በዳግም መርሻ
ችግሮችን ተቀራርቦ በመነጋገርና በመወያየት ስለመፍታት አስፈላጊነት የምንጠቀምቸው ለዘመናት የቆዩ የአገራችን ብሂሎች አሉ። ለምሳሌ ያህል ‹‹ካለመናገር ደጃዝማችነት ይቀራል›› የሚለው አንደኛው አባባል እያንዳንዳችን ፍላጎታችንን፣ ችግራችንንና በሆነ ጉዳይ ላይ ያለንን የግል አስተሳሰብ ሌላው ያውቅ ዘንድ፣ እኛም የእነሱን ፍላጎትና አቋም መረዳት እንድንችል ነፃና ግልጽ ውይይት ማድረግና ለችግሮች መፍትሔ መስጠት አስፈላጊ እንደሆነ ያመላክታል፡፡
‹‹ሕመሙን የደበቀ መድኃኒት አይገኝለትም›› የሚለው አባባል ሌላው በኢትዮጵያ ሥነ ቃል ውስጥ ስንሰማውና ስንናገረው የኖርነው ብሂል ነው። ይህም በተመሳሳይ ሕመሙን፣ ችግሩን፣ ፍላጎቱን፣ በደሉን…፣ ወዘተ. ለሌላ ያላወያየ፣ ያላማከረና ያልመከረ ያለበትን ችግር ለማስወገድ እንደሚቸገር ለማመላከት ስንጠቀምበት የቆየ አነጋገር ነው።
እነዚህ ምሳሌዎች በማኅበራዊም ሆነ በፖለቲካው ዓለም ውስጥ ያሉ ችግሮችንና አለመግባባቶችን በውይይትና በምክክር መፍትሔ መስጠት ካልቻልን፣ የሚያስከትለውን ውጤት ቆም ብለን እንድናጤን የሚያግዙ መሠረተ ሐሳቦች ናቸው ብዬ አምናለሁ።
የሐሳብ ልዩነት በሰው ልጆች ምድራዊ አኗኗር ውስጥ ያለና ወደፊትም የሚኖር ነገር ነው። የሰው ልጆች ግንኙነትና መስተጋብር ባለበት ቦታ ልዩነት አይጠፋም። ሰዎች ተመሳሳይ ሐሳብና ዕይታ ቢኖራቸው ኖሮ ዓለም አሁን ያላት ቅርፅና ይዘት ባልኖራት ነበር። ዓለም በማያቋርጥ የለውጥ/የዕድገት ሒደት ውስጥ የማለፏ አንዱ ሚስጥር በሰዎች መካከል የተለያየ አስተሳሰብና አመለካከት መኖሩ ነው። ይህንን አስመልክቶ ታዋቂው አሜሪካዊ የጦር ጄኔራል ጆርጅ ፓተን (George S. Patton) ሲናገር፣ ‹‹If everyone thinking alike, then somebody is not thinking›› ይላል። ትርጉሙም ‹‹ሰው ሁሉ ተመሳሳይ ሐሳብ ቢኖረው ኖሮ ሌላው ሰው ማሰብ አያስፈልገውም ነበር›› እንደ ማለት ነው። ይህ በማኅበራዊ ሳይንስ ባለሙያዎችም ተቀባይነትን ያገኘ መሠረተ ሐሳብ ነው።
የሥነ ልቦና ባለሙያዎች እንደሚያስረዱት ሰዎች በሚኖራቸው የእርስ በርስ ግንኙነት የሚያካሂዷቸው ውይይቶችና የሚሰጧቸው አስተያየቶች በከፊል በሚቃረኑ ሐሳቦች (Negative Communications) ላይ የተመሠረቱ ናቸው። ይህም የሐሳብ ልዩነት ተፈጥሯዊ (Real) መሆኑን ያሳያል።
በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ የምናያቸው የአስደናቂ ፈጠራዎችና ሳይንሳዊ ግኝቶች መሠረት የሰው ልጅ የአዕምሮ አቅሙን ተጠቅሞ በተለየና ባልተለመደ አቅጣጫ (Thinking out of the box) ማሰብ የመቻሉ ውጤት ነው። ስለሆነም በዓለም ላይ ካሉ ጥበቦች አንዱና ዋነኛው በጋራ ጉዳይ ላይ መወያየት፣ መነጋገርና የሐሳብ ፍጭት ማድረግ ነው ማለት ይቻላል።
