Saturday, September 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹በራሳችን ቴክኖሎጂ ከመጠቀም አልፈን ለውጭ ለመሸጥ መሥራት አለብን›› ናታን ዳምጠው፣ የኔታ ኮድ መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ

የኔታ ኮድ ከተመሠረተ ካለፉት አምስት ዓመታት ጀምሮ ልጆችን በመሠረታዊ የኮምፒውተር ፕሮግራሚንግ እያስተማረና የትምህርት ቴክኖሎጂዎችን እያበለፀገ ይገኛል፡፡ እስካሁን በትምህርቱ ዘርፍ ካበለፀጋቸው ቴክኖሎጂዎች ቢብሎኪ የተባለው የመማሪያ ቴክኖሎጂ (መተግበሪያ) ይገኝበታል፡፡ ይህ ልጆች ከሰባት ዓመት ጀምሮ በቀላሉ ኮምፒውተር ፕሮግራሚንግ መማር የሚችሉበት ነው፡፡ ይህንና ሌሎች ቀላል የማስተማሪያ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ታዳጊ ልጆች ከታች ጀምሮ የኮዲንግና ፕሮግራሚንግ ቴክኖሎጂን እንዲያውቁ፣ ፍላጎት እንዲያሳድሩና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል የተመሠረተው የኔታ ኮድ፣ አሁን ላይ አራት ቅርንጫፎችን በመክፈት ሥልጠና እየሰጠ ይገኛል፡፡ ወጣት ናታን ዳምጠው የየኔታ ኮድ መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ነው፡፡ በድርጅቱ ዙሪያ ምሕረት ሞገስ አነጋግራዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- የኔታ ኮድን ለመመሥረት ያነሳሳህ ጉዳይ ምን ነበር?

ወጣት ናታን፡- በ2007 ዓ.ም. አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮምፒውተር ሳይንስ ትምህርት ክፍል ስገባ፣ ኮምፒውተር ፕሮግራሚንግ ለእኔም ለክፍል ጓደኞቼም አዲስ ነበር፡፡ እኔ እንደውም ቅዱስ ዮሴፍ ትምህርት ቤት ስማር ሁለተኛ ደረጃ እያለን ትንሽ ተምረን ነበርና ሐሳቡ ነበረኝ፡፡ ሆኖም ዩኒቨርሲቲ ስገባ ለእኔም አዲስ ነው የሆነው፡፡ ምንነቱን መረዳቱ በራሱ ከባድ ነበር፡፡ በዩኒቨርሲቲ የመጀመርያ ዓመት ላይ የገጠመኝ ተግዳሮት ግን ሁለተኛና ሦስተኛ ዓመት ስደርስ እየቀለለኝ መጣ፡፡ ሦስተኛ ዓመት ላይ እያለሁ ትምህርቱን ማቅለል እንደሚቻል አሰብኩ፡፡ በወቅቱ ታዳጊ ሕፃናት የነበሩ ዘመዶቼ ይጫወቱት የነበረው ጌምና ቴክኖሎጂዎችን ሳይ ከእኔ ጋር የነበራቸው የዕድሜ ልዩነት ብዙ ባይሆንም ለቴክኖሎጂው ያላቸው ቅርበት ግን ከእኔ የተሻለ መሆኑን እንድገነዘብ ረድቶኛል፡፡ ውስብስብ የሆኑ ጌሞችንና ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ከቻሉ ኮንዲንግና ፕሮራሚንግ ከታች ዕድሜ ጀምረን ብናስይዝ ዩኒቨርሲቲ በሚገቡበት ጊዜ አይቸገሩም፣ ቴክኖሎጂውን በቀላሉ ይረዳሉ፣ ፍላጎትም ያድርባቸዋል ብዬ ጀመርኩት፡፡ በመሆኑም ሦስተኛ ዓመት መጨረሻ እያለሁ ነው ቢ ብሎኪ የተባለውን መተግበሪያ አበለፀኩኝ፡፡   

ሪፖርተር፡- ቢ ብሎኪ የተባለውን የትምህርት ማገዣ ቴክኖሎጂ ያለፀከው ብቻህን ነው ወይስ ከጓደኞችህ ጋር?

ወጣት ናታን፡- ብቻዬን ነው ያበለፀኩት፡፡ በኋላ አራተኛ ዓመት ስገባ ምርቴን ወደ ስታርት አፕ (ድርጅት) የምለውጥበትን ዕድል አገኘሁ፡፡ ሪች ፎር ቼንጅ ከተባለ ድርጅት የቢ ብሎኪን ሐሳብ ወደ ኩባንያ ለመቀየር የተለያየ ሥልጠናና የተወሰነ የገንዘብ ድጋፍ አግኝቼ የኔታ ኮድን ለመክፈት ችያለሁ፡፡ የኔታ ኮድን የከፈትኩትም በተመረቅሁ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የኔታ ኮድ ከተከፈተ በኋላ ምን መሥራት ጀመርክ?

