Saturday, September 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበስምንት ክልሎች የሚከናወነው የተሃድሶ ሥራ መንግሥትን የተዋጉ ከ371 ሺሕ በላይ ሰዎችን ብቻ...

በስምንት ክልሎች የሚከናወነው የተሃድሶ ሥራ መንግሥትን የተዋጉ ከ371 ሺሕ በላይ ሰዎችን ብቻ ይመለከታል ተባለ

ቀን:

  • ከመንግሥት ጎን ሆነው የተዋጉ ኃይሎች በመንግሥት የመልሶ ማቋቋም ዕቅድ ይሸፈናሉ ተብሏል

በስምንት ክልሎች በሚካሄደው የመልሶ ማቋቋም ወይም የተሃድሶ ሥራ፣ መንግሥትን የተዋጉ 371,971 የቀድሞ ተዋጊዎችንና ከውጊያ ጋር ቀጥታ ግንኙነት የነበራቸውን ግለሰቦች ብቻ እንደሚያካትት ተገለጸ፡፡

ከወራት በፊት መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ላደረጉ ዲፕሎማቶችና ዓለም አቀፍ የዕርዳታ ድርጅቶች በቀረበ ሰነድ 250 ሺሕ ያህል የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ ለማቋቋም 555 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ቢነገርም፣ ከክልሎችና ከአገር መከላከያ ሚኒስቴር የተገኘው አኃዝ ከፍ ማለት ገንዘቡን በከፍተኛ መጠን እንደሚያሻቅበው የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽነር ተሾመ ቶጋ (አምባሳደር) ተናግረዋል፡፡

የመንግሥት ኃይሎችን ሲዋጉ የነበሩ አካላትን ብቻ በሚመለከተው የመልሶ ማቋቋም ሥራ፣ ከፍተኛው ድጋፍ ከለጋሾችና ከዕርዳታ ድርጅቶች ይጠበቃል ብለዋል፡፡

በመስከረም ወር 2016 ዓ.ም. በሚጀምረው የመጀመሪያ ዙር የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ የማቋቋም ሒደት 50 ሺሕ ከትግራይ፣ እንዲሁም 25 ሺሕ ያህሉን  ከሌሎች ክልሎች እንደሚጀምር ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡

ኮሚሽኑ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ለሚጠበቀው የመልሶ ማቋቋም ሥራ ከሱዳን፣ ከማዕከላዊ አፍሪካ፣ ከታንዛኒያ፣ ከኡጋንዳ፣ ከኔፓል፣ ከአፍጋኒስታን፣ ከካምቦዲያና ከቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት ልምድ ተቀስሟል ብሏል፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የመንግሥትን ጥሪ ተቀብለው የተሳተፉ የኅብረተሰብ ክፍሎች በአማራ፣ በአፋርም ሆነ በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ ተዋጊዎች የሚስተናገዱት በአገራዊ የመልሶ ማቋቋምና ግንባታ ፕሮግራም በኩል በመሆኑ፣ ይኼኛው ዕቅድ መንግሥትን ሲዋጉ የነበሩትን ብቻ የሚያካትት ነው ተብሏል፡፡

ታጥቀው ከመንግሥት ጋር ሲዋጉ የነበሩ ተዋጊዎችን በአገር መከላከያ፣ በክልሎችና በኮሚሽኑ የልየታ ሥራው ተከናውኖ የሚያስማማ አጠቃላይ አኃዝ መያዙን ተሾመ (አምባሳደር) አክለው ገልጸዋል፡፡

በትግራይ ክልል በአመዛኙ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች ወደ ጦርነቱ ተንቀሳቅሰው እንደነበሩ የገለጹት ኮሚሽነሩ፣ ከሁሉም ክልሎች በተለይ በትግራይ ክልል ያለው ቁጥር ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡ ከመንግሥት ጎን በመሆን ጥሪ ተቀብለው የተሠለፉ ሰዎች በአገራዊ ግንባታና የመልሶ ማቋቋም ሒደት የሚሸፈኑ መሆናቸውን የገለጹት ተሾመ (አምባሳደር)፣ የፌዴራል መንግሥቱንም ሆነ የክልል መንግሥታትን ትጥቅ አንግበው ሲዋጉ የቆዩ እጅ የሰጡና የተማረኩ ኃይሎችን የማቋቋም ሥራ በተሃድሶ ኮሚሽን በኩል እንደሚከናወን አስረድተዋል፡፡

በትግራይ፣ በኦሮሚያና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ያሉ የቀድሞ ተዋጊዎችን አግኝተው እንዳነጋገሯቸውና የሚዲያ ተቋማት የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲጫወቱ ጥሪ ያቀረቡት ኮሚሽነሩ፣ ትችቶች ሲቀርቡ ገንቢ እንዲሆኑ ጠይቀዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት ለሁለት ጊዜያት የመልሶ ማቋቋም ሥራ ማከናወኗ ተገልጿል፡፡ የመጀመሪያው ኢሕአዴግ ሥልጣን በተቆጣጠረበት ማግሥት የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት (ኦነግ) ከሽግግር መንግሥት አፈንግጦ ትጥቅ በማንሳቱ በተቀሰቀሰ ጦርነት የተሳተፉ ታጣቂዎቹን እንዲሁም በደርግ መንግሥት ዘመን ያገለገሉ የሠራዊት አባላትን ከለጋሾች በተገኘ 193 ሚሊዮን ዶላር የመልሶ ማቋቋም ሥራ ማከናወኑ ተጠቁሟል፡፡

በተመሳሳይ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ከመንግሥት ጎን ሆነው የተሠለፉ ተዋጊዎችን ከዓለም ባንክ በተገኘ 174 ሚሊዮን ዶላር 148 ሺሕ ተዋጊዎችን መልሶ በማቋቋም ወደ ሕዝቡ ማቀለቀል መቻሉን፣ የኮሚሽኑ የመልሶ ማቋቋም ዳይሬክተር አቶ ገመዳ አላሚ ተናግረዋል፡፡

ብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ከመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ጋር በመልሶ ማቋቋም ላይ ሐምሌ 12 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ውይይት ያካሄደ ሲሆን፣ በዚህ መድረክ በመልሶ ማቋቋም ዕሳቤዎች ዙሪያ የመነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት አቶ ገመዳ የማቋቋም ሥራው ከፍተኛ የሆነ የማኅበረሰብ ተሳትፎና የፖለቲካ ቁርጠኝነት ይጠይቃል ብለዋል፡፡

የሚከናወነው የመልሶ ማቋቋምና የተሃድሶ ዕቅድ በቀድሞ ታጣቂዎች ፍላጎት ላይ የተመሠረተ ሆኖ፣ ዋነኛ ቢደቱ ታጣቂዎች ተመልሰው ወደ ትጥቅ የማይገቡ መሆናቸውም ይረጋግጣል ሲሉ አክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...