Saturday, September 30, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ብሔራዊ ባንክ የዋጋ ንረትን በአጭር ጊዜ ማረጋጋት ቀዳሚ ትኩረቱ መሆኑን አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በዋነኛነት ትኩረት አድርጎ እየሠራ ከሚገኝባቸው ሦስት ጉዳዮች ውስጥ ቀዳሚው፣ የዋጋ ንረትን በአጭር ጊዜ ማረጋገጥ እንደሆነ አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ለ20ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ትኩረት አድርጎ ባዘጋጀው ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምሕረቱ፣ ማዕከላዊ ባንኩ በልዩ ትኩረት የሚመለከታቸውንና እየተሠራባቸው ነው ያሏቸውን ጉዳዮች አስረድተዋል፡፡

የብሔራዊ ባንክ ገዥው እንዳስታወቁት፣ ባንኩ እንደ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ካሉ ተቋማት ጋር በመቀናጀት ሊሠራ ከሚችላቸው የተልዕኮ ሥራዎች አንዱ፣ የዋጋ ንረትን ማረጋጋት ነው፡፡

ብሔራዊ ባንክ በልዩ ትኩረት እየሠራበት ያለ ጉዳይ ‹‹የዋጋ ንረትን ማረጋጋት ነው፤›› ያሉት አቶ ማሞ፣ ‹‹ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆኑት የገንዘብ ፖሊሲ አቅጣጫዎች በልዩ ትኩረት የሚመለከቱት የዋጋ ንረት መቀነስን ነው፤›› ብለዋል፡፡

ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያደርሰው ከባድ ጉዳት በጣም የታወቀ ነው ያሉት የብሔራዊ ባንክ ገዥው፣ ይህም ቋሚ ገቢ ባላቸው ላይ ከሚያሳድረው ተፅዕኖ ባሻገር በኅብረተሰቡ ውስጥ በጣም ተጋላጭ የሆኑትን እንደሚጎዳ፣ እንዲሁም በከፍተኛ ሁኔታ የኢኮኖሚ ውሳኔዎችን እንደሚያዛባ አስረድተዋል፡፡

የዋጋ ንረት እንዲቀጥል መፍቀድ ራስን ለጥቃት ማጋለጥ እንደሆነ ያመላከቱት አቶ ማሞ፣ በአዲሱ የበጀት ዓመት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ይህንን ሁኔታ መለወጥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የዓለም ሁኔታ በየጊዜው ተለዋዋጭ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በተለያየ ዓለም የሚገኙ ፖሊሲ አውጪዎች ዘርፈ ብዙ ፈተናዎችን እየተጋፈጡ እንደሆነ፣ በኢትዮጵያም ያለው የዋጋ ንረት እንደ ሌሎች አገሮች ሁሉ ከነዳጅ፣ ከምግብና ከማዳበሪያ ዋጋ ማሻቀብ ጋር ተያይዞ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ጠቁመዋል፡፡

በሌላ በኩል ዓለም አቀፋዊ ተለዋዋጭ ሁኔታ ባለበት ወቅት ኢትዮጵያ የቆየችበት አስከፊው የውስጥ ግጭት የተጀመረውን የሪፎርም ፕሮግራም በትኩረት እንዳይሠራበት ከማድረጉ ውጪ፣ በተለይም በገንዘብ አጠቃቀምና ቁጥጥር ዕቅድ ላይ ተፅዕኖ እንደነበረው አቶ ማሞ አስታውቀዋል፡፡

ብሔራዊ ባንክ የዋጋ ንረት መረጋጋት እንዲኖር በፍጥነት ከሚሠራበት አንደኛው አካሄድ ባሻገር የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ የተረጋጋ፣ ዘመናዊና አካታች እንዲሆን የተጀመሩት ሥራዎች እንዲጠናከሩ ያደርጋል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም በራሱ በተቆጣጣሪው ተቋም ያለውን አሠራር ላይ ትኩረት በማድረግ ግልጽ፣ ተቀናጅቶ የሚሠራ፣ እንዲሁም ዕውቀትና ተሞክሮዎችን የሚያጋራ ተቋም እንዲሆን ለማድረግ እየተሠራ መሆኑንም አክለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ባዘጋጀው የሁለት ቀናት ኮንፈረንስ ላይ በተለያዩ ተመራማሪዎች የተሠሩ የጥናት ውጤቶች ላይ ውይይት የተደረገ ሲሆን፣ በተለይም በመክፈቻው ዕለት በቀረበው ‹‹የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ዕሳቤዎች፣ ይዘት ጥቅምና ትግበራ›› በሚል ርዕስ በቀረበው የውይይት መነሻ ሐሳብ ገለጻ ላይ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ምልከታቸውን አጋርተዋል፡፡

በኮንፈረንሱ ‹‹የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ዕሳቤዎች›› ላይ የውይይት መነሻ ገለጻ ያደረጉት የቀድሞ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ፕሬዚዳንትና በአሁኑ ወቅት የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር)፣ ዕሳቤውን በተለይም የኢኮኖሚክስ ምሁራን ገለልተኛ ሆነው የዓለም አቀፍ ተሞክሮን መነሻ በማድረግ ሳይሆን፣ ማኅበረሰባቸው የተመለከተውን ጉዳይ በትክክል መዳሰሳቸውን አፅንኦት ሰጥተው መመልከት ይገባል ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል አንጋፋው የሙያ ማኅበር ለረዥም ዓመታት በኢኮኖሚክስ ትምህርት አስተምህሮና ምርምር ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉት በፈቃዱ ደግፌ (ዶ/ር) በመድረኩ ላይ ዕውቅና ሰጥቷል፡፡

በፈቃዱ (ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር፣ ‹‹ለዕውቀት እንገዛ፣ በዕውቀት እንመራ፣ ትልቅና የመጨረሻው ነገር አገር ነው፡፡ አገር ከሌለ የትም አይደረስም፣ ዓላማችንን አገር እናድርገው፣ መንግሥትም አገር የሚጠቅም ሥራ እንዲሠራ እናድርገው፣ ያ ሥራ ደግሞ ምን እንደሆነ እኛ እናስተምረው፣ እናሳየው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ምን እንደሚሠራ፣ እንዴት እንደሚሠራ የምናውቀው እኛ ነን፣ እዚህ ያለን ሰዎች ነን የኢትዮጵያን ችግር ልንጨርስ የምንችለው፤›› ሲሉ በፈቃዱ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች