በጀማል ሙሐመድ ኃይሌ (ዶ/ር)
‹‹እንጀራ ሆነና – የሰው ቁም ነገሩ
አልቀበር አለ – የሰው ልጅ በአገሩ››…
ጥንታዊ ኢትዮጵያውያን እንጀራን ፈጥረዋል፡፡ ከደቃቋ ጤፍ እንጀራን በመጋገር በምግብነት ለመጠቀም በቅተዋል፡፡ ይህ ምጡቅ ችሎታን የሚጠይቅ ነው፣ አድርገውታልም፡፡ አዲስ የተገኘውን ሥልት ወይም ቀመር በመጠቀም፣ የዚያ የፈጠራ ውጤት (የእንጀራ) ተጠቃሚ መሆን ግን ከባድ አይደለም፡፡ ጤፍ በመዝራት ማምረት፣ ከዚያም ጤፍን መፍጨት፣ ማቡኳት፣ መጋገር፣ መብላት ነው፡፡ ሁሌም ከባዱ ነገር በተለየ መንገድ በማየት አዲስ ነገር ማምጣት ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ያለው ነገር ዕዳው ገብስ ነው፡፡
የሚያስገርመው ነገር የኖረውን ያህል ጊዜ ኖሮ፣ የጤፍ ወይም የእንጀራ ነገር ለኢትዮጵያውያን ዕዳው ገብስ አልሆን ማለቱ ነው፡፡ የድርቅ መከሰት ብዙ ፈተና አስከትሏል፣ እያስከተለም ነው፡፡ ክረምት ላይ እየዘለሉ የሚነጉዱት ወይም ዓመቱን ሙሉ የሚፈሱት ወንዞች ለድርቁ መላ ሊሆኑ አልቻሉም፡፡ ማለትም በተለየ መንገድ አስቦ፣ ወንዞቹን ወይም የከርሰ ምድር ውኃን ተጠቅሞ እህል ማምረት የሚያስችል መላ ማምጣት የሚችል ምጡቅ ችሎታ ያለው ሰው ጠፋ…፡፡
ያም ሆነ ይህ ኢትዮጵያውያን ለእንጀራ ያላቸው ፍቅር ተነግሮ የሚዘለቅ፣ ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም – አቶ ድርቅ ረሃብን በማስከተል እንጀራን ከመሶባቸው እያጠፋ የሚያስቸግርባቸው ጊዜ ጥቂት ባይሆንም፡፡ ከልክ ያለፈው ወይም ተነግሮ ሊያልቅ የማይችለው የእንጀራ ፍቅራቸው አንዱ ምንጭ፣ ምናልባትም ይሄው ጊዜ እየጠበቀ የመጥፋቱ መዘዝ ሊሆን ይችላል፡፡
ለማንኛውም ሐበሾች ለእንጀራ ያላቸውን ፍቅር በተገቢው መንገድ ለመግለጽ፣ ቃላት ጉልበትም – ውበትም እንደሚያጡ አትጠራጠሩ፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ እንጀራ የሁሉም የሕይወታቸው ዘርፍ መገለጫ የሆነ እስከሚመስል ድረስ በመወደሱ፣ የላቀ ደረጃ በመሰጠቱና በመንቆለጳጰሱ ጭምር ነው፡፡ እስኪ አንዳንዶቹን እያነሳን ለመመልከት እንሞክር፡-
‹‹እንጀራ ወጥቶለታል››
አንድ ሰው በኑሮው ስኬታማነት ከታየበት፣ ማለትም ትዳሩ ከተቃና፣ ጥሩ ገቢ የሚያገኝ ከሆነና ከኑሮ ጋር ያለውን ግብግብ በአሸናፊነት እየተወጣ ከሆነ፣ ‹‹እንጀራ ወጥቶለታል›› ይባላል፡፡ የዚህን አነጋገር ጉልበት ለማየት፣ ሰውየው ያለፈበትን የኑሮ ውጣ – ውረድ ልብ ብላችሁ እዩት፡፡ ቋሚ የገቢ ምንጭ ያለው ሥራ ላይ መሰማራትና ትዳር መመሥረት ከዚያም ሁለቱንም በስኬት መምራት በአጭር ጊዜ የሚገኝ አይደለም፡፡ አብዛኛውን ጊዜ በአንፃራዊነት ረዘም ባለ ጊዜ ውስጥ የሚገኝ ብቻ ሳይሆን፣ ውጣ – ውረድ ያለበት፣ ፅናትን የሚፈልግና ትዕግሥት የሚፈትን ሒደት ውጤት ነው፡፡ በመሀሉ መውደቅና መነሳት ያለበትና ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎች ሁሉ የሚያጋጥሙበት ነው፡፡