በዚህ መሠረት ሰዎች በማያግባቧቸው ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ እየተደራደሩና እየተነጋገሩ ተስማምቶና ተቻችሎ ከመኖር ውጪ ሌላ የተሻለ አማራጭ እንደሌላቸው ማመን ያስፈልጋል። ከዚህ ውጪ እንደ እኔ አስብ፣ እኔን ምሰል፣ የምልህን ብቻ ተግብር… ማለት የጫጨ አስተሳሰብ ማሳያ ነው። የብዙ ውዝግቦች፣ የብዙ ግጭቶት፣ የብዙ ጦርነቶች መነሻ እነዚህና መሰል አስተሳሰቦችና ዕይታዎች ናቸው።
ሳሙኤል ወልዴ (ዶ/ር) የተባሉ ደራሲ ‹‹ከመደነጋገር መነጋገር›› በሚል መጽሐፋቸው በመነጋገር የጋራ ዓላማን ማስጠበቅ፣ በመነጋገር የጋራ ግንዛቤ መፍጠርና በመነጋገር ጥርጣሬንና ሐሜትን ማስወገድ እንደሚቻል ያስረዳሉ፡፡ እንደ ጸሐፊው አባባል በግልጽ የተመከረበት ሐሳብ፣ በጋራ የዳበረ ጉዳይ ሩቅ ለመራመድ ጉልበት አለው። በተቃራኒው ያልተመከረበትና ውይይት ያልተደረገበት ሐሳብ መደነጋገርን ብቻ ሳይሆን ጥርጣሬንም ይፈጥራል ይላሉ።
የበርካታ አገሮች የመበታተን፣ የመፈራረስ፣ የሕዝብ ዕልቂትና ስደት መነሻና ምክንያቱ አለመነጋገርና የጋራ ምክክር ማድረግ አለመቻል መሆኑን በርካታ ጥናቶች ያሳያሉ። በመሆኑም መሠረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶች ውይይትና ምክክር አድርጎ የጋራ መግባባት ላይ መድረስ የውዴታ ግዴታ ነው።
የውስጥ ችግራቸውን በጨዋ ደንብ ተወያይተው መፍታት ያልቻሉ አገሮች የገጠማቸውን ፈተናና መከራ መግለጽም መናገርም ከሚቻለው በላይ ነው። ለምሳሌ ትናንት በብዝኃ ማንነቷ ትታወቅ የነበረችው ዩጎዝላቪያ ዛሬ ከዓለም ካርታ ላይ ስሟ ተፍቋል። ይህ የሆነው ዜጎቿ ባካሄዱት ብሔር ተኮር ጦርነት በመፈራረሷ ሲሆን፣ ይህንንም ተከትሎ በሥሯ የነበሩት ስድስት ሪፐብሊኮች የራሳቸውን ሉዓላዊ አገር ለመፍጠር ችለዋል። ጎረቤታችን ሶማሊያም ቁልቁል ወርዳ አዘቅት ውስጥ ከገባች ከሁለት አሠርት ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል። ምዕራብ እስያዊቷ ሶሪያም የገጠማት ዕጣ ፈንታም ከዚህ ብዙም የተለየ አይደለም። አገሪቱ በልጆቿ አለመግባባት የጦር ዓውድማ ሆና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎቿ በሁሉም የዓለም ማዕዘናት በስደት ተበትነዋል። ከተሞቿ በአሰቃቂ ሁኔታ ፈራርሰዋል። በአጠቃላይ አገሪቱ በቀላል የማይሽር ጠባሳ አርፎባታል። የመንም የዚሁ እውነታ ተጋሪ ናት። የብዙ አገሮች የመበታተን፣ የመፈራረስ፣ የሕዝብ ዕልቂትና ስደት መነሻው ይኼው ያለ መነጋገርና ያለ መደማመጥ አባዜ ነው፡፡
አስገራሚው ነገር ግን በርካታ መንግሥታት አስከፊ የመከራ ዝናብ ከወረደበቸው ከእነዚህ አገሮች ትምህርት መቅሰም ተስኗቸው፣ በፍጥነት ወደ እዚያው መንገድ እየተንደረደሩ መሆኑ ነው። ለዚህም በአሁኑ ወቅት ከባድ ግጭት እያስተናገደች የምትገኘውን ጎረቤታችን ሱዳንን በምሳሌነት ማንሳት ይቻላል። ይህ ሁሉ የሆነው መሪዎቹና የአገሪቱ ሊሂቃን ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ቁርጠኛ ሆነው መገኘት ባለመቻላቸው ነው። ሰሚም (አድማጭ) ሆነ ምላሽ ሰጪ በመታጣቱ… ነው።
በሌላ በኩል አንዳንድ አገሮች ካለፈው የተሳሳተ አካሄዳቸው ተፀፅተው፣ ትምህርት ቀስመውና ከደረሰባቸው አሰቃቂ መዓት ወጥተው በሁሉም መስክ ዓለምን ያስደመመ ለውጥ አስመዝግበዋል፣ እያስመዘገቡም ይገኛሉ። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የምትሆነው የመካከለኛ አፍሪካዊቷ አገር ሩዋንዳ ናት።
ሩዋንዳ እ.ኤ.አ. በ1994 አጋጥሟት ከነበረው የዘር ማጥፋት ወንጀልና ደም አፋሳሽ የእርስ በርስ ጦርነት በመውጣት ትክክለኛ አቅጣጫ ይዛ ወደፊት መስፈንጠር የቻለችው በደሎችን በመናዘዝ፣ ይቅር በመባባል፣ እንዲሁም የሕዝቡን አብሮነት የሚሸረሽሩ፣ እርስ በርስ የሚያቃቅሩና የሚከፋፍሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥተው በመሥራታቸው ነው።
ከዚህ አኳያ በ1994 ዓ.ም. ከተፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል በኋላ፣ ሩዋንዳ ውስጥ ማንም ሰው ሌላውን ‹‹ጎሳህ ምንድነው?›› ብሎ እንዳይጠይቀው በሕግ መከልከልን ጀምሮ ወሳኝ ፖለቲካዊ ዕርምጃዎችን በመውሰዳቸው፣ ዛሬ አገሪቱ ብሔርን መሠረት ካደረገ ጥላቻና ግጭት ነፃ ሆናለች፡፡ ብሔራዊ አንድነትን (Social Fabric) በመፍጠር ጠንካራ አገር ለመገንባት የሚያስችል ፅኑ መሠረት ጥላለች። ለዚህ ምንም የተለየ ሚስጥር የለውም። ከደረሰው የዘር ፍጅት ጭፍጨፋ በመነሳት የጋራ ጉዳያቸውን ሰከን ብለው በጠረጴዛ ዙሪያ የመነጋገራቸውና የመወያየታቸው ውጤት ነው።
ጀርመኖችና ጃፓኖችም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ከደረሰባቸው ውድመትና ጥፋት ተምረው ዛሬ የሚገኙበት ትልቅ ደረጃ ላይ የደረሱት፣ ውይይትና ንግግርን መሠረት ያደረገ አዲስ የፖለቲካ መስመር በመምረጣቸው ነው። በቁጭትና በእልህ ወደ ሠለጠነና ዘመኑን ወደ ዋጀ የፖለቲካ ምዕራፍ በመሸጋገራቸው ነው።
