Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገር‹‹መጀመሪያ ሰው መሆን ይቅደም!››    

‹‹መጀመሪያ ሰው መሆን ይቅደም!››    

ቀን:

በንጉሥ ወዳጅነው

በአንድ ወቅት ዕውቁ የአገራችን ኢንተርፕሩነርና የምጣኔ ሀብት ባለሙያ አቶ ብርሃነ መዋ በማኅበራዊ የትስስር ገጻቸው ላይ ‹‹መጀመሪያ ሰው መሆን ይቀደም›› የምትል አጭር መልዕክት አሥፍረው ነበር፡፡ ‹‹ሰው ሰውን መግደል የለበትም፣ ከገደለም እንኳን እንደ ሰው መግደልም የአባት ነው፡፡ ሰውን እንደ አውሬና በደመ ነፍስ እንደሚንቀሳቀስ ፍጥረት በግፍ የማይደረግ አድርጎ መግደል ግን አረመኔነት ነው፡፡ ከሰው ባህሪም የወጣ ነውር ነው፡፡ እናም መጀመሪያ እንደ ሕዝብ ሰው እንሁን፣ መንግሥም አረመኔነትና ኢሰብዓዊነትን አጥብቆ ይታገል፤›› ሲሉ ነበር መልዕክታቸውን ያሠፈሩት፡፡

በእርግጥ እንደ አገር በፖለቲካ አለመግባባት ወይም በብሔርና በሃይማኖት ልዩነት ሰበብ ባለፉት አምስት ዓመታት ምን ያልታየ ጉድ ይኖራል ብሎ መፈተሽ ይገባል፡፡ ከጅምላ ጭፍጨፋና የዘር ማጥፋት ምልክት ያላቸው ዕርምጃዎች አንስቶ፣ ሕፃናትና ሴቶች ሳይቀሩ ታሪክ ለማይዘነጋው ግፍና መከራ ሲዳረጉ ታይቷል፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መፈናቀልና ለችግር መዳረግ ብቻ ሳይሆን፣ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው የሕዝብ ሀብትና ንብረት ውድመት፣ የመኖር ዋስትና ማጣትና በነፃነት የመንቀሳቀስ መብት መገደብ ከፖለቲካ ኪሳራም በላይ አገርን ወደ ውድቀት የሚወስዱ አደገኛ ድርጊቶች ናቸው፣ አሁንም ያልተወገዱ ሳንካዎች፡፡

የአገራችን ሕዝቦች በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች በእርስ በርስ ውዝግብና ቁርቁስ ዘመናትን ማሳለፋቸው የሚታወቅ ነው፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖም በየአገዛዞቹም ቢሆን እረፍት ያገኘ፣ ሰላምና ዴሞክራሲን በወጉ ያጣጣመና የበለፀገ ማኅበረሰብ አይደለም ያለን፡፡ አንዱ ከሌላው ቢሻልም የመጣንበት ረዥሙ የአገረ መንግሥት ግንባታ ሒደት በተለያዩ ውጣ ውረዶች ታጅቦ እዚህ የደረሰ ነው፡፡ በሥርዓት አልበኝነትና ሕገወጥነት፣ ብሎም የሕግ የበላይነት መዳከምና የመኖር ዋስትና ማጣት ረገድ ግን የምንገኝበት ወቅት የሚወዳደር አስቸጋሪ ዘመን ይገኛል ብዬ አላምንም፡፡

መንግሥት አንዱን ቀዳዳ ለመድፈን ሲሞከር ሌላው እየተሸነቆረ፣ ሕዝቡም ስለአንዱ ችግር መፍትሔ ሲባጅ ሌላው እየተጨመረ መደነጋገሩ ቀጥሏል፡፡ መነጋገርና መደማመጥ ተዳክሟል፡፡ ከሁለት ዓመት በላይ በሰሜን ኢትዮጵያ በእርስ በርስ ጦርነት የደረሰው ውድመትና ጥፋት እንኳን በቂ ትምህርት የሰጠን አይመስልም፡፡ አሁንም ቦታውና ተዋናዩ ተቀየሩ እንጂ ግጭትና ጦርነት አልቆሙምና፡፡ ዕገታ፣ ማፈናቀል፣ ሥጋትና ውንብድናውም ብልጭ ድርግም ማለታቸው አልቀረም፡፡