ይህ ሁሉ የኑሮ ግብግብ ከታለፈ በኋላ የተገኘው ውጤት የተገለጸው ግን በሁለት ቃላት ብቻ ነው -‹‹እንጀራ ወጥቶለታል›› በሚል፣ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ የሚያስደስት፣ የሚያኮራና ሌላው ሰው ሁሉ ቢያገኘው የሚፈልገው ወይም የሚመኘው የሆነው ይህ የኑሮ ስኬት የተገለጸው በእንጀራ ነው፡፡ እንጀራ የኑሮ ስኬትን ወካይ ሆኖ ነው የቀረበው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ እንጀራ ለመውጣት (ማለትም ሲጋገር ዓይኑ ሳያሞጨሙጭ ወይም አንድያውን ሳይነኮር ከምጣዱ ለመውጣት) የሚፈጅበት ጊዜ እጅግ በጣም ትንሽ ነው – የደቂቃዎች ጉዳይ፣ የቡኮውንም ጊዜ ብንጨምር ከ3 ወይም አራት ቀናት ያልበለጠ፡፡ ሆኖም አንድ ሰው ለዓመታት ጥሮና ግሮ ለማሳካት የቻለው የኑሮ ውጤት የደቂቃዎች ወይም በጣት የሚቆጠሩ ቀናት ውጤት በሆነው እንጀራ እንዲወከል ወይም እንዲገለጽ ነው የተደረገው፡፡
‹‹የማታ እንጀራ ይስጥህ፡፡››
አንዳንድ በዕድሜ የገፉ ሰዎች ወይም ለማኞች ሲመርቁ፣ ‹‹የማታ እንጀራ ይስጥህ›› የሚል ምርቃት አላቸው፡፡ ይህ ምርቃት ደግሞ ጭራሹን አቶ እንጀራ በሕይወት የመጨረሻ ዕድሜ ላይ የሚገኝ መልካም ሕይወት ወይም ከዚያ ካነሰም በሕይወት የመጨረሻ ዕድሜ ላይ የሚገኝ የምግብ ዋስትና መረጋገጥ መገለጫ ሆኖ እንዲቀርብ ነው ያደረገው፡፡ ከፍ ሲል የቀረበውን (‹‹እንጀራ ወጥቶለታል›› የሚለውን) የሚያስንቅ ነው – በወጣትነትም ሆነ በጎልማሳነት ወይም በአዛውንትነት ወቅት እንጀራ ቢወጣ ዋጋ ቢስ መሆኑን በተዘዋዋሪ የሚናገር ብሂል፡፡ አንድ ሰው በሕይወቱ ውጤታማ ወይም ስኬታማ ተደርጎ ሊቆጠር የሚችለው፣ እርጅና በቁጥጥሩ ሥር ባደረገው ወቅት፣ ለሚበላና ለሚጠጣው በአጠቃላይም ለኑሮው የሚያስፈልገው ነገር ሳይጓደልበት መኖርና ዕድሜውን መጨረስ በሚችልበት ሁኔታ ላይ መገኘት ነው የማታ እንጀራ በማለት የተገለጸው፡፡ ይህ አባባል በአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ ሰዎች በእርጅና ዘመናቸው ጧሪ የማጣት ችግርና ሥጋት እንዳለባቸው ወይም ቢያንስ – ቢያንስ የምግብ ዋስትናቸው የተረጋገጠ አለመሆን የሚያሳስባቸው መሆኑን ይናገራል፡፡ በዚህ ውስጥ ደግሞ ከሁሉም ነገር ትልቁ ፈተና ሆድ ነው፡፡ ሆድ የሚፈልገው ደግሞ ግልጽ ነው – እንጀራ!