ዛሬ በዴሞክራሲ ስኬታቸው በተምሳሌትነት የሚጠቀሱት አሜሪካን ጨምሮ አብዛኞቹ ምዕራባውያን አገሮች አሁን ያሉበት ከፍታ ላይ የደረሱት በአጋጣሚ ሳይሆን አንድም የውይይት፣ ተነጋግሮ የመግባባት፣ በምክንያት የመሞገትና አገርን ሊያበለፅጉ የሚችሉ አማራጭ ሐሳቦችን የማመንጨት አቅማቸው የዳበረ በመሆኑ፣ አንድም እነዚህን ሁኔታዎች እንደ ምቹ መደላደል ተጠቅመው ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ወታደራዊ አቅማቸውን በማሳደጋቸው ነው። በዚህም ምክንያት የዴሞክራሲ ባህል እንዳልዳበረባቸው አገሮች ለተለያዩ ቀውሶችና አለመግባባቶች ሲጋለጡ ማየት አልተለመደም።
የመነጋገር፣ የመመካከር፣ የመቻቻልና የመተባበር ባህል ለእኛ (ለኢትዮጵያውያን) አዲስ ነገር እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ ማኅበረሰቡ ችግሮች ሲያጋጥሙት የሚፈታባቸው ለዘመናት የቆዩ ባህላዊ ሥርዓቶች አሉት። ችግሮችን በባህላዊ ዕርቅና ሽምግልና ሥርዓት በመነጋገር ማብረድና መቋጨት ለዘመናት የቆየ የአባቶቻችን እሴት ነው። እንደ አውጫጭኝ፣ አፈርሳታ፣ ሌባሻይና ሸንጎ የመሳሰሉ የግልግልና የዕርቅ ሥርዓቶችን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል። እነዚህ እሴቶች በተለይ ዘመነኛው (Contemporary) የፍትሕ ሥርዓት በቀላሉ ተደራሽ ባልነበረባቸው ገጠራማው የአገራችን ክፍሎች፣ ሰላማዊና ጤናማ ማኅበራዊ ግንኙነት እንዲኖር በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና ነበራቸው።
በሌላም በኩል ሕዝቦቿ በተደጋጋሚ የተቃጣባቸውን የውጭ ወረራ እምቢኝ አሻፈረኝ ብለው በጋራ በመመከት የአይበገሬነትና የነፃነት ተምሳሌት መሆን ችለዋል። የፍቅር፣ የመቻቻል፣ እንዲሁም የአብሮነት እሴት ባለቤቶች ስለመሆናቸውም አብሮ ሲመሰከርላቸው ቆይቷል።
‹‹በእጅ የያዙት ወርቅ እንደ መዳብ ይቆጠራል›› ሆኖብን፣ አሁን አሁን ይህንን ባህልና ትውፊታችንን አክብረን ከመያዝ ይልቅ ያቀለልነው ይመስላል፣ ዋጋው አንሶብናል፡፡ ሥጋቶችንም ሆነ ችግሮችን በሰከነ ውይይትና መደማመጥ እንዲፈቱ የማድረግ ባህላችን ተመናምኗል፡፡ ይህም በመሆኑ ‹‹ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል›› እንዲሉ፣ በእጃችን ላይ ያሉ አኩሪ እሴቶቻችንን ተጠቅመን የአገሪቱን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮቻችንን በቀላ መፍታት እንዳንችል አድርጎናል፡፡
ኢትዮጵያ የረዥም ዘመን ታሪክ ባለቤት እንደ መሆኗ በርካታ መልካምም መጥፎም ታሪክ ያሳለፈች አገር ናት፡፡ በእነዚህ ሒደቶች ውስጥ አንዳንዴ ያጋጠሟትን ችግሮች መፍታት በመቻሏ (ለዚህ አስረጂነት የዓድዋን ድል መጥቀስ ይቻላል) የአሸናፊነትና የጥንካሬነት ምሳሌ ሆና እንድትታይ ያደረጋት ሲሆን፣ በሌላ ወቅት ደግሞ ዜጎቿ ያላቸውን ልዩነት አጥብበውና አቻችለው ለተሻለች ኢትዮጵያ መፈጠር በደንብ ስላልሠሩ አገሪቱ ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ ደርሶባታል። ወደ ተሻለ የዕድገት ደረጃ ለመሸጋገር እንችልባቸው የነበሩ ብዙ ወርቃማ ዕድሎችም ዳር ሳይደርሱ መክነው ቀርተዋል።
በተለይ ከ1960ዎቹ ወዲህ ባሉ የተለያዩ ጊዜያቶች ተስፋ ሰጪ ዕድሎች አጋጥመውን የነበረ ቢሆንም፣ እነዚህን ዕድሎች በአግባቡ መጠቀም ባለመቻላችን ዕድገታችን ከመሻሻል ይልቅ እንደ ግመል ሽንት ወደኋላ እየተጓዘ እዚህ ደርሰናል። ያጋጠሙንን ዕድሎች እንዲጨናገፉ ያደረጉ ብዙ ምክንያቶች አሉ። ከእነዚህም መካከል የተለያየ ጥያቄ (ፍላጎት) ባላቸው የፖለቲካ ኃይሎች ለዘመናት ሲነሱ በነበሩ ጥያቄዎች ዙሪያ ጥልቅ ውይይት አድርጎ የጋራ መግባባትና መተማመን መፍጠር የሚያስችል (ምቹ መደላድል) መፍጠር አለመቻል አንደኛው ነው።
የሌላውን ሐሳብ ከማድመጥ ይልቅ፣ ‹‹እኔ ያልኩት ይሁን፣ የእኔ ፍላጎት ይፈጸምልኝ፣ እውነትም መንገድም እኛ ነን፣ አዳኝና መፍትሔ ሰጪዎቹ እኛ ብቻ ነን›› የሚለው ሰንካላ አስተሳሰብ ሥር መስደዱም ሌላው ምክንያት ነው። በዚህ ላይ ሰጥቶ የመቀበል የዳበረ ተሞክሮ (Trend) የለንም። የራስን ሐሳብ ሌላው ላይ መጫን እንጂ በምክንያት መከራከርና ሌሎችን ሐሳብ የማስተናገድ ባህል አልዳበረም። ይህንን ዕውቁ ባለቅኔ ፀጋዬ ገብረ መድኅን ‹‹እናት ዓለም ጠኑ›› በሚለው ቴአትሩ፣ ‹‹የእኛ ሰው አመሉ ቀልተናል ቅሉ፣ ጠልተናል ጥሉ፣ በልተናል ብሉ›› ብሎ በግጥም ስንኙ ለማስተላለፍ በሞከረው ቁምነገር በደንብ ተገልጿል።
ችግሩ ይህ ብቻ አይደለም። ዕድል ገጥሟቸው ወደ ሥልጣን መንበሩ በመጡ ገዥ ፓርቲዎችና በተቃውሞው ጎራ በተሠለፉ ኃይሎች መካከል ያለውም ግንኙነት ጤናማ የሚባል እንዳልሆነ በተለያየ አጋጣሚ ታይቷል። ግንኙነታቸው በአብዛኛው በሴራ፣ በመጠላለፍ፣ በመካሰስ፣ አንዱ ለአንዱ የመቀበሪያ ጉድጓድ በመማስ ላይ ያተኮረና ያመዘነ ነው።
ሥልጣን የጨበጡት የፖለቲካ ተዋንያን የሚያራምዱትን ፖሊሲና አቋም የሚተች/የሚገዳደር አካል በዋዛ አይታለፍም። ትችቶችንና ምክንያታዊ አስተሳሰቦችን በመመርመር ገዥውን ሐሳብ አንጥሮ በማውጣት ያለውን ችግርና ክፍተት ከመሙላት ይልቅ፣ ‘ከእኔ (እኛ) በላይ ዕውቀት ለአሳር ነው’ በሚል መታበይ የሐሳቡን ባለቤቶች ሥልታዊ በሆነ ዘዴ ጥግ ማስያዝ፣ ማናናቅ፣ ባስ ካለም በኃይል ማሸማቀቅና ዝም ማሰኘት የአብዛኛው የፖለቲካው ልሂቃን ዋና መለያ (Trend) ነው።
‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› ሆኖ የትግላቸው ዓላማ ዴሞክራሲያዊ እንዲሰፍን ማድረግ እንደሆነ በሚናገሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሠፈርም ያለው የውይይትና የንግግር ባህል ያን ያህል የዳበረ የሚባል አይደለም። የሐሳብ ልዩነቶችን ተፈጥሯዊ አድርጎ መገንዘብ ካለመቻል አንስቶ እስከ ውስጣዊ ሽኩቻና ክፍፍል፣ ከመካሰስ ቂም እስከ መያያዝ የጠብና የቅራኔ ምንጮች ሲሆኑ በተደጋጋሚ አስተውለናል፡፡ ይህ ነው የንግግርና የምክክር ፀር ሆኖ እዚህ የዘለቀው።
የሚገርመው ሁሉም ፖርቲዎች (ሥልጣንና መንበሩን የያዙትን ጨምሮ) ያለመታከት ስለዴሞከራሲ ያነበንባሉ፣ ዴሞክራሲን ይሰብካሉ፣ ዘወትር ስለዴሞክራሲ ትሩፋት ይቃኛሉ። ሆኖም ‹‹ከበሮ ሲያዩት ያምር ሲይዙት ያደናግር›› እንዲል ተረቱ፣ አማላይ ንግግራቸው መሬት ላይ ካለው ነባራዊ ሀቅ ጋር አልጣጣም እያለ አገራችንን ብዙ ዋጋ እንድትከፍል አድርጓታል፣ እያደረጋትም ይገኛል። ለምሳሌ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ፣ የመሰብሰብ፣ የመደራጀትና ሰላማዊ ሠልፍ የማድረግ መብት… ዛሬም እንደ አገር ብሎም እንደ ትውልድ የሚያሳስቡንና የሚያጨቃጭቁን ጉዳዮች ናቸው።
ለበርካታ አሠርት ዓመታት ሲያጨቃጭቁና ሲያወዛግቡ የነበሩ፣ ሕዝቡ ጠይቋቸው ሳይመለሱ የቀሩ ችግሮች፣ እንዲሁም ከትናንት ተንከባለው ዛሬም የዘለቁ አገራዊ ጉዳዮች አሁንም ዋነኛ የመነታረኪያ፣ የግጭትና የክፍፍል አጀንዳዎች እንደሆኑ ቀጥለዋል።
አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የሰላም፣ የፍቅር የመልካምነት፣ አብሮ የመኖር እሴቶቻችንን… ትተን አትምጣብኝ አልመጣብህም እየተባባልን እንገኛለን። ልጆቻችንን የጥላቻ፣ የጎሰኝነትና የዘረኝነት ትርክት እየቀለብናቸው ለጥላቻና ለፀብ እየገፋናቸውና እያዘጋጀናቸው ነው። ይህ አልበቃ ብሎ ምክንያት እየተፈለገ በየቦታው እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ የሰው ሕይወትና ንብረት በመጥፋት ላይ ነው፡፡ በርካታ ዜጎች
ያለ ማቋረጥ እየተፈናቀሉና እየተሰደዱ ይገኛሉ። የዜጎች መታፈን የዜጎች መታገት እየጨመረ መጥቷል። በየአካባቢው ግጭቶችና ውጊያዎች ተበራክተዋል፡፡ በሰላም ወጥቶ መግባቱ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል። በዚህ ላይ በማንስማማባቸው ጉዳዮች ላይ ተነጋግረን እንዳንግባባና ሰላም እንዳናገኝ ላይና ታች እያሉ የሚገኙ የግጭት ነጋዴዎች እኩይ ሴራም፣ በነበሩ የፀጥታ ችግሮች ላይ ሌላ ተጨማሪ ሥጋት ደቅኗል።
