በአሁኗ ኢትዮጵያ ለበርካታ ዘርፈ ብዙ ችግሮች በምክንያትነት ከሚጠቀሱ ተግዳሮቶች መካከል አንዱ የትምህርት ጉዳይ ነው፡፡ ትምህርት ወላጆችን፣ ተማሪዎችን፣ የትምህርት ቤት ማኅበረሰብን፣ መንግሥትንና ሌሎች በርካታ ባለድርሻ አካላትን የሚመለከት መሠረታዊ ነገር ነው፡፡ አንድ ወጣት ከቅድመ አንደኛ ደረጃ እስከ መጀመሪያ ዲግሪ ቅበላ ለመድረስ፣ በትንሹ 18 ዓመታት ይፈጅበታል፡፡ ቤተሰብ አንድን ተማሪ በእነዚህ ዓመታት አስተምሮ ለወግ ለማዕረግ ለማብቃት የሚከፍለው መስዋዕትነት በዋጋ የሚተመን አይደለም፡፡ መንግሥትም ሆነ የሚመለከታቸው የትምህርት ዘርፍ አካላት የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ ትልቅ ነው፡፡ በትምህርት ዘርፍ ውስጥ የሚመደበው በጀት ከትምህርት ቤቶች ግንባታ፣ የትምህርት መርጃ ቁሳቁሶችን ከማቅረብ፣ መምህራንና ድጋፍ ሰጪዎችን ቀጥሮ ከመመደብ፣ እንዲሁም ለመማር ማስተማሩ ሒደት የሚጠቅሙ ተጨማሪ ግብዓቶችን ከማቅረብ አኳያ ያሉ ተግባራትን ለማከናወን የሚረዳ የሕዝብ ሀብት ነው፡፡ እነዚህና ሌሎች ጥረቶች ብቃት ባለው አመራር፣ የትምህርት ፖሊሲና ስትራቴጂ ሳይመሩ ሲቀሩ የትምህርት ጥራት ይጓደላል፡፡ ኮታ ላይ ትኩረት ተደርጎ ጥራት ወደ ጎን ሲገፋ ውጤቱ አረም ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያ የትምህርት ዘርፍ ከፖለቲካ ጥገኝነት ይላቀቅ፡፡
ከ120 ሚሊዮን በላይ ከሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ውስጥ ከ70 በመቶ የሚልቀው ወጣት ሲሆን፣ ከዚህ ወጣት ኃይል ውስጥ ከ30 ሚሊዮን በላይ የሚሆነው ትምህርት ላይ እንደሚገኝ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በየዓመቱም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከዲፕሎማ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ድረስ ይዘው ይመረቃሉ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተወሰዱ ባሉ ዕርምጃዎች ምክንያት የትምህርት ጥራቱ ገመና በሚገባ እየታየ ሲሆን፣ አምና ከአጠቃላይ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ተፈታኞች መካከል ሦስት በመቶ ብቻ ማለፊያ ነጥብ ማግኘታቸው አይረሳም፡፡ ዘንድሮ ደግሞ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ከተሰጠው መውጫ ፈተና ከመንግሥት ከ40 በመቶ በታች፣ ከግል ደግሞ 17 በመቶ ብቻ ማለፋቸው ያለውን ችግር ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡ ለመምህራን ተሰጥቶ በነበረ የብቃት ምዘና ፈተና የተገኘው ውጤት ሪፖርት ሲደረግ የደረሰው መደናገጥ አይዘነጋም፡፡ ይህ ሁሉ ችግር የተፈጠረው ትምህርት የፖለቲካ ሰለባ በመሆኑ ነው፡፡ ብሔራዊ ችግር ስለሆነ የጋራ መፍትሔ ነው የሚያስፈልገው፡፡