‹‹እንጀራ ይውጣልህ››
ምርቃቱ ‹‹የማታ›› የሚለውን ትቶ፣ ‹‹እንጀራ ይውጣልህ›› ወይም ‹‹እንጀራ ይውጣልሽ›› በማለት ሊገለጽ ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ ከ‹‹ሀ›› እስከ ‹‹ፐ›› ያለውን ሁሉ የሚጠቀልል ነው፡፡ ከጉርምስናም ሆነ ከጉልምስና እስከ እርጅና ያለውን ጊዜ በሙሉ ጠቅልሎ የሚያስገባ ነው፡፡ ስለዚህም ከፍ ሲል ከተጠቀሰው ምርቃት ከፍተኛውን ደረጃ የያዘ ነው – ያንኛው ለእርጅና ዘመን የተለየ ትኩረት መስጠቱ እንደ ተጠበቀ ሆኖ፡፡
ከወደ ቅኔው መንደር ጎራ ስንል ደግሞ ለማታ እንጀራ እንዲህ በሚል ተቀኝቶለት እናገኛለን፡-
ለማለዳ ቁርስስ፣ ቡን (ቡና) ሲያውል አየነው፣
የሚያስቀና ለሰው፣ የማታ እንጀራ ነው፡፡
ይህ ቅኔ በሰሙ፣ የእራትን በላጭነት እየተናገረ፣ በወርቁ ግን በዘመነ እርጅና ቢያንስ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ ከፍ ሲል ደግሞ የተደላደለ ኑሮ መኖርና መምራት በሰው ሁሉ የሚያስቀና መሆኑን የሚያውጅ ነው፡፡
የዕድሜ መጨረሻ አካባቢ ያለው የሆድ ነገር ትልቅ ቦታ ተሰጥቶት፣ በእንጀራ ትርክት ውስጥ ትልቁን ቦታ ሲያገኝ፣ ከእርጅና በመለስ ባለው ዕድሜ ውስጥ ያለው የሆድ ነገር የተተወ ወይም የተረሳ ሊመስል ይችላል፣ ሀቁ ግን እሱ አይደለም፡፡ ከዚያው ከቅኔው መንደር እንጥቀስ፡-
ራሴን አሞኝ እያያችሁ፣
ምነው ሰከረ ትላላችሁ፣
አሁን ማን ሰጠኝ ለእኔ ጠጅ፣
እንጀራ አዞረኝ እንጂ፡፡
ግለሰቡ በዚህ ቅኔው፣ ያዞረው፣ ሊወድቅ የተወለጋገደው፣ ጠጅ ጠጥቶ በመስከሩ ሳይሆን፣ የሚበላው እንጀራ ባለማግኘቱ የመጣ ችግር መሆኑን ነው እየነገረን ያለው፡፡
ሐበሾች የሚተዳደሩበትን የሥራ መስክ ‹‹እንጀራዬ›› ብለው የሚጠሩበት አጋጣሚም አለ፡፡ የእንጀራ ውክልና የሚጋገረውና የሚበላው እንጀራ ከመሰላችሁ ተሸውዳችኋል፡፡ በ‹‹እንጀራዬ›› የተወከለው ‹‹ያ ሥራ ከሌለ የምንበላው ምግብ የለም›› ለማለት ከመሰላችሁም፣ ‹‹እንጀራዬ›› የወሰደው ውክልና የገባችሁ በግማሽ ነው፣ እናም በግማሽ ተሸውዳችኋል፡፡ ‹‹እንጀራዬ››፣ በአጠቃላይ ደመወዝን ወይም አጠቃላይ የገቢ ምንጭን ወክሎ ነው የቀረበው፡፡
የሰው ልጅ በኑሮ ሒደቱ ውስጥ የሚያጋጥመውን የኑሮ ትግልና ግብ – ግብ፣ በትግሉና በግብ – ግቡ የሚያጋጥመውን ሽንፈት፣ ከሽንፈቱ ሜዳ (ከራስ አገር ወይም አካባቢ) የሚደረግን ሽሽት፣ ወደ ሌላ ቦታ የሚደረግን ስደት፣ በተሰደዱበት አካባቢ ወይም አገር ኖሮ እዚያው መሞትን ጭምር ወክሎ አቶ እንጀራ የቀረበበት አባባልም አለ – ለዚያውም በግጥም ነዋ! መግቢያ ላይ ያለው ግጥም እንዲህ ይላል፡-
‹‹እንጀራ ሆነና – የሰው ቁም ነገሩ
አልቀበር አለ – የሰው ልጅ በአገሩ፡፡››
የኑሮን ጣጣውን፣ ውጣ ውረዱን፣ ግብግቡንና ‹‹እንካ ስላንትያውን›› ጭምር እንጀራ እንዲወክል አድርገው፣ ትርክታቸውን ‹‹የተቀኙት›› ሐበሾች፣ በእንጀራ ብሂላቸው የልጅነት ወይም የወጣትነት ዘመንን የዘነጉት እንዳይመስላችሁ፡፡ እንጀራ፣ የሐበሾች ሁለነገራቸው ሆኖ ነው የቀረበው ስላችሁ! (ማለቴ፣ እንጀራን ሁለነገራቸው አድርገው ነው ያቀረቡት)፡፡
‹‹የሚወጣ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል››
አንድ ወጣት በባህሪው ምሥጉንና በሥራው ታታሪ ከሆነ ‹‹የሚወጣ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል›› በማለት ያወድሱታል፡፡ ‹‹የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል›› የሚል ተለዋጭ አባባልም አላቸው፡፡ እዚህ ላይ ልብ ማለት ያለብን ጉዳይ እንጀራ የወከለው ስኬታማነትን ብቻ ሳይሆን፣ ጊዜን ጭምር ነው፡፡ ከፍ ሲል የነበረው ንፅፅር ተጋግሮ ከወጣ እንጀራ ጋር ነበር፡፡ እዚህ ግን ገና ካልወጣው ጋር ነው፡፡ ከምጣዱ ላይ ያለውን ሁኔታ በማየት/በማጥናት ብቻ የተሰጠ ድምዳሜ ነው፡፡ እናም ገና ከምጣዱ ላይ ያለ እንጀራ ነው – የወጣት ጥሩ ባህሪና ታታሪነት መገለጫ ሆኖ የቀረበው፡፡ ሐበሾች እንጀራን ገና ምጣዱ ላይ እያለ ጭምር በምሳሌነት የመጠቀማቸው ሚስጥር ምን ይመስላችኋል? እንጀራን መውደድ ብቻ ሳይሆን፣ እንጅራን ከልክ በላይ መውደድ ያመጣው ‹‹ጣጣ››!
በሐበሻ ምድር ሆድን ለመሙላት በሚደረገው ትግል ውስጥ፣ ቁልፉን ቦታ የያዘው እንጀራ ነው – ድሮም፣ ዘንድሮም፡፡ ‹‹እንጀራ ካልበላሁ ምግብ የበላሁ አይመስለኝም›› የሚሉ ስንትና ስንት ወጣቶች በዘመናችን ጭምር እንዳሉ አታውቁምን? ስለእንጀራ የተጻፈ ነገር ሳስስ፣ ‹‹ጉርሻ›› ከሚባል የፌስቡክ ገጽ ላይ፣ በልጅነቱ እንጀራ በልቶ በመታመሙ ምክንያት፣ እንጀራ ስለማይወድ ባል ቃለ መጠይቅ የመሰለ ነገር ሠፍሮ አየሁ፡፡ እ.ኤ.አ. መስከረም 9 ቀን 2022 የተለጠፈ ነው፡፡ አነበብኩት፡፡ ቀልድም ይመስላል፡፡ ከሥሩ የወንድና የሴት ፎቶ አለ፡፡ ፎቶው እንጀራ የማይወደው ባልና የሚስቱ ስለመሆኑ ምንም የተጠቀሰ ነገር የለም፡፡