አሁን ችግሩን ደግሞ ደጋግሞ መደብደብ ሳይሆን እንደ ሰው ከችግሩ ለመውጣት ምን ይደረግ፣ መፍትሔውስ ምን ይሁን ብሎ መነጋጋር አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡ እናም በመጀመሪያ ‹‹ሰው መሆን ይቅደም› ብሎ መነሳት አስፈላጊ መሆኑን ማጤን ይገባል፡፡ በመግቢያዬ እንደጠቆሙኩትም ሆነ ሰው የሆነ ሁሉ እንደሚያምንበት (መተግበር ፈተና ቢሆንም) መላው የአገራችን ሕዝቦች ልጅ አዋቂ ሳይባሉ፣ የብሔርና የሃይማኖት መሳሳብ ሳይገድባቸው፣ የመደብና ሥልጣን ደረጃ ሳይለያያቸው ሰው መሆንን ማስቀደም ይኖርባቸዋል፣ አለባቸውም፡፡ ንፁኃንንና ምርኮኞችን ለገንዘብ ተብሎ የተያዙ ወገኖችን፣ በጉዳት ላይ ያሉትን… ሁሉ ማትረፍ የሚቻለው ሰው በመሆንና በአርቆ አሳቢነት ነውና፡፡

እንዴት በሥነ ምግባርና በግብረ ገብነት አድገን፣ በየማኅበረሰቡ ለዘመናት ሥር በሰደዱ ትውፊቶችና ወጎች ታንፀን፣ የአማኝነትና ፈሪኃ ፈጠሪ ፀጋ ተላብሰን እንደ አውሬ በጭካኔ የምንበላላና ሰዎችን ካለ ኃጢያታቸው የምናጠቃ ኋላቀሮች ሆንን ብሎ መፈተሽ ከሁላችንም የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡ አገር በድህነትና በኑሮ ውድነት እየተናጠች፣ የኢኮኖሚ ሴራ በመጎንጎንና በሰዎች የመንቀሳቀስ መብት መገደብስ ምን ሊተረፍ ተግባሩን ተመኘን መባልም አለበት፡፡ የወደቁትን ማንሳትና ያጡትን መደገፍ የሚቻለው በታይታ ሳይሆን ሰውነትን በመመለስ ብቻ ነው፡፡

በአዲስ ትውልድና በተቀየረ ፖለቲካ ኢኮኖሚ ውስጥ ትናንት በነበረ ትርክት ላይ ተመሥርቶ የተዘራን የተሳሳተ የጥላቻ ፖለቲካ እያጋነኑና እያመነዠኩ መኖርስ ከሰውነት ያወርድ እንደሆን እንጂ ምን ሊያስገኝ ይችላል፡፡ ሕዝቦች አብረው የማይኖሩበትን የቂም በቀል አካሄድ ከውጭ ባላንጣ ወርሶ ማላዘን መቆም አለበት። የፖለቲካ ትግል ማድረግ ተፈጥሯዊ ቢሆንም በመነጋገርና በመደማማጥ፣ ይበልጡንም በሐሳብ የበላይነት መሆኑን ተገንዝቦ ችግሮችን በሰጥቶ መቀበል ሥልጡን መንገድ መፍታት የሚሳነንስ እስከ መቼ ነው መባልም አለበት፡፡ እስከ መቼ ሰው ሆነን ሰው መሆን ሲሳነን ይኖራል፡፡

ከሁሉ በላይ ‹‹እኔ እበልጥ››፣ ‹‹እኔ እበልጥ›› ፉክክርና የ‹‹እኛ›› እና የ‹‹እነሱ›› ጭቅጭቁ የለየለት የጥገኛ መንገድና መስገብገብ የወለደው ኋላቀርነት እንጂ፣ ሩቅ የሚወስድ መንገድ እንዳልሆነ ግንዛቤ መያዝ አለበት። ትናንት በሴራ ሕዝቦችን ለማቃቃር የተቀነበበን የወሰንና የማንነት ጥያቄ በግብታዊነት እየመዘዙ፣ በሕግና ሥርዓት፣ ወይም ሕዝብን በማዳመጥ ከማስተካከል ይልቅ በፀብና በግጭት ለመፍታት መሞከርም ራስን እንደመካድ ነው መቆጠር ያለበት። በመዳማት ሳይሸናነፉ መሳቂያ መሳለቂያ ሆኖ መድቀቅ እንዳለስ መረዳት ለምን ይሳነናል፡፡

መንግሥትም ሆነ አብዛኛዎቹ የፖለቲካ ልሂቃን መጠላለፍና መገፋፋትን ትተው መቀረራብን ማስቀደም ያለባቸው፣ መካረሩና ከሰውነት የሚያስወጣው የጭካኔ መንገድ መፍትሔ የሚያመጣ ባለመሆኑ ነው፡፡ እዚህ ላይ መንግሥትም ቢሆን ‹‹ወቅት ሰጠኝ›› ብሎ በራሱ ግምግማ ብቻ ያሻውን ከማድረግ መቆጠብ አለበት፡፡ የአንድ ወገንን ፍላጎት ብቻ ለማሟላት በኃይል በሌላው ላይ ሐሳብን ለመጫን መሞከርም አስተማማኝ ሰላም እንደማያመጣ የታየ ሀቅ ነው፡፡ ታሪክ እንደሚያስተምረንም ውድቀትን እንጂ መነሳትንና በጋራ ማደግን አያስገኝም፡፡

እናም ምንም ዓይነት አወዛጋቢ ወይም አከራካሪ ጉዳዮች ከአገርና ከሕግ በታች እንደ መሆናቸው፣ እውነታውን እየተጋፈጡና የሕዝቡን ውሳኔ እያዳመጡ ወደ አዲስ ምዕራፍ መሸጋገር ነው የሚጠቅመው፣ ከጥፋት የሚያድነውም። አሁን በምንገኝበት አገራዊ ሁኔታ በዋና ዋናዎቹ ክልሎች ቀውስና ግጭት አልተወገደም፡፡ ለኢትዮጵያውያን አይደለም ለሌሎች ሕዝቦችም ቢሆን የማይመጥኑና ሰው መሆንን የማያረጋግጡ አረመኔያዊ ግፎች አሁንም በየአካባቢው መስተዋላቸውም አልቆመም፡፡ በአብዛኛው ቅቡል የሆነ መንግሥታዊ አመለካከትና ተግባር መኖሩ ላይም ጥርጣሬ አለ፡፡ ይህንን ተሸክሞ እስከ የት መጓዝ ይቻላል ነው ጥያቄው፡፡

በመሠረቱ ምንም ያህል የሴራ መጠላለፍና የመነጣጠል አዚም ቢበረታ፣ ከቀደሙት ዘመናት የተሻለ ወይም ከአባቶቻችን የላቀ አገር ወዳድነትና አንድነት ለማምጣት ነበር መትጋት ያለብን፡፡ እንደ ሕዝብ ስክነትና ምክንያታዊነት ማበብ ያለበትም ሆነ፣ ከወደቅንበት አገራዊ መራቆት በመውጣት ቢያንስ እፍረታችንን ሸፍነን በመደማመጥ ፈተናዎቻችንን ለማለፍ መነሳትም ነበረብን፡፡ ቆም ብሎ ከልብ ምን እናድርግ መባል ያለበትም ለዚሁ ነው፡፡ ታዲያ ይህንን ማድረግ ለምን ከበደን፣ ኃይልና መገዳደልስ ምን ሊያስገኝ ይመረጣል ብሎ የሽምግልናና የአባትነት ሚና የሚጫወት ኃይል ሊፈጠር ይገባል፡፡

ስለሆነም በቀዳሚነት ሰብዓዊነትና መተሳሰብን በማስቀደም፣ አገራዊ አንድነትና አብሮነታችንን በማስቀጠል፣ የብሔረሰቦችን የየራሳቸው ማንነትና ታሪክ እየገነቡ፣ የየትኛውም መብትና ጥቅም ጉዳይ ሳይገፋፉ በአብሮነት ጠንካራ የጋራ አገር በሚገነባበት ቁመና ላይ ለመገኘት ያደፈጠውና እንደ ሰጎን አንገቱን የቀበረው ሁሉ ወደ መድረኩ መጥቶ መነጋገር አለብን፡፡ ወዳጅና ጠላት በመባባል ‹‹ተራው የእከሌ ነው፣ የእከሌ መንግሥት፣ ያኔ ተበድለህ አሁን ተራህን በድል›› ዓይነት ኋላቀር ዕሳቤዎች የሚያስከትሉት ጥፋት ብቻ ነው፡፡ እንዲህ ያሉ አጉል ዕሳቤዎች እንዴት የምንገኝበትን ዘመን ሊዋጁ ይችላሉ? አስተማማኝ ሰላምስ በምን መለኪያ ሊረጋገጥ ይችላል?