ለዚህ ሁሉ የዳረገን በሐሳብ ልዕልና ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ሥርዓት አስተማማኝ በሆነ መንገድ አለመዘርጋቱና ከአሮጌው የቆየ አስተሳሰብ የዞረ ድምር መላቀቅ አለመቻላችን ነው። ሕዝብን እያሸበሩና አገርን እየናጡ ያሉት ችግሮች በዝምታ ያለፍናቸውና በመነጋገርና በመመካከር መፍትሔ ያልሰጠናቸው እንከኖች ናቸው፡፡
ስለሆነም አገራችን ከገጠማት ችግር ለመውጣት ቁልፉ ነገር ካለንበት ጥልቅ ዝምታና የአለመተማመን ስሜት ወጥተን፣ በአገራዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ ስለነጋችን የሰከነ ውይይትና ምክክር ማድረግ ነው።
በታሪክ ላይ ያሉን የተዛቡ አመለካከቶችንና በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉ ቅራኔዎችን መፍታት የሚቻለውና ጥላቻዎች የሚሻሩት፣ በጠረጴዛ ዙሪያ ተመካክሮና ተማምኖ አገራዊ መግባባት ላይ መድረስ ሲቻል ብቻ ነው። በአሁኑ ጊዜ በእጃችን ያለው ብቸኛ መፍትሔ ይኼ በመሆኑ ዕድሉን በብልኃት፣ በጥበብና በአርቆ አሳቢነት ልንጠቀምበት ይገባል። ከዚህ ውጪ የሆነ ሌላ መንገድና መፍትሔ አለ የሚል እምነት የለኝም። ከዚህ አንፃር ተስፋ ከተጣለበት የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን በርካታ የምንጠብቀው ነገር አለ።
ስለሆነም በጉጉት የምንጠብቀው አገራዊ ምክክር የተሳካ እንዲሆን ግጭትንና አለመግባባቶችን ከሚፈጥሩ ትርክቶችና አሉባልታዎች መራቅ፣ የጋራ ችግሮቻችንን ለመፍታት ለዘመናት ስንጠቀምባቸው የኖርነውንና አሁን እየተዘነጉ የመጡትን ነባር ባህላዊ እሴቶቻችንን ፈጠራ በታከለበት መንገድ ለአገራዊ ምክክሩ ውጤታማነት እንደ አስፈላጊነቱና እንደ ተጨባጭ ሁኔታው ሥራ ላይ ማዋል፣ እንዲሁም ለሥልጡን የፖለቲካ ሒደት ራሳችንን ማዘጋጀት ያስፈልጋል።
ከሁሉም በላይ ግን መንግሥት በየቦታው የሚፈጠሩ ግጭቶችንና ብጥብጦችን ከአሁኑ በበለጠ እንዲረግቡ በማድረግ ኃላፊነቱን መወጣት፣ እንዲሁም ኮሚሽኑ ፖለቲካዊ ችግሮቻችንን በአካታች አገራዊ ምክክር ለመፍታት ለሚያከናውነው መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ አስፈላጊ ግብዓቶችን በማሟላት ምቹ መደላድልና ምኅዳር መፍጠር የበለጠ ይጠበቅበታል።
ቸር እንሰንብት!
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