በጣም የገረመኝ ምን መሰላችሁ? ከሥር የሠፈሩት አስተያየቶችና ከአስተያየቶቹ እየወጣ የሚጮኸው ድምፅ፡፡ ከ50 በላይ አስተያየቶች የሠፈሩ ሲሆን፣ ከ95 በመቶ በላይ የሚሆኑት ባል ተብሎ በተገለጸው ሰውዬ ላይ የስድብና የእርግማን መዓት የሚያወርዱ፣ ለዘብ ያሉት ደግሞ አምርረው የሚተቹ ናቸው፡፡ እዚህ ላይ እንጀራ ‹‹በክፉ ዓይን›› ለምን ታየብን ብለው የሚሳደቡት፣ የሚራገሙትና የሚተቹት ብዙዎቹ ወጣቶች ግፋ ቢልም ጎልማሶች እንደሆኑ መገመት አያዳግትም፡፡ በአጭሩ አዲሱ ትውልድም ለእንጀራ ሟች ነው እያልኳችሁ ነው፡፡
ይህ ችግር የለውም፡፡ ሆኖም የቀረበው ቃለ ምልልስ ቀልድ ሳይሆን እውነት ነው ብለን እንውሰደውና (‹‹ኮማቾቹም›› እውነት አድርገው ነው የወሰዱት) አንድ ሰው እንጀራ በመብላቱ ምክንያት በመታመሙ፣ እንጀራን ቢጠላ ይህን ያህል ውግዘትና ስድብ የሚወርድበት ለምንድነው? አንድ ሐበሻ በእንጀራ ምክንያት ምንም ነገር ሳይደርስበት፣ በራሱ ስሜት እንጀራን መጥላት አይችልም ወይ ‹‹አይፈቀድለትም›› ይሆን? እንጀራን በተመለከተ ለኢትዮጵያውያን ያለው ምርጫ ‹‹አንድና አንድ ብቻ ነው – እሱም መውደድና መውደድ ብቻ›› ያለው ማን ነው?
ከእዚያ ልጥፍ ሥር በስድብ፣ በሽሙጥና በእርግማን ስለተረባረቡት ዜጎች ሳስብ፣ ስለእኛ ኢትዮጵያውያን አዕምሯዊ መዋቅር (Mind-Set) የግዴን ማሰብ ጀመርኩ፡፡ ‹‹እኛ የወደድነው ሁሉ ጥሩ ነው›› ብቻ ሳይሆን፣ ‹‹እኛ የወደድነው ሁሉ ለሌላውም ሁሉ ጥሩ ነው›› ብሎ ማሰብ ክፋት የለውም፡፡ ችግሩ ያለው፣ ‹‹እኛ የወደድነውን ሁሉ፣ ሌላው ሰው ሁሉ የግድ መውደድ አበትም›› ብሎ ማሰብና የሚወድ ሆኖ ሳይገኝ ሲቀር በጠላትነት መመደቡ ላይ ነው፡፡ በዚያ ሰው ወይም ቡድን ላይ የጥላቻ ዘመቻ መክፈቱ ላይ ነው፡፡ ይኼ በባህላችን ውስጥ ያለ አንድ ሽንቁር ነው – በግልፅነትና በቀናነት በመወያየት ልንደፍነው (ልናርመው) የሚገባ…፡፡
ፖለቲካችንስ እንዲህ ቅጥ – አምባር የለሽ የሆነበት፣ ‹‹የእኔና የእኔ ብቻ ትክክል›› ከማለት አልፎ፣ ‹‹የሌሎቹ ሙሉ በሙሉ ስህተትና መጥፋት ያለበት (‹አንዳንዴም› ከእነ ሰዎቹ ጭምር)›› ከማለትም ተሻግሮ፣ ‹‹አገሪቱ በእኔ ርዕዮተ ዓለም ካልተራመደች ዓለት ላይ የወደቀ ማሰሮ…›› ከሚል ፅንፈኛ አቋም ላይ የሚቸነከርበት አንዱ ዋና ምክንያት ከዚሁ ከአዕምሯዊ መዋቅራችን የሚመነጭ ሳይሆን ቀረ ብላችሁ ነው?…
ለማንኛውን ስለእንጀራ ገና እናወጋለን፣ ሐበሾች ስለእንጀራ የተረኩት በቸርነት ነውና እኛ ልንሰስት አይቻለንም…፡፡
(በክፍል አሥራ ሦስት እንገናኝ – ኢንሻ አሏህ!)
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected]. ማግኘት ይቻላል፡፡