Saturday, September 23, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከሕንፃ ከፍታና ፕላን አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 የሚደረግ ግንባታ እንዲቆም ታዘዘ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በቦሌ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ራማዳ ሆቴል አካባቢ ላልተወሰነ ጊዜ ምንም ዓይነት ግንባታ እንዳይፈቀድና የተፈቀዱ ሕንፃዎችም ግንባታ እንዲቆም፣ የአዲስ አበባ ከተማ የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን አዘዘ፡፡

ተቋሙ ውሳኔውን ለማስተላለፍ የወሰነው ካለፈው ዓመት ጀምሮ የተለያዩ የከተማ ስታንዳርዶችን በከተማዋ ተግባራዊ ማድረጉን ተከትሎ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ፕላንና ልማት ኮሚሽን አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ከሕንፃ ከፍታና የፕላን አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ተጨማሪ ጥናት እንዲደረግ አቅጣጫ በመስጠቱ ነው ተብሏል፡፡

ላልተወሰነ ጊዜ የግንባታ ፈቃድ እንዳይፈቀድ ውሳኔ የተላለፈበት በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 በተለምዶ ራማዳ ሆቴል ግራና ቀኝ የተለያዩ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ዙሪያ ነው፡፡ የተለያዩ አገሮች ኤምባሲዎችና ዲፕሎማቶች ያሉበት አካባቢ በመሆኑና በነባሩ ፕላንና አሠፋፈር ስታንዳርዳይዝ የሆኑ ቤቶች ስላሉበት፣ ከሐምሌ 12 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ምንም ዓይነት ግንባታ እንዳይፈቀድ ባለሥልጣኑ ለቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን ጽሕፈት ቤት በጻፈው ደብዳቤ አዟል፡፡

አክሎም አካባቢው መልሶ እስኪጠና ድረስ በአካባቢው የተፈቀዱ ግንባታዎች ለጊዜው ቆመው በቀጣይ እንዲሻሻሉ እንዲደረግና የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ጽሕፈት ቤቱ ክትትል እንዲያደርግ አሳስቧል፡፡

የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ስጦታው አካለ (ኢንጂነር) ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ ውሳኔው የተላለፈው አካባቢው ላይ ያለው የፕላን አጠቃቀም፣ የሕንፃ ከፍታና የመንገዶች ስፋት መልሶ እንዲታይ ስለተፈለገ ነው፡፡

‹‹አካባቢው ነባር፣ ብዙዎቹ ሕንፃዎችም ጂፕላስ ዜሮና ጂፕላስ 1 የሆኑ መንደሮች ናቸው፤›› ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ይህ በራሱ ውበት ቢሆንም የከተማ አስተዳደሩ ስታንዳርድ የሚባለው ሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎችን መገንባት ብቻ ሳይሆን የከተማ ልማት ፖሊሲን የተከተሉ፣ ለነዋሪዎች ምቹ የሆነና አንዱ ሌላውን የማይረብሽና ተጣጥሞ ሊሄድ የሚችል ግንባታ መፍጠር ይገባል የሚለውን ባለሥልጣኑ ከፕላንና ልማት ኮሚሽን ጋር በመነጋገር በጋራ የተግባቡት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

‹‹አሁን ይጠና ነው ያልነው፣ እንዲህ ይሁን አላልንም፡፡ ጥናቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ተግባራዊ ይደረጋል፤›› ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

ምናልባት የሚቀየር ነገር ካለ እስከዚያ ድረስ ግንባታዎች ለአላስፈላጊ ኪሳራ እንዳይዳረጉ ለጊዜው ወይም ለተወሰኑ ቀናት ባሉበት እንዲጠብቁ መደረጉን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡ ለምን ያህል ጊዜ ይቆያል የሚለው በቀጣይ ለአካባቢው ነዋሪም ሆነ ለመገናኛ ብዙኃን የሚገለጽ መሆኑን አክለዋል፡፡

ፈቃድ የተሰጣቸው ገንቢዎች ዕጣ ፈንታን በተመለከተ ከሪፖርተር ጥያቄ የቀረበላቸው የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተሩ፣ ፈቃድ ተሰጥቷቸው ቢሆንም የትም አካባቢ ከተማ ሲለማ የሚያጋጥም ጉዳይ እንደሆነና በየጊዜው ፕላኖች ሲሻሻሉ ምንም ዓይነት ግንባታ ፈቃድ የወሰደ ሰው አካባቢው ላይ የለም የሚል ዕይታ አይኖረንም ብለዋል፡፡

‹‹እዛ አካባቢ እንኳን አራት የሚደርሱ ሰዎች አሉ፡፡ ከዚህ በላይም ቢሆን መታረም ካለበት እንዲታረም ይደረጋል እንጂ፣ የግንባታ ፈቃድ የወሰደ ሰው ስላለ ከተማ ይበላሽ አንልም፤›› ሲሉ ስጦታው (ኢንጂነር) ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ውሳኔው በቦሌ ክፍለ ከተማ ብቻ ሳይሆን በቂርቆስና በየካ ክፍላተ ከተሞች በሚገኙ በተለዩ አካባቢዎች እየተተገበረ ያለ መሆኑን፣ በቀጣይም በቀሪዎቹ ክፍላተ ከተሞች የሚቀጥል መሆኑን የግንባታና ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን አስታውቋል፡፡

የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን ውሳኔን ተከትሎ የተለያዩ ሐሳቦች እየተንፀባረቁ እንደሆነ ሪፖርት ከሰበሰበው መረጃ የተረዳ ሲሆን፣ አስተዳደሩ የግንባታ ፈቃድ ሰጥቶ ገንቢዎች ምናልባትም ከባንክ ተበድረው ግንባታ እያከናወኑበት ባለ ወቅት፣ እንዲህ ዓይነት ውሳኔዎችን ማስተላለፍ የከተማዋን ስታንዳርድ ለማስጠበቅ ያለመ ነው ለማለት ያዳግታል የሚለው አንደኛው ነው፡፡

የተለያዩ አገሮች ኤምባሲዎችና ዲፕሎማቶች መኖሪያ በመሆን በሚታወቀው ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 በተለምዶ ራማዳ ሆቴል አካባቢ መሠረት ወጥቶ ግንባታቸው እየተከናወኑ የሚገኙ ያልተጠናቀቁ ግንባታዎች መኖራቸውን፣ ሪፖርተር በቦታው ተገኝቶ ተመልክቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች