Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናለወልቃይት ጉዳይ መፍትሔ የሚጠብቀው ከፌዴሬሽን ምክር ቤት መሆኑን የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ ገለጹ

ለወልቃይት ጉዳይ መፍትሔ የሚጠብቀው ከፌዴሬሽን ምክር ቤት መሆኑን የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ ገለጹ

ቀን:

  • የትግራይ ክልል በበኩሉ አስተዳደራዊ ወሰኑ ከጦርነቱ በፊት ወደ ነበረበት እንዲመለስ እየጠየቀ ነው

የአማራና የትግራይ ክልሎች የሚዋሰኑባቸውንን የወልቃይት፣ የጠለምትና የራያ አካባቢዎች ይገባኛል ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ላቀረቡት ጥያቄ የሚሰጠውን ውሳኔ እየተጠበቁ መሆናቸውን፣ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የሰላምና የፀጥታ መምርያ ኃላፊ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ አስታወቁ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በቅርቡ የመንግሥታቸውን የ2015 በጀት ዓመት አፈጻጸም ለፓርላማ ሲያቀርቡ ሁለቱ ክልሎች የሚዋሰኑባቸውን አካባቢዎች በሕዝብ ውሳኔና በሕጋዊ መንገድ መፍታት አለባቸው ያሉትን እንዴት ተቀበላችሁ በማለት ለምክትል አስተዳዳሪው ሪፖርተር ጥያቄ አቅርቦላቸዋል፡፡

‹‹በወልቃይት ጉዳይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ እናደርጋለን ሲሉ በግልጽ አልሰማንም፡፡ ነገር ግን በሕጋዊ መንገድ ቢፈታ ይሻላል የሚለውን ምክር አዘል ነገር ለፓርላማው ሲናገሩ ሰምተናል፡፡ ግን በዚህኛው ቀጣና በዚህኛው ዞን ብለው ሲያነሱ እኔም በግል አልሰማሁም፣ እኛም የምናውቀው ነገርም የለም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ነገር ግን የወልቃይት ጉዳይ በየትኛው መንገድ ነው ሊፈታ የሚገባው የሚለውን ቀደም ሲል በተደጋጋሚ ተናግረናል፡፡ ሊፈታ በሚገባው መንገድ እንዲፈታ ለመንግሥት አመልክተናል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ራያም፣ ጠለምትም፣ ወልቃይትም ስላሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለየትኛው እንደተናሩ ግልጽ እንዳልሆነላቸው ገልጸው በግምት መልስ ለመስጠት ያስቸግራል ብለዋል፡፡ ‹‹ብዙ ሰው መላምት ሊኖረው ይችላል፡፡ ነገር ግን የወልቃይት ጉዳይ ሊፈታ የሚገባበትን መንገድ ጠቅሰን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ስላቀረብን ውሳኔውን እየጠበቅን ነው፤›› ብለዋል፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅትም ሆነ አሁን ከማኅበረሰቡ ጋር እንዳሉ ገልጸው፣ ‹‹የአገር መከላከያ ሠራዊት የወልቃይት አካባቢን እየተከላከለና እየጠበቀ እንዳለ ነው የምናውቀው፤›› ያሉት ኮሎኔል ደመቀ፣ ‹‹በአካባቢው ከመከላከያ ጋር ምንም ዓይነት ጦርነት የለም፣ ተባብረን ነው እየሠራን ነው፡፡ አካባቢው ሰላማዊ በመሆኑ ፋኖ በሚል ምክንያት ምንም ዓይነት ግጭትም ሆነ ጦርነት የለም፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡   

 የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳዳር በበኩሉ የክልሉ አስተዳደራዊ ወሰን ከጦርነቱ በፊት ወደ ነበረበት እንዲመለስ፣ በጦርነቱ ምክንያት ከምዕራብ ትግራይና ከሌሎች የአማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈናቀሉ የክልሉ ነዋሪዎቸ በአፋጣኝ ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ በተደጋጋሚ ጥያቄ እያቀረበ ነው፡፡

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አመራር አባል ክንደያ ገብረ ሕይወት (ፕሮፌሰር) ከጥቂት ሳምንት በፊት በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹የወሰን ጥያቄ ለምን ይነሳል አንልም፡፡ ነገር ግን ጥያቄው በሕገ መንግሥቱ መርህ ይፈታል ብለን ነው የምናምነው። የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነትም የሚያስቀምጠውም ይህንኑ ነው፤›› ማለታቸው ይታወሳል፡፡

ጦርነት አማራጭ ባለመሆኑ ችግሩ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ክልላቸው እንደሚፈልግ፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩ አመራሮች በቅርቡ በባህር ዳር ያደረጉት ጉብኝትም ችግሩን በንግግር ለመፍታት በር የከፈተ እንደሆነ ተናግረው ነበር፡፡

በኤርትራ ጦር የተያዙ የትግራይ አካባቢዎችን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ ደግሞ፣ ‹‹የኢትዮጵያን ግዛት የሚመለከት ጉዳይ በመሆኑ ይህንን የማስፈጸም ኃላፊነት ያለበት የፌዴራል መንግሥት ስለሆነ ከመንግሥት ጋር እየተነጋገርን ነው፡፡ ስለዚህ ወደ ግጭት ሳይገባ በውይይት ይፈታል ብለን እናስባለን፤›› ማለታቸው አይዘነጋም፡፡

