Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ለምርጫ ቦርድ ሰብሳቢነት ዕጩዎች ሲቀርቡ ምክክር እንዲደረግ...

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ለምርጫ ቦርድ ሰብሳቢነት ዕጩዎች ሲቀርቡ ምክክር እንዲደረግ ጥያቄ አቀረበ

ቀን:

  • ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽን አመቻቺነት የመንግሥት ተሿሚዎች እየገቡ እንደሆነ ጥቆማ ደርሶኛል አለ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ በጤና እክል ምክንያት ከኃላፊነታቸው ለመልቀቅ መወሰናቸውን ካስታወቁ በኋላ፣ ለሰብሳቢነት በዕጩነት የሚቀርቡ ግለሰቦችን ሊመከርበት እንደሚገባ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ለመንግሥት ጥያቄ አቀረበ፡፡

ቦርዱን ከአራት ዓመት በላይ ሲመሩ የቆዩት ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ከነሐሴ 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ከኃላፊነታቸው ለመልቀቅ መወሰናቸውን፣ ሰኔ 5 ቀን 2015 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ማሳወቃቸው ይታወሳል፡፡

የቦርድ ሰብሳቢዋ ከሥልጣናቸው የመልቀቃቸው ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቶ በኃላፊነታቸው መቀጠል የማይችሉ ከሆነ፣ መንግሥት በእሳቸው ቦታ ለመመደብ የሚያቀርባቸውን ዕጩዎች የጋራ ምክር ቤቱ ሊመክርበት እንደሚገባ፣ የጋራ የምክር ቤቱ ሰብሳቢ መብራቱ ዓለሙ (ዶ/ር) ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

- Advertisement -

የወ/ሪት ብርቱካን ከሥልጣን የመልቀቅ ጥያቄን በተመለከተ ከአፈ ጉባዔው ጋር ተደረገ ባሉት ምክክር፣ ሰብሳቢዋ ከመንግሥት የደረሰባቸው ጫና አለመኖሩንና ከሕክምና ከሄዱበት ሲመለሱ መቀጠል የሚችሉበት ሁኔታ ካለ እንዲቀጥሉ የሚል ሐሳብ መቅረቡን መረዳታቸውን ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ አዲስ ሹመት የሚከናወን ከሆነ ቦርዱን በሰብሳቢነት ለመምራት በዕጩነት የሚቀርበው ወይም የሚመረጠው ግለሰብ፣ ከማንኛውም የፖለቲካ ጫናና ግፊት ነፃ የሆነና ለምርጫ ጉዳይ ቅርበት ያለው እንዲሆን ምክር ቤቱ እንደሚፈልግ መብራቱ (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡

በተመሳሳይ የምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ ራሔል ባፌ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ከአራት ዓመታት በፊት የቦርዱ ሰብሳቢ ሆነው የተሾሙት ወ/ሪት ብርቱካን መመረጣቸው በፓርቲዎች ተቀባይነት የነበረው ጉዳይ ቢሆንም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተፎካካሪ ፓርቲዎችን ቀርቶ የብልፅግና ፓርቲን እንኳን ሳያማክሩ በግል ውሳኔያቸው እንዲሾሙ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡   

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ እንደሚያብራራው፣ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 102 መሠረት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሾማሉ፡፡ በአዋጁ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዕጩ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት ስም ዝርዝር ከሚመለምለው ገለልተኛ ኮሚቴ ከተቀበለ በኋላ፣ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ጋር በቀረቡት ዕጩዎች ላይ ምክክር እንደሚደርግ ያትታል፡፡ ይህ በአዋጁ ቢብራራም ከዚህ በፊት የነበረው አፈጻጸም ግን እንደዚህ አለመሆኑን ዋና ጸሐፊዋ ተናግረዋል፡፡

እንደ ምርጫ ቦርድና የሰብዓዊ መብቶች የመሳሰሉ የዴሞክራሲ ተቋማት ከተፅዕኖ ነፃ ሆነው እንዲመሠረቱ ቢጠበቅም፣ አገሪቱ አሁንም ከዚህ ችግር አለመውጣቷን ራሔል (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡ አክለውም ወ/ሪት ብርቱካን ከኃላፊነት ሲለቁ ቦርዱ ራሱን የቻለና ጠንካራ ሆኖ እንዲቆም መንግሥት የሚጠበቅበትን ባለመሥራቱና ሥራው በግለሰቦች ላይ በመንጠልጠሉ፣ አሁንም ሰው ሲለቅ ሥጋቱ ቀጥሏል ብለዋል፡፡ በግለሰቦች ላይ የመንጠልጠል አሠራር አዋጭ ስለማይሆን መንግሥት በቁርጠኝነት ዘላቂና ጠንካራ ተቋማዊ ግንባታ ላይ መሥራት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ መንግሥት ለቦርዱ አዲስ ሰብሳቢ በሚሾምበት ወቅት፣ በሚቀርቡ ዕጩዎች ላይ ተገቢ የሆነውን ምክክር ከፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጋር እንዲያካሂድ ጠይቀዋል፡፡

በተመሳሳይ ዜና የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን የአመቻቾች መረጣና ልየታ ላይ የመንግሥትና የገዥው ፓርቲ አካላት መሳተፋቸውን ለምክር ቤቱ ጥቆማ እየደረሰ እንደሆነ ራሔል (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡ ‹‹ለኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲና ለጋራ ምክር ቤቱ በስልክና በማኅበራዊ ትስስር ገጾች አማካይነት፣ የገዥው ፓርቲ ካድሬዎችና የቀበሌ ሊቀመንበሮች ጭምር ስማቸውና ኃላፊነታቸው ተጠቅሶ በአመቻችነት ለመሥራት እየገቡ ነው የሚል ጥቆማ ደርሷል፤›› ብለዋል፡፡

ገዥው ፓርቲ በዚህ ዓይነቱ ድርጊት ከመሳተፍና የታሪክ ተወቃሽ ከመሆን እንዲቆጠብ ዋና ጸሐፊዋ አሳስበዋል፡፡ ለእያንዳንዱ ፓርቲም ሆነ ለጋራ ምክር ቤቱ የደረሰውን አቤቱታ የጋራ ምክር ቤቱ የተጠቀሱት ቦታዎች ድረስ በመሄድ እንደሚያጣራ ጠቅሰው፣ ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑም ቅሬታውን አቅርበው አዎንታዊ ምላሽ ማግኘታቸውን ራሔል (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽነር ዮናስ አዳየ (ዶ/ር) ለዚህ ጉዳይ ማብራሪያ ሲሰጡ፣ ያጋጠመው አዎንታዊ እንጂ አሉታዊ ተደርጎ መወሰድ የለበትም ብለዋል፡፡ በአመቻችነት የመጡት ግለሰቦች ታስቦባቸውና ታቅዶባቸው አለመሆኑን የገለጹት ዮናስ (ዶ/ር)፣ አንዳንዶቹ ግለሰቦች ለማገዝ በሚልና ባለማወቅ ለመሳተፍ ጭምር የመጡ ስለመሆናቸው አብራርተዋል፡፡ ኮሚሽኑ የሚፈጠሩ ችግሮችና በየጊዜው እየተፈታ እንደሚሄድ ጠቁመው፣ የተፎካካሪ ፓርቲዎችም ቢሆን እያደረጉት ያለው ትብብርና አስተያየት በቀናነት የተሞላ መሆኑንና ለኮሚሽኑ ዕገዛ እያደረጉ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...