በሰላማዊት መንገሻ
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በመንግሥት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና አስተዳደር ላይ ባተደረገው የክዋኔ ኦዲት፣ ከኦሮሚያ ክልል የተለያዩ የመንግሥት ተቋማት የተሰባሰበ 1.4 ቢሊዮን ብር የሠራተኞች የጡረታ መዋጮ ለአስተዳደሩ ገቢ አልተደረገም ማለቱ ውዝግብ ፈጠረ፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የክትትል ኦዲት ቡድን በሰኔ ወር ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው ሪፖርት ለመንግሥት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና አስተዳደር፣ በኦሮሚያ ክልል ፋይናንስ ቢሮ ተሰብስቦ ገቢ ያልተደረገ 1.4 ቢሊዮን ብር የጡረታ መዋጮ መኖሩን አስታውቆ ነበር፡፡
በሪፖርቱ ላይ እንደተገለጸው የአስተዳደሩ የሥራ ኃላፊዎች ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ በኦዲቱ መሠረት ገንዘቡን ለማስመለስ ጥረት ቢደረግም፣ የኦሮሚያ ክልል ፋይናንስ ቢሮ ገንዘቡ የአስተዳደሩ አለመሆኑን መልስ መስጠታቸውን ገልጿል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ፋይናንስ ቢሮ በበኩሉ የባንክ የሒሳብ ቁጥሩ የተከፈተው ለአስተዳደሩ አገልግሎት ብቻ የሚውል ሳይሆን፣ አጠቃላይ ሥራውን ለማስኬድ የሚጠቀምበት መሆኑን ለሪፖርተር ገልጿል፡፡
በአስተዳደሩ የጡረታ መዋጮ ገቢ ዳይሬክተር አቶ ሙሉብርሃን ካሳ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በኦሮሚያ ክልል ያለውን የጡረታ ገቢ ለመከታተል የራሱን ባለሙያዎች አሰማርቶ ከረዥም ዓመታት በፊት ተንከባሎ የመጣ 209 ሚሊዮን ብር ብቻ ተገኝቷል፡፡
‹‹የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በኦዲት ክትትል አገኘሁት ያለው 1.4 ቢሊዮን ብር የኦሮሚያ ክልል ፋይናንስ ቢሮ ለጡረታ መዋጮ የሚሰበሰብበት የሒሳብ ቁጥር ውስጥ የተገኘ በመሆኑ ብቻ፣ የአስተዳደሩ ገንዘብ ነው በማለት እንድንሰበስብ የክትትል ኦዲት ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፤›› ሲሉ አቶ ሙሉብርሃን ገልጸዋል፡፡
አቶ ሙሉብርሃን አክለውም፣ ለጡረታ የሚሰበሰብበት አካውንት ውስጥ መገኘቱን እንጂ ገንዘቡ የአስተዳደሩ መሆኑ ማረጋገጫ የለም ብለዋል።
ባለበጀት ተብለው የሚጠሩ መሥሪያ ቤቶች የጡረታ መዋጮ ገቢ የሚደረገው በክልሎች ፋይናንስ ቢሮ በኩል ተሰብስቦ መሆኑን፣ በፌዴራል ሥር ያሉት ደግሞ በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል መሆኑን አቶ ሙሉብርሃን ተናግረዋል፡፡
የዋና ኦዲተር ኦዲት ሪፖርት ላይ በድጋሚ በሪፖርቱ የተካተተበት ምክንያት ክትትል የሚደረግበት ሥርዓት ባለመኖሩ፣ አስተዳደሩ ገቢውን በትክክል ሳይሰበስብ እንዳይቀር ለማድረግ መሆኑን አክለዋል፡፡
‹‹ሥርዓት›› የሚባለው በየክልሉ የሚገኙ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሠራተኞቻቸውን የጡረታ መዋጮ ገቢ የሚያደርጉት ቀጥታ በሠራተኛው ስም ሳይሆን፣ በመሥሪያ ቤቱ በመሆኑ ከእያንዳንዱ ሠራተኛ በቀጥታ የሚቆረጠውን ጡረታ ወደ አስተዳደሩ የሚገባበትን ቴክኖሎጂ እንዲኖር በማስፈለጉ ነው ብለዋል፡፡
የጡረታ መዋጮ ውክልና ወስደው በሚሰበስቡ የክልል ፋይናንስና ኢኮኖሚ ቢሮዎችና ፌዴራል መሥሪያ ቤቶችን በሚሰበስበው ገንዘብ ሚኒስቴር አዋጅ መሠረት፣ በቀጣዩ ወር የመጀመሪያዎቹ የሥራ ቀናት ጀምሮ እስከ 30 ቀናት ድረስ ወደ ጡረታ ፈንድ መግባት እንዳለበት ይገልጻል፡፡
አስተዳደሩ ከክልሎችና ከፌዴራል የተሰበሰበውን ጡረታ መግባቱን ክትትልና ቁጥጥር የሚያደርጉ የኦዲት ባለሙያዎች በመላክ ክትትል ማድረግ እንደሚገባ አስተዳደሩ የሚተዳደርበት አዋጅ ይገልጻል፡፡
ጉዳዩን በተመለከተ ሪፖርተር ለፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የኦዲት ክትትል ቡድን ላቀረበው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ከኦሮሚያ ክልል የተሰበሰበ ገቢ አልተደረገም የተባለው 1.4 ቢሊዮን ብር መረጃ የመጣው ከራሱ ከአስተደደሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
‹‹ክልሉና አስተዳደሩ የራሳቸው ስምምነት ሊኖር ይችላል፡፡ የእኛ ተግባር ተቋሙ መሰብሰብ የነበረበትን አለመሰብሰቡን አግኝተን ሪፖርት ማድረግ ነው፤›› ብለዋል፡፡
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ በኦሮሚያ ክልል ፋይናንስ ቢሮ የሚገኙ ኃላፊ በበኩላቸው፣ ‹‹ከክልሉ የሚሰበሰብ ጡረታ የሚታወቅ ሒሳብ ነው፡፡ ከማን እንደተቆረጠና በየአንዳንዱ ዞንና ወረዳ ተሰብስቦ ገቢም ይደረጋል፡፡ ችግሮች ሲፈጠሩ ከአስተዳደሩ ጋር በመነጋር እያስታረቅን እንሄዳለን፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል በኩል ያልተከፈለ ሲንከባለል የመጣ የተወዘፈ የጡረታ መዋጮ የነበረ ቢሆንም፣ አስተዳደሩ ከእነ ወለዱ ጭምር እየጠየቀ ገቢ እንደሚደረግለት ተናግረዋል፡፡
ክልሉ ከአስተዳደሩ የደረሰው ምንም ዓይነት ቅሬታ አለመኖሩን በመግለጽ፣ ከዚህ በፊት በክልሉ የነበሩ ችግሮችን ከአስተዳደሩ ጋር መረጃ በመቀያየር እንዲስተካከል ማድረጋቸውንም አስረድተዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል በአጠቃላይ 21 ዞኖችና 340 ወረዳዎች ውስጥ 54 የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሚገኙ ሲሆን፣ በእነሱ ሥር 600 ሺሕ ሠራተኞች መኖራቸውን የክልሉ ፋይናስ ቢሮ መረጃ ይገልጻል፡፡
የመንግሥት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና አስተዳደር የመንግሥት ልማት ድርጅቶችን ጨምሮ ከ3,254 የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሥር ከሚገኙ 2.5 ሚሊዮን ሠራተኞች እስከ አራት ቢሊዮን ብር ድረስ በየወሩ ይሰበስባል፡፡
በአዋጁ መሠረት ከሲቪል ሠራተኛ የሚቆረጠው የደመወዝ የጡረታ መጠን ከሠራተኛው ሰባት በመቶ፣ ከአሠሪው 11 በመቶ፣ በአጠቃላይ 18 በመቶ፣ እንዲሁም በአዋጁ መሠረት ከመከላከያና ከፖሊስ የሚቆረጠው የደመወዝ ጡረታ 40 በመቶ መሆኑ ይታወቃል።