ከዚህ አንፃር ሁሉም አካሄዱን ቆም ብሎ መፈተሽ ነው ያለበት፡፡ ግለሰቦችም ሆኑ መንግሥታት ይሄዳሉ፣ ይመጣሉ፡፡ ቋሚዎቹና ቀሪዎቹ ሕዝብና አገር ናቸው፡፡ ለሚያልፍ የፖለቲካ ውዝግብና ለርካሽ ተወዳጅነት ብሎ ሕዝብን ወደ እሳት መማገድና የአገርን ህልውና ለአደጋ ማጋለጥ፣ በየትኛውም ወገን ቢከናወን መወገዝ ነው ያለበት፡፡ ከሰውነት ተራ እያወጣን ያለው ችግር በፅንፈኝነትና በብሔር ካባ ተሸፍኖ የሚፈጸመው መተጋተግ የወለደው እንደሆነ የሚስተው የለም፣ ሊኖርም አይችልም፡፡

  መተሳሰብ፣ መደማመጥ፣ ያሉንን ትሩፋቶች በፍትሐዊነት መካፈል፣ ሁሉንም ለመጠቅለል ብሎ ሁሉንም ከማጣት ያድኑናል፡፡ ለትውልዱ መልካም ፍሬና ተጨባጭ ጥቅሞቹን እያካፈልን እንደትውልድ ማለፍም ያስችለናል፡፡ ስለሆነም በቀዳሚነት እየተሳቡ ያሉ አገራዊ የምክክር ምድረኮችን በቅንነትና በአገር ወዳድነት መንፈስ ፈጥኖ ማስጀመር፣ ሁሉም በነፃነት እንዲሳተፍ ማድረግ፣ የአብላጫ ድምፆችንና ሐሳቦች ማዳመጥና አጣጥሞ መተግበር ከሁሉም ወገኖች የሚጠበቅ ነው፡፡ መንግሥትም ከገባንበት አገራዊ ቀውስ ለመውጣት ከዚህ የበለጠ ዕድል እንደሌለ መረዳት አለበት፡፡

እንደ መንግሥት ለብሔራዊ ሕዝባዊ ምክክርም ሆነ ለፖለቲካ ንግግርና ድርድር ምቹ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ትኩረት መስጠት ግድ ይለዋል፡፡ ተወደደም ተጠላም በትግራይ እንደሆነው በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች እየተካሄዱ ያሉ ውጊያዎች ቆመው የፖለቲካ መፍትሔ መፈለግ አገርን ለመታደግ ብቸኛው መፍትሔ ነው፡፡ አሸናፊም ተሸናፊም በሌለበት የእርስ በርስ መተላለቅ ከሰውነት ተራ እየወጣን ይባሰ እንጨካከንና አገርም ትንኮታኮት እንደሁ እንጂ፣ የሚመጣ አስተማማኝ መፍትሔ አይገኝም፡፡ ማንም ሆነ ምንም ከሕግ በታች መሆኑን አምኖ ይነጋገር፡፡

እንደ አገር የከፋ ጉዳት ሳይደርስ፣ እስካሁን በደረሱብን የጋራ ኪሳራዎች ተወስነን፣ ቀልባችንንና ሰውአዊነታችንን መልሰን መነጋገር ከቻልን የማይፈታ ቀውስና ችግር አይኖርም፡፡ በቀዳሚነት ሕግና ሥርዓት በተለይም በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት በመግባባት እስኪስተካከል መከበሩን ማረጋጋጥ፣ አገራችን የምትከተለውን ፌዴራሊዝም ጉድለቶች መሙላትና ዝንፈቶቹን ማረም፣ ራስን በራስ ለማስተዳደር፣ ለመዳኘትና ለመጠበቅ የሚያስችል፣ ትውልድን በራስ ቋንቋ ለማስተማር የሚያግዝ፣ የአናሳውንም ሆነ የብዙኃኑን ባህል፣ ታሪክና ማንነት ለማጎልበትና ለማሳደግ የሚረዳ ሥርዓት መገንባት ከተቻለ አገረ መንግሥቱ ይፀናል፡፡

