Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትለዓለም ሻምፒዮና የሚዘጋጀው ብሔራዊ ቡድን ምን ገጠመው?

ለዓለም ሻምፒዮና የሚዘጋጀው ብሔራዊ ቡድን ምን ገጠመው?

ቀን:

የኬንያ አትሌቲክስ ቡድን እ.ኤ.አ. በ2022 በአሜሪካ ዩጂን በተሰናዳው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በነበረው ተሳትፎ ውጤቱ ያሽቆለቆለበት ጊዜ ነበር፡፡ ቡድኑ በሻምፒዮናው ሁለት ወርቅ፣ አራት ብርና አንድ ነሐስ ሜዳሊያ፣ በአጠቃላይ አሥር ሜዳሊያዎችን በማግኘት ከዓለም አራተኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቁ ኬንያውያን ያስቆጨ ነበር፡፡

በዓለም ሻምፒዮና፣ በኦሊምፒክና በተለያዩ የአትሌቲክስ መድረኮች ድምቀት የሆኑት ኬንያውያን አትሌቶች በአሜሪካ ውጤት ሊቀናቸው አልቻለም፡፡ እ.ኤ.አ. በ2005 በሄልሲንኪ ዓለም ሻምፒዮና ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ11 በታች ሜዳሊያዎችን ከአነስተኛ ወርቅ ጋር ያገኘችበት የዓለም ሻምፒዮና ነበር፡፡

በዚህም መሠረት ውጤት በኬንያውያን ዘንድ ቁጣን ያስነሳና ከፍተኛ ቁጭት የፈጠረ አጋጣሚ ሆኖ አልፏል፡፡

በመካከለኛና በረዥም ርቀት ከኢትዮጵያውያን ጋር ከፍተኛ ፉክክር የሚያደርጉት የኬንያ አትሌቶች፣ በዘንድሮ የሃንጋሪው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የዓምናውን ቁጭት ሊቀለብሱ ቆርጠው የተነሱ ይመስላሉ፡፡

የኬንያ አትሌቲክስ በአጭር፣ በመካከለኛ፣ በረዥም ርቀቶችና በማራቶን ጥሩ ሰዓት ያስመዘገቡ አትሌቶችን በአገሪቱ ስታዲየም ማጣሪያ ውድድር በማድረግ ወደ ሃንጋሪ የሚያመሩት አትሌቶች ከወዲህ ተለይተዋል፡፡

ኬንያ ከምትታወቅበት የመካከለኛና ረዥም ርቀት ውድድሮች ባሻገር፣ በ100 ሜትር ሩጫ የሚወክላት ፈርድናድ አማንያል ጭምር በመጨረሻው ቡድን ውስጥ በማካተት መደበኛ ዝግጅት ጀምራለች፡፡

በአገሪቱ ጥሩ ሰዓት ያለው አትሌት በሙሉ በተሳተፈበት በዚህ የማጣሪያ ውድድር፣ ወደ መደበኛ ልምምዳቸው መግባታቸው ተገልጿል፡፡ የአንድ ወር ዕድሜ በቀረው የዘንድሮ የዓለም ሻምፒዮና፣ ኬንያ የቀኑን መዳረስ በናፍቆት እየተጠባበቀች መሆኑን የኬንያ አትሌቲክስ ድረ ገጽ መመልከት በቂ ነው፡፡

የተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያ ተከታዮች የኬንያ አትሌቲክስ ቡድን ዓምና የነበረውን ውጤት ዘንድሮ በሃንጋሪ ሊያሳካው ከሚችለው ውጤት ጋር በማነፃፀር ተጠምደዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር የበርካታ ርቀቶች ክብረ ወሰኖች፣ በግል ውድድሮች ጭምር በኬንያውያን አትሌቶች እየተመዘገቡ መምጣታቸውን ተከትሎ፣ ኬንያ በዓለም ሻምፒዮና የሚኖራት ተሳትፎ ከወዲሁ ከፍተኛ ግምት እንድታገኝ አስችሏታል፡፡