ወጣት ናታን፡- የኔታ ኮድ ከተከፈተ በኋላ የኮምፒውተር ፕሮግራሚንግ መሠረታዊ ትምህርትን ከአምስት ዓመት ጀምሮ ላሉ ታዳጊዎች በተለያየ ደረጃ መስጠት ጀመርን፡፡

ሪፖርተር፡- የልጆቹ የትምህርት አቀባበል እንዴት ነው?

ወጣት ናታን፡- ከአምስት ዓመት ጀምሮ ያሉ ልጆችን ተቀብለን እናሠለጥናለን፡፡ ወላጆች እንዴት ከአምስት ዓመት ጀምሮ ታስተምራላችሁ? ይሉንም ነበር፡፡ እኛ ልጆችን የምናስተምረው ዩኒቨርሲቲ ገብተን በተማርንበት ደረጃ ዓይነት አይደለም፡፡ ብሎክ ቤዝድ ኮዲንግ (ብሎኪ) የተባለ ቴክኖሎጂ ተከትለን ነው የምናስተምረው፡፡ ይህ ልጆች በቀላሉ መሠረታዊ የኮዲንግ ሰዋሰውና አጠቃቀም እንዲያውቁ ያደርጋቸዋል፡፡ ለልጆቹ በቀላል አቀራረብ ስለምናስተምር ከሚያውቁት ቴክኖሎጂ ጋር ተደማምሮ ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ፣ ችግርን እንዲፈቱ ያስችላቸዋል፡፡ እኛ ጋር ከመምጣታቸው በፊት የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን አውቀው ስለሚመጡ አቀባበላቸው ፈጣን ነው፣ ብዙ ነገር ለመማርም ዝግጁ ናቸው፡፡ የኮዲንግ ትምህርት ፈታኝ እየሆነ የሚሄድበት ደረጃ አለ፡፡ ነገር ግን ልጆቹ ከታች ጀምሮ እያወቁት ስለሚሄዱ ፈተናውን ለመሸከምና ለማለፍ አይቸገሩም፡፡ ይወጡታል፡፡

ሪፖርተር፡- ከወላጆች በኩል ያለ አስተያየት ምን ይመስላል?

ወጣት ናታን፡- የዛሬ አምስት ዓመት ስንጀምር አዲስ ስለነበረ ለማስተዋወቅም ይቸገሩ ነበር፡፡ ከእኛ በፊት አይኮግለቭ ይቀድሙን ነበር፡፡ ሆኖም እኛም ስንጀምር ለወላጆች አዲስ ነገር ነበር፡፡ እኛም ጥረት አድርገንና ዲጂታል ቴክኖሎጂው እያደገ ሲመጣ የወላጆች ግብረ መልስ እየተቀየረ ነው፡፡ ፓወር ኦፍ ኮድ በሚል በየሦስት ወሩ በነፃ ለአንድ ሰዓት የሚከናወን ፕሮግራምም አለን፡፡ በዚህ በርካቶችን መሳብ ችለናል፡፡ ፕሮግራሙ ተማሪዎችና ወላጆች እንዴት በቀላሉ መማር እንደሚቻል የሚያስገነዝብ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ዲጂታል ቴክኖሎጂ ቅድሚያ ከተሰራባቸው ሥራዎች አንዱ ነው፡፡ ኃላፊነት የተሰጣቸው መንግሥታዊ ድርጅቶችም እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ከእነሱ ጋር ያላችሁ ግንኙነት ምን ይመስላል?

ወጣት ናታን፡- እስከ ዛሬ ጥልቅ የሆነና ለረዥም ጊዜ የቆየ ትብብር አላደረግንም፡፡ ድርጅታችን ግን ለማንኛውም ዓይነት ትብብር ክፍት ነው፡፡ ድርጅታችን ከሥልጠና ውጭ ቴክኖሎጂንም ይገነባል፡፡ የሞባይል መተግበሪያን ጨምሮ ለተለያዩ ትምህርቶች ዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን እንሠራለን፡፡ በቴክኖሎጂ፣ በማማከርና በሌሎችም ቴክኖሎጂዎችን ለመሥራትም በራችን ክፍት ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- በዓለም አቀፍ ደረጃ ሥራዎች ሁሉ ወደ ዲጂታል ቴክኖሎጂ እየተቀየሩ ነው፡፡ ኢትዮጵያም ዲጂታል ኢኮኖሚ ላይ እየሠራች ነውና ትምህርት ላይ ምን መደረግ አለበት ብለህ ትመክራለህ?

ወጣት ናታን፡- ዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባትና ለማጠናከር በአገር አቀፍ ደረጃ ፖሊሲዎችና ዕቅዶች አሉ፡፡ ዲጂታል ኢኮኖሚውን ለመገንባት በከፍተኛ ደረጃ የተማረ የሰው ኃይል  ያስፈልጋል፡፡ በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካ እስካሁን ድረስ ባለው አካሄድ ሥራዎች እየተመሩ ያሉት ከውጭ በሚገዙ ቴክኖሎጂዎች ነው፡፡ በአገራችን በቴክኖሎጂዎች ላይ ብልሽት ሲያጋጥም የሚጠገኑት በውጭ ባለሙያ ነው፡፡ ይህ የሆነው በመያው ብቁ ሆኖ የሠለጠነ የሰው ኃይል ስለሌለን ነው፡፡ የምንፈልገውን ዲጂታል ኢኮኖሚ ለማምጣት አቅም ያስፈልገናል፡፡ ዲጂታል ኢኮኖሚውን ለማጠናከር ከታች ጀምሮ በልጆች ላይ መሠራት አለበት፡፡ ከታች ጀምሮ ልጆች ላይ ከሠራን ዲጂታል ቴክኖሎጂውን ለመገንባት የሚያስችል የሰው ኃይል እንዲኖረን ያስችለናል፡፡ ካሁኑ ከሠራን ከጥቂት ዓመታት በኋላ ክህሎትና ዕውቀት ያላቸው ባለሙያዎች አፍርተን ትላልቅ ቴክኖሎጂዎችን መገንባት እንችላለን፡፡ ቴክኖሎጂዎችን በራሳችን ካመነጨን ከአገራችን አልፈን ለውጭ መላክ እንችላለን፡፡ ቴክኖሎጂን ወደ ውጭ መላክ የምንችልበት ደረጃ ድረስ መሥራትና የውጭ ምንዛሪ ማግኘት አለብን፡፡ ፌስቡክን ጨምሮ ትላልቅ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ቴክኖሎጂን ወደ ውጭ ልከው ነው ተጠቃሚ የሆኑት፡፡ በኢትዮጵያም የዲጂታል ኢኮኖሚው ዕቅድ እንዳለ ሁሉ ይህንን ለማሳካት የሰው ሀብት ላይ ከታች ጀምሮ መሠራት አለበት፡፡ በሰው ኃይል ላይ መሥራቱ ግለሰቦች ጭምር እንዲጠቀሙ ያደርጋል፡፡ በዓለም ላይ ከፍተኛ ተከፋይ ከሆኑ ሙያዎች አንዱ የፕሮግራሚንግ ባለሙያዎች ናቸው፡፡ እኔም ኔታ ኮድን የመሠረትኩት ኢትዮጵያውያን በቴክኖሎጂው ከራሳቸው አልፈው ለዓለም መሸጥ እንዲችሉ ከታች መሠረት ለመጣል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በሥራችሁ ያጋጠማችሁ ችግር ምንድነው?

ወጣት ናታን፡- ሥራ ስንጀምር በዘርፉ የሚሠራ ብዙም ስላልነበረ ተቀባይነት ችግር ገጥሞን ነበር፡፡ አሁን ነገሮች ተቀይረዋል፡፡ በጊዜ ሒደት ወላጆች ልጆቻቸውን ለማስተማር ፍላጎት እያሳዩ መጥተዋል፡፡ ስንጀምር የነበረን አንድ ቅርንጫፍ ዛሬ ላይ አራት ደርሷል፡፡ የመቀበል አቅማችንም ወደ 300 ተማሪ ሆኗል፡፡ በዲጂታል ቴክኖሎጂን የምንነካቸው ነገሮች በሙሉ ኮዲንግ አላቸው፡፡ በእኛ በኩል የኮዲንግ ትምህርትን ለልጆች ለመስጠት እየሠራን ቢሆንም፣ ከ18 ዓመት በላይ ያሉትም መማር እንደሚፈልጉ ፍላጎት እየመጣ ነው፡፡ በመሆኑም ማሠልጠን ጀምረናል፡፡ ከሌሎች ጋር በመተባበር በሺዎች የሚቆጠሩ ለማሠልጠንም አቅደናል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች