Saturday, September 23, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

አዲሱ የግብይት አማራጭ በቡና ላይ ተስፋ የቆረጠውን አርሶ አደር አነቃቅቷል

በሻፊ ዑመር አጋ  

ሪፖርተር ጋዜጣ እሑድ ሐምሌ 2 ቀን 2015 ዓ.ም. ‹ሸማች› በሚል ዓምድ ሥር ‹‹ለወጪ ንግድ ገቢ መቀነስ ምክንያቶችን መደርደር ችግሩን አይፈታም!›› በሚል ርዕስ አቶ ናታን ዳዊት የተሰኙ ግለሰብ አንድ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡ ይህ ጽሑፍ በቡና ዘርፍ በተለይም በቅርቡ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ከኅብረተሰቡ፣ ከፌዴራል ፖሊስ፣ እንዲሁም ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ጋር በመተባበር ጥናትን መሠረት አድርጎ በወንጀል የተጠረጠሩ የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱን ሠራተኞች በቁጥጥር ሥር መዋል ይጠቅሱና፣ ነገር ግን ለዚህ ወንጀል መከሰት ምክንያቱን በማከል ቁጥጥር በማይደረግበት ሁኔታ ቡናን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ በመፈቀዱና ግብይቱም በማዕከላዊነት በምርት ገበያው ብቻ ስላልተገበያየ የመጣ ችግር እንደሆነ፣ እንዲሁም ለወንጀሉም መፈጸምና ለውጭ ምንዛሪ ገቢ ማነስ ዋነኛው ምክንያት ይህና ይህ ጉዳይ እንደሆነ የግል አመለካከት (Opinion) ነው በሚል አስረግጠው ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል፡፡

ሆኖም ግን እውነታው እሳቸው እንዳሉት ሳይሆን በተቃራኒ እንደሆነ በተጨባጭ ማየት ይቻላል፡፡ ይህም በመጀመርያ ደረጃ በምርት ገበያው በኩል የሚፈጸም ግብይት አንደኛው አማራጭ ሆኖ እስካሁንም ድረስ እያገለገለ እንደሚገኝ፣ ከዚህኛው አማራጭ በተጨማሪ ግን ሪፎርሙ ሌሎች አምስት ዓይነት ዘመናዊና አርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ዕውን ሊያደርጉ የሚያስችሉ የግብይት አማራጮች በሪፎርሙ በሕግ ተደግፎ እንደተቀመጡ አለማወቃቸው አንድም የዕውቀት ችግር፣ አሊያም ደግሞ ሆን ብሎ ሕዝቡንና ሚዲያቸውን ለማደናገርና ለማሳሳት የተደረገ አሻጥር እንደሚሆን እንገነዘባለን፡፡

በዚህ በኩል የቨርቲካል ኢንተግሬሽን ተግባራዊ መደረጉን ቀርቶ ስሙን እንኳን መስማት የማይፈልጉ በአርሶ አደሩና ሕጋዊ አቅራቢና ላኪ መካከል ሆነው የድለላ ሥራ በመሥራት ያላግባብ የደሃውን አርሶ አደር ላብ መምጠጥና የሚገባውን ገቢ እንዲያጣ ሲያደርጉ የነበሩ ጥቅማቸው የተነካባቸው ግለሰቦች የሚያደርጉት ደባና ሁኔታውን ወደኋላ ለመቀልበስ የሚያደርጉበት ርብርብ መኖሩን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

አርሶ አደሩም በአሁኑ ወቅት የሚጠይቀው ምን እንደሆነና ከእጅ ወደ አፍ እንኳን መሆን ያቃተውን ኑሮውን ሪፎርሙ ተግባራዊ ከሆነ በኋላ ያለውን ለውጥ በመረዳት ለማንም ጎትጓችነት የሚሆነውንና የሚጠቅመውን ተረድቶ ከቀረቡለት የግብይት አማራጮች መካከል መርጦ ግብይቱን በመፈጸም ላይ ይገኛል፡፡ ያን ደግሞ ለምን አደረግህ ስለምንስ ወደቀደመ የድህነትና የስቃይ ሕይወትህ አልተመለስክም ብሎ የሚያስከስሰውና የሚያስወቅሰውም ጉዳይ ሊሆን አይችልም፡፡

ከዚህ አንፃር ሊጠቀስ የሚችለው በተካሄደው የሪፎርም ተግባር የዘርፉ ተዋናዮች በሚስማማቸው የግብይት አማራጭ መገበያየት የሚችሉበት አሠራር ተግባራዊ ከተደረገበት 2013 ዓ.ም. ጥር ወር ወዲህ አገራችን ለመጀመርያ ጊዜ ከቡና እያገኘች ያለው ገቢ ከቢሊዮን ዶላር እየተሻገረ መሆኑን ልብ ሊባል ያስፈልጋል፡፡ የቨርቲካል ኢንተግሬሽን ግብይት ከተጀመረ ወዲህ የድህነት ቀንበር ተሸክሞ፣ ኑሮ አቀበት ሆኖበት በቡና ላይ ተስፋ የቆረጠውን አምራች አርሶ አደር ዕንባ እያበሰ እንደሚገኝና በመካከል ምንም ሚና የሌላቸውንና የደለበ ኪሳቸውን ብቻ አስበው የሚሠሩትን ደላሎች እንቅስቃሴ መግታት ተችሏል፡፡ የግብይት አማራጩ አርሶ አደሩን ብቻ ሳይሆን አልሚውን፣ አቅራቢውንም ሆነ ላኪውን ተጠቃሚ ያደረገ አሠራር በመሆኑ፣ ይህንን አማራጭ እጅግ በርካቶች እየተጠቀሙበትና ቡና ዱካው ታውቆ በጥራት እንዲመረት፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ለማምጣት፣ በገዥዎቻችን ዘንድ አመኔታ እንዲኖር ለማድረግ፣ ዘላቂነት ያለው ምርት ለዓለም ገበያ እንዲቀርብና የአገር ገጽታንም ለመገንባት ያለው ፋይዳው የጎላ መሆኑን ሁሉም ልብ ሊለው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡

ሆኖም ግን ያልለፉበትን ማግኘት የለመዱ አንዳንዶች፣ እንዲሁም ስለጉዳዩ አንዳች ዕውቀት እንደሌላቸው በሚመሰክር ሁኔታ (ቨርቲካል ኢንተግሬሽን ብቸኛ አማራጭ እንደሆነ በምርት ገበያ በኩል መገበያየት የሚችልበት ሁኔታ እንደሌለ) አድርገው ይህንን አማራጭና መሬት ላይ ያለውን እውነታ ለማጣጣል መሞከር የአገርንና የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ሊሸረሽር የሚችል ተግባር መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ሐሳብ ያንሸራሸሩ ግለሰብ ታች ወርደው የጉዳዩን ባለቤት አርሶ አደሮች፣ አቅራቢና ላኪዎች፣ እንዲሁም ቡናን ከሚመራው ተቋም ተገቢውን መረጃ በመውሰድ ሚዛናዊ ሐሳብን ማቅረብ ይገባቸው እንደነበር መረዳት ያስፈልጋል፡፡

በመሆኑም ሪፖርተር ጋዜጣ ይህንን ያልተጨበጠ፣ በበቂ መረጃ ባልተደገፈና አሳሳች/የአገርንም ሆነ የሕዝብን ጥቅም አሳልፎ የሚያሰጥ መረጃ፣ በመንግሥት በኩል እየተካሄደ ያለውን እጅግ የሚያበረታታ ሥራ ጥላሸት የሚቀባ ሐሳብ ከማንሸራሸሩ በፊት የሚመለከተውን መሥሪያ ቤት መረጃ መጠየቅና ሚዛናዊ ዘገባ እንዲሠራ ማድረግ ይገባው እንደነበር ከቅሬታ ጭምር ለመጠቆም እንወዳለን፡፡

ከአዘጋጁ፡- የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን የገበያ ልማትና ቁጥጥር ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተር ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት