Saturday, September 23, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊአደጋ የተደቀነባቸው የአገር በቀል ሕክምና ዕውቀትና ዕፀዋቱ

አደጋ የተደቀነባቸው የአገር በቀል ሕክምና ዕውቀትና ዕፀዋቱ

ቀን:

የዓለም ጤና ድርጅት መሪ ቃል ‹‹ጤና ለሁሉም›› ነው፡፡ ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ በዘመናዊ ሕክምና ብቻ የሚቻል ባለመሆኑ ዘመናዊውን ከባህላዊው ሕክምና ጋር አስተሳስሮ መንቀሳቀስ እንደሚገባ ያሳስባል፡፡ ይህ ዓይነቱን እንቅስቃሴ የተከተሉ ታላላቅ አገሮች ውጤታማ ሆነዋል፡፡ በኢትዮጵያ አሁን ያለው ሁኔታ ግን ገና ጅማሮ ላይ ነው፡፡

ዘመናዊውንና ባህላዊውን ሕክምና በአንድነት አስተሳስረው በመንቀሳቀሳቸውና ከፍተኛ ውጤት ከተቀዳጁት አገሮች መካከል ቻይና በግንባር ቀደምትነት ትጠቀሳለች፡፡ በዚህች አገር 40 ከመቶ የጤና ሽፋን ባህላዊ ሲሆን፣ 60 ከመቶ ያህሉ ደግሞ ዘመናዊ ነው፡፡ እያንዳንዱ የጤና ተቋም የባህል መድኃኒት ዲፓርትመንት አለው፡፡ ከ30,000 በላይ የትምህርት ተቋማትም በባህል ሕክምና ዘርፍ ሥልጠና ይሰጣሉ፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ መምህርና ተመራማሪ ኤርምያስ ልዑለቃል (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ዘመናዊ ሕክምና መነሻው ባህላዊ መድኃኒት ነው፡፡ ይህም ሆኖ ግን በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ሲታይ በዘርፉ ሥልጠና የሚሰጥ ተቋም የለም፡፡ በባህል ሕክምና ዙሪያ የሚታየው ትልቁ ክፍተትም ይኸው ነው፡፡

ከዚህም ሌላ ከባህል ሕክምና ጋር ተያይዞ ብዙ ተግዳሮቶች እንዳሉ፣ ከነዚህም አብዛኞቹ የዕውቀቱ ባለቤቶች በዕድሜ መግፋት የተነሳ በሞት እንደተለዩ፣ ለባህል መድኃኒት የሚያገለግሉ ዕፀዋት በምንጣሮ እየጠፉ እንደመጡ ነው የተናገሩት፡፡

‹‹የአገር በቀል የሕክምና ዕውቀት ለጤናው ዘርፍ ያለው አስተዋጽኦ›› በሚል ርዕስ በሳይንስ ሙዚየም አዳራሽ በተከናወነው ዓውደ ጥናት ኤርምያስ ልዑለቃል (ዶ/ር) እንዳብራሩት፣ በኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ያሉት የመድኃኒታዊ ዕፀዋት ብዛት 1,320 ሲሆኑ ከእነዚህም መካከል 80 ከመቶ ያህሉ የሚሰበሰቡት ከጠፋ ወይም ከበረሃማ አካባቢ ነው፡፡ 30 በመቶ የሚሆነው ሰው ደግሞ የሚጠቀመው የዕፀዋቱን ሥር ሲሆን፣ በዚህም ዕፀዋቱን ገድለው ተጠቃሚዎቹ ግን እንደሚድኑ ወይም ካደረባቸው በሽታ እንደሚፈወሱ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