እሱ ብቻ አይደለም አሁን የሚታዩ ክፍተቶችን በመሙላት፣ በመነጋገር፣ ጠንካራ የአገር አንድነትና የሕዝቦች መስተጋብርን መፍጠር የሚቻልበት የአስተዳደር ሥልት ማዋቀርም ያስፈልጋል፡፡ መላው የአገራችን ሕዝቦች በየዘመናቱ አብረው ችግርና መከራን የገፉ፣ ደስታንም የተካፈሉ፣ የተዋለዱና የተሰናሰሉ መሆናቸው እየታወቀ፣ በጥላቻ ፖለቲካ ለማትረፍ የሚመኙ ኃይሎችን በጋራ መታገልም ከውድቀት መዳኛው መንገድ ነው፡፡ እዚህም ላይ የመንግሥት ኃላፊነት ከፍተኛ ነው፡፡

ሥርዓቱ ሌላው ቀርቶ እምነትና ሃይማኖት ወይም/እና የባህልና የማኅበረሰብ ልማዶችን ለይቶ ለማጉላትና ለማሳደግ የሚያመች፣ የታሪክና የቅርስ ፀጋዎችን ለላቀ ጥቅም ለማብቃት የሚያግዝ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ሌላው ቀርቶ በየእምነት ተቋማቱ ውስጥ የገቡ የፖለቲካ ነጋዴዎች ከፍተኛ ትርምስ እየፈጠሩ ነው፡፡ ለምን ሕግና ሥርዓት፣ ቀኖና ትውፊቶች አይከበሩም ብሎ በጋራ መቆም ከመንግሥትም ከሕዝብም የሚጠበቅ ወሳኝ ተግባር የሚሆነውም ፈተናው ብዙና ተለዋዋጭ በመሆኑ ነው፡፡

የተጀመረው የለውጥ ሒደትና አገርን የማፅናት ትግል ምንም ያህል ፈተናዎች እየተደራረቡበት ቢሆንም፣ ዋስትና ባለው ዴሞክራሲና በጠንካራ ሰላማዊ ጉዞ ከታጀበ የዕድገትና የብልፅግና መሠረት መጣላቸው አይቀርም፡፡ በችግር ውስጥም ቢሆን እየታዩ ያሉ የልማት ተስፋዎች አሉና፡፡ የተሟላው ቁመና ላይ ለመድረስ ግን መተማመን፣ ሰውነትን ማስቀደም፣ አብሮነትና አንድነት ብሎም መደማመጥን ማጠናከር አስፈላጊ ናቸው፡፡ ነገ ሳይሆን ከአሁን ጀምሮ፡፡

በእርግጥ አሁን ባለው የፌዴራል ሥርዓት ውስጥ ለመለያየትና ለቁርሾ ፖለቲካው በር የሚከፍተው የታሪክ ዝንፈቱ ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም አብሮ ለዘመናት የኖረው ሕዝብ ባለፉት 50 ዓመታት ገደማ በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋና በሌሎች ምክንያቶች የተከፋፈለበትን ሥነ ልቦና እንዲያድግ በመደረጉ ነው፡፡ በተለይ ክልሎች ቋንቋና ብሔር ተኮር በመሆናቸው፣ ‹‹በአስተዳደር የየራሳቸው ሉዓላዊ ሥልጣንና መዋቅር ያላቸው ክልሎች በጋራ የሰየሙት አንድ ፌዴራላዊ መንግሥት ይኖራቸዋል›› ከሚለውና ወደ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት የመምጣት ዕሳቤ ጋር የሚጋጭ በመሆኑ እንደሆነ ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ መንግሥታዊ ሥርዓትን ወደ ከፍተኛ ሥልጣን በመጡ ሰዎች ማንነት የመፈረጁ ልክፍት እየተተባባሰ እንጂ እየተቃለለ አለመምጣቱም እንዲህ ካሉ መደናገሮች ጋር በተያያዘ ነው፡፡

ከዚህ አንፃር አገራዊ እሴቶችና ማንነቶችን ብሎም የጋራ ጥቅሞችን እያጠናከሩ፣ ፍትሐዊ የሀብትና የሥልጣን ክፍፍልን እየጎለበቱ፣ ለዴሞክራሲና ለመልካም አስተዳደር መጎልበት በቂ ትኩረት እየሰጡ መሄዱ ነው የሚበጀው፡፡ ነገም ቢሆን አገር የሚመራበት ወንበር ውስን ምናልባትም በአንድ ሰው የሚያዝ ስለሆነ የእከሌ መንግሥት፣ የእከሌ ካቢኔ መባባሉ ሊቀር አይችልም፡፡ እናም በመላው አገራችን ለሁላችንም የሚያገለግል መንግሥታዊ ሥሪት፣ ሰላምና ልማት፣ ብሎም መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን በጋራ መትጋቱ ነው የሚበጀው፡፡

በሁሉም አካባቢ ቢሆን አሁን እየተፈጠረ ያለው የዜጎች የመኖር ዋስትና ማጣት ችግር የሁላችንም ጭንቀት ሊሆን ይገባል፡፡ በተለይ በታሪክ አጋጣሚ በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ተበትነው፣ ተዋልደውና ተጋባተው ኑሯቸውን የመሠረቱ ወገኖች፣ በብሔርና በእምነታቸው ምክንያት ብቻ የሚጠቁበት ወንጀል በሕግም ሆነ በፖለቲካ አግባብ መስተካከል ካልቻለ አገር የሚለው ትልቅ ዕሳቤ ዋጋ ማጣቱ አይቀርም፡፡ ሁሉም በየጎሬው ወደ ማሰብ መውረዱም የሚጠበቅ ነው፡፡ የሕዝብን ህልውናና ደኅንነት ሳይጠብቁስ እንዴት መንግሥት መሆን ይቻላል ብሎ መጠየቅ አስፈላጊ ሆኗል፡፡

ባለፉት አምስት ዓመታት በ‹‹ለውጥ›› ስም በተለያዩ አካባቢዎች፣ ኢትዮጵያዊ ሆኖ በኢትዮጵያዊ ላይ ይህንን ሁሉ ግፍና ጥፋት እስከ ማድረስ የሚያስጨክነውን በሽታ ለይቶ ማከም ካልተቻለም ሰው መሆንን በምን ማግኘት ይቻላል? አሁን ባለው ሁኔታ በብዙዎቹ የአገራችን አካባቢዎች የሚኖሩ አናሳዎች ይገፋሉ፣ በቂ የሕግ ከለላና የፖለቲካ መብት አጠቃቀምም የላቸውም፡፡ ይህንን ዜጋውን በገዛ አገሩ ባዕድ የሚያደርግ ራስ ምታት ማስተካከል ሳይቻል፣ ስለአገር ግንባታና ኅብረ ብሔራዊ አንድነት መነጋገር ከንቱ መሸነጋገል ስለሚሆን ቆም ብሎ መፍትሔ መፈለግ ያሻል፡፡

በአጠቃላይ የአገራችን ዜጎች ማንነታቸውንም ሆነ የግል እምነታቸውን ፈቅደውና ወስነው እንዳልመረጡ ይታወቃል፡፡ የዘር ሐረጋቸው ፈጣሪ በቀደደለት ቦይ እየተፋሰሰ ነው እዚህ ያደረሳቸው፡፡ በዚህ ሒደት ደግሞ ክፉም ደግም ታሪክ እያለፉ የትውልድ ሽግግር ለመፈጸሙ መጠራጠር አይቻልም፡፡ የዓለም ታሪክም ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ ከሁሉ በላይ ኢትዮጵያውያን የነበረንንና ያለንን ሰብዓዊነትና ርኅራኄ ማን ቀማንና ነው ወገን በወገኑ ላይ እንዲህ እየተጨካከነ፣ ተጨማሪ ቂምና በቀል ለትውልድ የሚያስተላልፈው ብሎ መቆጨት፣ መነጋገርና ለለውጥ መነሳት ይኖርብናል፡፡ እስኪ ‹‹መጀመሪያ ሰው መሆን ይቅደም!››፡፡

ሰላም ያሰንብተን!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...