የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና ወስደው ላላለፉ ተማሪዎች ዲግሪ ሲሰጡ ቢገኙ፣ ሕጋዊ ዕርምጃ እንደሚወሰድና ተሰጥቶ የተገኘው ዲግሪም የሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ በሚዳኝበት መንገድ እንደሚታይ የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የትምህርት ሚኒስቴር በመጪዎቹ ዓመታት የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል እየወሰዳቸው ካሉ ጠንካራ ዕርምጃዎች መካከል አንዱ ነው ያለውን የመውጫ ፈተና (Exit Exam)፣ ለተመራቂ ተማሪዎች ባለፈው ሳምንት መስጠቱ ይታወሳል፡፡
በሁሉም የመንግሥትና የግል የከፍተኛ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰጠውንና ከሰኔ 30 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ለተከታታይ ቀናት በተሰጠው የመውጫ ፈተና፣ 62 በመቶ የመንግሥትና 17 በመቶ የግል ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የማለፊያውን 50 በመቶና ከዚያ በላይ ማስመዝገባቸውን የትምህርት ሚኒስቴር ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡
ለዓመታት ትምህርታቸውን ሲማሩ የነበሩና የመውጫ ፈተናውን ወስደው የምረቃ ቀናቸውን እየጠበቁ የነበሩ፣ ነገር ግን የመውጫ ፈተናውን ያላለፉ ተማሪዎች ዕጣ ፈንታቸው ምን እንደሆነ ሪፖርተር ለትምህርት ሚኒስቴር ጥያቄ አቅርቧል፡፡
የሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አመለወርቅ ህዝቅኤል እንዳሉት፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከ2015 ዓ.ም. ጀምሮ ዲግሪ ለማግኘት መሥፈርት የሆነውን ፈተና ላለፉ ተማሪዎች ዲግሪ ሲሰጡ ከተገኙ ሕጋዊ ዕርምጃ ይወስዳል፡፡ ፈተናውን ያላለፉ ተማሪዎች ዲግሪውን ይዘው ከተገኙም እንደ ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ይቆጠራል ብለዋል፡፡
የማስፈጸሚያ መመርያ ወጥቶለት ለተካሄደው የመውጫ ፈተና ከተቀመጡ ከ150 ሺሕ በላይ ተማሪዎች መካከል 61 ሺሕ ተማሪዎች 50 በመቶና ከዚያ በላይ ውጤት ማምጣታቸውን የትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ የመውጫ ፈተናውን ያላለፉ ተማሪዎች ከጥር 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በተከታታይ በሚሰጡ የመውጫ ፈተናዎች እየተመዘገቡ ፈተና እንደሚወስዱ የገለጹት የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊዋ፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ፈተናውን ላላለፉ ተማሪዎች ዲግሪ የሚሰጡበት ምንም ዓይነት ምክንያት የለም ሲሉ አስረድተዋል፡፡
የትምህርት ሚኒስቴር የሐሰተኛ ትምህርት ማስረጃን በትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን በኩል እየተፈተሸ መሆኑን ኃላፊዋ ጠቁመው፣ አሁንም የመውጫ ፈተና ሳያልፉ ዲግሪ ይዞ የተገኘ ግለሰብ የሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ በሚስተናገድበት መንገድ ይስተናገዳል ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ የመውጫ ፈተና ያለፉ ተማሪዎች በደረሱበት ደረጃ በ‹‹ሌብል›› እየተመዘኑ ሰርተፊኬት መውሰድ የሚችሉበት ዕድል ስለመኖሩ ተናግረው፣ አሠራሩ ወደፊት እንደሚገለጽ አስታውቀዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት በተሰጠው የመውጫ ፈተና በተለይም የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ የታየው ውጤት፣ የትምህርት ሚኒስቴር ወደፊት ብዙ ሥራ እንደሚጠብቀው ማሳያ እንደሆነ አመለወርቅ አክለዋል፡፡