰውም በተመሳሳይ ሕይወቱ ማለፉን ገልጸዋል።

ዓርብ ዕለት የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በከተማዋ እየተዘዋወሩ ወጣቶችን እያፈሱ መውሰዳቸውንና በከተማው እንቅስቃሴ መቆሙን የገለጹት የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ዓርብ ከቀትር በኋላ የተኩስ ድምፅ መቆሙን ነገር ግን የከተማው ነዋሪዎች በከፍተኛ ሥጋት ውስጥ መሆናቸው አስረድተዋል።

ዓርብ አመሻሽ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የቆቦ ከተማ ጤና ጣቢያ ኃላፊ አቶ ብርሃኔ፣ ‹‹አሁን ድባቡ ሲታይ ፀጥ ያለ ነው። ምንም ዓይነት እንቅስቃሴም የለም፤›› ብለዋል።

በቆቦ ከተማና አካባቢው ስለተከሰተው ግጭት ማብራሪያ እንዲሰጡ ሪፖርተር በስልክ ያነጋገራቸው የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው፣ ስብሰባ ላይ በመሆናቸው መረጃ ለመስጠት እንደማይችሉ ገልጸዋል።

ይህ በዚህ እንዳለ ‹‹የሰላም ተመላሾች›› የተባሉ ታጣቂዎች በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ግልገል በለስ ከተማ ሰኔ 30 ቀን 2015 ዓ.ም. በከፈቱት ጥቃት ስምንት ሰዎች መገደላቸውንና ሌሎች 16 ሰቪል ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱን፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሐምሌ 6 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

በክልሉ መንግሥትና በአካባቢው ነዋሪዎች ‹‹የሰላም ተመላሾች›› በሚል ስያሜ የሚታወቁት የጉሙዝ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉሕዴን) ተብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን አባላት መሆናቸውን የገለጸው ኮሚሽኑ፣ ታጣቂዎቹ ሰላማዊ የፖለቲካዊ ትግል ለማራመድ ከመንግሥት ጋር ተስማምተው የተመለሱና ትጥቅ ለማስፈታት በሚል አንድ ካምፕ ውስጥ እንዲሠፍሩ የተደረጉ መሆናቸውን አስታውቋል።

ታጣቂዎቹ ጉዳት ያደረሱት በአካባቢው የሚኖሩ በተለምዶ ‹‹ቀዮች›› ተብለው የሚታወቁ ነዋሪዎች (ከጉሙዝ ብሔር ውጪ ያሉ ሌሎች ብሔሮች) ላይ መሆኑን የኮሚሽኑ መግለጫ ያስረዳል። ታጣቂዎቹ ጥቃቱን የሰነዘሩበት ምክንያት ‹‹ከመንግሥት ጋር የተደረሰው የሰላም ስምምነት አልተተገበረም›› የሚል መሆኑን፣ ኮሚሽኑ ካነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች መረዳቱንም አስታውቋል።

በየካቲት ወር 2015 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰባት አባላት ያሉትና በመተከልና ሌሎች አካባቢዎች የተፈጠሩ የፀጥታ ችግሮችን በመገምገም የመፍትሔ አቅጣጫ እንዲያቀርብ የተቋቋመ ኮሚቴ፣ በመተከል ዞን ያለውን ሁኔታ ጎብኝቶ፣ ከሦስት ሺሕ በላይ ታጣቂዎችና በእነሱ አማካይነት ‹‹ጫካ ገብተው›› የነበሩ ከ68 ሺሕ በላይ የጉሙዝ ብሔረሰብ አባላት ወደ ሰላማዊ ሕይወት መመለሳቸውን እንደገለጹ ኮሚሽኑ በመግለጫው አስታውሷል።

ይህንንም ተከትሎ ታጣቂዎቹ ትጥቃቸውን ለመፍታት ከመንግሥት ጋር በተስማሙት መሠረት፣ በከተማዋ ምሥራቅ በኩል በሚገኝ ካምፕ እንዲሰፍሩ የተደረገ መሆኑንና በተለምዶ ‹‹የሰላም ተመላሾች›› በመባል እንደሚጠሩ፣ ነገር ግን ትጥቃቸውን እስካሁን እንዳልፈቱ ኮሚሽኑ ካሰባሰበው መረጃ መረዳቱን አስታውቋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...