ባለፈው ሳምንት ስድስተኛ መደበኛ ጉባዔውን ያካሄደው የአማራ ክልል ምክር ቤት፣ በትግራይና በአማራ ክልሎች መካከል ይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸውን አካባቢዎችና የክልሉን የፀጥታ ሁኔታ በተመለከተ በርካታ ጥያቄዎች መነሳታቸው ተነግሯል፡፡ በምክር ቤቱ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ወኪል የሆኑትና በጉባዔው የተሳተፉት በቃሉ ታረቀኝ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የክልሉ ምክር ቤት ከዚህ በፊት በቴሌቪዥን በቀጥታ ሥርጭት ሲተላለፍ የነበረውን የምክር ቤት ውሎ በቴሌቪዥን አለመተላለፉን ጠቅሰው፣ ይህ ድርጊት ‹‹አፈና›› የተደረገበት ስለመሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

 በምክር ቤቱ ታሪክ የመጀመርያው ክስተት ተፈጥሯል የሚሉት አባሉ፣ የምክር ቤቱ አባላት ከፖለቲካ ሥራ በተጨማሪ ሕዝብን ወክለው የሕዝብን ይሁንታ ያገኙ ተወካዮች የመሠረቱት ተቋም በመሆኑ ለሕዝብ የሚሞግቱ፣ የሚጠይቁና ለሕዝብ ጥያቄ መፍትሔ የሚያነሱ ሰዎች ስብሰባ ቢሆንም፣ በሕዝባቸው በተሰጣቸው ሥልጣን መሠረት የሚጠይቁ አባላት ከመርህና ከሕግ አግባብ ውጪ ሥልጣናቸው መታፈኑን ገልጸዋል፡፡

ከክልሉ ፀጥታ ጋር በተገናኘ በምክር ቤት ውሎ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጥያቄ ሲያነሱ የነበሩ አባላት ድምፅ መታፈኑን የተናገሩት የምክር ቤት አባሉ፣ በጉባዔው የተለዩ ሐሳቦችን ያነሳሉ ተብለው የተገመቱ ሰዎች አስተያየት እንዳይሰጡ ቢከለከሉም ከራሱ የገዥው ብልፅግና ፓርቲ ጠንካራ የሚባሉ ሐሳቦችን መሰንዘራቸውን አስረድተዋል፡፡

በአማራ ክልል የአገር መከላከያ ሠራዊት ከመርህና ከሕግ ውጪ በሌለው ሥልጣን ወደ ክልሉ መግባቱንና የልዩ ኃይል መፍረስን በተመለከተ በርካታ ጥያቄዎች በጉባዔው መነሳታቸውን የጠቆሙት አባሉ፣ ለተነሱት ጥያቄዎች የተሰጡት መልሶች ግን ‹‹ከላይ ያሉ ጌቶቻቸውን ለማስደሰትና ይኼንን በሉ ተብለው አሉት እንጂ፣ ሕዝብ የወከላቸው የምክር ቤት አባላት ያነሱትን ጥያቄ ለመመለስ አግባብ ባለው መንገድ አልመለሱትም፤›› ብለዋል፡፡ የራያ፣ የወልቃይትና የጠለምት ጉዳይ ከየአካባቢው በተወከሉ አባላት ጥያቄ መነሳቱን ገልጸዋል፡፡

በአገሪቱ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 52 በግልጽ በተቀመጠው መሠረት ክልሎች የራሳቸው ሥልጣንና ተግባር መኖሩን፣ እንዲሁም በአንቀጽ 87 የአገር መከላከያ ሠራዊት መብትና ግዴታ በደንብ ቢደነግግም ተግባራዊ እየተደረገ አይደለም ሲሉ ወቀሳ አቅርበዋል፡፡ ‹‹ሕገ መንግሥቱ መሠረት ክልሎቹ በተሰጣቸው ሥልጣን የራሳቸውን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ በማይችሉበት ወቅት አስቸኳይ ጊዜያዊ አዋጅ ሊታወጅ ይችላል፡፡ ያም የሚሆነው የክልሉ አስፈጻሚ አካል ሥልጣኑን ለሰጠው የክልል ምክር ቤት አልቻልኩም ብሎ በማቅረብ፣ ወይም የፌዴራል መንግሥቱን ዕገዛ እንፈልጋለን በሚል ምክር ቤቱ ሊስማማበት ይገባ ነበር፤›› ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ አሁን መከላከያ እንዲገባ ማን ፈቀደ ለሚለው ምክር ቤቱ አያውቀውም ብለዋል፡፡ ሕገ መንግሥታዊ መሠረት ሳይኖረው ዘመቻውን ማን እንደሚመራው አይታወቅም ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ወልቃይትና ራያን የሚመለከቱ ጉዳዮች በምክር ቤቱ አባላት ጥያቄ ቢነሳም በተገቢው አለመመለሱ ያልጠራ ጉዳይ መኖሩ ማሳያ ነው የሚሉት የምክር ቤት አባሉ፣ ‹‹ጦርነቱ እንደ ምክር ቤት አባልነቴ ከማን ጋር ነው የሚለውን አላውቅም፤›› ብለዋል፡፡

የክልሉ ፕሬዚዳንት ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ፀጥታን የተመለከቱ ጥያቄዎች ሲያብራሩ፣ ‹‹ለሰላም አማራጭ ቅድሚያ እንስጥ በማለት ከአዲስ አበባ ጀምሮ የአገር ሽማግሌዎች፣ ታዋቂ ሰዎችና ባለሀብቶች ጭምር ተሳትፈውበት በሸዋ፣ በወሎ፣ በጎጃም፣ በጎንደር ውይይት ተደርጓል፤›› ብለዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ‹‹የአማራን ሕዝብ እርስ በርስ በማዳከምና ለጥቃት በማጋለጥ የሚመጣ ትርፍ እኔ በበኩሌ አይታየኝም፡፡ በእነሱ በኩልም ታይቷቸው ከሆነ ስህተት ነው፤›› ብለው፣ ልዩነት ያለው ሁሉ ችግሩን በውይይት ለመፍታት ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲመለስ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...