በአንፃሩ በዓለም ሻምፒዮና የኬንያ ብቸኛ ተፎካካሪና የበርካታ ዓለም ሻምፒዮና ድምቀት የሆነው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ዝግጅት አለመጀመሩ እያነጋገረ ይገኛል፡፡

በኦሪገን ዓለም ሻምፒዮና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድን አራት ወርቅ፣ አራት የብር ሜዳሊያና ሁለት ነሐስ፣ በአጠቃላይ 10 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ፣ ከዓለም አሜሪካን ተከትሎ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቅ ከፍተኛ ድል ማስመዝገብ የቻለበት ዓመት ነበር፡፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን በማራቶን በሁለቱም ጾታ ሁለት ወርቅ፣ በ10 ሺሕ ሜትርና በ5 ሺሕ ሜትር ወርቅ በመሰብሰብ ደማቅ ጊዜ ያሳለፈበት ሻምፒዮና ያደርገዋል፡፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለዓለም ሻምፒዮና የታጩ 31 አትሌቶች፣ 11 አሠልጣኞችና ሁለት የማሳጅ ባለሙያዎች ሰኔ 30 ቀን 2015 ዓ.ም. ጥሪ እንደተደረገላቸው አሳውቆ ነበር፡፡

በማስታወቂያውም ስማቸው የተዘረዘሩ አትሌቶች በሃንጋሪ ቡዳፔስት ከነሐሴ 13 እስከ 21 ቀን 2015 ዓ.ም. በሚካሄደው ሻምፒዮና ዝግጅት የልምምድ ትጥቃቸውን በመያዝ ከሐምሌ 2 ቀን ጀምሮ ለቅድመ ዝግጀት አራራት ሆቴል እንዲገቡ አሳስቧል፡፡

ከጥሪው ጋር ተያይዞም በዕለቱ የማይገኙ አትሌቶች ጥብቅ የዲሲፕሊን ዕርምጃ የሚወስድ መሆኑን ጠቅሶ፣ ቅሬታ ያላቸው አትሌቶች ካሉ እስከ ሐምሌ 6 ቀን ድረስ  ለፌዴሬሽኑ ማቅረብ እንደሚችሉም አስታውቋል፡፡

ሆኖም በተጠቀሱት ቀናት ስም ዝርዝራቸው ይፋ የሆኑት አትሌቶች በተባለው ቦታ አለመገኘታቸውን ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በይፋዊ ማኅበራዊ ገጹ ገልጿል፡፡

ፌዴሬሽኑ ባደረገው ጥሪ መሠረት፣ ከአሠልጣኞችና ከጥቂት የፌዴሬሽኑን ሕግ አከበሩ ካላቸው አትሌቶች በስተቀር ሌሎች ሪፖርት አለማድረጋቸውን ጠቁሟል፡፡

በዚህም መሠረት የተላለፈውን አገራዊ ጥሪ በመቀበል ሆቴል ያልገቡት አትሌቶች ምክንያታቸውን በመያዝ፣ ሐምሌ 6 ቀን አራራት ሆቴል ቀርበው ሪፖርት እንዲያደርጉ ማስጠንቀቂያ አዘል ማሳሰቢያም አስተላልፏል፡፡

ሪፖርት የማያደርጉ አትሌቶችና አሠልጣኖች ላይ የዲሲፕሊን ዕርምጃ እወስዳለሁ ብሏል፡፡

የብሔራዊ ቡድኑ አትሌቶች ያልተገኙበት ምክንያት በግልጽ ባይጠቀስም፣ የተወሰኑ አትሌቶች የዳይመንድ ሊግ ውድድር ስላለባቸው፣ የዓለም አትሌቲክስ የሚኒማ ሰዓት ማሟያ ጊዜ ያለመዘጋቱና ከአሠልጣኞች ምርጫ ጋር በተያያዘ ቅሬታ መኖሩ እንደ ምክንያት ተነስቷል፡፡

የዓለም አትሌቲክስ የሚኒማ ማሟያ ቀነ ገደብ ሐምሌ 23 ቀን በመሆኑና በርካታ አትሌቶች ቅድሚያ ተመራጭ ለመሆን በቀሪ ውድድሮች ላይ መሳተፍ ስለሚሹ ጥሪ በተደረገው ዕለት አለመገኘታቸውን ምንጮች ለሪፖርተር አብራርተዋል፡፡

በሌላ በኩል የአሠልጣኞች በዕጩነት አመራጥ ቅሬታ እንዳስነሳ ተጠቅሷል፡፡ ይህም ኢትዮጵያ በቡዳፔስት በአንደኝነት የተቀመጡ አትሌቶች ያሏት ሲሆን፣ እነዚሁን አትሌቶቹን ያስመረጡ አሠልጣኞች መመረጥ ሲገባቸው አለመመረጣቸው ቅሬታ ማስነሳቱ ተጠቅሷል፡፡

እንደ ሪፖርተር ምንጭ ከሆነ በ10 ሺሕ ሴቶች ሜትር ለተሰንበት ግደይ፣ በ5000 ሜትር  ጉዳፍ ፀጋይ፣  በ3000 ሜትር መሰናክል በወንዶች ለሜቻ ግርማ፣ በሴቶች  ሲምቦ ዓለማየሁ በየምድባቸው በአንደኝነት የሚመሩ የኢትዮጵያን አትሌቶች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

ሆኖም የእነዚህን አትሌቶች አሠልጣኞች ከፊሎቹ በምርጫው አለመካተታቸው ቅሬታ አስነስቷል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም ለቡዳፔስቱ ዓለም ሻምፒዮና በአንደኛ ደረጃ ስማቸው የተዘረዘሩ አትሌቶችና አሠልጣኞች በምርጫው ቅድሚያ ሊሰጣቸው ሲገባ በተቃራኒ መቀመጡ የበለጠ ችግሩን እንዳባባሰው ተብራርቷል፡፡ 

በሌላ በኩል አትሌቶች እንዲያርፉበት ከተመረጠው ሆቴል ጋር በተያያዘ፣  አትሌቶች ያነሱት ቅሬታ ሆኗል፡፡ ይህም አትሌቶቹ ለማረፊያ ከተዘጋጀላቸው ሆቴል ሚመገቡበት ሆቴል ሲያመሩ ችግር ሊገጥማቸው ስለሚችል ሥጋት መፍጠሩ አልቀረም፡፡

በተለይ አትሌቶቹ በእራት ሰዓት ከአንዱ ሆቴል ወደ ሌላ ሆቴል ሲያመሩ ለአደጋ ሊጋለጡ ስለሚችሉ ሥጋት እንደገባቸው ተጠቅሷል፡፡

በአንፃሩ አትሌቶች ለቀሪ የዳይመንድ ሊግ ውድድር መሰናዳታቸውና ብሔዊራዊ ቡድኑ ተጨማሪ አማራጭ እንዲኖረው ያስችላል ተብሏል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም በቀሪ ጊዜያት ማለትም በሞናኮ ዳይመንድ ሊግ በወንዶች 5,000 ሜትር በሪሁ አረጋዊ፣ ሳሙኤል ተፈራ፣ ሐጎስ ገብረ ሕይወትና ጥላሁን ኃይሌ ይወዳደራሉ፡፡

በዚህ ውድድር የተሻለ ብቃት የሚያሳይ አትሌት ለቡዳፔስቱ የዓለም ሻምፒዮና  ለመምረጥ ዕድል ይፈጥራል ተብሏል፡፡

ጥሪ የተደረገላቸው አትሌቶች ወደ ሆቴል እየገቡ እንደሚገኙ የተጠቀሰ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዴሚና በተለያዩ ሥፍራዎች መደበኛ የብሔራዊ ቡድን ልምምዳቸውን ይጀምራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...