ዘንድሮ ለ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የሚቀመጡ ተማሪዎች፣ ቤተሰቦቻቸውና መምህራኖቻቸውና ሌሎች የአገር ጉዳይ የሚመለከታቸው ወገኖች ጭንቀት ውስጥ እንዳሉ ማንም ጤነኛ ሰው ይረዳዋል፡፡ የትምህርት ጥራት ጉዳይ ድንገት የደረሰ እንግዳ ሳይሆን፣ ለዓመታት ሲንከባለል ኖሮ የአሁኑን ትውልድ ዕጣ ፈንታ የፈተነ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ በመሆኑም ሁሉም ባለድርሻ አካላት የትምህርት ሥርዓቱ ተስተካክሎ መስመሩን እስኪይዝ ድረስ ቆመው የሚጠብቁት ሳይሆን፣ ውስጡ ሰርስሮ የገባውን የፖለቲካ ተፅዕኖ ለማስወገድ በኅብረት ይዘጋጁ፡፡ በደካማ የትምህርት አሰጣጥና በጥራት መጓደል ሳቢያ የሚገኘውን ውጤት በደፈናው ተቀበሉ ብሎ ተማሪዎችን እንዳሻችሁ ማለት እንደማይቻለው ሁሉ፣ የትምህርት ጥራት እስኪስተካከል ድረስ የልጆቹ ጥረትና ትጋት እንዲጨምር ዕገዛ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ወላጆች፣ ትምህርት ቤቶች፣ የትምህርት ሚኒስቴርና ሌሎች አጋር አካላት ከታች ጀምሮ መሠረቱን ለማደላደል የምክክር መድረክ መፍጠር አለባቸው፡፡ የዘርፉ አመራሮችም ሆኑ ባለሙያዎች የራሳቸውን አሉታዊ ድርሻ እየመረመሩ፣ ለትምህርት ዘለቄታዊ መፍትሔ ራሳቸውን ያዘጋጁ፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ በመማር ማስተማር ሒደት ውስጥ ለረጅም ዘመን ያገለገሉ ዕውቅ ባለሙያዎች ሲኖሩ፣ በተጨማሪም በተለያዩ አገሮች ከትምህርት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው በርካታ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አሉ፡፡ የመማር ማስተማሩን ሒደት ቀልጣፋ፣ ጥራት ያለው፣ አካታች፣ ዘመናዊና በጥናት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ለማስቻል በፈቃደኝነት ዕገዛ ሊያደርጉ የሚችሉ ወገኖችን ከአገር ቤትም ሆነ ከውጭ ማግኘት አያዳግትም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በትምህርት ብቻ ሳይሆን በሌሎች ዘርፎች ልምዳቸውንና ዕውቀታቸውን ለማጋራት ፈቃደኛ የሆኑ ብዙ አገር ወዳዶች ስላሉ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ትምህርት ከአንድ ትውልድ ወደ ሌላው በሒደት የሚተላለፍ የተከማቸ ዕውቀት በመሆኑ፣ የአንጋፎችን ልምድና ተሞክሮ በመውሰድ ሥራ ላይ ለማዋል የሚደረግ ጥረት መኖር አለበት፡፡ ዘመኑ የደረሰበትን የቴክኖሎጂ ልህቀት መጎናፀፍ የሚቻለው ጥራት ያለው የመማር ማስተማር ሥርዓት ማስፈን በመሆኑ፣ በትምህርት ዘርፍ አመራር ላይ ያሉ በሙሉ ለዚህ ጉዳይ ትኩረት ይስጡ፡፡ የትምህርት ጉዳይ ለአንድ ወገን ተትቶ ውጤት የሚጠበቅበት ሳይሆን፣ ሰፊና ጥልቅ የጋራ ብሔራዊ መግባባት የሚያስፈልገው ነው፡፡
ፈተና በደረሰ ቁጥር ኩረጃን ለመከላከል ሲባል ከፍተኛ የአገር ሀብት ማባከንና አላስፈላጊ ትርምሶችን ለማስቆም፣ ከታችኛው እርከን ጀምሮ ጥራት ያለው የትምህርት ምኅዳር እንዲፈጠር ከአሁኑ ርብርብ መጀመር አለበት፡፡ ተማሪዎች ፈተና በተቀመጡ ቁጥር የሚኖረው ጭንቀት የሚቀንሰውና በራስ መተማመን የሚፈጠረው፣ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ለዚህ ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት ሲሰጡ ነው፡፡ የፈተና ስርቆት ዓለም አቀፍ ችግር እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ይህ ችግር ዓለም አቀፋዊ ክስተት ነው ብሎ ችላ ማለት ነው ዋጋ እያስከፈለ ያለው፡፡ ብቁ የትምህርት ዘርፍ መሪዎች፣ መምህራን፣ ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞችና ሌሎችም የሚገኙት ለመስተካከልም ሆነ ለማስተካከል ፈቃደኝነት ሲኖር ነው፡፡ ችግሩ የጋራ እንዳልሆነ አስመስሎ ጣት መጠቋቆም ትርፍ ሳይሆን ኪሳራ ነው የሚያሸክመው፡፡ የትምህርት ሚኒስቴር ፈተናን አስመልክቶ እየወሰዳቸው ያሉ ዕርምጃዎችን በጭፍን ከመቃወም በፊት፣ የራስን ድርሻ በመወጣት ብቁ ሆኖ ለመገኘት ጥረት ማድረግ የግድ መሆን አለበት፡፡ የትምህርት ሚኒስቴርም የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ያስገቡ ገንቢ ዕርምጃዎች ላይ ያተኩር፡፡
መንግሥት በበኩሉ የትምህርት ዘርፉ የገጠመውን ፈተና በልዩ ትኩረት በመከታተል የሚፈለግበትን ኃላፊነት ይወጣ፡፡ ለትምህርት ዘርፉ የሚመደቡ አመራሮች ብቃት ያላቸውና ተልዕኮአቸውን በሚገባ የሚወጡ እንዲሆኑ፣ ከፖለቲካዊ መሳሳብና ከኮታ ምደባ ይታቀብ፡፡ ይህ ማሳሰቢያ ከታችኛው እርከን ጀምሮ እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚመደቡ አመራሮችን የሚመለከት ሲሆን፣ ለዚህም የፌዴራሉ መንግሥትም ሆነ የክልል ብሔራዊ መንግሥታት ያስቡበት፡፡ እንዲሁም ተሿሚዎችም ቢሆኑ ያለ ብቃታቸው በፖለቲካዊ ወገንተኝነት የሚሰጣቸውን የትምህርት ዘርፍ አመራር ሹመት ባለመቀበል ለአገር ውለታ ይዋሉ፡፡ የመምህራን ቅጥር፣ ምደባ፣ ዕድገት፣ ዝውውርም ሆነ ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች ከትምህርት መሠረታዊ መርህ ጋር እንዳይጣረሱ ይደረግ፡፡ የኢትዮጵያ የትምህርት ጥራት እያሽቆለቆለ እዚህ አዘቅት ውስጥ የተገኘው ትምህርት የፖለቲካ መሣሪያ እንዲሆን በመደረጉ እንደሆነ ልብ ይባል፡፡ ለመሪነት የማይመጥኑ ግለሰቦችና ለማስተማር ብቁ ያልሆኑ መምህራን እንደ አሸን የፈሉበት የትምህርት ዘርፍ ነፃ የሚወጣው፣ ለተገቢው ቦታ ተገቢው አመራርና ባለሙያ ተመድቦ ሲሠራ ብቻ ነው፡፡ እንዲህ ማድረግ ሲቻል ውጤቱ በሚገባ ይታያል፡፡ የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠውም ብቃት ባለው አመራር እንደሆነ ይታወቅ፡፡ ስለዚህም ትምህርት የፖለቲካ መሣሪያ አይሁን!