‹‹እኔ በምሠራበት ክፍል በሁለተኛና በሦስተኛ ዲግሪ የባህል መድኃኒት ዕውቀትን ለትውልድ የማትረፍ ሥራ እየተከናወነ ሲሆን፣ ክንውኑም እየተካሄደ ያለው ከሌሎች ተቋማት ጋር በመተባበር ነው፡፡ በዚህም ዕፀዋትን መሰነድ ጀምረናል፡፡ የመጠበቅና የጠፉትንም የማዳን ሥራ እያካሄድን ነው፤›› ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ በባህል መድኃኒት ዙሪያ በርካታ ዕውቀቶችና ዕፀዋት እንዳሉ፣ ነገር ግን ሳይመዘገቡና ጥቅም ላይ ሳይውሉ ባለዕውቀቶች እያለፉና ዕፀዋቱም እየጠፉ መሆኑን ኤርምያስ (ዶ/ር) ገልጸው፣ ይህቺ አገር ይኼን ሁሉ ምሁር አፍርታና ይኼ ሁሉ ተቋም መሥርታ ጥቅም ላይ ሳይውል ቢቀር ከትውልድ ወቀሳ ማምለጥ እንደማይቻል አስረድተዋል፡፡

‹‹የባህል ሕክምና ዕውቀትን አስመልክቶ የተሰነዱ በርካታ የብራና ጽሑፎቻችን በተለያዩ ምክንያቶች አጥተናቸው ከአገር ወጥተዋል፡፡ አብዛኞቹም በጀርመንና እንግሊዝ አገሮች ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ የእኛ የነበሩ አሁን ግን የእኛ አይደሉም፡፡ ልናስመልሳቸውም አንችልም፤›› ያሉት ደግሞ በአዲስ አበባ የዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስን ኮሌጅ የፋርማሲ ትምህርት ቤት መምህርና ተመራማሪ አርአያ ሀይመት (ፕሮፌሰር) ናቸው፡፡

የባህል ሕክምና አዋቂዎች በአብዛኛው በዕድሜ የገፉ አባቶችና እናቶች ሲሆኑ፣ ነገር ግን ዕድሜ እየከዳቸውና እያጣናቸው እንደሆነ፣ የሕዝባችንም ቁጥር ከ120 ሚሊዮን በላይ እንደሆነና ይህን ሕዝብ ለመመገብ ደግሞ የእርሾ ቦታዎች እየተስፋፉ እንደመጡ፣ በዚህም ደኖች እየመነጠሩ፣ ለማገዶነትና ለቤት መሥሪያነት የሚውሉ ብቻ ሳይሆን ለመድኃኒትነት የሚውሉ ዕፀዋትም አብረው እየጠፉ እንደሆኑ ነው የተናገሩት፡፡

‹‹የባህል ሕክምና አዋቂዎችና የባህል መድኃኒት ግብዓቶች እየጠፉ ከሆነ ስለባህል ሕክምና ጠቃሚነትና አስፈላጊነት መነጋገሩ ለእኔ ፋይዳ የለውም፡፡ ዕውቀቱ የሚተላለፍበትም ትምህርት ቤት አልተከፈተም፡፡ ወይም መንገዱ አልተመቻቸም፣ ያለውን ትንሽ ዕውቀትም ቢሆን ልጆች ሊቀበሉ የሚችሉበት አጋጣሚ ስላልተፈጠረላቸው የመቀበል ፍላጎት የላቸውም፡፡ በዚህም የተነሳ ዕውቀት እየጠፋ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለዓለም ጭምር የሚያገለግል የባህል መድኃኒት ላይ ትኩረት ያደረገ ዕውቀት እንዳላት፣ እየጠፋ ያለው ይህ ዕውቀት በጊዜው ሊያዝ፣ ሊሰነድና ለትውልዱ ማስተላለፉና ዕፀዋቱንም ማትረፍ ካልተቻለ አገሪቷ ብቻ ስትሆን ዓለምም ጭምር እንደሚጎዳ መታወቅ እንደሚኖርበት ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

በኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የአገር በቀል ሕክምና ተመራማሪ አስፋው ደበላ (ዶ/ር)፣ ከኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል 80 ከመቶ በላይ የሚሆነው ለሰው፣ ከአርብቶ አደሩ ማኅብረሰብ ደግሞ 90 ከመቶ የሚሆነው ለእንስሳት የባህል መድኃኒት እንደሚጠቀም፣ የባህል መድኃኒቶቹም የሚገኙት ከዕፀዋት፣ ከእንስሳት፣ ከማዕድናት አስተዋጽኦ እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡

የባህል ሕክምናን ወደ ዘመናዊ መንገድ ለማምጣት ከተፈለገ ምርምር ማካሄድ እንደሚያስፈልግ፣ ለዚህም ዕውን መሆን ዕውቀትንና አዋቂዎችን ማለትም የጥበብ አባቶችንና ማኅበረሰቡን ማሰባሰብና ዕውቀቱን መሰነድ፣ የዕፀዋቱን ሳይንሳዊ ስምን መለየት፣ ፍቱንነቱንና ደኅንነቱን በቅድመ ክሊኒካል ጥናት ማረጋገጥ፣ ከዚያም በእንስሳትና ሰው ላይ መሞከር እንደሚያስፈልግ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

እንደ አስፋው (ዶ/ር) ማብራሪያ፣ ማኅበረሰቡ የባህል ሕክምናን በብዛት እንዳይጠቀም ያደረጉት በርካታ ምክንያቶች አሉት፡፡ ከምክንያቶቹም መካከል አንደኛው በባህል መድኃኒት/ሕክምና ዙሪያ ላይ ያተኮረ ፖሊሲ ቢኖርም እስካሁን ግን አለመተግበሩ፣ መድኃኒትን አስመዝግቦ የማውጣት ጥረት ደካማ መሆን፣ በላቦራቶሪ የተደረገና በክሊኒካል የተጀመረው ጥናት አናሳ መሆን ይገኙበታል፡፡

ፋብሪካዎች የባህል መድኃኒትን የማምረት ፍላጎትና ለምርምር የሚውል በቂ ገንዘብ አለመኖር፣ በዚህም የተነሳ በተመራማሪዎች ዘንድ ፍላጎት ማጣት፣ ቅንጅትና ተባብሮ መሥራት ላይ ውስንነት መታየት ከምክንያቶቹ መካከል ተጠቃሽ እንዲሆኑ ነው የጠቆሙት፡፡

ከአስፋው (ዶ/ር) ማብራሪያ ለመረዳት እንደተቻለው፣ በኢትዮጵያ ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች፡፡ ባሉት ልክ የዘመናዊ ሕክምና ተደራሽነት ውስን ነው፡፡ በባህል ሕክምና ዙሪያ ያለውን እምቅ ሀብት በምርምር አስደግፎ ሥራ ላይ እንዲውል ቢደረግ ከኢትዮጵያ አልፎ ለሌሎችም አገሮች አስተዋጽኦ ማድረግ ይቻላል፡፡

የባህል ሕክምና የራሱ የሆነ ፍኖተ ካርታና ስትራቴጂ (የአፈጻጸም ስልቶች) እንዳሉት፣ ከእነዚህም መካከል የፍኖተ ካርታው ዋናው ዓላማ ደኅንነቱና ፍቱንነቱ የተረጋገጠ የባህል ሕክምና በሳይንሳዊ ፎርም ተደግፎ ማኅበረሰቡ እንዲጠቀምበት ማድረግ ነው፡፡ ለዚህም ዕውን መሆን ፍኖተ ካርታው ከሁለት ዓመት በፊት ፀድቆ ትግበራ ላይ ግን እንዳልዋሉ ነው የተናገሩት፡፡

የአፈጻጸም ስልቶቹም ዕውቀቶችና ልማዶች ተመዝግበው የሚቆዩበት፣ ምርምርና ሥርዓት የሚከናወኑበት፣ ለጤናና ለኢኮኖሚ ጠቀሜታ ሲባል ወደ ገበያ የሚወጣበት፣ የአዕምሮአዊ ሀብት ንብረት ለባህል ሕክምና አዋቂዎች የሚሰጥበት መሆኑን አስፋው ደበላ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...